ጌትነት ተስፋማርያም
ዶክተር በከር ሻሌ በምዕራብ አርሲ ዶዶላ ወረዳ ቡራጫሌ የተሰኘ የገጠር መንደር ውስጥ ከአርሶአደር ቤተሰብ ነው የተወለዱት። እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በአደጉበት አካባቢ ከተማሩ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዶዶላ ከተማ ተከታትለዋል።
በመቀጠልም ሮቤ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው የአንድ ዓመት የመምህርነት ትምህርት ወስደዋል። በመጀመሪያ ሥራቸው መምህር ሆነው ሥራ ጀምረዋል። በመምህርነት እያገለገሉ ሳለ በትውልድ ቦታቸው የወረዳ አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተመረጡ። በወቅቱም የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን /ኦህዴድ/ ተቀላቅለው የኢህአዴግ አባል ሆነዋል።
ከዚያም የባሌ ዞን ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ሰርተዋል። በ1998 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ሲመሰረት እርሳቸው የዞኑ አስተዳዳሪ ሆነው በሻሸመኔ ከተማ ሥራ ጀመሩ። ባሌ ዞንንም በአስተዳዳሪነት መርተዋል። በቀጥታም ወደ ክልል አመራርነት በመሸጋገር የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው በ2000 ዓ.ም ተሹመዋል።
የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ፣ የፌዴራል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል። የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነውም ሠርተዋል።
ለሦስተኛ ዲግሪ ወደ ደቡብ ኮሪያ ካቀኑ በኋላ የፖሊሲ ጥናት ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደሀገር ቤት ተመልሰዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ይገኛል። ዶክተር በከር ሻሌ ባሳለፏቸው የፖለቲካ ህይወትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን:- በክልል አመራርነትዎ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩ የተለያዩ ጫናዎች በተለይ ከህወሓት እንደነበረብዎት ይነገራል፤ ምን አይነት ተጽዕኖ ነበር የነበረው?
ዶክተር በከር ሻሌ:- በወቅቱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆኜ ስመደብ የቀድሞ አመራርነት ልምዴ የዞን አስተዳደር ላይ ነበር። ምደባው ሲሰጠኝ በወቅቱ የነበሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው። አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ። ለቢሮው እና ለክልሉ ፕሬዚዳንት ነው ሪፖርት የማደርገው። በቀጥታ ከህወሓት ትዕዛዝ አልቀበልም። ትዕዛዙ የሚመጣው ከራስህ አመራር ነው።
ነገር ግን በሥራችን ላይ ያለውን የህወሓት ጣልቃ ገብነት ሳንወድም ይሁን በዝምታ አሊያም በአድርባይነት ፈቅደንላቸው ነበር። ይህን ችግር ህዝብ ሲተቸን ይውላል፤ ያድራል። እኛም ውስጥ ለውስጥ እንነጋገርበታለን። በመሆኑም ህወሓት በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ በእጅ አዙር የምታደርገው ተጽዕኖ ነበር።
በፀጥታ መዋቅር ላይ የጥምር አመራር ኮሚቴ ተብሎ በመከላከያም ሆነ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ በነበራቸው አመራርነት ጣልቃ ገብተው ክልሉ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን መካድ አይቻልም። ህወሓቶች አዘውኝ ይህንን ፈጽሜያለሁ የምለው ነገር ግን የለም።
ይሁንና ሥርዓቱ በእራሱ ህወሓትን የኢህአዴግ ዋና ማዕከል አድርገው ፈጥረውታል። በመሆኑም ተጽዕኖ መፍጠራቸውን መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ይተገብሩታል። ለአብነት ኦነግን በአሸባሪነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈርጀው አባላቶቹ በህጋዊ መንገድ በተገኙበት እንዲያዙ እና እንዲታሰሩ ይደረጋል። ይህ የህወሓት ተቋማዊ የእጅ አዙር አሠራር ውጤት ነው። በእጅ አዙር ግን የሚፈልጉት ጉዳይ ላይ በኢህአዴግ በኩልም ሆነ በክልል አመራር በኩል የእራሳቸውን ሃሳብ ማራመዳቸው አይቀሬ ነበር።
