ተገኝ ብሩ
ለቃሉ ልዩነት ብዙም ትኩረት ሰጥቼ አላውቅም። ባለፀጋነት ከባለሀብት እንደሚለይ ጠቅላይ ሚኒስሩ ሰሞኑን ባለፀጋ የሆኑ አንድ ግለሰብ ባሠሩት ታላቅ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ ላይ ሲናገሩ ሰምቼ የማላውቀውን ልዩነት ተረዳሁ። በእርግጥ ይህች አገር በርካታ ባለሀብቶችና ጥቂት ባለፀጎች በርክተውባታል። እነዚያ በርካታ ባለሀብቶች ወደባለፀጋነት ቢቀየሩ አገሬን ተለውጣ ህዝቧ ካለበት የኑሮ ጫና ተላቆና ተስፋው ለምልሞ የሰከነ ህይወት ብሎም የተረጋጋ የፖለቲካ ሁናቴን አስተዋልኩ።
ባለሀብቶቻችን ባለፀጋ እንዲሆኑ ይገባል። ባለሀብት ያደረጋቸው ህዝብ ባለፀጋ ሆነው ሊክሱት ይገባል። ባለፀጋነት ማግበስበስ አይደለም። የሰበሰቡትን በትክክል መጠቀም አገርና ህዝብ በሚጠቅም እራስን ወደተሻለ ስኬት በሚያዳርስ መልክ መጠቀም ነው። ባለፀጎች በገንዘብ ብቻ አይደለም ፀጋውን የተላበሱት በህዝብ ፍቅርም ነው።
መጀመሪያ መነሻ የሆናቸው ለዕድገታቸው ዋንኛ ምሶሶ ህዝብ መሆኑን አይረሱምና። የሰበሰቡትን ለህዝቡ ጠቀሜታ መልሰው በተለያየ መልኩ ያውሉታል።
ባለሀብቶች በተለየ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ ማሰብ እንጂ ህዝብ በምን መልክ ልጥቀም እንዴትስ ባደርግ ህዝብ ተጠቅሞ እኔም ወደተሻለ ደረጃ እደርሳለሁ ብለው ማሰብ አይችሉም። ይህን ለማሰብ ባለፀግነትን መላበስ ከባለሀብትነት ተላቆ ባለፀጋ መሆን ያስፍልጋል። ባለፀጎቹ የባለፀግነታቸው መለያው ህዝብን በተለየ መልኩ የሚጠቅምን ፕሮጀክት በመንደፍ እኔም ህዝቡም ይጠቀም እንጂ እኔ ብቻ ልሰብስብ አይሉም። የባለፀጎቹ መለያ ባህሪ ህዝብ ተኮር ለውጥ ነው። ብዙ ባለሀብቶች ግን ህዝብን ተጠቅሞ ማድግ ብቻ የለውጥ ስኬት ይመስላቸዋል።
በእርግጥ ባለሀብትነት ከባለፀጋነት የተሻለ ትርፍ የላቀ ለውጥ የሚያስገኝ ቢመስልም፤ የባለፀግነት ያህል የተሻለ ቦታና የማያወላዳ ቅሪት ለመቋጠር አያስችልም። ህዝብ የሚወደው ደንበኛ የሚያከብረው ሀገር የምትሸልመው ባለፀጋውን እንጂ ባለሀብቱን አይደለም። ባለሀብቱ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እቅድ ሲያወጣ ባለፀጋው ሀብቴን በምን መልክ ብመነዝረው እኔንም ለውጦ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ስሌት ውስጥ ይገባል።
ባለሀብት ለመሆን አጋጣሚው ከተገኘ እጅጉን የቀለለ መንገድ ነው። በምንም መንገድ እጅ የደረሰን ገንዘብ እጥፍ እንዲሆን ማሳደግ፤ ከሩቅ አገር ምርቶችን አምጥቶ እየቸበቸቡ ብር ማጋበስ፤ ስለህዝብ ሳይጨነቁ እቃዎችን ሸምቶ በማጋበስ ቁሳቁስ ላይ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ መልሶ አውጥቶ በእጥፍ መሸጥ በአጭር ጊዜ ነገር ግን ተገቢ ባልሆነና ኢ ሞራላዊ በሆነ መንገድ የሚለወጡበት ነው። ይህ ግን ሰላም አይሰጥም ባለሀብቱም ተከታዮቹም ባለሀብት እንጂ አምላካዊ ፀጋን ህሊና የሚባል እስር ቤት ውስጥ ይከታል።
ገዝፈው ቢታዩም አድሮ ያሳንሳል፤ ልቀው ቢታዩም በአንዲት ጀምበር የዝቅታ መዳረሻ ላይ ያደርሳል። ባለሀብትነት ወደ ባለፀጋነት ተቀይሮ እኔም ህዝቤም በእኩል እንጠቀም ማለት ምንኛ የማትረፍ ከፍታ ነው? ባለፀጎች የሀብታቸው ጠባቂ ህዝቡ የንብረታቸው ተንክባካቢ ተገልጋዩም አገልጋዩ ነው። ባለፀጋነት ለሀገር ግንባታ ለህብረተሰባዊ ለውጥ ድርሻው የጎላ የሚሆነውም ለዚህ ነው። ከባለሀብትነት ባለፀጋነት የተሻለ የሆነውም በዚሁ መስፈሪያ በዚሁ ዕይታ ነው።
