ምህረት ሞገስ
አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ በሰላማዊ ትግል ከሚጠቀሱ ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው። ትግላቸውን ሲያካሂዱ የእርሳቸው ትልቅ ተስፋ ገድሎ እና ንብረት አውድሞ በጦርነት አሸንፎ መንግሥት መሆን አይደለም። እርሳቸው ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት ምርጫ እና ምርጫን ብቻ ነው።
በምርጫ ተስፋ አይቆርጡም። በኢትዮጵያ በተካሄዱ ምርጫዎች ተሳትፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገብተዋል። ‹‹በምርጫ ተሸንፈዋል›› ሲባሉም በዩኒቨርሲቲ የመምህርነት እና የምርምር ሥራቸውን ከማከናወን ጎን ለጎን፤ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸውን ባለሟቋረጥ ፓርቲያቸውን በማጠናከር ያለቻቸውን ጊዜ በሥራ በማሳለፍ ይታወቃሉ።
አሁን ደግሞ ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው በተጨማሪ የጥናት እና ምርምር ተቋም ም/ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ፤ በቅርቡም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰላማዊ ትግልን ከሚደግፉ ወገኖች የእውቅና ፕሮግራም ከማዘጋጀት በተጨማሪ ሽልማትም አግኝተዋል። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዕውቅና እና ሽልማቱን በሚመለከት፤ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ እና መጪው ምርጫ ላይ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ በመጠየቅ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰላማዊ መንገድን ብቻ በመምረጥ ላደረጉት ተሳትፎ ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶሎዎታል፤ በቅድሚያ እንኳን ደስ አለዎት እላለሁ።
ፕሮፌሰር በየነ፡- እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለመጀመር ያህል ዕውቅናው ምን ስሜት ፈጠረብዎ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከተሰጠኝ ዕውቅና መካከል አንደኛው ‹‹ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አንድምታው›› በሚል የእኔን የፖለቲካ ኑሮ እንደምሳሌ የወሰደ ቡድን ነበር። እዚያ ላይ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ምንነት እና ለኢትዮጵያ የሚኖረውን ጥቅም በሚመለከት ሁለት ሰዎች ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበዋል።
ሰዎቹን የማውቃቸው በሩቅ እንጂ የኔን ውሎ የሚያውቁ ናቸው ብዬ ልገምት የምችላቸው ሰዎች አይደሉም። አንደኛው ታዋቂው የፍልስፍና መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው። ተገናኝትን ተጨዋውተን አናውቅም።
ምናልባት መንገድ ላይ አንድ ሁለቴ ሰላምታ ከመሰጣጣት ያለፈ ግንኙነት አልነበረንም። እርሳቸው ፍልስፍናውን ተሞርኩዘው ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት በሰላማዊ መንገድ ለውጥ አምጪነትን በማብራራት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ መንገድን ይዘው ከተንቀሳቀሱት መካከል በየነ ጎልቶ የሚታይ ነው በማለት አቅርበዋል።
ሌላው ማህበራዊ ተሳትፏቸው ከፍ ያለ በሩቅ የማውቃቸው ዶክተር ወዳጄነህም፤ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሃሳብ ሲሰጡም ሆነ ሲተቹ አያለሁ፤ እሰማለሁ። ከዚያ ውጪ ግንኙነት የለንም። እርሳቸውም እንደዚሁ የበየነ የፖለቲካ አካሄድ ኢትዮጵያን ጠቅሟታል የሚል አካሄድ ይዘው እኔ ራሴን ከምገምተው በላይ ሊታወቁ እና ሊከበሩ ይገባቸዋል ብለውኛል።