አዲስ ዘመን:- በፖሊስ ኮሚሽነርነት የሚሰሩ ኃላፊዎች በአብዛኛው ከቦታቸው ቢነሱም በፖለቲካ አመራርነት ነው ይበልጥ የሚያተኩሩት፤ እርስዎ ደግሞ ከፖሊስ ኮሚሽነርነት ሲነሱ ከፖለቲካ ራቅ ወዳለ ቦታ ማለትም ወደኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ነው የተመደቡት፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶክተር በከር ሻሌ:- ምርጫ 2002 ዓ.ም ተከትሎ አቶ አባዱላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤነት ተሸጋገሩ። ወደፖሊስ ኮሚሽነርነት በመደቡኝ አቶ አባዱላ ገመዳ ምትክ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆነው አሁን በህይወት የሉም ነብሳቸውን ይማርና አቶ አለማየሁ አቶምሳ ተተኩ። እርሳቸው ሲመጡ እኔን ወደኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ መደቡኝ።
በወቅቱ ቃል በቃል የተነገረኝ ሕብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከር አለብን፤ ወደእዛ መሄድ አለብህ የሚል ነው። በዚህ ጊዜ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፍተኛ የማዳበሪያ ግዥ ዕዳ የነበረባቸው ሲሆን፤ በርካታ ሀብት የሚጠፋበት ቦታ ነበር።
ማህበራቱ ከፍተኛ የሙስና ቦታ ስለሆኑ እንደክልል ይህን መግታት አለብን ስለሆነም ካለን የሰው ኃይል ወደ ኤጀንሲው መድበን ችግሩን መግታት አለብን የሚል እምነት ነበር። የፖሊስ ኮሚሽኑን ቦታ ደግሞ በሙያው ልምድ ባለው ፖሊስ መምራት እንችላለን በሚል አንድ ኮማንደር ወደቦታው ተመደቡ። እኔም ወደህብረት ሥራ ሄጄ ማህበራትን መልሶ ለማጠናከር እና ከገቡበት አደጋ ለማውጣት የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ።
የአመራር ለውጥ ሲደረግ በክልል ደረጃ የስልጣን ሽግሽግ ይኖራል። አቶ አለማየሁ የእራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል፤ አሁን ላይ በህይወት ስለሌሉ መውቀስ አሊያም ይሄ ነው ማለት አይቻልም። የራሳቸው እይታ ስልነበራቸው በምደባ ነው ወደኤጀንሲው ያቀናሁት።
አዲስ ዘመን:- የቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ህልፈት አነጋጋሪ ነበር፤ የእርሳቸው ህልፈተ ህይወት በኦህዴድ ፓርቲው ውስጥ የፈጠረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር በከር ሻሌ:- የአቶ አለማየሁ አቶምሳን ህልፈት ምክንያት ለማወቅ አልችልም። በወቅቱ በሥራ ላይ እያሉ ታመው ወደውጭ ሀገር ለህክምና መሄዳቸውን አውቃለሁ። የፓርቲያቸው ሥራ አስፈፃሚም ሆነ የክልሉ መንግሥት እንዲታከሙ በቂ ድጋፍ አድርጓል። የህመማቸው ምክንያት በቤተሰብ እና በሐኪም ነው የሚታወቀው። ከዚያ ውጭ ያለውን የሚናፈሰው ጉዳይ በመርዝ ነው ወይም በሽኩቻ ነው የሚሉትን አሁን ይሄ ነው ለማለት ያስቸግረኛል።
እውነት ለመናገር ከህሊናዬ በላይ ነው። ወይ በግምት አውርቼ ልዋሽ ስለምችል ለቤተሰብ እና ለሕክምና ባለሙያዎች ብተወው ይሻላል። በህይወት እያለ ግን ይሄ ነው ብሎ የነገረኝ ነገር የለም።
እንደፓርቲ ግን በወቅቱ የነበረውን ጊዜ በእርጋታ መርተነዋል። አቶ አለማየሁ ታሞ ሳለ አስታመነዋል። የፓርቲው መሪ በመሆኑ ጊዜ ወስዶ ድርጅታቸው አሳክሟል። ይህን ማድረጋችን ተገቢ ነው። ለህክምና የቆዩበት ከሁለት ዓመት በላይ በመሆኑ ግን የአመራር ክፍተት ፈጥሯል። ተመልሶ አገግሞ ይመጣል የሚል ተስፋ ነበር።
በፓርቲም ሆነ በፕሬዚዳንት ቢሮ በኩል በምክትል ነው ክልሉ ሲመራ የቆየው። ያንን ማድረጋችን እንደድርጅት ዋጋ አስከፍሎናል። ምክንያቱም ውሳኔ የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች ተጓተዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በወቅቱ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ የነበረው የፊንፊኔ ዙሪያ እና የአዲስ አበባ ማስተርፕላን ጉዳዮች እርሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ የተጀመሩ ጉዳዮች በመሆናቸው ለማየት እና ለመወሰን ክፍተት ፈጥሯል።
ውሳኔ ለመስጠት የወሰደው ጊዜ እና ክፍተት ደግሞ ኪሳራ አስከትሏል። ጓዱ ካረፈ በኋላ በእርጋታ ነው በሀዘን የተሸኘው፤ ከዚያም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈፃሚው በቅንጅት ምርጫ ተደርጎ መተካካት ተደርጓል። የነበረውንም የፓርቲ ስሜት በአጠቃላይ በእርጋታ አልፈነዋል።
አዲስ ዘመን:- በወቅቱ በፓርቲው ውስጥ የተደረገው የሥልጣን ሽግግር ወይም መተካካቱ የተሳካ ነበር ብለው ያስባሉ?
