@ 600 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል
የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቶን ዕቃ ማጓጓዙና እና 600 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘቱን የኢትዮ-ጅቡቲ ትራንስፖርት አገልግሎት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ዕቃው የተጓጓዘው መስመሩ ሥራ ከጀመረበት ካለፈው መጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የጭነት አገልግሎት እየሰጠ ያለውም በየቀኑ ከሞጆ-አዲስ አበባ በአንድ ባቡር ሲሆን፤ ባቡሩ 53 ፉርጎዎች ያሉት በመሆኑ በአንድ ጊዜ የ60 የጭነት መኪኖችን ያህል ያጓጉዛል። በዚህም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቶን ተጓጉዟል።
ከዕቃ በተጨማሪ ከሞጆ-ጀቡቲ በቀጥታ ለመንገደኞች በየሁለት ቀኑ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
ይህም አንድ ባቡር 12 ፉርጎዎች ያሉት በመሆኑ በአንድ ጊዜ የ12 አውቶቡሶችን ያህል አገልግሎት መስጠት ይችላል።
በክፍያ ረገድ በመኪና ከሚሰጠው አገልግሎት የ25 በመቶ ወይም የአንድ አራተኛ ቅናሽ እንዳለው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጀቡቲ የዲሜሪጅ ክፍያ ሳይከፍል ከወደብ በቶሎ ዕቃዎቹን ለማንሳት አስችሏል።
ኢትዮጵያ በጅቡቲ በኩል በዓመት 10 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ታስገባለች። ከዚህ ውስጥ ባለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን በባቡር ስላስገባን እኛም አንድ አስረኛውን ድርሻ ይዘናል። ገበያ እያለማን ስለሆነ የመንገደኞች ቁጥርና የምናጓጉዘውም ዕቃ መጠን እያደገ ነው የመጣው፤ ገበያው ከለማ በየቀኑ ከአዲስ አበባና ከጅቡቲ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባቡሮችን፤ ለሰዎች ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አንድ ለማሰማራት እንችላለን። አንድ የዕቃ ባቡር ስንጨምር በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን እናነሳለን ማለት ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 800 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ይህ ቁጥር ወደ 3ሺ ያድጋል ብለዋል።
እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አንዳንድ ጊዜ በባቡሩ መስመር ማለፊያ አካባቢዎች የሚያጋጥመው የጸጥታ ችግሮች ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል። በከተማ እንደሚያጋጥመውም ሁሉ በባቡር መስመር የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ያጋጥማል ያሉት ኃላፊው፤ የአገናኝ የባቡር መስመሮች አለመጥናቀቅም ዋና ችግር መሆኑን ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት መስመሩ ከሚያልፍባቸው ክልሎች መስተዳድሮች ጋር በጋራ እየሠራን ነው። የኤሌክትሪክ መቆራረጡ በቀጣይ የኃይል አቅርቦት ሲስፋፋ ችግሩ እየተቃለለ ይሄዳል ብለዋል።
ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር አገልግሎት ገቢ የኢትዮጵያ ድርሻ 75 በመቶ ሲሆን፤ ቀሪው 25 በመቶ የጅቡቲ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