ባለሀብቶቻችን ለእነሱም ለእኛም የተሻለ መንገድ ወደሆነው ባለፀጋነት እንዲለወጡልን መመኘታችንም መነሻው ይህ ነው። ባለፀጋነት ከባለሀብትነት በእጥፍ የሚያተርፉበት እጅጉንም በዘላቂነት የሚከበሩበት ነው። በአገር ግንባታና በህዝብ ለውጥ ታላቅ ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻልበት ባለፀጋነት መበርከቱ ባለሀብትነት የሚፈጥረውን የተሳሳተ ጎዳና ለመዝጋት ይረዳል።
ሁላችን የዚህች አገር ባለቤቶች ነን። ባለፀጎች፣ ባለሀብቶች፣ባለስልጣናት፣አልያም ደግሞ ተራው ህዝብ በእኩል አስጠልላ በጋራ አቅፋ የምታስጉዘን። ለዚህች አንድ አገር ለውጥ የጋራ ርብርብ ለዚህች አንድ ምድራችን የአብሮነት ቅን እሳቤ ግድ ይለናል። ለለውጧ በጋራ ማበር ግድ ይሆንብናል። ባለፀጎች በርክተው ሀገራዊ ፀጋን እንዲያጎናፅፉን ህዝባችንም ካለበት ችግር እንዲላቀቅ ምኞቴ ነው።
ብዙ ባለሀብቶችና ጥቂት ባለፀጎች ያሉባት ይህቺ አገር ያላትን ሀብት በወጉ መጠቀም ያልቻለች፤ ከተጠቀመች ደግሞ ከራሷ አልፋ ብዙዎችን አቅፋ ማሻገር የምትችል ናት። ኢትዮጵያ በልጆቿ ያልተቋረጠ ጥረት የምትበለጽግ፤ በጋራ ጥረት የምትለወጥ የተስፋ ምድር ናት። አገራዊ ራዕዩ ተሳክቶ አገራዊ ግቡ ተሳክቶ ብልጽግናዋ እውን እንዲሆን በየዘርፉ የተለያየ ጥረት ማድረግ ይገባል።
አገር በትውልድ ቅብብሎሽ በዜጎች ያልተቆጠበ ጥረት ትለወጣለች። ይህቺ ታላቅ አገር ትላንት ያለፈችበትን ምስጢር መመርመር ዛሬ የተገኘችበትን ማሰብና ነገ ልደርስበት ያለመችውን ራዕይ መገንዘብ ተገቢ ነው። ተፈጥሯዊ ፀጋን የተላበሰችው ምድር ባለፀጎች የበረከቱባት ከሆነች ለውጧ ይፈጥናል። መበልፀጓ አስቸጋሪ አይሆንም። ዛሬ ያለችበት ድህነት ነገ በታሪክ የሚነገር ለሌሎች መማሪያ ሰነድ ሆኖ የሚቀርብ ይሆናል።
ከራስ ይልቅ ህዝብ ማለት ከግል ጥቅም ይልቅ አገር ማሰብ አገራዊ ራዕይ በተሳካ መልኩ እንዲጓዝ ያደርጋል። ይህች አገር በትጉኋን ልጆቿ ጥረት ትንሳኤዋ እንዲቀርብ ቅኑን መንገድ የሚያመላክት ምሁር፣ በስርዓት የሚመራ ባለስልጣን፣በህግ የሚተዳደር ህዝብ፣ወደ ባለፀጋነት የተቀየረ ባለሀብት ይገባታል። ሀብትን በተገቢው ሁኔታ መጠቀም፤ከራስ አልፎ አገራዊ ግብ ለማሳካት በሚያስችልና ህዝብን በሚጠቅም መልኩ መተግበር ስብእናዊ ፀጋ የመላበስ ምልክት ነው።
ሰሞኑ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ቡሬ የተመረቀው የዘይት ፋብሪካ ባለቤት ባለፀጋው አቶ በላይነህ ክንዴ ንግግራቸው አንድ ነገር አመለከተኝ። ባለሀብቱ በንግግራቸው “ብር ብፈልግ ኖሮ አዲስ አበባ ላይ የበዙ ፎቆችን ገንብቼ በጥቂት ሰዎች ብቻ ብርን መሰብሰብ በቻልኩ ነበር፤ነገር ግን የማህበረሰቡን ችግር በሚፈታ መልክ ሀብቴን መገልገል ፈለኩና ይህን አሰብኩ፤እናም አደረኩት” አሉ። ይህ የባለፀጋው ንግግር ብዙ አመላካች ነው። በመስጠት የሚላበሱት ከፍታ።
ከራስ ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም፤አገር ከመውደድ የሚመነጭ ስብዕናዊ ፀጋ። ንግግሩ ከባለፀጋነት የሚመነጭ ከባለሀብትነት መራቅን የሚያስመኝ ባለፀጋ መሆን የሚያስናፍቅ። የምንወዳት አገራችን እድገቷ እንዲፈጥን፤ ህዝባችን ተለውጦ እንድናይ ባለሀብቶቻችን ባለፀጋ ያድርግልን..አሜን! አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013