ዶክተር በከር ሻሌ:- እንደኦህዴድ በመተካካት ሂደቱ ከገባንበት ችግር ይዞን ሊሻገር የሚችል ሁኔታ ሳንፈጥር ቀርተናል። በእኔ እምነት በወቅቱ ከአቶ አለማየሁ ህልፈት በኋላ መተካካቱ ያመጣቸው አመራሮች ችግሮቹን ይበልጥ እንዲባባሱ አደረጉ። ውጥንቅጡ እየተባባሰ ነው የሄደው። ጓድ ሙክታር ከድር ነበሩ አመራር የሆኑት።
የተከማቹ ችግሮች መደራረብ አመራሩ ሊፈታው አልቻለም። ከሁለት ዓመት በላይ ፕሬዚዳንቱ ለህክምና ባለመኖራቸው ምንም አመራር ቢተካ ከችግሮቹ ልንወጣ አንችልም። የተተኩትም አመራሮች እንዲሁ ሥራቸውን እንዲለቁ ተደርጎ ነው እንዲስተካከል የተደረገው።
አዲስ ዘመን:- በአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ ማስተር ፕላን ጉዳይ በፓርቲያችሁ ውስጥ የነበረው ግልጽነት እስከምን ድረስ ነበር? በአጀንዳው ላይ የህወሓት ሚና ምን ነበር?
ዶክተር በከር ሻሌ:– እኔ እስከማውቀው ድረስ ማስተርፕላኑን የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሳያውቀው ነው ለአጀንዳነት እንዲቀርብ የተደረገው። በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በነበሩ ግለሰቦች አነሳሽነት የተጀመረ ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ ለሁሉም ነገር ህወሓትን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ብዬ አላምንም። ከኋላ የህወሓት ሰዎች ግፊት ሊኖር ይችላል።
ይህን መቋቋም አለመቻል ግን የእኛም ድክመት ነው። ግፊት፣ ተጽዕኖ እና ፍላጎት ከህወሓት ሊኖር ይችላል። ይህን ግን አንጥሮ ለይቶ ይበጃል አይበጅም በሚል ለይቶ መደገፍ እና መቃወም አለመቻል ግን የራሳችን የውስጥ ድክመት ነው ብዬ ነው የማስበው።
ማንም ይገፋፋው ማንም ግን ጉዳዩን ያስፈጽሙ የነበሩት የእኛው ሰዎች ናቸው። ጉዳዩ ወደማዕከል ተወስዶ የኢህአዴግ አጀንዳ ሆኗል። ኦህዴድ ከላይ እንደኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ይህ አጀንዳ የልማት አጀንዳ በመሆኑ መፈፀም አለበት እንጂ በተወሰነ ቡድን አሊያም በህዝብ አማካኝነት መፍረስ የለበትም የሚል ጫና ተደርጎበታል። በሌላ በኩል ህዝብ ስላልተቀበለው ኦህዴድ በመካከል ሳንድዊች ሆኗል።
ነገሮች ከተካረሩ እና ህብረሰተቡም የማስተር ፕላኑን ጉዳይ መቃወሙን ሲገፋበት የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ ጉዳዩን ማጤን ጀመረ። ሥራ አስፍፃሚው ውስጥም የግንዛቤ እና የግልጽነት ልዩነት አለ፤ ሁሉም አላመነበትም።
በወቅቱ የልማት አጀንዳ ቢሆንም ህዝቡ ግን አላመነበትም ነበር። ባላመነበት ግን እንዲቀበለው ግፊት አድርገናል። አንድ ጊዜ የህዝብ ጫና ሲበረታ የማስተርፕላኑን ጉዳይ በይደር አቆየነው። ይህ በመሆኑ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል።
በእኛ ሀገር የፖሊሲ አወጣጥ ታሪክ አስተማሪ ሆኖ ማለፍ ያለበት ነው ብዬ የማምነው ጠቃሚም ይሁን ሳይንሳዊ ጉዳይ ህዝብ እስካላመነበት እና እስካልደፈው ድረስ ፋይዳ እንደሌለው ያስተማረ ወቅት ነው።
በህዝብ ቅሬታ የተነሳ የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ በድጋሚ ጉዳዩን በማጤኑ አጀንዳው በክልሉ ተፈፃሚ እንደማይሆን ደምድሞ በውሳኔ አስተላልፈናል። ኦህዴድ በኢህአዴግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን ጉዳይ አላስፈጽምም፤ ህዝብ ያልተቀበለው አያስኬደኝም ብሎ በአቋም ካስኬዳቸው ጉዳዮች ተጠቃሽ የሆነ ውሳኔ አስተላለፈ።
አጀንዳውን ተግባብተንበት ብንፈጽመው ልማትና ውጤት እያመጣ አይደለም፤ በግፊት ፈፃሚ የሆነው ህዝብ ሳያምንበት የምንወስደው ውሳኔ ከፍተኛ ጉዳት አለውና ከዚህ የባሰ ችግር ሳይመጣ ስለማስተርፕላኑ ጉዳይ ማቆም አለብን የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ።
አዲስ ዘመን:- በወቅቱ በኢህአዴግም ሆነ በህወሓት በኩል የደረሳችሁ አጸፋዊ ምላሽ ምንድን ነበር?
