አዲስ አበባ፦ የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በስድስት ወር ውስጥ ለ63 ሺ 89 ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታወቀ።
ከተፈጠረው የሥራ ዕድል 1‚147 አካል ጉዳተኞች፣ 2‚000 ከስደት ተመላሾች፣ 20‚506 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና 24‚615 የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ አሰፋ ፈረደ የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
የሥራ ዕድሎቹ የተፈጠሩባቸው የሥራ መስኮች በመደበኛ፣ በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና በቅጥር መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በመደበኛ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ ቋሚ 57 በመቶ ጊዜያዊ 43 በመቶ ሲሆን፤ በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና በቅጥር ቋሚ 48 በመቶ ጊዜያዊ 52 በመቶ የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ ይህም ሊፈጠር ከታሰበው 906,547 ውስጥ አፈፃጸሙ 70 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር ደረጃ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሚደርሱና ምንም ዓይነት ገቢ የሌላቸውን ዜጎች በዓመት ሁለት ጊዜ በመመልመል የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት አቶ አሰፋ፤ አብዛኞቹ ሥራ ፈላጊዎች ወጣቶች በመሆናቸው እንዲደራጁ በማድረግ በቅድሚያ የሥራ ክቡርነትንና የሥራ ፍቅርን እንዲያዳብሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ለሥራ ፈጠራ ዝግጁ የማድረግ ሥራም ይሠራል ብለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ በመንግሥት ድጋፍ የሚንቀሳቀስ በመሆኑም ከመንግሥት 80 በመቶ ብድር ይወስዳሉ፤ ኢንተርፕራይዞቹ ወይም የተደራጁ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ደግሞ 20 በመቶ በመቆጠብ በመረጡት የሥራ መስክ ይሰማራል። መንግሥት ከብድር በተጨማሪ ለሁሉም ባይሆን የመስሪያ ወይም የማምረቻ ቦታ በጊዜያዊነት ይሰጣል። በመሆኑም በቅድሚያ በቤታቸውና በአካባቢያቸው ባለው ቦታ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረጋል።
ሥራው እየሰፋ ሲሄድ መንግሥት ለተወሰኑትና በተሻለ አቅም እያመረቱ ላሉ ኢንተርፕራይዞች በተሻለ አቅም ማምረት እንዲችሉ የመስሪያ ቦታ በጊዜያዊነት ለአምስት ዓመታት ክላስተሮችንና ሼዶችን እየገነባ ይሰጣል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በስድስት ወራት ውስጥ 1‚163 ሄክታር የለማ መሬት ዝግጁ በማድረግ ለከተማ ግብርና እና ለሼዶች ግንባታ ተላልፏልም ብለዋል።
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በመደበኛና በመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለ8.4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተያዘው ዕቅድ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ እየቀረው ለ5‚163‚962 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
በፍሬህይወት አወቀ