እሥማኤል አረቦ
የተወለዱት አርሲ ነው። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አሰላ ከተከታተሉ በኋላ ወደ ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በማቅናት በአግሪካልቸራል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሄድም በውሃና መስኖ ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተው ተመልሰዋል።
ከ1984 አካባቢ ጀምሮም ከሚኒስትርነት እስከ አምባሣደርነት ድረስ በሙያቸው ሀገራቸውን አግልግለዋል። በፖለቲካው መስክ በነበራቸው ተሣትፎም የኢሕአዴግን ባለሥልጣናት ፊት ለፊት በመሞገት ይታወቃሉ። የሱዳን አምባሣደር ሆነው ባገለገሉበት ወቅትም የሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይላትን በማስማማት ሱዳን ከመፍረስ እንድትድን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከእኚሁ አንጋፋ ባለሙያና ፖለቲከኛ ጋር በሀገራዊና በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን- የውሃና መስኖ ባለሙያ ሆነው እንዴት ወደ ፖለቲካው ዓለም ሊገቡ ቻሉ?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ- እንደአጋጣሚ ሆኖ የእኛ ትውልድ ለፖለቲካ ቅርብ ነው። በተለይም በ1960ዎቹ የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በርካታ ወጣቶችን የሚስብና የተጋጋለ ነበር። እኔ በዚያን ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ። በወቅቱ ከዩኒቨርስቲ እየመጡ ተማሪውን የሚያነቁና የሚያታግሉ ወጣቶች ስለነበሩ በድርጊታቸው እሣብ ነበር። ከዚያም በፊት ቢሆን እኔ የተወለደኩበት አርሲ አካባቢ ከመሬት ጋር በተያያዘ በርካታ ነዋሪዎች ጭሰኞች በመሆናቸውና ብዙ ውጣ ውረዶችንም ያዩ ስለነበር የነበረውን ሥርዓት አብዝተው የሚቃወሙ ወጣቶች ነበሩ። ይህም የእኔን ቀልብ ይስበው ነበር። የንጉሱ ዘመን አብቅቶ ደርግ እንደመጣ ደግሞ በ1967 ዕድገት በሕብረት ዘምቻለሁ። ይህም ኢትዮጵያን በአግባቡ እንዳውቃት ረድቶኛል።
አዲስ ዘመን – ኢሕአዴግን አንዴት ተቀላቀሉ?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ- የማስተርስ ዲግሪዬን ጨርሼ ከእንግሊዝ የተመለስኩት በ1982 አካባቢ ነው። ብዙም ሣይቆይ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ቆየት ብሎም የክልል መዋቅሮችን መዘርጋት ጀመረ። በዚህን ወቅት አዳዲስ የፖለቲካ አመራሮች የሚፈለጉበት ጊዜ ስለነበረ የሚያውቁኝ ሰዎች ወደ ድርጅቱ እንድገባ ጋበዙኝ። እኔም በሙያዩ ብቻ እንድሠራ የምትፈቅዱልኝ ከሆነ አብሬ መሥራት እችላለሁ አልኳቸው። እነሱም በሙያዬ ብቻ እንደምሠራ አረጋገጡልኝ። በዚሁ መሠረትም በ1985 አካባቢ የኦሮሚያ የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ሆኜ ተመደብኩ። በዚህ ኃላፊነት ላይ ሦስት ዓመታት እንዳገለገልኩ የሕገ መንግሥቱ ጥናት በመጠናቀቁ ክልሎች በይፋ ተቋቋሙ። እኔም ወደ ፌዴራል መንግሥት በመዘዋወር የመጀመሪያው የውሃ ሃብት ሚኒስትር ሆኜ ተሾምኩ። በዚህ ኃላፊነትም ለ10 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ። ቀጥዬም በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሆኜ ለሦስት ዓመታት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆኜ ለሁለት ዓመት ተኩል፣ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ለሁለት ዓመት ተኩል እንዲሁም በመጨረሻ ሁለት ዓመት በኮርያ የኢትዮጵያ አምባሣደር በቅርቡ ደግሞ ለሁለት ዓመት ያህል በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሣደር ሆኜ አገልግያለሁ። በአጠቃላይ የፖለቲካ ቆይታዩ ይህንን ይመሥላል።
አዲስ ዘመን- በኢሕአዴግ ውስጥ በነበርዎ ቆይታ የፖለቲካ ውጣ ውረዱ ምን ይመሥል ነበር?