ዶክተር በከር ሻሌ:– በውሳኔያችን ተገመገምንበት። ተሸንፋችኋል ህዝብን ማሳመን አልቻላችሁም ተባልን። አዎ ተሸንፈናል፤ የተሸነፍነው ደግሞ በህዝብ ነው
ብለናል በወቅቱ። ኦህዴድም የማስተርፕላኑን ጉዳይ በውሳኔ አቁሞ ሥራውን ቀጠለ። ከዚያ በኋላ እናንተ በግድ ፈጽሙ ብሎ የመጣብን የለም። ፓርቲው ከለውጡ በኋላ ኦዲፒ ተብሎ መጠራት ከጀመረ በኋላም ጉዳዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምድሞ እንደተወሰነ ነው የቀረው።
አዲስ ዘመን:- ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የህወሓት የበላይነት እንዴት ይገለጽ ነበር፤ ምን ታዝበዋል በወቅቱ?
ዶክተር በከር ሻሌ:- ኢህአዴግ ውስጥ አባል በነበሩ ፓርቲዎች ላይ የህወሓት የበላይነት አለ፣ ተጽዕኖ አለ የሚለው በመጀመሪያ ትክክልኛ ጉዳይ ነበር። ህወሓት ሲጀምሩ አንስቶ የነበራቸው የበላይነት አስተሳሰብ ተዳምሮበት በተለያዩ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በሌሎቹ ፓርቲዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
እንደኢህአዴግ አንድ ወቅት ላይ የህወሓት የበላይነት አለ? ወይስ የለም? የሚል ክርክር ነበር፤ አዎ የበላይነቱ አለ ካልክ ትገመገምበት ነበር። ይሁንና አንድ በሥልጣን ደረጃው ዝቅ ያለ የህወሓት አባል በየተቋሙ ውስጥ ከእርሱ በላይ ያለውን አመራር ሲያዝ እና ሲያስፈራራ እንደሚውል ግን የሚታወቅ ነው።
ለአብነት እኔ እራሴ ከላይ ሆኜ የሰራሁባቸው ቦታዎች አሉ፤ እኔ በየተቋማቱ የበላይ ነኝ ማለት ግን በሁሉም ውሳኔዎች ላይ የበላይ ነኝ ላያስብል ይችላል። አንድ ሰው ከላይ ስለሆነ አመራር ነው ማለት አይደለም። የተጫነበት ጽንሰሃሳብ ታች ያለውን የበላይ አድርጎ የሚቀርጽ ከሆነ ችግሩ እዛ ጋር ነው። በተግባርም እንደታየው ህወሓቶች ከበታችም ይሁኑ ከላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ፍላጎታቸውን ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል።
በሕግ ደረጃ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ አራቱም ፓርቲዎች እኩል የአባላት ቁጥር ቢኖራቸውም ህወሓት ግን ሲስተማቲካል በሆነ አካሄድ የሃሳብ የበላይነቱን ወስዶ የሚገዛው እርሱ ነበር። በአካልም የበላይ የሆኑባቸው ቦታዎች ነበሩ።
ለአብነት መከላከያ ሠራዊት ውስጥ፣ የደህንነት ተቋማት እና ሌሎች በፀጥታ ዘርፎች ሥር በቁጥርም በርካታውን ቦታ የያዙት እንሱው ነበሩ። በተጨማሪ በኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ሆን ተብሎ የበላይነቱን ቦታ ይዘው ሀገሪቷን ሲመሩ ቆይተዋል። ኢህአዴግ ውስጥ ህወሓት የሚለው ሃሳብ ተፈፃሚ እየሆነ ሌሎች ተሳታፊ ሆነው ነው የኖሩት።
አዲስ ዘመን:- ከክልል አመራርነት በተጨማሪ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋልና በወቅቱ ይፈፀም የነበረውን የሙስና ወንጀል እንዴት ይገልጹታል፤ የተቋሙ ኃላፊነት ትልቁስ ፈተና ምንድን ነበር?