በሌላ በኩል በፖለቲካው ዓለም በ1997 ምርጫ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት በሚል የፓርቲዎች ስብስብ ላይ አብረን የሠራነው በወቅቱ በውጭ ሀገር የነበረውን ፖለቲካ በበላይነት ሲመሩ የነበሩት ዶክተር አረጋዊ በርሔ ናቸው። በህብረቱ ላይ ከምስረታው ጀምሮ እስከ አመራርነት አብረን ሠርተናል። እርሳቸው በፖለቲካው ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ እንደመቆየታቸው የሚያውቁትን ምስክርነት እና አስተያየት ሰጥተዋል።
በተጨማሪ ሌላኛው ሰው ከሽግግር መንግሥት በኋላ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አቶ አባተ ኪሾ ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ደግሞ በተለያየ ፅንፍ ውስጥ ሆነን እንተዋወቅ ነበር። እርሳቸው የኢህአዴግ ሰው ናቸው። እኔ ደግሞ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎችን ሳራመድ ነበር።
የእነርሱን መንገድ ስናጥላላ እና አማራጩ የሚሻለው ይሄ ነው ስንል ነበር። በተለይ እኔ የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረትን ስመራ ካድሬዎቻቸውን ከሚያሰማሩብኝ መካከል አንደኛው አቶ አባተ ነበሩ።
ያም ሆኖ ግን እኔ በማደርገው ላይ የከረረ ጥላቻ እንዳልነበራቸው ተረድቻለሁ። ያንን ያደረጉት ሥራ ሆኖባቸው ነው። ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች በበጎ አንስተውኛል። ወደ ፊት የካቲት 21/2013 ላይ ሰፋ ያለ የእውቅና ሥነስርዓት ይኖራል ተብሏል። እርሱ ገና እየተሠራበት ነው። የእነዚህ ሰዎች እውቅና እጅግ አስደስቶኛል።
ሌላው ዳያስፖራው ነው። በተቃውሞ መንቀሳቀስ ከጀመርኩኝ አንስቶ በተለይ አውሮፓ እና አሜሪካ ኢትዮጵያውያን በብዛት ባሉባቸው አገራት ‹‹በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ትሰጣለህ›› በሚል እየተጠራሁ ከአንዱ ወደ ሌላ ስወራጭ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ከማደርገው በተጨማሪ ውጭ አገር በመሄድ ‹‹ኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር የማድረግ ትግል የሁሉም መሆን አለበት›› በሚል ስሠራ ነበር።
‹‹ካልተባበርን ኢህአዴግን ማሸነፍ እና ዴሞክራሲን ማስፈን አንችልም። ትግላችን መበጣጠስ የለበትም›› በማለት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ስንቀሳቀስ ነበር። እዚያ ብቻ ሳይሆን አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም አገሮች ሄጃለሁ። አገራችሁ ገብታችሁ ታገሉ ብያለሁ። ዶክተር አብይ በውጭ ያላችሁትም ግቡ ሲሉ እዚያ ያለው ማህበረሰብ ከለውጡ መንፈስ ተነሳስቶ፤ ጦር ያነሳውም ሁሉም ገባ።
‹‹ይህማ ድሮም በየነ ጴጥሮስ ሲለው የነበረ ጉዳይ አልነበረም ወይ?›› በሚል አንድ ዓይነት እውቅና ለመስጠት የተንቀሳቀሱ አካላት በቃላት ብቻ ሳይሆን በገንዘብም ጭምር ለማገዝ ጥረት አድርገዋል። ከ500 በላይ ሰዎች በመዋጮም በሌላ መልኩም በመሳተፍ አገር ውስጥ መጥተው ሆሳዕና ላይ መኪና ገዝተው ስጦታ ሊሰጡኝ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል። በፕሮግራሙ ከሃዲያ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ አብረውኝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በግብዣው ላይ ተሳትፈው ነበር። ዝግጅቱ የብልፅግና ፓርቲ አባላትንም ያገለለ አልነበረም። የዞኑ እና የወረዳ ኃላፊዎች ነበሩ።
አዲስ ዘመን፡- መኪናው እጆት ገባ?
ፕ/ሮ በየነ፡- በደንብ ነዋ። ከመኪናውም ባሻገር ድግሱም ቀላል አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሌላኛው ጉዳይ እንሂድና፤ ከመድረክ መውጣታችሁን ይፋ አድርጋችኋል፤ ከመድረክ እንድትወጡ ያስገደዳችሁ ምንድን ነው?