አቶ ሽፈራው ጃርሶ- እኔ ፖለቲካውን ሥቀላቀል የመጀመሪያ ትኩረቴ ሕዝብን ማገልገል ነበር። ኢሕአዴግ ውስጥ በርካታ ችግሮችና ውጣ ውረዶች እንደሚኖር ባውቅም ሕዝቤን ካገለገልኩ በእኔ በኩል የሚመጣብኝን ችግር መቋቋም እችላለሁ የሚል ፅናት አንግቤ ነው ወደ ኢሕአዴግ የገባሁት። በእርግጥ ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ፈታኝ ነው። ሙያህን ተጠቅመህ ያሠብከውን መሥራት አትችልም። የሕወሃት ባለሥልጣናት ፍቃደኝነት መጠበቅ ይኖርብሃል። በየስብሰባው ከፍተኛ ፍጭት አለ። እኛ ባልንህ መንገድ ብቻ መሄድ አለብህ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አለ። ይህን ሁሉ መቋቋምና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ከጅምሩ አንስቶ የሕወሃት የበላይነት የነበረበትና ሌሎችን አሣንሶ የመመልከት አባዜ ስለነበር እነሱ ፈቃደኛ ባይሆኑም እንኳን ይህን እየተጋፈጡ ማለፍ ይጠይቅ ነበር። በዚያን ወቅት በነበረው የድርጅቱ አሠራር ክልሎችን የሚዘውሩት የሕወሃት አባላት ነበሩ። ለሥሙ የክልል ፕሬዚዳንቶች አሉ ቢባልም ክልሎች የሚተዳደሩት በሞግዚት ነበር። በሌላ በኩል ብሔር ከብሔር፣ አመራር ከአመራር የመከፋፈል ሥራ በሥፋት ይሠራ ነበር። ይህ አካሄድ አግባብ አይደለም ብለህ ሥትናገር ‹‹ኦነግ ነው፤ ጠባብ ብሔርተኛ ነው›› ወዘተ… የሚል ሥም ይለጠፍብሃል። በአጠቃለይ ፈጣሪ ጠብቆን እንጂ ብዙ አሥጊ ሁኔታዎች ነበሩ።
አዲስ ዘመን – እርስዎ ከሚታወሱባቸው ነገሮች መካከል ከኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጋር በተይም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የሚያደርጓቸው እሰጣ ገባዎች ናቸው። ለአብነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹እናንተን ከየትም አምጥተን ሚኒስትር አድርገናችኋል›› የሚል ትችት ሲያነሱ እርስዎ በበኩልዎ ‹‹እናንተም እኮ ከጫካ መጥታችሁ ሀገር እየመራችሁ ነው›› የሚሉና መሠል ምልልሶች እንደነበሩ ይነገራል። እስኪ በዚህ ዙሪያ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለው ያስታውሱን?
አቶ ሽፈራው ጃርሶ – በእኔ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ከሌሎች ካድሬዎች የሚሰጡ ትዕዛዞችን እንዳለ አልቀበልም። የማላምንበትን ፊት ለፊት እናገራለሁ። በተለይም በ1993 ከነበረው የሕወሃት መከፋፈል በኋላ በነበረው ተሃድሶ ሰፊ የሚባሉ ግምገማዎች ነበሩ። የተወራወርናቸውን ቃላት አሁን መድገም ባልፈልግም በነበረው ሂደት ግን የተለያዩ ሙግቶች ነበሩ። እነሱ ባይወዱትም የሕወሃት የበላይነት ገዝፎ የሚታይበትን አሠራር ለመቀየር ብዙ ታግያለሁ። አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነና ሄዶ…ሄዶ ድርጅቱን ለውድቀት እንደሚዳርገው ደጋግሜ አነሣ ነበር። እነሱ ግን በአቋማቸው በመጽናት የበላይነታቸውን አስጠብቀው ለመጓዝ ብቻ ነበር ምኞታቸው። የእኔ እምነት ደግሞ በሙያዬ የትም ሄጄ ማገልገል እችላለሁ፤ ነገር ግን ፖለቲካ ውስጥ ከገባሁ ሕዝቡን የሚጠቅም ነገር ሠርቼ ማለፍ አለብኝ የሚል አቋም ስለነበረኝ ፊት ለፊት እጋፈጥ ነበር። የመሠለኝንም ከመናገር ወደ ኋላ ብዩ አላውቅም። ስለዚህም የምንወራወራቸው ቃላት ብዙ ነበሩ።
አዲስ ዘመን – ደፋር ተናጋሪ በመሆንዎ ከሕወሃት ባለሥልጣናት የደረሰብዎት ጫና ነበር?