ዶክተር በከር ሻሌ:- በገቢዎችና ጉምሩክ አመራርነት ቆይታዬ ትልቁ ፈተና ብዬ የማስበው መስሪያ ቤቱ የባለብዙ ድርሻ ተቋም በመሆኑ ብዙ ባለጉዳዮች አሉት። መንግሥት ባለጉዳይ ነው የግብር ገቢ ይፈልጋል።
ከሸጡት ላይ ታክስ የሚከፍሉ ነጋዴዎች አሉ። ተቀጥረው የሚሰሩበት ብቻ ሳይሆን ብዙ ለቃቃሚ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ነበሩ። በሌላ በኩል ኮንትሮባንዲስቱ እና በአቋራጭ ማካበት የሚፈልጉ አሉ። የውጭዎቹ ደግሞ ሠርተው ከዚህች ታዳጊ ሀገር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው በአውሮፕላን ባህር አሻግረው የሚያሸሹ አሉ። የእነዚህን ተዋናዮች ባህሪ አውቆ መምራት ጥበብና ትዕግስት ይጠይቃል።
በወቅቱ የመንግሥትን የወጪ ፍላጎት ለመሸፈን ትልቅ ጥረት አድርገናል። ቢሮክራሲውንም ለማጽዳት ሞክረናል። ጭንቅላት ላይ በመሥራት እና ከዚያ አልፎ የመጣውን ባለችን ትንሽ የምርመራ ሥራ እና ማስረጃ ለማጥራት ሞክረናል።
ጥገኛ ነጋዴው መስመር ይዞ እንዲሠራ ተሞክሯል። የተቋሙ ከፍተኛ ችግር ግን ሠርቶ በሠራው ልክ ግብር የሚከፍለው ነጋዴ ውስን መሆኑ ነው። ካገኘው ሀብት እያምታታ ግብር መክፈል የማይፈልግ ብዙ ነው።
በርካታ ተሳታፊዎች ያሉበት ኮንትሮባንድ ንግድ ደግሞ አለ። የጦር መሣሪያ ነጋዴ አለ፤ የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር የጥቁር ገበያ ነጋዴ አለ፤ ቀረጥ ሳይከፍል ዕቃ መርካቶ የሚያወርድ አለ። በርካታ ጊዜ በመከላከያ ተሽከርካሪዎች ዕቃዎች ተጭነው ወደሀገር ይገባሉ ይባላል፤ እኔ በዓይኔ ይህን ባላይም በተደጋጋሚ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ውዝግቦች ነበሩ። በመረጃ ላይ ተመርኩዤ ለማጥራት ሞክሬያለሁ።
ያን ያክል ግን ተቋሙን አሻግሬዋለሁ/ ትራንስፎርም/ አድርጌዋለሁ ብዬ ባላምንም የማረጋጋት ሥራ ግን ተሠርቷል። የሌብነቱ መስመር አንደኛ ነጋዴውና ባለስልጣኑ ወይም የጉምሩክ ሠራተኛው የመናበብ ሁኔታ ነበረው።
የድንበር ጠባቂዎችም ይሁን የጉምሩክ ሠራተኛው አሊያም በየክልል ያለው ሚሊሻ እና የፀጥታ ሃይል ከኮንትሮባንዲስቶች ጋር ተናቦ ነው የሚሰራው። በሌላ በኩል በዋናው በር ቀረጥ ተከፍሎበት መግባት ባለበት የአየር መንገድም ይሁን የወደብ መስመር በኩል የሚመጣ ዕቃ ላይ የሚሰሩ ሸፍጦች ነበሩ።
ሙሉ በሙሉ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ዕቃዎች ይገባሉ ወይም ቀረጣቸውን አሳንሶ የመተመን ደባ ነበር። ይህ ውስብስብ በሆነ መንገድ በቅንጅት ከባለሀብትም ሆነ ባለሥልጣናት ጋር ይሠራል።
ካልዋሸሁ በስተቀር ግን እገሌ የሚባል የመንግሥት ባለሥልጣን ኮንትሮባንዲስት ነው ብዬ የምናገርበት ሰው የለም። እንደ ኢዴህአዴግ ግን በወቅቱ የነበረው አጠቃላይ ሥርዓት ሙሰኛ ነው። <<ስቴት ካፕቸርድ>> እንደሚባለው በመንግሥት ደረጃ ሙስና ተስፋፍቷል። ለሙስና የተመቸ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሰፍኖ ነበር። ከላይ እስከታች ያለው ባለሥልጣን እና ሠራተኛና ነጋዴ ንፁ አይደለም። ይህ የሚገለፀው ደግሞ ከአስተሳሰብ ጀምሮ እስከ ተግባር ድረስ ነው።
