ክፍለዮሐንስ አንበርብር
የጎንደር ከተማ ከ750ሺ በላይ ህዝብ የሚኖርባት ጥንታዊት ከተማ ናት። የቆዳ ስፋትዋ 23ሺ ሄክታር ሲሆን በስድስት ክፍላተ ከተሞችና 11 የገጠር ቀበሌዎች የተከፈለች ናት። ከዚህም በተጨማሪ አንድ የሳተላይት ከተማ/ከትላልቅ ከተሞች ጋር ተጠግተው የሚመሰረቱና ከከተሞች አነስ ያለና ከገጠር ቀበሌዎች ደግሞ ከፍ ያሉ ነገር ግን የራሳቸው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ያላቸው ከተሞች/ ይገኝባታል።
በከተማዋ እና በአካባቢው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች መገኛ ናት። ፋሲል አብያተ መንግሥት፣ ሰሜን ፓርክ እና ጣና የእንስሳት እና እፅዋት ብዝሃነት ከመገለጫዎቿ ጥቂቶቹ ናቸው።
ጎንደር በአገራችን የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ከተሞች አንዷ ናት፤ ነዋሪዎቿም እንግዳ አክባሪ ናቸው። ሁሉም ኃይማኖቶችና ብሄሮች ተስማምተው የሚኖሩባት ከተማ ነች። ከአዲስ አበባ 748 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር 182 ርቀት ላይ ትገኛለች።
ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ደግሞ 220 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከኤርትራ 314 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የአየር ንብረቷ ወይና ደጋማ ነው። ዓመታዊ የዝናብ መጠኗ እስከ 1ሺ800 ሚሊ ሜትር ይደርሳል። ዓማካይ የሙቀት መጠኗም 20 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል። ከፍታዋ ደግሞ ከ2000 እስከ 2ሺ200 ሜትር ነው።
የጎንደር ከተማ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ያላት ምቹ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶችና እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ባዩህ አቡሃይ ጋር ያደረገውን ቆይታ በዚህ መንገድ አቅርበናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- አሁናዊ የጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ባዩህ፡- ኢንቨስትመንት በአንድ አገር ውስጥ የእውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ቴክኒክ ሽግግር በማምጣት ለፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና በመጫወት በኩል የማይተካ ሚና አለው። ከተማችን ጎንደርም ሰፊ የሰው ሃብት ያለበት አካባቢ ነው። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን እምቅ ሀብት ያለበት አካባቢ መሆኑ ይታወቃል።
ከምንም በላይ ደግሞ ለቱሪዝም መስፋፋት አመቺ የሆኑ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ናት። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ሀብቶችን በመጠቀም ከተማችን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ለበርካታ ዓመታት በተደረገው ጥረትም እጅግ አበረታች የሚባሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ይሁንና ጥረቶቹ እና ውጤቶቹ በሚፈለገው መንገድና ደረጃ ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም።
በመሆኑም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች፣ በጎንደር እና አካባቢው ባሉ የሃብት መሰረቶች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ምቹ ሁኔታዎች፣ በሥራ ሂደት እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ለመፍትሄ መሥራትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት መሥራት ይገባል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ አስፈላጊ ክልላዊ ውይይቶች እና ምክክሮች ተዘጋጅተው የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገውበታል። በቀጣይም በተናበበ መንገድ ለመሥራት አስፈላጊ መድረኮች የሚዘጋጁ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከጎንደር ታሪካዊ ከተማነት አንፃርና አሁን ላለችው ኢትዮጵያ አበርክቶዋን እንድታሳድግ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ባዩህ፡– ጎንደር ከተማዋ ከተቆረቆረች ከ380 ዓመታት በላይ ሆኗታል። በርካታ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሁነቶችን ያሳለፈች ከተማ ናት። በዚያው ልክ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘች ከተማ ናት። ከታሪክ ድርሳናት መረዳት እንደሚቻለው ጎንደር ለ250 ዓመታት የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ሆና ቆይታለች።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሁሉም መስክ የራሷ አሻራ አኑራለች። በመሆኑም ጎንደር ታሪክን ሰንዳ ከዛሬ ላይ ደርሳለች። በቀጣይም በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ከሚኖራቸው ከተሞች መካካል አንዷ ሆና እንድትቀጥል ሁላችንም ኃላፊነታችንን የመወጣት ግዴታ እንዳለብን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት የአገሪቷ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ መጠን እንደ ከተማ ምን እየተሰራ ነው ?