አቶ ሽፈራው ጃርሶ- እንደዕድል ሆኖ የተለየ የደረሠብኝ ችግር የለም። ምናልባት በወቅቱ እኔ በተሠማራሁበት በውሃው ዘርፍ ብዙም ባለሙያ ስለሌለ ይሆናል። እንደምናገረውና እንደምቃወመው ያህል ብዙም ትኩረት አይደረግብኝም ነበር። ዞሮ…ዞሮ ግን ገደቤን እንዳላልፍ የማሸማቀቅ ሥራ ይሠራ ነበር። አልፎ አልፎም ከድርጊቴ እንድታቀብ ማስጠንቀቂያ ይደርሰኝ ነበር። ነገር ግን ሙያዬን አብዝተው ስለሚፈልጉት በሌሎች ላይ ሲያደርጉት እንደነበረው ክፉ ነገር በእኔ ላይ አላደረጉብኝም። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1984 ግብጽ ደርሠው ከተመለሱ በኋላ ለውሃ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሠጥተዋል። በዚህም የእኔ ሙያ በእጅጉ ስለሚያስፈልጋቸው ይመሥለኛል ግንኙነታችን በአብዛኛው ሙያን የተመለከተ ነበር።
እኔ ሚኒስትር ሆኜ ከመሾሜ በፊት የውሃ ሀብት ሚኒስቴር የሚባል መሥርያ ቤት አልነበረም። ኢትዮጵያ ሠፊ የውሃ ሀብት ቢኖራትም ለውሀው ዘርፍ ግን በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። የውሀ ልማትን የሚመለከተው መሥሪያ ቤት በኮሚሽን ደረጃ ነበር የተቋቋመው። እኔም ኢትዮጵያ ሠፊ የውሀ ሀብት ያላትና ዕድገቷም ሊረጋገጥ የሚችለው ባላት ዕምቅ የውሃ ሀብት መሆኑን ስላምንኩ በወቅቱ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በማሣማን የመጀመሪያው ውሀ ሀብት ሚኒስቴር እንዲቋቋም አደረግኩ። ከላይ እንደገለጽኩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግብጽ ደርሠው ከተመለሱ በኋላ ለውሀ ሀብታችን ትኩረት መስጠት ጀመሩ። ያሉንም የውሀ ሀብቶች እንዲጠኑ አዘዙ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወቅት አሜሪካኖች ካደረጉት መጠነኛ ዳሰሳ ውጪ ኢትዮጵያ ያሏትን ውሀ ሀብቶች የሚያሣይ ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረም። የኢትዮጵያ ዋነኛም ችግር በውሀ ላይ የተደረጉ በቂ ጥናቶች አለመኖራቸው ነው። ያለውሀ ያደገ አንድም ሀገር ስለሌለ የውሀ ሀብትን ማወቅ ለአንድ ሀገር የዕድገት መሠረት ነው። እሥራኤላውያን ማደግ የቻሉት ከዝዋይ ሐይቅ ያነሰ የውሀ ሀብታቸውን በማልማት ነው።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የውሀ ሀብት አላት? ለምን ጥቅም ሊውሉ ይችላሉ? እንዴትና መቼ ወደጥቅም ሊቀየሩ ይችላሉ? የሚሉና መሠል ጥናቶችን በማካሄድ በእኔ አስተባባሪነት የመጀመሪያውን የውሀ ሀብት ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ቻልን። በቅድሚያም ማስተር ፕላኑን ሥናጠና በአባይ ላይ ትኩረት በማድረግ አሁን ግድቡ የሚያርፍበትንም አካባቢ ጭምር በጥናቱ መለየት ችለናል።
አዲስ ዘመን – አሁን ያለው የሕዳሴ ግድብ የእርስዎ የጥናት ውጤት ነው ማለት ነው?
አቶ ሽፈራው ጃርሶ – እኔ ብቻ ሣልሆን በወቅቱ የነበሩ የተለያዩ ባለሙያዎች አሁን በግንባታ ላይ ያለው የሕዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን ብዙ ደክመናል። የተለያዩ ሀገራትን በተለይም የቱርክን ልምድ በመቀመር እና የራሣችንንም ጥናት በማከል ነው የሕዳሴን ግድብ ፕሮጀክት ወደ መሬት ማውረድ የቻልነው። አሁን ግድቡ ያረፈበትን አካባቢ ጨምሮ ወደ አራት ቦታዎች ለግድብ ልማት እንደሚውል በጥናታችን መልሠናል። በጥናታችን መሠረትም በቀሪዎቹ ቦታዎችም ግድቦችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል።
የሕዳሴ ግድብ ከመሠራቱ በፊት ግን ልምድ ለማግኘት እንዲቻል በራሣችን ጥናት አካሂደን በራሣችን የገንዘብና የቴክኒክ አቅም የተከዜ ግድብን ሠራን። ይህ ሥራ ኢትዮጵያ በግድብ ሥራ አቅም እየፈጠረች መሆኑን ያሣየና ግብጾችንም ያስደነገጠ ነበር። ከተከዜ ግድብ ቀጥሎ የጣና በለስን ግድብ በመሥራት ኢትዮጵያ በግድብ ሥራ አቅም እየፈጠረች መምጣቷን ያሣየችበት ነበር። በተለይም እነዚህን ግድቦች ኢትዮጵያ በራሷ አቅም መገንባቷ ሀገሪቱ በአዲስ ጎዳና መራመድ መጀመሯን ያሣየና በርካታ የውጭ ኃይሎችን ጭምር ያስደነገጠ ነበር። የተከዜ እና የጣና በለስ ግድቦች መሠራታቸውም የሕዳሴ ግድብን ለመሥራት መሠረት ሆነውናል።
የግብጾች ጩኸትም የተጀመረው ተከዜና ጣና በለስ መሠራት በተጀመሩበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያ እየለማች መሄዷና በቀጣይም የአባይን ውሀ የማልማት አቅም እንደምትፈጥር ስለገባቸው ከጅምሩ የኢትዮጵያን የግድብ ሥራ ሲቃወሙ ቆይተዋል። ችግሩ በጣም ጎልቶ ወደ ውዝግብ ውስጥ የተገባው ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ በጣለችበት ወቅት ቢሆንም ተቃውሞው ከተከዜ ግድብ ጀምሮ የመጣ ነው። የሕዳሴ ግድብ ለግብጽ ሆነ ለሱዳን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ቢታወቅም በተለይ