ፕ/ሮ በየነ፡– የመድረክ ጉባኤም ሆነ አመራር የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓን) አስወጥቶት አይደለም። እኛ መቀጠል ባለመቻላችን ነው። መድረክ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ መለስተኛ ወቅታዊ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ማዕከል ያደረገ ፕሮግራም ቀርፀን እየተንቀሳቀስን ነበር። ነገር ግን ከለውጡ በኋላ የኦፌኮ አካሄድ የተለየ ሆነ። በዚህ አካሄድ ለሁለት ዓመት መስመር ለማስያዝ ጥረት ተደረገ።
‹‹በመድረክ ውስጥ ከተንቀሳቀሳችሁ መድረክ የማያውቃቸው ድርጅቶች ጋር እየሄዱ መጣመር፤ መግለጫ መስጠት፤ ስሜት ቀስቃሽ ዕርምጃዎች ላይ ማለትም አክቲቪስቶች ነን ከሚሉ ግለሰቦች ጋር የምታደርጉት እንቅስቃሴ አይመቸንም። በዚህ አገር ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ የምንሠራ ነን። የትግል መስመራችን ሰላማዊ መሆን አለበት›› ተብለው ቢመከሩም ጭራሽ እየባሰባቸው ሄዷል።
እኛ አትግፉን እያልን ቆየን። አሁንም ቢሆን ጥል የለንም። አለመግባባት ተፈጥሯል። መድረክ ከማያውቃቸው የኦሮሞ ድርጅቶች፤ግለሰቦች እና ከሌሎችም ድርጅቶች ጋር ስምምነት ፈፀመ። መግለጫም አወጣ። ለምሳሌ ኦፌኮ በተደጋጋሚ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያወጣው መግለጫ እኛ የምንስማማበት አልነበረም። ከዚያ ውስጥ እንደአንኳር የሚጠቀሰው የምርጫ ጉዳይ ነው።
ምርጫ ቦርድ ‹‹ኮረና በመኖሩ ምርጫውን ማከናወን አልችልም›› ባለበት ወቅት ምርጫው መራዘሙ የግድ ነበር። በዚያ ጊዜ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አብቅቷል›› በሚል አገር ያለመንግሥት ትቆይ በማለት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። መንግሥት የሚመሰረተው ደግሞ በምርጫ ነው። ስለዚህ ምርጫውን ማራዘም የግድ ነበር።
ታሪኩን ለማሳጠር የምርጫው ጉዳይ ህገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ በህገመንግሥት ትርጉም ይታይ ሲባል ኢሶዴፓ ሃሳቡን ተቀብሏል። የመድረክ አባል ሁለት ድርጅቶችም ይህን ተቀብለዋል። በዚያ ወሳኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ የተገኘነው መድረክን ወክለን ሳይሆን እያንዳንዳችን የየራሳችንን ፓርቲ ወክለን ነው። አገር ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር በሚል የምርጫው ጉዳይ በህገመንግሥት ትርጉም ይታይ ያልነው እና የወሰንነው እኛ ብቻ ሳንሆን ከመድረክ ውስጥ ተጨማሪ ሁለት ፓርቲዎችም ነበሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ስብሰባ ላይ እኛ በፊትም ስንነጋገርበት የነበረ ስለነበር የህገመንግሥት ትርጉም ይሰጠው የሚለውን ተቀበልን። ሲዳማ አርነት ንቅናቄ እና አረና እንደኛው አማራጩን ተቀበሉ። የኦፌኮ ተወካይ ፕ/ሮ መራራ ግን ‹‹ጊዜ ይሰጠን፤ በዚህ ፍጥነት አንወስንም›› አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ‹‹እኛ ጥድፊያ ውስጥ ነን። መዘግየቱ ለአገሪቱ አይጠቅምም፤ የቀረበው አራት አማራጭ ነው። ሦስቱ አማራጮች ስለማይሆኑ ህገመንግሥት ይተርጎም›› ሲሉ ፤ ኦፌኮ መቀበል አልፈለገም።
በዚያ ጊዜ በስንት ዓመት ትግል ያቃተንን ብሔራዊ መግባባት ይፈጠር የሚል እና ሌሎች ጥያቄዎችን አነሱ። ይሄ ነገር በዚህ ጊዜ እንዴት ይነሳል ? አገሪቱን ወደ ባሰ ችግር መክተት አይገባም በሚል ፤ በመነጋገር የምርጫውን ጉዳይ ማየት ወዳለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመልከተው በሚል መግባባት ላይ ደረስን።