አቶ ባዩህ፡– በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች አሉ። በአጠቃላይ 680 ሄክታር ይሸፍናሉ፡ አራቱ መሰረተ ልማት የተሞላላቸው ሲሆኑ፤ አንዱ ደግሞ በአዲስ መልክ የሚለማ ነው። በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ 155 አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ መንደር እና ከኢንዱስትሪ መንደር ውጭ አሉ።
አግሮፕሮሰሲንግ ምግብና ፋርማሲሲዮቲካል ዘርፍ 44፣ እንጨትና ብረታብረት ዘርፍ 79፣ ኬሚ ካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ዘርፍ አስራ አምስት፣ ጨርቃጨርቅ ቆዳ እና አልባሳት ዘርፍ አስራ ሰባት፣ በቅድመ ግንባታ ሃያ ሰባት፣ ግንባታ ላይ 48፣ ግንባታ ያጠናቀቁ ደግሞ 60 ደርሰዋል። ምርት ማምረት የጀመሩት ደግሞ 33 ፕሮጀክቶች ሲሆኑ በአራቱ የኢንዱስትሪ መንደር 168 ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ደግሞ ለ2ሺ966 ሴቶች እና 2ሺ554 ወንዶች በድምሩ 5ሺ520 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማ አስተዳደሩ በተግባር የሚታዩና ተምሳሌት ሆነው የሚጠቀሱትን ለይቷል?
አቶ ባዩህ፡– በአራት ሄክታር ላይ ያረፈው ዓባይ ኢንዳስትሪ አክሲዮን ማህበር የልብስ ስፌት ጋርመንት (ፋብሪካ) ካፒታል በ450 ሚሊየን ብር ካፒታል ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ696 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ እና አስፈላጊ ሁኔታዎች ሲሟሉ አቅሙ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል አምስት ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
ኤስ ኤፍ የተባለው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ደግሞ ካፒታል ደረጃ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን እስካሁን 80 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በ170 ሚሊዮን ብር ወደ ኢንቨስትመንት የገባው ቢ.ኬቲ.ኤም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም በተመሳሳይ መንገድ ለ80 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ዞብል ቆርቆሮ ፋብሪካ ለ17 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን 29 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ በጎንደር ከተማ 14 ባለ ኮከብ ሆቴሎች አሉ። ባለ አራት ኮኮብ የደረሱ ሁለት ሆቴሎች፣ ባለ ሦስት ኮኮብ ያገኙ ስድስት ሆቴሎች እንዲሁም ባለ ሁለት ኮኮብ ደረጃ የተሰጣቸው ሦስት ሆቴሎች አሉ። ጃካራንዳ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል (ሎጅ) በ170 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለ110 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
በአጠቃላይ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ እና እቅዳቸውን ወደ ተግባር ቀይረው ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል የፈጠሩ ፕሮጀክቶች እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑ ታሳቢ መደረግ ያለበት ቢሆንም ጥሩ ተምሳሌት እንደሆኑ መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህም በተጨማሪ አርባ አምስት ሆቴሎች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ ነው።
በእርግጥ ይህ ቁጥር ጎንደር የቱሪስት ከተማ ከመሆኗ አኳያ በቂ አይደለም። በመሆኑም መሰል ጥረቶች በማገዝ እና ወደ ኢንቨስትመንት የሚመጡ ሌሎች ባለሃብቶችን በመደገፍ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ጎንደር የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ መጠን በአገልግሎት ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንትስ ምን ይመስላል?