ግብጾች በሀገር ውስጥ የሚነሣ ማንኛውን የፖለቲካ ትኩሣት ማስቀየሻ አድርገው ስለሚጠቀሙበት ውዝግቡ መልኩን እየቀያየረ እስካሁን ድረስ ዘልቋል። እኔ እስከሚገባኝ ግብጽ ውስጥ ስለአባይ ፖለቲካ ካላነሳህና የአባይ ጠበቃ ነኝ ካላልክ በስተቀር በሥልጣን ላይ መቆየት አትችልም። ይህ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ እየሄደች ያለውን የልማት መንገድ ትክክለኛነት ቢያውቁትም ሕዝቡን ለማደናገር እና በሥልጣን ላይ ለመቆየት ባለሥልጣናቱ ሁልጊዜ የአባይ ጠበቃ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያህል አባይን የማልማት ፍላጎት ቢኖረንም በነበረን ድህነትና የእርስ በእርስ አለመስማማት ለዘመናት አንቀላፍተን ኖረናል። አሁን ጊዜው ፈቅዶ አባይን ማልማት ችለናል። ግድቡንም በማገባደድ ላይ እንገኛለን። በተለይም የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ አባይ በፍጥነነት ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅና ለኢትዮጵያ ብርሐንም ዳቦም እንደሚሆን እኛም ሆንን የግድቡን መሠራት የሚቃወሙ በሙሉ በአግባቡ ተረድተውታል። በተለይም ባለፈው ክረምት ውሀ ሙሌቱን ካከናወንን በኋላ የመደራደር አቅማችን ከፍ ብሏል። ግድቡ ውሀ የያዘ በመሆኑ በግድቡ ላይ የሚደርስ ጉዳት በሙሉ ሱዳንን ለአደጋ የሚያጋልጣት በመሆኑ ግድቡ ራሱን በራሱ የሚጠብቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የያዘቻቸውን ተጨማሪ ፕሮጀክቶች እንዳትሠራ ለማሠናከል በሀገር ውስጥ ብጥብጥና ሁከት በመፍጠር ያልተረጋጋች ሀገር እንድትሆን በውጭ ኃይላት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎችን በገንዘብ በመርዳትና በማደራጀት እንዲሁም ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች በማጉላት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩና ወደ ሁከትና ጦርነት እንዲገቡ ሥራዬ ብለው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። አሁን የሚታየውም ይኸው ነው።
አዲስ ዘመን – በርካታ ሰዎች የሕዳሴ ግድብ ጥናት በኃይለ ሥላሴ ዘመን የተጀመረና በገንዘብ እጦት ምክንያት ሣይሰራ እንደቆየ ሲናገሩ ይደመጣሉ፤ እርስዎ እንደነገሩን ደግሞ በእርስዎ አስተባባሪነት ጥናቱ እንደተጠናና ወደ ሥራ እንደተገባ እየነገሩን ነው፤ የቱ ነው ትክክል?
አምባሣደር ሽፈራው – በእርግጥ አሜሪካኖች አመላካች የሚሆን የመነሻ ጥናት አካሂደዋል። ሆኖም ግን ጥልቀት ኖሮት የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት የሚያስችል አቅም የሚፈጥር አይደለም። አሜሪካኖቹ በሄሊኮፕተር ዳሰሳ በማድረግ መነሻ ጥናት አድርገዋል። እኛ ደግሞ በአሥራ ሁለቱም ተፋሰሶች ውስጥ በየቦታው በመገኘት ጥልቅ ጥናት ነው ያካሄድነው። አሜሪካኖች ጥናቱን ባካሄዱበት ወቅት ማለትም በኃይለ ሥላሴ ወቅት በዓለም ላይ የነበረው ቴክኖሎጂ ኋላ ቀር ነበር። በውሀ ላይ የሚደረጉት ጥናትና ምርምሮችም ገና ብዙ የዳበሩ አልነበሩም። እኛ ጥናት ባደረግንበት ወቅት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምጥቀት የታየበትና በውሀ ዘርፍ ላይ የሚደረጉ ጥናቶችም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱበት ወቅት ነበር።
ስለዚህም እኛ ያደረግነውን ጥናት አሜሪካኖች ካደረጉት የመነሻ ጥናት ጋር ማወዳደር ፈጽሞ አይቻልም። አሜሪካኖች ይህንን መነሻ ጥናት ያደረጉት ራሺያዎች ከግብጽ ጎን በመቆም የአሥዋን ግድብ በመሥራታቸው ለዚያ ምላሽ ለመሥጠት ነው እንጂ መሬት ላይ የሚተገበር የውሀ ተፋሰስ እና የግድብ ሥራ ለመሥራት አይደለም። የግዳሴ ግድብ ዲዛይን እኮ እኛ ነን የሠራነው። አሜሪካኖች ጥናቱን ሠርተውት ቢሆንም ዲዛይኑንም አብረው ይሠሩት ነበር። የሕዳሴ ግድብ ዲዛይን በጣም ዘመናዊና አሁን በዓለም ላይ ያለውን ዕውቀት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሠራ ነው። ስለዚህ አሜሪካኖች የሕዳሴ ግድብን ጥናት አካሂደዋል የሚለው ከእውነት የራቀና ለራስ ዕውቀትም ተገቢውን ክብር አለመስጠት ነው።
አዲስ ዘመን – አሜሪካኖች አመላካች ጥናት ነው ያካሄዱት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አምባሣደር ሽፈራው – አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ያላትን የውሀ ተፋሰስ ብዛት ከፋፈሉ፤ አባይ ተፋሰስ ይህን ያህል የውሀ መጠን አለው፤ የተከዜ ይህን ያህል የውሀ መጠን አለው ወዘተ…እያሉ የ12 ቱን ተፋሰሶች ውሀ መጠን አስቀምጠውልናል። በአጠቃላይ አሜሪካኖቹ ያዘጋጁት ጥቅል ማስተር ፕላን (General master plan) ነው:: ይህ እኛ በየተፋሰሶቹ በመገኘት ዝርዝር ጥናቶችን እንድናካሂድና በተለይም በአባይ ላይ የተለያዩ ግድቦችን ለመሥራት ፕሮጀክት እንድናዘጋጅ መነሻ ሆኖ አገልግሎናል። የአሜሪካኖች ጥናት ብቻውን እንኳን ግድብ ድልድይ እንድንሰራ የሚያደርገን አይደለም። ነገር ግን እኛ ላደረግናቸው የተለያዩ ጥናቶች መነሻ ሆኖ አገልግሎናል። ለዚህ ነው መነሻ ጥናት ያልኩት። እንኳን የአሜሪካኖቹ የእኛም እኮ በቂ አይደለም፤ ገና ብዙ ጥናትና ምርምር ሊካሄድበት ይገባል።