በአደረጃጀት እና በሰው ኃይል ደረጃ በዘመድ የሚቀጠር እና ሙያ የሌለው ይበዛል፤ ሀገሩን የሚወድ ሳይሆን ለመጠቃቀም የሚፈልግ የተሰባሰበበት ነበር። ያዡም አይዝም፤ ሰራቂውም አይጋለጥም። በመጨረሻ ሰዓት ማነው የሰረቀው? ማን ሙስና ሠራ? የምትለው መጨረሻ ላይ ከደመወዙ በላይ ከኑሮው በላይ ሀብት አከማችቶ ስታየው ብቻ ነው ለማወቅ የምትሞክረው። ሙስናው የሥርዓቱ ውጤት ሲሆን እገሌ እና እገሌ ሳይሆን እንደአጠቃላይ ነው ሙሰኛ የነበረው። ሙስናው እንዲስፋፋ ሥርዓቱ ፈቅዶ ነበር ያልኩት ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን:- በወቅቱ አልሰረቀም፤ ሙስና አልሰራም የምንለው ባለሥልጣን ያልፈለገው ብቻ ነበር እንጂ ወንጀሉን ቢፈጽምም ማንም የሚከለክለው የለም ማለት ይቻላል?
ዶክተር በከር ሻሌ:- እኔ በእራሴ አልሰረኩም። እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው አለመስረቄን ነው። በጥቅሉ ፍረጃ /ጄኔራላይዝ/ አድርጎ ሁሉም የኢህአዴግ ባለሥልጣን ሙሰኛ ነው ዘርፏል ማለት አይቻልም። ከገቢዎች የተወሰኑት ንፁህ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ ይገባል። ሁሉን በአንድ መጨፍለቅ አይገባም።
የአሠራር ሁኔታው ግን ለሙስና የሚጋብዝ ነበር። በሀገር ደረጃ የበላይ አመራሩ በሙስናው ተሳታፊ ነው፤ መካከለኛ አመራሩ እና የመጨረሻ እንጥፍጣፊ የሚደርሰው አመራርም በተመሳሳይ ተሳታፊ ነበር። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ነው በወቅት ሥርዓቱን ያጨቀዩት። እኔም በበከሉሌ እፍጨረጨር ነበር የእራሴን ጥረት በዜሮ ማባዛት አልወድም።
አዲስ ዘመን:- እፍጨረጨር ነበር ሲሉ በግልጽ ባለሥልጣናትን ሄደው ከሙስና እና ዘረፋቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው ያውቃሉ?
ዶክተር በከር ሻሌ:– (ረጅም ሳቅ…)፤ እዚህ ሀገር ስላለፈው ነገር ስታወራ ያለፈ ነው ትባላለህ፤ ማን ምንድነው ብሎ የመለየትና እውቅና የመስጠት ሁኔታ አልተለመደም ። ዝም ብሎ አጠቃላይ ድምዳሜ ነው የሚሰጠው። ወደዋናው ጥያቄ ልምጣና እፍጨረጨር ነበር ማለት ምን ማለት ነው፤ በተቋም ውስጥ በየዕለቱ እጅ ከፍንጅ ሳይቀር የሚሰርቁትን ልጆች እንይዛለን ለሕግ እናቀርባለን።
የሚያጠፉ ነጋዴዎችን እናርማለን ከዚያ ለሕግ ይቀርባሉ አሊያም የመንግሥት ዕዳ እናስከፍላለን። ከባለሥልጣን አንፃር ግን የሙስና ሥርዓቱ ረቂቅ ስለሆነ አመራሩ አይገኝም። እንደሀገር ያንን የሙስና ሰንሰለት ተከትሎ አመራሩን የሚይዝ አሠራርም ሆነ ለመከታተል ፍላጎቱ ስለሌለ አመራሩ ጋር ሲደርስ ጉዳዩ በኖ ይጠፋል።
ማነው ሌባ ከአመራር የሚለውን አይተህ ብቻ አታውቀውም፤ ስለዚህ በተቋሙ ውስጥ ምርመራዊ አሰራር እንዲኖር ጥረት አድርገናል። አመራር በነበርኩበት ወቅት አሳሪ የነበሩ ሕጎች እና የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ እንዲቀየር ተደርጓል። ስለዚህ ሰው ይመንም አይመን የበኩሌን ተፍጨርጭሬያለሁ ማለት እችላለሁ።
አዲስ ዘመን:- ከለውጡ በኋላ ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደሥልጣን ሲመጡ እና በኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ሲቀየር ህወሓቶችም በበኩላቸው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ወደመሆን የተሸጋገ ሩበትን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ታዝበውታል?