አቶ ባዩህ፡– በቱሪዝም ሃብት ከተማችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ ታላላቅ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ ከፍተኛ የሆነ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስት የሚጎበኟት ከተማ ነች። ለአብነት ፋሲል ግንብ፣ ጉዛራ ቤተመንግሥት፣ ፋሲል መዋኛ፣ ደብረብርሃን ስላሴ ገዳም፣ የቁስቋም ገዳም፣ ሸህ ዓሊ ጎንደር፣ የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ፣ ከ200 በላይ አንበሶች የሚገኙበት አልጣሽ ፓርክና የመሳሰሉት ቱሪስቶችን በእጅጉ ከሚስቡና ዕይታቸውን ከሚማርኩ የጎንደር ከተማና እና አካባቢዋ ፀጋዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። የመገጭ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለው ሀይቅ ለሎጅ እና ሪዞርት አቅም የሚፈጥር መሆኑ፣ በከተማችን የተራራ ልማት ለማልማት የዲዛይን ሥራም እየተከናወነ ነው።
ለባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ የሚውል መሬትም በጨረታ ለባለሃብቶች የሚቀርብበት አሰራር ወደተግባር ተቀይሯል። ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑም የታመነበት ሲሆን አስፈላጊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ መጠን ይህን የቱሪስቶችን ፍሰትና ፍላጎት ሊያስተናግድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሁንም በቂ ባለመሆናቸው ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ አዋጭ ነው። መንግሥትም ለስኬታማነቱ ያላሰለሰ ጥረትና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ጎንደር ሃብቷ እንዲሁ በጥቂቱ የተወሰነ አይደለም። በብዙ መልክ፣ በትልቅ መጠንና ስፋት፣ በተለያዩ አቅምና ገጽታዎች ባለሃብቶችን የመሳብ አቅም ያላት ከተማ ናት። በውሃ ሃብት በኩልም የመገጭ-ሰራባ፣ ርብ እና ጉማራ የመስኖ ፕሮጀክቶች 80ሺ ሄክታር መሬት የሚያለሙ እና ሰፊ የግብርና ምርት ማግኘት የሚቻልበት አካባቢ ነው። ይህን ተከትሎም ለሚገነባው አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶች ከወዲሁ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል ብለን እናምናለን።
አብዛኛው የጣና ሀይቅ ክፍል መገኛ አካባቢ መሆኑ ሌላው አማራጭ ነው። የታሸገ ውሃ ማምረት የሚቻልባቸው ምቹ ሁኔታዎችም አሉ። አካባቢው የተማረ፣ የሰለጠነ፣ ሥራ ወዳድ እና እንግዳ አክባሪ ህዝብ የሚገኝበት ነው።
የመንግሥትና የግል የትምህርት ተቋማት በሁሉም አካባቢዎች በመገንባታቸው የትምህርት ሽፋን እያደገ ነው። በመሆኑም ኢንቨስትመንትን ሊያሳልጥ የሚችል የሰለጠነ ወይንም ደግሞ በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል በአካባቢው መኖሩ ትልቅ ፋይዳ አለው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ከተማ አስተዳደር ባለሃብቶች በምን ላይ ቢሰማሩ ትርፋማ ይሆናሉ ብሎ ያምናል?
አቶ ባዩህ፡– በርካታ ያልተሰራባቸው ዘርፎች አሉ። ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ፣ ባለሃብቱ የሚጠቀምበት ብሎም እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን ኢንቨስትመንቶች ለማካሄድ ጥሩ አማራጮች አሉ።
በከተማዋ አዳሪ ትምህርት ቤት የለም። ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ቢሳተፉ ራሳቸው ተጠቅመው ከተማችን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማዘጋጀት ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይችላሉ።
በግብርናው፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ያልተነካ እምቅ ሃብት ያለው አካባቢ ነው። የአየር ፀባዩ እና የሚገኝበት አካባቢ ስትራቴጂክ መሆኑ በብዙ መንገድ ተመራጭ ያደርገዋል። በመሆኑም ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉ በመሆኑ በጥቂቱ የተገደበ አይደለም። ይህም በመሆኑ ባለሃብቶች ትኩረታቸውን የሚጥሉበት ስፍራ እንደሚሆን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ባለሃብቶችን ሊስብ የሚችል መሠረተ ልማት አኳያ ምን ምን ሥራዎች ተሰርተዋል?