በመካከል ፕሮፌሰር መራራ የመድረክ የወቅቱ ሰብሳቢ ነበሩ። እኔ ደግሞ ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ነበርኩ። ኢሶዴፓ በሌለበት ሳንጠራ እና ሳናውቅ ስብሰባ አካሄዱ። በዚያ ላይ መድረክ ‹‹ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ይቋቋም›› ብሎ ወሰነ የሚል ዜና በመገናኛ ብዙሃን ሲወራ ሰማን። በዚህ ጊዜ ‹‹ይህ የእኛ አቋም አይደለም›› በማለት መግለጫ ለመስጠት ተገደድን ።
በኋላም ክፍተቱ እየሰፋ ሄደ። እንደገና ኦፌኮ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር( ኦብነግ) ፣ ከኦነግ እና ከሌሎችም ፓርቲዎች ጋር የትብብር መድረክ ፈጥረናል አሉ። የመድረክ አባላት የማናውቀው ትብብር ምንድን ነው አልን።
በእርሱ አማካኝነት ደግሞ እንደገና መንግሥት የሚቀጥልበት ሁኔታ ከመገለጹ በፊት፤ ‹‹ይሄ መንግሥት ለአንድ ዓመት ይቀጥል፤ ነገር ግን ውጭ ጉዳይ እና መከላከያን ከተቃዋሚዎች ጋር ሆኖ ይምራ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰናል›› ብለው ይፋ አደረጉ።
ይሄ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ወጥ አቋም አልያዙም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታን ፓርቲያችን አይቀበለውም። ደጋፊዎቻችንም አይቀበሉትም በሚል ወጣን። በተለይ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን ላይ ቅሬታ የተፈጠረው ኦፌኮ አንድን ታዋቂ አክቲቪስት ‹‹የድርጅቴ አባል አድርጌ ተቀብዬዋለሁ›› ሲል እና ሰውየው ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ሲቀመጥ ነው።
ደጋፊዎቻችን አባላቶቻችንን ‹‹መድረክ ብላችሁ ከኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ከሆነ ሰው ጋር ትሠራላችሁ›› ብለው ዓይናችሁ ላፈር አሉን። ምርጫ ቦርድ ያመጣውን 10ሺህ አባላትን አሰባስበን ማስፈረም አቃተን። ‹‹ከእነርሱ ጋር እየሠራችሁ እንዴት ከኛ ጋር ትሆናላችሁ›› ተባልን።
በእርግጥ የመድረክ አባል ድርጅት ግለሰብ መመልመል ይችላል። ነገር ግን ግለሰብ ቢሆንም መንግሥት ነኝ እስከ ማለት የደረሰውን ሰው አባል ማድረግ አደጋ አለው። እራሱ አደባባይ ወጥቶ በሱ ስም የሚደረገውን እርሱ እንደሌለበት አላስተባበለም። የሚሆነው ሁሉ ያስደሰተው ይመስላል።
‹‹እዚያ መንገድ ተዘጋ ፤እዚያ እንዲህ ሆነ›› ሲባል ይህ ሰላም ስላልሰጠን የአባላቶቻችን ግፊትም ስለበረታ ኦፌኮ ባለበት ሌሎችም አባል ድርጅቶች የአቋም ፅናት በማያሳዩበት ሁኔታ መድረክን ከ10 ዓመት በላይ ዓቅማችን ከሚችለው በላይ ገንዘብ በማሰባሰብም ሆነ በተለያየ መልኩ ፓርቲውን ለማቆየት የታገልን እና ከትቢያ አንስተን የፈጠርነው ቢሆንም ከእነሱ ጋር አልቆረብንም በማለት እና ድርጅት የትግል መሳሪያ በመሆኑ፤ በመድረክ ምክንያት ጭራሽ ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚለይ ሁኔታ ሲመጣ ራሳችንን ማግለል አስፈላጊ ሆኖ በማግኘታችን ከፓርቲው ወጥተናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢሶዴፓ በኩል ለምርጫው እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? በምርጫ አሸንፋችሁ የፓርላማ ወንበርን የምትቆጣጠሩ ይመስላችኋል?