አዲስ ዘመን – የሱዳን አምባሣደር ሆነው የተሾሙበትን አጋጣሚ ቢያጫውቱን።
አቶ ሽፈራው ጃርሶ – ወደ ሱዳን ለአምባሣደርነት የተጠራሁት የደቡብ ኮርያ አምባሣደር ሆኜ እያገለገልኩ ባለበት ወቅት ነው። ዶክተር አብይ ወደሥልጣን እንደመጡ በ2010 አካባቢ ማለት ነው። በዚያን ወቅት ሱዳን በቀውስ ውስጥ ነበረች። የአልበሽር አስተዳደር ተወግዶ አዲሱ አስተዳደር ገና ሥልጣኑን ያልተረከበበት ወቅት ነበር። ስለዚህም ሁከትና አለመረጋጋት በሥፋት ይታይ ነበር። ሀገሪቱም ወደለየለት ቀውስ ታመራለች የሚል ሥጋት ነበር። በዚህ ወሣኝ ወቅት ኢትዮጵያ የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች፤ ተሣክቶላታልም።
አዲስ ዘመን – ሱዳንን ለማረጋጋት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና ምንድን ነበር?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – በወቅቱ የነበረው የሱዳን ቀውስና አለመረጋጋት አለም ዓቀፍ ትኩረት የሣበና ሀገሪቱንም እስከመበታተን የሚያደርስ አደገኛ ሁኔታ ነበር። በተለይም በግጭት ውስጥ የገቡት ወገኖች የተለያየ ጽንፍ የረገጠ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ እነዚህን አካላት ለማስማማት እጅግ አዳጋች ነበር። ወታደራዊ ክንፉ የራሱ ፍላጎት አለው፤ ሲቪሉም እንዲሁ መሆን አለበት ብሎ የሚሟገትለት ፍላጎት አለው፤ በርካታ የውጭ አካላት በሱዳን የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን በመሥደድ ፍላጎታቸውን ለመጫን ይሞክሩ ነበር። በዚህ ወቅት የአብዛኛው ሱዳናዊ ፍላጎት ኢትዮጵያ እንድትሸመግላቸው ነበር ሲጎተጉቱ የነበረው። ሁሉም ሱዳናዊ በሚባል መልኩ ከኢትዮጵያ ውጭ ማንም በሽምግልና ሂደቱ ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት አልነበረውም። በሌላም በኩል ዐረቦችና አውሮፓዎችም የሱዳን ችግር ሊበርድ የሚችለው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካደራደሩ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጡ ነበር። እኛም ይህንኑ ፍላጎት መነሻ በማድረግ ከዶክተር አብይ ጋር በመምከር እርሣቸው የሽምግልናውን ሂደት እንዲመሩት አደረግን። ተፋላሚ ወገኖችም ኢትዮጵያ በሽምግልና ውስጥ ከተሣተፈች ለመደራደር ፍቃደኛ መሆናቸውን ገለፁ። ስለዚህም ኢትዮጵያ ኃላፊነቱን ወስዳ እና ትኩረት ስጥታ የሚወዛገቡትን አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጣ ማወያየት ጀመረች። የድርድር ሂደቱ አሠልቺና ብዙ ጊዜም ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በጭቅጭቅና በንትርክ የሚያልፍባቸው ጊዜያት ነበሩ። ኢትዮጵያ ሣትሰለች ጽንፍ የረገጡትን የሱዳን ፖለቲከኞች ወደ መሃል ለማምጣትና ከሁሉም በፊት ሀገራቸውን እንዲያስቀድሙ በብርቱ ሥትመክር ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ኃላፊነት ወስዳና ትኩረት ሰጥታ ተፋላሚ ሃይሎችን ባታደራድር ኖሮ ሱዳን ተበታትና የመቅረት አስከፊ ዕድል ያጋጥማት ነበር። ይህንኑ የኢትዮጵያ ውለታ በማስታወስም ሕዝቡ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ወጥቶ አድናቆቱን ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድንም ደማቅ አቀባበል በማድረግ የጀግንነት ክብር ሠጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን – ኢትዮጵያ ከዋለችው ውለታ አንጻር የሱዳንን የሠሞኑን ድርጊት እንዴት ያዩታል?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ድንበር ውዝግብ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ዛሬ ላይ ደርሷል። በሱዳን በኩል ከአጼ ዮሐንስ ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ የመግባትና ድንበሩን የመቆጣጠር ሙከራዎች ነበሩ። ብዙን ጊዜ ግን በአካባቢው አርሦ አደሮችና ሚሊሻዎች እየተመከቱ ይመለሳሉ። በተለይም ሠብል በሚደርስበት ወቅት በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ የመግባት ሙከራዎች የተለመዱ ናቸው። አሁን ሱዳን ይገባኛል ብላ የምታነሳቸው በገላባት፣ በመተማ፣ በአሚራ፣ በአብድራፊህ እና በአብርሐጅራ አካባቢዎች ሲኖሩ የቆዩት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ሱዳናውያን የሉም። ዋናውም ቁም ነገር ሊሆን የሚገባው በቦታው ማን ነው የሚኖርበት የሚለው ነው። በአለም ዓቀፍ የድንበር ድርድርም ቢሆን በቅድሚያ የሚታየው ይኸው ሀቅ ነው።