አቶ ባዩህ፡– እንደ ሀገር ሆነ እንደ ከተማ ሲታይ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ይታወቃል። መንግሥትም ይህን በሚገባ ስለተገነዘበ ክፍተቶቹን ለማሟላት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ነው። እኛም እንደ ከተማ አስተዳደር አቅም በፈቀደ መጠን የሚጠበቅብንን እየሠራን ነው።
መሰረተ ልማት ለኢንቨስትመንት ስኬት ዋንኛውና ለውጤቱም ቁልፍ ሚና እንዳለው እንገነዛባለን። አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጎንደር ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለሃብቶች ሊገነዘቧቸው የሚገባው ብዙ መልካም ዕድሎች መኖራቸውን ነው። ለአብነት ከጅቡቲ-ወረታ-አዘዞ- ሱዳን የሚዘረጋው የባቡር መስመር መኖሩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
በከተማዋ አየር መንገድ ያለ መሆኑም የተቀላጠፈና በአጭር ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ስለሚያስችል ከምቹ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ነው። የወረታ ደረቅ ወደብ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱም ፋይዳው የጎላ ነው።
በቀጣይ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ እና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስመጣትም የኤርትራን እና የሱዳንን ወደብ በቀላሉ የመጠቀም ዕድል መኖሩ ትልቅ ዕድል ነው። በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናም ከመሰረተ ልማት ባሻገር ለኢንቨስትመንት መፋጠንና ማደግ ሚና የጎላ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን ለመሣብ የሚያግዙ አስቻይ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ባዩህ፡– የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመተግበርና ባለሃብቱን ለመሳብ በሁሉም ረገድ አስቻይ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው። በዚህ ረገድ እንደ ሀገር፣ ክልል ብሎም ከተማ አስተዳደር ጥሩ ጅማሮዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት የተመቻቸ ፖሊሲ እየተተገበረ ነው። በተወሰኑ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ፕሮጀክቶች ከሁለት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ከገቢ ግብር ነፃ መብት ተሰጥቷል።
ቢያንስ 60 ከመቶ የሚሆነውን ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ወደ ውጭ የሚልክ ወይም ወደ ውጭ ለሚልክ ባለሀብት በምርት ወይም በአገልግሎት ግብዓትነት የሚያቀርብ ከሆነ በኢንቨስትመንት አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ላይ ከተፈቀደለት ማበረታቻ በተጨማሪ ለሁለት ዓመት ከገቢ ግብር ነፃ መሆኑ ትልቅ እምርታ የሚያመጣና ከምቹ የፖሊሲ ማዕቀፎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ለሚያቋቁሙት አዲስ ወይም ነባር ድርጅት ለማስፋፋት ወይንም ደግሞ ለማሻሻል የሚያስፈልጉ የካፒታል እና የግንባታ እቃዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ማስገባት መቻላቸው ለባለሃብቱ ትልቅ እፎይታ ነው። የኢንቨስትመንት አዋጁ እንደ ኢንቨስትመንት ኘሮጀክቶች ዓይነትና ባህርይ የተወሰነ ቢሆንም ተሽከርካሪዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ነፃ ማስገባት መፍቀዱም ፋይዳው የጎላ ሲሆን ባለሀብቶችን ለመሳብ ከአስቻይ ሁኔታዎች ውስጥ ሌላኛው ነው።
እንደ ክልል ሲታይ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እና ትልቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በሊዝ በዝቅተኛ ዋጋ በምደባ እያቀረበ ይገኛል። የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር ጥናት እያጠናቀቀ ሲሆን ይህም ብዙ ችግሮችን ለማቃለል ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።
መመሪያዎችን በማውጣት እና ለሥራ እንቅፋት የሚባሉትን በማሻሻል በኩል ፈጣን ምላሽ እየተሰጠም ይገኛል። የባለሙያዎችን እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን አቅም ለመገንባት ስልጠና በየጊዜው እየተሰጠ መሆኑም ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ ትልቅ ድርሻ አለው።
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ከተማ አስተዳደሩ በራሱ አቅም የሚያከናውናቸው ተግባራትስ ምንድን ናቸው?
አቶ ባዩህ፡- እንደ ጎንደር ከተማ ብዙ ሥራዎችን እየተከናወኑ ነው። 490 ሄክታር መሬት ተለይቶና በሳይት ፕላን ተመላክቶ ካሣ ለመክፈል ሽንሻኖ እየተሰራ ነው። አምስት ኢንዱስትሪ መንደር በመከለል መሰረተ ልማት አሟልቶ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ፕሮጀክቶች እያስተላለፈ ይገኛል። ለከተማዋ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እና የተመረጡ አገልግሎት ዘርፍ ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳደሩ የውሳኔ አስተያየት ለክልል ቀርቦ እየተወሰነና እየተላለፈ መሆኑም ለኢንቨስትመንቱ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም።