ፕሮፌሰር በየነ፡– በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ለእኛ አዲስ አይደለም። እኔም ተወዳድሬ አሸንፌ ሁለት ጊዜ ምክር ቤት ገብቻለሁ። ለኛ አዲስ አይደለም። ህዝቡ ያውቀናል። ከማወቅ አልፎ እየሸለመን ነው። እውቅናም እየሰጠን ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ መቶ በመቶ ተደላድሏል ለማለት ያስቸግራል። ብዙ ጉዳዮች አሉ። እኛም ተሳትፈን አዋጆች ወጥተዋል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ነው ማለት አይቻልም። ክፍተቶች አሉ።
እኛ ትልቁ ስጋታችን ዕጩ ስናቀርብ አብዛኛዎቹ አባሎቻችን የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። እኔም የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። ዕጩ ሆነው የሚወዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች ያለደሞዝ ፈቃድ ወስደው መወዳደር አለባቸው የሚለው ከባድ ነው። የቅስቀሳ ጊዜን ጨምሮ የምረጡኝ ውድድር ሦስት ወር ሊፈጅ ይችላል። ያንን ጊዜ በተለይ ጠንካራ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችንን ሥራ ለቃችሁ ተሰማሩ ለማለት ስጋት አለብን። ‹‹ ቤተሰቤን በምን ላስተዳድር ›› የሚል ጥያቄ ከተነሳ ለመመለስ ከባድ ነው።
የኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኛ በድህነት የሚኖር መሆኑ ይታወቃል። ሌላ አገር ዕጩ አቅራቢው ፓርቲ ድጎማ ያደርጋል። እኛ ግን ራሳችንም ያለችንን እያወጣን እየተንቀሳቀስን ነው።
ከዚህ አንፃር ዕጩዎችን ማቅረብ ላይ ተቸግረናል። ዝግጁነት ይጠይቃል። በዚያ ደረጃ የሚታዩ ሰዎች ለውድድር ይቀርቡልናል? የሚለው አስግቶናል። ያም ሆነ ይህ 547 መቀመጫ ላይ በሙሉ እንወዳደራለን አንልም። ነገር ግን አቅም እስከ ፈቀደ ድረስ ብቁ ፈቃደኛ ዕጩዎችን እናቀርባለን።
አዲስ ዘመን፡- የት የት ዕጩ ታቀርባላችሁ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ደቡብ እና ቤንሻንጉል ላይ ዕጩዎችን እናቀርባለን። ቀድሞም ቢሆን በፓርቲያችን አንድ ሰው ዕጩ የሚሆንበት መስፈርት አለ። ያንን መከለስ ካስፈለገ አይተን እናወርዳለን። በቀጣይ ከሌሎች ፓርቲዎች የምንለይበትን መንገድ ማኒፌስቶአችንን እናስተዋውቃለን።
አዲስ ዘመን፡- የአገራችንን ሰላምና ደህንነት ሁኔታ በሚመለከት በተለይም በመተከል እና በሌሎችም በአንዳንድ አካባቢዎች ስላሉ ስጋቶች፣ የንፁሐን ህይወት መጥፋትን በሚመለከት ምን ይላሉ? የጸጥታ ስጋቱ በምራጫው ላይ የሚያሳርፈው ጥላ የለም?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዜጋ ዜጋን የሚያጠቃበት ሁኔታ መኖሩ የሚያኮራ አይደለም። የጸጥታ ችግር ምርጫውን እንዳይካሄድ እንቅፋት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። ከምርጫው ጋር በተያያዘ የጸጥታ ችግር መኖሩ ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም።
ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ምርጫዎች ያለኮሽታ በተረጋጋ መልኩ የተካሄዱ አይደሉም። ምርጫ በሚታወጅበት ጊዜ ከኢህአዴግ ውጪ ያለን ፓርቲዎች ጦርነት እንደታወጀብን የምንቆጠርበት ሁኔታ ነበር። ካድሬዎች ያዋክቡን ነበር። የህግ የበላይነት ጠፍቶ፤ ፍትህ ተረስቶ፤ ወገንተኛ ሆነው ስብሰባ እየበተኑብን፤ ለቅስቀሳ የወጡትን አባሎቻችንን ሲያስሩ እና ሲገድሉ ነበር።