ነገር ግን የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በተለይም ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ሠላሟ ሲናጋ ሱዳን በተደጋጋሚ ወደ ድንበሩ ዘልቃ ለመግባት ስትሞክር ቆይታለች። የሁለቱ ሀገራት ድንበር ባልተካለለበትና በተለይም ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር በመሆኗ በቅኝ ግዛት የድንበር ውል እንድትገዛ የሚያስገድዳትም ነገር የለም። የፈረመችው አንዳችም ሠነድ የለም።
አዲስ ዘመን – አሁን ሱዳን ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ አልፋ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በድፍረት ዘልቃ መግባቷ መነሻው ምን ይሆን?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ይመሥለኛል። አንደኛው ያው እንደተለመደው ኢትዮጵያ ተዳክማለች የሚል የተሣሣተ እሣቤ በመያዝ ይህ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት ሊያደርጉ ይችላሉ። በሌላም በኩል በሦስተኛ ወገን ግፊት ይህን ውሣኔ ሊወስዱ ይችላሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ደግሞ የወታደራዊ ካውንስሉ መሪ አብድልፈታህ አልቡርሃን በድንበሩ አካባቢ ተወላጅ መሆኑና ከራሱ ጋር አያይዞ ስለሚመለከተው ከሌሎቹ ባለሥልጣናት በተለየ መልኩ ይህን ጥያቄ ሲያነሣ ይታያል። በተገናኘን ቁጥር ሌሎች ባለሥልጣናት ጉዳዩን ሣያነሱና በሌላ አጀንዳ በምንነጋገርበት ጭምር የድንበሩን ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ሲጥር ተመልክተናል። በድንበሩ አካባቢ ያለው መሬትም ሠፊና ለም በመሆኑ ለእርሻ ሥራ በርካታ ዐረብ ሀገራትን ቀልብ መሣብ ችሏል። ስለዚህም ወታደራዊ ኃይሉ መሬቱን ለዐረቦች አከራይቶ ዶላር የመሰብሰብ ፍላጎት አለው።
ሌላውና ዋነኛው ደግሞ ከሥልጣን ዕድሜ ማራዘም ጋር የተያያዘ ነው። በሱዳን ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምና ወታደራዊው ኃይል የመጀመሪያውን ዓመት ከስድስት ወራት ቀሪውን ደግሞ በአብደላ ሃምዶክ የሚመራው ሲቪል መንግሥት እንዲመራ ከሥምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል። በዚሁ መሠረትም ወታደራዊ ካውንስሉ ሥልጣኑን በማገባደድ ላይ ይገኛል። በመሆኑም ሥልጣኑን ማስረከቢያው ወቅት ስለተቃረበ በድንበር አሣቦ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሮ ሥልጣኑን ማራዘም ይፈልጋል። በተለይም ወታደራዊ ኃይሉ የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉና የኑሮም ውድነት እያየለ በመምጣቱ ሕዝባዊ አመጽ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ሕዝባዊ አመጽ ለማፈንና የሕዝቡንም አቅጣጫ ለማሥቀየስ ወታደራዊ ኃይሉ የድንበሩን ጉዳይ ማጦዝ ይፈልጋል። ከሱዳን የተለያዩ ኃይላት ጋር ሥንወያይም ከወታደራዊ ኃይሉ ውጪ ሌሎቹ የሱዳን ባለሥልጣናት በምንም ዓይነት መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አይፈልጉም። ያለው የድንበር ውዝግብ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብደላ ሐምዶክ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለእኔም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የድንበሩ ውዝግብ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ስለዚህም የሲቪል መንግሥቱ ሥልጣኑን ሲረከብ አሁን ያለው ፀብ አጫሪነት እንደሚወገድና በሠላማዊ መንገድ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉ አይቀርም።
