ነጭ ፋሺስት የተመኛት
ክብሯን ገፎ ሊያሳንሳት
ባህር ተሻግሮ ቅጥሯን አልፎ
እልፍ አእላፍ አሰልፎ
የጦቢያን ገነት ምድር
የአበውን ስጋና ደም ህያው አፈር
ለቀኝ ግዛት
እርስት ጉልት
ቅርጫ አድርጎ ሊመትራት
በነጭ ሴራ በሞት እብሪት ተሸፋፍኖ
አልሰማ ቢል ልቡን ደፍኖ
ካሰበበት ደግሞ ሊደርስ
በእሳት የታጠረ ቅጥሯን ሊያፈርስ
ለፋሺስት
ከንቱ ቅዠት
ግሳንግሱ
ዓደዋ ነው መራራ ጽዋ ሊጠላት ምሱ
ዓድዋ 1 ዓድዋ
ለምኒሊክ አጽመ ርስቱ
የወረሰው ከአያት ቅድመ አያቱ
ቅም አያቱ
ምንጅላቱ
ለእም አበው ሕይወት ሞቱ
ዓደዋ ! የሰማይ አድማስ ጥቁር አለት
የቀለመው በደም ፍሰት
በነጭ ሴራ ተጠንስሶ
በአበው ትግል ደም ተክሶ
የቆየልን እርስታችን
ባለ ብዙ ህብር መኖሪያችን
ጦቢያ ነች ሀገራችን
ከአማራ ያይደል ከጉራጌ
ከሲዳማ ወይም ከሀረርጌ
ከጋምቤላም በለው ከሺናሻ
በዓደዋ የከተመ
ምኒሊክ ሲታመም ሁሉ የታመመ
ዓደዋ ! ዓደዋ!
የእም አበው አጥንት ስብርባሪ
ሕያው ልሳን ተናጋሪ
ከዘመን ዘመን ተሻጋሪ
የነፃነት ድል አብሳሪ
የአልደፈር ባይነት አኩሪ ገድል
ጠላትን በጦር በጎራዴ ቆራርጦ የሚጥል
ጥልቅ ነው የሙት ባህር
ፋሺስት ኢጣሊያን አስጥሞ የሚያስቀር፡፡
ለጠላቱ ሲኦል መቃብሩ
ለእም አበው ሀገር ምድሩ
ስጋና ደሙ ነው ምስክሩ
ከትውልድ ትውልድ የአበው ውርስ
ዘመን የማይሽረው ህያው መንፈስ
በደም የቀለመ ህያው የማይጠፋ
አዲስ ዜና አዲስ ብስራት
የጥቁር ህዝብ ነፃነት
የወጣበት ከባርነት
ዓደዋ ነው ህያው እውነት
ዓደዋ ታሪካችን የጦቢያ ክብር ሞገስ
የድላችን ዓርማ በልባችን ጽላት የሚቀረጽ
ህያው ታሪክ ድርሳናችን
ያበው ሥራ ነው ክብራችን
ለጦቢያ አጥንት ስጋና ደም ሀገር ምድሩ
ዓደዋ ነው ምስክሩ
የደም ጅረት የደም ዕንባ
ዓደዋ ዓደዋ ዓደዋ፡፡
ክብርና ሞገስ
ለቀደሙት አባቶቻችን
125ኛ ዓመት መታሰቢያ በአል
ከኢዩኤል ገላሼ
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013