አሁን ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ደህንነቱ ከመንግሥት አቅም በላይ ከሆነ ይታለፋል። የትግራይ ክልል ይቆይ እንደተባለው ሁሉ በሌሎች አካባቢዎችም እንዲሁ ይቆይ ሊባል ይችላል። ምዕራብ ወለጋም ሆነ ቤንሻንጉል ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አዳጋች ከሆነ ይታለፋል። አመቺ ጊዜ ሲመጣ ደግሞ ማሟያ ምርጫ ይካሄዳል። ይህ አካሄድ በፊትም የተለመደ ነው። ምርጫ ማለት ውክልና ነው።
ምርጫ ቦርድ ከ50 ሚሊየን ሰው በላይ ምርጫ ያካሂዳል ብሏል። ከዚያ ውስጥ ከ51 ከመቶ በላይ ድምፅ ከሰጠ፤ በዘመናዊ ውክልና ስልጣን ላይ የሚወጣውም መቶ በመቶ አያገኝም፤ 49 ድምፅ ያገኘው ሳይሆን 51 በመቶ የሆነው መንግሥት ይሆናል። ስለዚህ አብላጫ ድምፅ በመሆኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የደህንነት ችግር ከምርጫው ጋር ተያይዞ ቢዘለል አያሳስብም።
አዲስ ዘመን፡- ከጀርባ በኢትዮጵያ ትርምስ እንዲኖር የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስ የደህንነት ስጋት መቅረፍ ቀላል አይደለም ይባላል። በእርሶ እምነት በኢትዮጵያ ትርምስ እንዲኖር የሚፈልጉት እነማን ናቸው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ከአገር ማተራመስ ጀርባ ያሉ አካላት ዓላማቸው ትልቅ ነው። ለምሳሌ ህወሓት ካሳየው ፀባይ አንፃር ለምን ከኔ የወጣ የብልፅግና ፓርቲ ተፈጠረ በሚል አገር እንድትተራመስ ይፈልጋል። ይህንን አገር በድጋሚ መቆጣጠር እና መንግሥት ሆኖ መቀጠልን ይሻል።
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ የኢትዮጵያ መፍረስ ይጠቅመናል ብለው የሚያምኑ አካላት አሉ። የአፍሪካ ቀንድ የውሃ ማማ የሆነችው ኢትዮጵያ ከተራራዎቿ የሚፈልቀው ውሃ በአካባቢው ያሉ አገራት በሙሉ፤ ምናልባት ኤርትራ ስትቀር ሁሉም አገሮች በአብዛኛው የኢትዮጵያን ውሃ ያገኛሉ።
በዋናነት ግን ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ በዚያ አካባቢ የአረብ አገሮች ‹‹ጥቅማችንን ይነካል›› በሚል የኢትዮጵያን መብት ለመግፈፍ የሚሞክሩበት ሁኔታ አለ። ብቻቸውን ለዘላለም መጠቀም የሚፈልጉ አሉ፡ ፡ ኢትዮጵያ መጠቀም እንዳትጀምር የሚሞክሩ አካላት አገሪቱ ጠንካራ እንዳትሆን እንደፈለጉ ወዲያ እና ወዲህ የሚያደርጓት እንድትሆን ይፈልጋሉ። የዚያ ሁሉ ስሜት ውጤት አገሪቱን እያወከ መሆኑ አይካድም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር የዘር ፖለቲካ ውጤት ነው ብለው የሚያምኑ አካላት አሉ። በእርሶ እምነት የዘር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አስጊ ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- እኛ ዘርን መርጠን አልተወለድንም። እዚህ ልወለድ ብሎ የመረጠ ማንም የለም። እያንዳንዱ ቡድንም ሆነ ግለሰብ በምርጫ ዘሩን አላገኘም። ወያኔ ብቻ ያንን አስተሳሰብ አምጥቶ የዘራው አይደለም፤ በፊትም ያለ ነው።
ነገር ግን በአግባቡ ተግባብቶ በጋራ ተስማምቶ መኖር ጥቅም መሆኑን ተገንዝቦ የሚኖር ህዝብ እና ያንንም ህዝብ የሚመራ አስተዳደር በአገራችን መጥፋቱ በእርግጥ ችግር ፈጥሯል። እዚያም እዚህም መቆራቀዝ የመጣው ሁሉም ዘርፎች የሚሄድ፤ ሌላውን የሚያሳንስ፤ ራሱ ብቻ በልጦ መገኘት የሚፈልግ በመሆኑ ነው ችግሮች እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ያሉት።