አዲስ ዘመን – የሱዳን ሕዝብ ፍላጎትስ ምንድን ነው ?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – የሱዳን ሕዝብ ኢትዮጵያን እንደሀገሩ የሚወድ ሕዝብ ነው። በምንም ዓይነት መልኩ ወደጦርነት መግባት አይፈልግም። ሱዳን ከኢትጵያ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ያለው መሬት እጅግ ሠፊና ብዙም ሰው ያልሠፈረበት አካባቢ በመሆኑ የመሬት እጥረት የለም። የሱዳን ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በልማት ችግር፣ በኑሮ ውድነት፣ በመልካም አስተዳደር ችግር ፍዳውን እያየ ያለ ነው። ከኑሮ ውድነቱ የተነሣ ሕዝቡ መብላት አቅቶታል። ስለዚህም የሱዳን ሕዝብ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱለት እንጂ ከጎረቤቱ ኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት አንዳችም ፍላጎት የለውም። የሱዳን ሕዝብ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እምነት ያለውና ሱዳን በተቸገረችባቸው ወቅቶች ሁሉ ከገኗ የምትቆም የቁርጥ ቀን ወዳጇ መሆኑን ያውቃል። ስለዚህም ከጥቂት የወታደራዊ ኃይሉ ባለሥልጣናት ውጪ የሱዳንም ሕዝብ ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ ጋር በሠላምና በሥምምነት ከመኖር ውጪ ወደ ጦርነት መግባት ሐሳብ ያለው የለም። ወታደራዊ ኃይሉም ቢሆን ሥልጣኑን ለሲቪሉ ሲያስረክብ ችግሩ ረግቦ ሁለቱ ሀገራት ወደነበሩበት ሠላማዊ ሁኔታ ይመለሳሉ የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህም ጥቂት ወታደራዊ ባለሥልጣናት ያደረጉት ድርጊት የሱዳን ሕዝብና መንግሥት እንዳደረጉት ተደርጎ መታሠብ የለበትም።
አዲስ ዘመን – በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ውዝግብን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – ዘላቂው መፍትሄማ እኤአ በ1972 የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት በደረሱበት ሥምምነት መሠረት ችግሩን በሠላማዊ መንገድ መፍታት ነው። ሁለቱ ሀገራት ቀደም ብለው ያቋቋሙትን የድንበር ኮሚቴ በማንቀሳቀስ ወደ ውይይት ማምራትና በመጨረሻም ድንበሩን ወደ ማካለሉ መግባት አለባቸው። ከውይይት ውጪ በጦርነት የሚመጣ ዘላቂ መፍትሄ አይገኝም። ከቻሉ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሁለቱ ሀገራት በውይይት ችግራቸውን ቢፈቱ ተመራጭ ነው። ካልሆነም ዓለም አቀፍ ሸምጋዮችን በማሣተፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥ መሞከር አለባቸው።
ወደዓለም አቀፍ አሸማጋዮች ቢኬድም አሁን መሬቱ ላይ ማን ነው የሚኖረው የሚለው ጥያቄ ገዢ ነው። ኢትዮጵያ ድንበሩን በተመለከተ የፈረመችው አንዳችም ሠነድ የለም። ለእኔ በማንኛውም መልኩ ቢሆን ሱዳኖች በድርድርም ሆነ ከድርድር ውጪ ባለው አማራጭ ኢትዮጵያን የመርታት አቅም እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ጋር በመሆን ውስጣዊ ሠላምን የማወክና ያሉትን ልዩነቶች በማሥፋት ያልተረጋጋች ሀገር እንድትኖር ጥረት እያደረጉ ነው። በቤኒሻንጉል፣ በወለጋ፣ በአፋርና በሶማሌ እየተደረገ ያለውም የዚሁ ሴራ አንዱ አካል ነው። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሙሉ ብቃት ያለው በመሆኑ ለጊዜው ከሚፈጠሩ መጠነኛ ችግሮች ውጪ እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ሀገሪቱ ወደ ሁከት አትገባም። ስለዚህም የተጀመረውን ሀገር የማረጋጋትና ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን በመቆም የውጭ ኃይላት የሚያደርጉትን የማተራመስ ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን – ሱዳኖች የያዙትን ድንበር ለቀን አንወጣም ካሉ መጨረሻ ላይ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – እኔ ከላይ እንደገለጽኩት ወታደራዊው ኃይል ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደሩ ሲያስረክብ የሱዳን ኃይል ከያዘው መሬት በመውጣት ወደ ድርድር ይገባል የሚል እምነት አለኝ። የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማሲን በማስቀደም ሱዳን ከያዘችው መሬት በቅድሚያ ለቃ እንድትወጣና ድርድሩ እንዲቀጥል ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል። ምክንያቱ ሱዳኖች መሬቱን ይዘው ባሉበት ሁኔታ መደራደር በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ድርድሩ ሊካሄድ የሚችለው ሱዳኖች ከያዙት መሬት በቅድሚያ ለቀው መውጣት ሲችሉ ነው። በእኔ እምነት በቅርቡ ሱዳኖች የያዙትን የኢትዮጵያ መሬት ለቀው በመውጣት ወደ ድርድሩ ይመለሳሉ የሚል እምነት አለኝ። ያ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ድንበር ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነትም፣ ብቃትም አለው።
አዲስ ዘመን – ከሱዳን ጉዳይ እንውጣና የስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ስለነበሩበት ወቅት እናንሳ። በቅድሚያ ግን የተረከቡት የስኳር ኮርፖሬሽን ምን ይመሥል ነበር?