፣ በክልሉ ፀድቀው በመጡ መመሪያዎች መሰረት የሚቀርቡ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ለማስተናገድና ባለሃብቶችንና ዜጎችን ለመጥቀም እየተሰራ ይገኛል። የኢንቨስትመንት ቦርዱ በየጊዜው እየተገናኘ ተግባሩን እየመራ መሆኑ፣ መሬት በምደባና ከሊዝ በሚታሰብ ካሣ ክፍያ የሚሰጥ መሆኑ፣ መሬት ወስደው አጥረው የሚያስቀምጡ ባለሀብቶችን ነጥቆ ለትክክለኛ አልሚዎች በማስተላለፍ በኩል እየተሰራ መሆኑም እንደ መልካም አጋጣሚና አስቻይ ሁኔታዎች የሚወሰዱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ባሻገር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ባዩህ፡– ጥረቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። እነዚህም ከባለሃብቱ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የመነጨ ነው። የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ ባለመሆኑ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት በኩል አሁንም ችግሮች አሉ።
ወደ ሥራ ባልገቡት ላይ ተከታትሎ እርምጃ አለመውሰድ፣ መሰረተ ልማት የተሟላለት የለማ መሬት በስፋት አለማቅረብ፣ የሚቀርብን ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት በአግባቡ አለመገምገም፣ የአካባቢውን የመልማት አቅም የሚሸከም ኢንዱስትሪ ፓርክ አለማቋቋም፣ ከተማዋ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ያላትን አቅም ለመጠቀም የሊዝ አዋጁ መሬትን በምደባ እንድናስተናግድ የሚፈቅድ አለመሆኑ፣ አጋር አካላት የኢንቨስትመንት ጥያቄን በፍጥነት በማስተናገድ በኩል ችግሮች መኖራቸው፣ በተፈለገው መጠንና ፍጥነት ብድር አለማግኘት፣ የመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እጥረት በመንግሥት በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።
በባለሃብቱ በኩል ደግሞ መሬት አጥሮ የመቀመጥ እና በፕሮጀክቱ መሰረት ወደ ሥራ አለመግባት፣ በበቂ ጥናት ወደ ሥራ አለመግባት በዚህም ምርት ጀምሮ ማቆም ይስተዋላል።
በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በቅድመ ዝግጅትም ሆነ በፕሮጀክት አመራርና አፈፃፀም ላይ የአቅም ውሱንነት መታየት፣ በተፈቀደ ስታንዳርድ መሰረት አለመስራት፣ አንዳንድ ባለሃብቶች የሚቀርፁት ፕሮጀክት ትኩረት ቦታን ለመውሰድ ብቻ መምጣት፣ በፕሮጀክት በተቀመጠው መሠረት የሥራ ዕድል አለመፍጠር፣ ከማበረታቻ ነፃ የገባ ንብረትን ለታለመለት ዓላማ ያለማዋል ዋንኞቹ ችግሮች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ በቀጣይ ምን ዓይነት ሥራዎች ይከናወናሉ?
አቶ ባዩህ፡ ማኑፋክቸሪንግ በተለይ አግሮፕሮሰሲንግ እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ የወደፊት ትልቅ ዕድሎች በመሆናቸው በልዩ ትኩረት ይሰራል። ኢንዱስትሪ መንደር ቁጥር አምስት 490 ሄክታር መሬት በፍጥነት መሰረተ ልማት አሟልቶ በከተማችን ትኩረት በተሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የሚያመለክቱ ባለሃብቶችን ማስተናገድ ይጠበቅብናል። የማኑፋክቸሪንግ እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪን ዕድገት ሊሸከም የሚችል የሠለጠነ የሰው ሃይል ዝግጅት ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን የሚል እምነት አለን።
የተራራ ፕሮጀክት ዲዛይን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለትክክለኛ አልሚዎች እንዲተላለፍ ይደረጋል። የመገጭ ግድብ አካባቢ ዲዛይንና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት በማጠናቀቅ ለሎጅ እና ሪዞርት ለትክክለኛ አልሚዎች ክፍት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። ከአጋር አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር የጠነከረ ይሆናል። የኢንቨስትመንት የምክክር ቡድን በማቋቋም በየጊዜው ተግባሩ እየተገመገመ እንዲመራ ይደረጋል።
በባለሃብቶች በኩልም፤ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በከተማችን ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በመሆኑም የአካባቢውን ጂኦግራፊያዊ ጠቀሜታ የተገነዘበ ፕሮጀክት በማዘጋጀት ወደ ልማት እንዲገቡ ይደረጋል። የዳያስፖራው ተሳትፎ በከተማችን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዲኖረውም ብዙ ሥራዎች ይጠበቁብናል ብለን እናምናለን።
በቀጣይ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንደስትሪ እንዲቋቋም ግብዓት በማምረት ሰፊውን ድርሻ እንዲወጡ ይደረጋል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ ያለብንን የዶላር እጥረት በማቃለል በኩል ትልቁን ድርሻ ይወጣሉ። ከተማችን ከቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን መሥራትም ዋንኛ ሥራችን ነው። በመሆኑም ለኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማዘጋጀት ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅብን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ ችግሮችና ቀጣይ ሥራዎችን በማስመልከት ለአንባቢያን ለሰጡት መረጃ አመሰግናለሁ።
አቶ ባዩህ፡- በዝግጅት ክፍላችሁ የሚዲያ ሽፋን ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013