አብዛኛው ጥያቄ ወደ ታች ይታይ ከተባለ ጥያቄው የመሬት ጥያቄ ነው። ሌላው ትርፍ ነው። መሬታችንን ወረሩ የሚባልበት ሁኔታ አለ። የሰው ልጅ ደግሞ ዝም ብሎ ቅድመ አያቶችን እና አያቶችን ባሉበት መሬት ላይ እዚያው ተወልዶ እዚያው አይቀርም። ዕድል ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳል።
እንኳን አገር ውስጥ ከአገር ውጪ ስደትም ይካሄዳል። ይህ ሁሉም ጋር ያለ ነው። ቅድመ አያቶች ካሉበት ቦታ መለየት፤ በዚህ አገር ብቻ እንደተከሰተ አድርጎ መመልከት አይገባም። በመሰረቱ ፖለቲካችንን ማስተካከል አልተቻለም።
መንግሥትም ቢሆን በህዝብ ፈቃድ መጥቶ አልተቀመጠም። ህውሓት ስልጣን ከያዘ በኋላ የተንሰራፋው የካድሬ መንግሥት ነው። እነዚህ ካድሬዎች ደግሞ የሚያውቁት የፖለቲካ ጥቅምን ብቻ ነው። በራሳቸው እምነት ውስጥ ያልሆነውን መጨቆን ሥራቸው ነው።
ነገር ግን ዘረኝነትን የጋተን የለም። ሁሉም የራሱ የማሰብ ችሎታ አለው። ትናንት ልጁን የዳረ ሰው ዛሬ ተነስቶ ሌላውን ሰው እገላለሁ የሚለው መንፈስ የህግ የበላይነት እና የመልካም አስተዳደር መጥፋት ያመጣው ነው። ይህንን የሚያደርጉ ካድሬዎችን የሚጠይቃቸው ማጣት ችግር ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በየክልል የተደራጁ ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ኦ! እርሱ ትልቅ ችግር ነው። ለአገሪቱም የአደጋ ምንጭ ነው። በአገራችን ለተከሰተው አገሪቱ ለገባችበት ለማሰብ የሚዘገንን፤ የአንድ ክልል ኃይል የአገሪቱን ሠራዊት ደፍሮ የሚወጋበት ሁኔታ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ነው። ለዚህ ሁሉ መነሻ ልዩ ኃይል ነው። ሶማሌ ክልል ላይ ያጋጠመውን አይተናል። አብዲ ኢሌን ተመልክተናል። ደቡብ ላይም ልዩ ኃይል አለ።
የልዩ ኃይል ጉዳይ ለእኔ እብደት ነው። ይህንን አስወግዱ ብዬ ቀድሜም ተናግሬያለሁ። ፖሊስ መኖሩ መልካም ነው፤ ችግር የለም። ከህገመንግሥት ውጪ የተቋቋመ ልዩ ኃይል ብሎ ነገር ሊታሰብበት ይገባል። ሶማሌ እና አፋር አካባቢ የተፈጠረው ችግርም ከዚሁ ጋር የሚገናኝ ይመስለኛል። እኔ መጀመሪያም ጥያቄ አቅርቤ በሰላም ሚኒስቴር በኩል ‹‹እየተጠና ነው። መፍትሔ ይበጅለታል›› ተብያለሁ። ይሄ መንግሥትንም አሳስቦት እየተጠና መሆኑ ትክክል ቢሆንም አፋጣኝ ዕርምጃ መወሰድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከልዩ ኃይሉ ባሻገር ባንኮች ሳይቀሩ በብሔር የሚቋቋሙበት አካሄድ ላይስ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በተናጥል መጥራት አያስፈልግም። በክልሉ ስም ሳይቀር ባንክ እየተቋቋመ ነው። ይህንን የሚያደርጉት አወቅን ረቀቅን የሚሉ ናቸው። በብሔር ስም ባንክ እና ኢንሹራንስ በማቋቋም የሼር ገዢዎችን ብሔር ሳይቀር የሚመዘግቡ እና የሚለዩ አሉ። ይህ አሉባልታ አይደለም።
የንግድ ድርጅት ሥራው ትርፍ ብቻ ነው። አንድ ጓደኛዬ የአንድ ብሔር ባንክ የቦርድ አባል ነው። ‹‹ባንካችሁ ላይ ሼር ለመግዛት ብሔር እንደሚጠየቅ ታውቃለህ?›› ስለው አላውቅም አለ። ይሄን የሚሠሩት ህብረተሰቡን የመከፋፈል እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው። የሚገርመው የሚሠሩት በአዋቂነት ስም ነው። በዘር ላይ ተንተርሰው ሊያተርፉ ይፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት እርሶም ሆሳዕና ባንክን ከሌሎች ሰዎች ጋር በማቋቋም ላይ ነዎት፤ አይደለም እንዴ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ሆሳዕና የብሔር ባንክ አይደለም። የኢትዮጵያ ባንክ ነው። ስሙን ከመፅሐፍ ቅዱስ ወስደን ያቋቋምነው