ዶክተር በከር ሻሌ:– እኔ ኢህአዴግ ወደብልጽግና ከመቀየሩ በፊት ነው ወደደቡብ ኮሪያ ለትምህርት ያቀናሁት። ይሁንና በሩቁም ቢሆን እከታተል ነበር፤ አንዳንዴም ለእረፍት ወደሀገር ቤት ስለምመጣ ከጓደኞቼም አንዳንድ መረጃዎችን አገኛለሁ።
የዶክተር አብይ ወደመሪነት መምጣት ለህወሓትም ጥሩ እድል ነበር። ምክንያቱም ኢህአዴግ እንደፓርቲ የሥልጣን ክፍፍል አያደርግም የሚለውን ተጽዕኖ ይቀንስለት ነበር። በተለይም በሥልጣን ክፍፍል ጉዳይ የኦሮሞ ህዝብ ኩርፊያ ነበረበት።
ኦህዴድም ከሚወቀስባቸው አንዱ መንገድ በህዝቡ ቁጥር ልክ ገፍታችሁ ኃላፊነት አይሰጣችሁም፤ ተላላኪ ነበራችሁ ብሎ ህዝብ ይወቅሰናል። የተላላኪነት ሥራ ማለት ምንም የረባ ሥራ የማያከናውን ነው፣ በእርግጥ በወቅቱ ኦህዴድ ተላላኪ ብቻ ሳይሆን ሥራም ሠርቷል ብዬ አምናለሁ።
ሕዝብ ይህን አይነት ቅሬታ ባለበት ወቅት ኦህዴድ ዶክተር ዐብይን ወክሎ ወደአመራርነት ሲልክ ለኢህአዴግም አንድ ጫና ነበር የሚቀንሰው፡፡ በሥልጣን ክፍፍል ፍትሃዊነት ረገድ የህዝብን ቅሬታ ይቀንሳል።
ህወሓቶች ያንን ዕድል ተጠቅመው እያገዙ አብረው ቢሰሩ ተበደልኩ የሚለውን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር ለመካስ ዕድሉ ይኖራቸው ነበር። ዕድሉን አበላሽተው እራሳቸውን ወደውህደቱ ባለማምጣታቸው ስህተት ሠርተዋል።
ህወሓት ከውህደቱ የወጣችው የውህደቱም ጊዜው አሁን አይደለም በሚል ቢሆንም በውስጡ ሌላ ምክንያት ነበረው። ዋናው ምክንያት የዶክተር ዐብይ አመራርነት ወደሥልጣን ሲመጣ የሚያሳጣቸው ነገር እንዳለ ስለሚያምኑ ነው። ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የበላይነት ስለሚያስቡ በውህደቱ ተጠቃሚ አንሆንም ከሚል ስጋት ነው ።
ከለውጡ በኋላ የህወሓት አመራሮችም ከመንግሥት ኃላፊነት ተነስተዋል፤ በወንጀል የሚጠየቁ ሰዎችም ስለሚኖሩ ይህንን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ማፈግፈግን ነው የመረጡት። ባይሆን ኖሮ እና እራሳቸውን ወደእኩልነት አምጥተው ሀገራዊ ፓርቲዎች ያሉበትን ብልጽግናን ቢቀላቀሉ አሁን ከደረሰው አደጋ ጋር ስናነፃፅረው የሚገናኝ አይሆንም።
አዲስ ዘመን:- የህወሓት አመራሮች መቀሌ ላይ ከመሸጉ በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት አድርሰዋል፤ ይህን ጥቃት ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?
