ኢትዮጵያ በዓመት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለወረቀት ግዢ እንደምታወጣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዐቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የወረቀት የፓኬጂንግና ፕሪንቲንግ ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ለገሰ የሀገሪቱ የወረቀት ፍላጎት በዓመት ከ200 ሺህ ቶን በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደምታወጣ፤ በ2030 ዓ.ም የፍላጎቱ መጠንም ከሁለት እጥፍ በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ ያሉት ሰባት ኢንዱስትሪዎች እስከ 90 ሺ ቶን የማምረት አቅም ቢኖራቸውም አሁን እያመረቱ ያሉት ግን ከ60 ሺህ ቶን አይበልጥም ያሉት ኃላፊው፤ ኢንዱስትሪዎቹ የወረቀት ፓኬጂንግ ፍላጎት ለማሟላት ያልቻሉበትን ምክንያት ገልጸዋል።
«በመሰረታዊነት ችግሮቹ በሁለት መልኩ የሚገለጹ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ገና ወደኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመግባት ያለው እንቅፋት፤ ከመሬት አሊያም ከመስሪያ ቦታ ጋር ተያይዞ ያለ ችግር፣ አስፈላጊ ማሽነሪዎችን በበቂ ሁኔታ ማስገባት አለመቻል ይጠቀሳሉ። በሌላ ወገን፤ ማምረት ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ጥሬ ዕቃ መግዣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል አቅርቦት ችግሮች መኖራቸው አቅማቸውን አሟጠው ለመሥራት እንቅፋት መፍጠሩን እንዲሁም፤ የወረቀት እና የወረቀት ማምረቻ ግብአት ፐልፕ ማምረቻ ፋብሪካዎች አለመኖራቸው ናቸው» ብለዋል።
አቶ አንዷለም እንደተናገሩት፤ መስሪያ ቤታቸው ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራና መፍትሔ ለማበጀት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም፤ ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ ዞን ወይም ፓርክ እንዲጠለሉ በማድረግ፤ የኢንፍራስትራክቸር ችግር እንዳያጋጥም ተመጋጋቢ ስርዓት ለመፍጠር፤ አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በማስተዋወቅና አገር ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ በማበረታት ብሎም አሁን ያሉት አምራቾች በሙሉ አቅማቸውን እንዲያመርቱ ለማስቻል ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የወረቀት ፓኬጂንግ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ በመሆኑ ያለውን ፍላጎትና አቅም ላይ ማድረስ ትልም ይኖራል ያሉት አቶ አንዷለም በቀጣይም ፤ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድና በውጭ የሚገኙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ኢንዱስትሪዎቹ ራሳቸውን እንዲያዘምኑ፤ ሙያተኞችን እንዲያሰለጥኑና እንዲያበቁ እገዛ በማድረግ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ይሠራል፤ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
በዳንኤል ዘነበ