ባንክ ነው። ከከተማው ጋር ግንኙነት የለውም። እንደውም ሌላ አካባቢ ተፎካካሪ ተፈጥሮ ይህ መሆን የለበትም ብዬ አቋም ወስጃለሁ። ሼር የሚገዛበትን ሁኔታ ከባንኮች ጋር ስንዋዋል ትግራይም ሆነ አማራ በሌሎችም ክልሎች ተዋውለናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ምርጫው ምን ያህል አስፈላጊ ነው። ምርጫውን አስመልክቶ የመንግሥት፣ የምርጫ ቦርድ እና የፓርቲዎች ዝግጁነት ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- መቶ በመቶ የተጠናቀቀ ዝግጁነት የትም አገር አይኖርም። ዋናው አቅም በፈቀደ መጠን ተሳትፎ እንዲኖር ሜዳው መኖሩ ነው። የምርጫው አስፈላጊነት ከተባለ ከምርጫ ውጪ ምንም ዓይነት የሰላማዊ ትግል አማራጭ የለም። ዴሞክራሲ ማለት በሰላማዊ ትግል መንግሥት መመስረት ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ምርጫ ነው። የህዝብ ድምፅን አልፎ መሔድ አይቻልም። ምርጫ የግድ ነው።
ኮቪድ አስደንግጦን ነበር። በዚያ ጊዜ ፍርሐት ነበር። አሁን ግን ከኮቪድ ጋር ተያይዞ መላመዱ ስለመጣ መንግሥትም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ምርጫውን ማካሄድ እና ከምርጫ ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚያነሱትን አጀንዳ ማሳጣት አለበት። ህዝባዊ ይሁንታ ያለው መንግሥት ስልጣን ከያዘ ዋጋው ከዋጋዎች ሁሉ በላይ ትልቅ ነው።
አሁን እየተናቆርንም ቢሆን ምርጫውን መቀጠል አለብን። በእኛ በኩል ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ መገፋፋት አንፈልግም። የምንፈልገው በሰለጠነ መንገድ መወዳደር ነው። ምርጫ ውስጥ ተሳትፈን ፓርላማ ስንገባ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት አስከፍለን ነበር። አሁን ያንን ማየት አንፈልግም። እንደዚያ ዓይነት መስዋዕትነት የሚያስከፍል አካባቢ አንሔድም።
አዲስ ዘመን፡- በህዝብ ይሁንታ መንግሥት የሚሆነው አካል በአገሪቱ ከባድ የሚባሉ ጥያቄዎችን ለምሳሌ የወሰን፣ የህገመንግሥት እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ይመልሳል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ሌላ አማራጭ የለንም። ህገመንግሥት የሚሻሻለው ፓርላማው እንደገና በህጋዊነት ሲቋቋም ነው። አሁን ያለው ይህን ሊያደርግ አይችልም። ሌላ አማራጭ የለም። ስህተትን በስህተት ማረም ሳይሆን ህጋዊ በሆነ መልኩ በሚቀጥለው ህዝቡ የተሻለ ይሁንታ የሰጠው ፓርላማ ህገመንግሥቱን ያሻሽላል።
አዲስ ዘመን፡- ከህወሓት በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ አስመልክቶ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- መንገራገጭ መቼም አለ። ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች። እኔ በኢትዮጵያ ላይ ፍርሐት የለብኝም። አንዳንዶች ይሄዳሉ አገሪቱ ትቀጥላለች። በመንገራገጭ ኢትዮጵያ አትገለፅም፤ ትልቋ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች። ብዙ የምንማማርበት እና መተማመን የምንፈጥርባቸው ነገሮች ይቀራሉ።
ይህ ሁሉ ሆኖ እንዴት ችግር አይኖርም? ከአሁን በኋላም ገና ብዙ ነገር አለ። እዚህም እዚያም ገና አልተጨረሰም። በቅድሚያ የሚመረጠው መንግሥት ተአማኒ መሆን አለበት። ከዚያ በጉዳዮች ላይ መተማመንን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013