ዶክተር በከር ሻሌ:– በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ስሰማ እጅግ ነው ያዘንኩት። ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው። ህወሓት ግን በትግራይን ህዝብ ስም ተሸሽጋ መቆየቷ ሳያንስ መከላከያ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ታሪካዊ ስህተት ፈጽማለች። ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ማሰብና መሞከር ትልቁ ስህተት ነበር ።
ህወሓቶች እራሳቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ውህደት ማግለላቸው የመብት ጉዳይ ነው፤ ሙሉ ለሙሉ እራሳቸውን ከፌዴራል ተልዕኮ ማግለላቸው ግን ፍፁም ተገቢ አልነበረም። የመከበብ ስሜት ውስጥ መግባታቸው ነው ችግር የፈጠረባቸው። እራሳቸውን ወደጽንፍ መውሰድ እና ጉልበትን ለመፍትሄነት መጠቀማቸው ጎድቷቸዋል።
መከላከያ እና የፀጥታ ኃይል አጥቅተን በኃይል መንግሥትን እንገለብጣለን ብለው ልክ እንደ 1960ዎቹ አድርገው ማሰባቸው ነው ጥፋቱ። ይህን ማድረጋቸው ወደሥልጣንም ሲመጡ ደርግን በትጥቅ ትግል ገልብጠው ስለሆነ አሁንም ይህንኑ የአፈሙዝ ድል ለመድገም ማሰባቸው ወቅቱን ያላገናዘበ ትልቅ ስህተት ነው።
በህወሓቶች መካከል አለመደማመጡ ስለነበረ እና ጀብደኝነቱ ስለበዛ ሀገርን ለቀውስ የትግራይን ህዝብ ለከፋ አደጋ አጋልጠውታል። ለኪሳራ የተጋለጠ አማራጭ ነው የተጠቀሙት፤ በዚህ የተነሳ የአመራር እጥረትም አጋጥሟቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚያዋጡ መንገዶችን አለማየታቸው ክልሉ ላይ ጉዳት አድርሷል። ቢሳካላቸው ሀገርንም ደግሞ የማፍረስ አደጋ ነበረው። መከላከያ ሠራዊት እርስ በእርሱ ለማጋጨት መሞከራቸው የህወሓት አመራሮች ኃላፊነት በማይሰማቸው ደረጃ መንቀሳቀሳቸውን ያሳያል። በዚህ በጣም አዝኛለሁ።
አዲስ ዘመን:- አሁን ላይ በትግራይ ክልል ላለው ሰብአዊ ችግር ተጠያቂው ማን ነው ብለው ያስባሉ?
ዶክተር በከር ሻሌ:- በትግራይ ክልል አሁን ላይ ላለው ሰብአዊ ቀውስ ተጠያቂዎቹ እራሳቸው ህወሓቶች ናቸው። ለዚህም በሕግ ጭምር እየተጠየቁ ያሉበት መንገድ አግባብ ነው። ትግራይ ላይ ህዝቡ ለሰብአዊ ዕርዳታ የተዳረገው በህወሓቶች ምክንያት ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም።
አሁን ላይ እነሱ ተወግደዋል፤ የማስተዳደር ኃላፊነቱን የወሰደው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ነው። ህዝቡ ከችግሩ እንዲወጣ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌዴራል መንግሥት ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው የተቻላቸውን ሁሉ መሞከር አለባቸው። ህወሓት ግን ተመልሶ ተቋም ይሆናል አሊያም ተመልሶ መንግሥት ሆኖ ሕዝን ይመራል የሚል እምነት የለኝም። ለሰሩት ታሪካዊ ስህተት ተጠያቂ መሆናቸውን እያየን ነው።
አዲስ ዘመን:- መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ችግር ለመቀነስ እየወሰደ ያከለውን እርምጃ እንዴት ያዩታል፤ በቀጣይስ ምን አይነት ሥራዎች ያስፈልጋሉ ?
ዶክተር በከር ሻሌ:– የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በእራሱ ለግጭቶች ተጋላጭ ሆኖ የቆየ ነው። የህወሓት ባለሥልጣናት ሀገርን ሊበትን የሚችል አደጋ ሲፈጥሩ ቀጣናውን ሊያተራምስ የሚችል አደጋ ስለመሆኑ አላሰቡም፤ አልተጨነቁም።
አደጋው እንዳይስፋፋ እና ከታሰበው በታች ጉዳቱ እንዲቀንስ መደረጉ ትልቅ ዕድል ነው። የመንግሥትን አመራር ጥቡብ ማድነቅ እፈልጋለሁ። በመንግሥት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች ከአሁኑ በላይ የከፉ ጉዳቶች እንዳይመጡ ተከላክሏል።
የህወሓትን ሀገር የመበተን አደጋ በዚህ ደረጃ ማቆም ከተቻለ፤ ክልሉን መልሶ ማዋቀር እና የበለጠ ማረጋገት የማይቻልበት መንገድ አይኖርም። የከፋ ጉዳት የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በምግብ ፍላጎት ማሟላት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።
በሰላም እጦት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው። በፖሊሲ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ዋነኛ ችግር የሆኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በማዋቀር እና ህዝቡ የሚፈልገውን ሰው እንዲመርጥ በማድረግ ክልሉን ይበልጥ የተረጋጋ ማድረግ ይገባል። ህዝቡ በቀጥታ ተሳትፎ የእራሱ የሆነ አመራር እንዲመርጥ እና በእርሱ እንዲወስን ዕድሉን በመስጠት የማረጋጋት ሥራውን ማጠናከር ይቻላል።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
ዶክተር በከር ሻሌ:- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013