የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት በማምጣትና የመረጃ አብዮት በመፍጠር ረገድ ያስገኘው ፋይዳ እጅጉን ላቅ ያለ ስለመሆኑ ዓለም ያወቀው ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው።
ከዚህ አብዮት መፈጠር ጋር በተያያዘ በዓለም አንድ ጫፍ የተከሰተው ነገር በሌላኛው ጫፍ በሰከንዶች ውስጥ ይዳረሳል።
ሰዎች ብዙ ሳይለፉና ሳይደክሙ እጃቸው ላይ ባለ ሞባይል ብቻ ሬዲዮኑንም ቴሌቪዥኑንም ሆነ ጋዜጣና መጽሄቱን ያገኙታል። ሰዎች በሚፈልጉት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳይ መረጃ በፍጥነት የሚያገኙበትም ዕድል እንዲሁ ቀላል ሆኗል። ከዚህ አንጻር በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት የተጫወተው ሚና እጅጉኑ የገዘፈ ነው።
ይሁንና በበይነ-መረብ ላይ የምናገኛቸው ዜናዎች ወይም መረጃዎች ሁሉ እውነት እንዳልሆኑ መረዳት በተለይም በአሁኑ ወቅት እጅጉኑ ያስፈልጋል።በበይነ-መረብ
ያገኘናቸውን መረጃዎች ተገቢውን ማጣራት ሳናደርግ እኛም መልሰን ለሌሎች የምናጋራ ከሆነ ደግሞ በበለጠ ሁኔታ በርካታ ሰዎች መረጃውን እንዲያምኑ እድል እንፈጥራለን፡፡
ሃሰተኛ መረጃዎች ሰው ጆሮ ሲደርሱ እውነትን የያዙ መረጃ እና ዜናዎች መስለው እንዲደርሱ መጀመሪያ የተፈጠረ ነገር ይኖራል።በመሆኑም በበይነ-መረብ ላይ የምናገኛቸውን መረጃዎች ከማጋራታችን በፊት ትክክለኝነታቸውን እናረጋግጣለን? ወይ የሚለውን ጥያቄ ወሳኝ ሆኖ እናገኘዋለን።
ውሸት ፈብራኪዎች ሃሰተኛ ዜናን ለመስራት ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደርጋሉ።ከዚህ አንጻር ሁለት ዓይነት የሀሰት ዜናዎች መጥቀስ ይቻላል። አንደኛው ሰዎች ትክክለኛ ያልሆኑ ነገሮችን እንዲያምኑ ወይም ድረ-ገጾቻቸውን እንዲጎበኙ ሆን ተብሎ እና ታቅዶ የሚሠራጩ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ሙሉ በሙሉ እውነተኛ ያልሆኑ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ እውነታን የያዙ የሀሰት ዜናዎች ናቸው።ከዚህ ባለፈም ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ፣ ለውግንና ወይም ስለእውነታው ሰዎች የተሳሳተ ምስል እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል የሚፈጠሩ የሀሰት ዜናዎችም አሉ።
በአሁኑ ወቅት በርካቶች ብዙ ማጋራቶችን (share) ለማግኘት፣ ርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማጋበስና አገርን ለማተራመስ ሲባል ትክክለኛነታቸው በአግባቡ ያልተረጋገጡ የውሸት ታሪኮች በየዕለቱ ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ።መረጃዎቻቸው ተቀባይነት እንዲያገኙም የተለያዩ ፎቶግራፎችንና ፊልሞችን በረቀቀ መንገድ ኤዲት በማድረግ፣ ሀሰተኛ ድረ-ገጾችን በመክፈት እና እውነተኛ የሚመስሉ ታሪኮችን በመፍጠር ያሰራጫሉ።
ካላቸው ተፈጥሯዊ ባህሪ የተነሳም በተለይም ማህበራዊ ሚዲያዎች የሀሰት ዜናዎችን በቀላሉና በፍጥነት ለማሰራጨት እየዋሉ ሲሆን በውጤቱም የተለያዩ ጉዳቶችን እያስከተሉ ይገኛሉ።ከዚህ አንጻር በአገራችን በተለይም በአሁኑ ወቅት በጁንታው ርዝራዦች እየተከናወነ ያለው የሀሰት ወሬዎች ፍብረካና ስርጭትን ስንመለከት ይህ ስግብግብ ኃይል በጦርነት አልሳካ ያለውን ዓላማ በውሸት መረጃዎች ለማሳካት ሌት ተቀን እየሰራ ስለመሆኑ ያመላክቱናል።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው አገርንና ህዝብን በሴራ ሲያደማ የኖረው ጁንታ ለዓመታት ሲፎክርበትና ሲሸልልበት የነበረው የጦርነት ትርክት ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጀግናው የመከላከያ ሃይላችን አኩሪ ገድል ብን ብሎ ጠፍቷል። ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን የሚለው ትምክህትም ትዝብት ብቻ አትርፎ እርቃኑን ቀርቷል።
ስለሆነም አሁን ላይ የጁንታው ርዝራዥ ያለው አቅም ምላስ ብቻ ሆኗል። ስለሆነም የሌት ተቀን ሥራው ሁሉ የውሸት ዜና መፈብረክና በዚህም የአገርንና የጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንን ገጽታ ለማጠልሸት መሥራት ሆኗል።
ይህ ደግሞ ከንቱ ልፋት እንጂ ምንም ውጤት እንደማይኖረው የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም ውሸት የቱንም ያህል ብትወጣጠርና ብትገዝፍ እውነት ፊት ስትቆም መሟሸሿ አይቀርምና ነው።
ይህንን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከሰሞኑ ባስተላለፉት መልዕክት “ዛሬም የጁንታው ሞት ያልተዋጠላቸው ከዥንጉርጉር ማህጸኗ የፈለቁ ሰዎች ከሀገራችን ጠላቶች ጋር እያበሩ፣ የተዛቡ መረጃዎች መርጨቱን የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል።
እንዳሻቸው መሆን ካልቻሉ ኢትዮጵያ እንድትኖር አይፈልጉም። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያጡትን ድል በወሬ ግንባር ለመመለስ ተንኮልን መሣሪያ፣ ሐሰትን ጥይት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በመሆኑም በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ስለ ሀገራችሁና ስለ ወቅታዊው ጉዳይ ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመናገር፤ የሀገራችንን መልካም ክብርና ስም ለማጥፋት የተነሱ ሰዎችን ድል በመንሳት፤ ሐሰትን በእውነት እንድታሸንፉ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።
ስለሆነም አገሩን የሚወድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጁንታውን ርዝራዦች የሀሰት ደን በመመንጠርና ውሸታቸውን እርቃኑን በማስቀረት ታሪካዊ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013