አቶ ሽፈራው ጃርሶ – ስለስኳር ኮርፖሬሽን ባትጠይቀኝ ደስ ይለኝ ነበር። ያለቀ ካዝና ነው የተረከብኩት። ሁሉም ብክነቶች ከተፈፀሙና እርቃኑን ከቀረ በኋላ ነው ያስረከቡኝ። በዕዳ የተነከረ ተቋም ነበር። ከመጀመሪያው የብድር ውል ጀምሮ እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ ሕገ ወጥ ተግባራት ተፈጽመውበታል። ለአብነት የተንዳሆን የስኳር ፕሮጀክት ለመሥራት ከሕንድ የተበደርንበት መንገድ ሕገ ወጥ ነው። ብድሩን በኢትዮጵያ ሥም የተበደረው የውጭ ካምፓኒ ሲሆን፤ ይኸው ካምፓኒ ምንም ዓይነት የስኳር ፋብሪካ ያልዘረጋና ልምድ የሌለው ከመሆኑም ባሻገር ገንዘቡን እንደፈለገ የማስተዳደር ሥልጣንም ተሰጥቶታል። በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሥም የተገኘ ብድር አንድ ካምፓኒ እንደፈገለገ እንዲያዝበትና በመጨረሻም ባክኖ እንዲቀር መደረጉ እስካሁን በጣም የሚያሣዝነኝ ጉዳይ ነው። ነባር ፋብሪካዎች ሣይቀሩ ኤክስፖርት አድርገው ማግኘት የሚገባቸውን 15 በመቶ ገቢ ይኸው የሕንድ ካምፓኒ ራሱ ሲወስድ ቆይቷል። እንግዲህ ይህ የውጭ ካምፓኒ እንዲህ የልብ…ልብ የተሠማው በወቅቱ ከነበሩ ባለሥጣናት ጋር በነበረው ግንኙነት የተነሣ መሆኑ ግልጽ ነው። በአጠቃላይ ሀገሪቱ የስኳር ዘርፉን ለማሥፋፋት በሚል የወሰደቻቸው ብድሮች እንዲሁ ሜዳ ላይ ባክነው ቀርተዋል። ይህ ደግሞ ወደ ፊት ትውልድ ፈልፍሎ የሚያወጣው ሀቅ ነው። በአጠቃላይ የስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ተብዩ ብሾምም ለእኔ የባከኑ ጊዚያት ነበሩ በሚል ባጠቃልለው ደስ ይለኛል።
አዲስ ዘመን – በኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ መጨቺውን ጊዜ በሥጋት ሌሎቹ ደግሞ በተሥፋ ይመለከቱታል። እርስዎ የቱጋ ነዎት?
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – እኔ ካሣለፍነው አንጻር ወደፊት ለኢትዮጵያ ብሩህ ቀን እንደሚወጣላት አምናለሁ። እየወጣላትም ነው። የዶክተር አብይ አስተዳደር ከመጣ በኋላ የማያቸው ለውጦች ተሥፋ ሰጪዎች ናቸው። አሁን እኮ እንደቀድሞ የሚጓተቱ ፕሮጀክቶችን አታይም። ይልቁንም በሚያሥገርም ሁኔታ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የመጨረስ አቅም ፈጥረናል። ለአብነት ዶክተር አብይ በአዲስ አበባ የጀመራቸው የሸገር ልማትና እንጦጦ ፕሮጀክቶችን ብታይ በጥራትም በፍጥነትም የተጠናቀቁ ናቸው። ኦሮሚያ ላይ 100 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንና ሰባት ቦርዲንግ ትምህርት ቤቶችን በሰባት ወራት ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለው ርብርብና በታቀደው መሠረት ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ጥረት ስትመለከት ሀገራችን ከፍታ አቅም እየገነባች መሆኑን ታያለህ። ሕዳሴ ግድብም ቢሆን ለአፍታም ሣይቆም እየተገነባ ነው። በአጠቃላይ ቀድሞ በፕሮጀክቶች መጓተት የምንታወቀውን ያህል አሁን በፍጥነትም በጥራትም ሲሰራ ስታይ ማመን ይከብድሃል። ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሸገርና የእንጦጦ ፕሮጀክቶችን ሠርተው ማሣየታቸው በየቦታው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለባቸው የሚል ተመሣሣይ አቋም እንዲያዝ አድርጎታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዕድለኛ ሀገር ነች። ዶክተር አብይንና ባልደረቦቻቸውን የመሠለ አመራር ማግኘቷ እንደ ዕድል ነው የምቆጥረው። በተለይም ከመጀመሪያ ጀምሮ ከኢሕአዴግ ጋር የሠራን ሰዎች ለውጡ ምን ያህል አሥፈላጊና በተለይም ለውጡን ይዘውት የመጡት አመራሮች ያላቸውን ራዕይና በጎ አመለካከት ስለምናወቅ ሕዝቡ ከደገፋቸው ሀገሪቱን ትልቅ ደረጃ ላይ ያደርሷታል የሚል ሙሉ እምነት አለን።
አዲስ ዘመን – ለነበረን ቆይታ በጣም አመሠግናለሁ፤
አምባሣደር ሽፈራው ጃርሶ – እኔም ለተሠጠኝ ዕድል አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም