አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ሞት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰትና ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው የሞት መጠን የካንሰር ህመም እንደሚሸፍን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የዓለም ካንሰር ቀን አስመልክቶ ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተዘጋጀው መርሐግብር ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለም አቀፍና በሃገር ደረጃ ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተሉ መጥተዋል፡፡
በቅርቡ ከግሎባል ናንሴንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተካሄደ የሁለት ዓመት ጥናት በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከሌሎች አደጋዎች ጋር ተዳምረው 52 በመቶ የሚሆነውን የሞት ድርሻ እንደሚይዙ ዶክተር ሊያ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥም የካንሰር ህመም በዓመት 5 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነውን የሞት መጠን ሸፍኗል ብለዋል፡፡
ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን አለመከተል፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአልኮልና አደንዛዥ እፆችን የመጠቀም ዝንባሌ መጨመርና የተለያዩ አካባቢያዊ ለውጦች በካንሰር ምክንያት ለሚከሰት ሞት መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልጸዋል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለውን የካንሰር ህመም በአግባቡ ለመቆጣጠር ከመከላከሉ ጀምሮ ሥራዎች ተጠናክረው መሠራት እንዳለባቸው ሚኒስትር ዲኤታዋ የጠቀሱ ሲሆን፣ የካንሰር ህመም አንዴ ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚጠይቅ፣ የረጅም ጊዜ ስቃይን የሚያስከትልና የህሙማን ቤተሰቦችንና ሃገርንም ጭምር ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚዳርግ በመሆኑ ጠንካራ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የካንስር ህመምን ከመከላከል አኳያ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩም ሚኒስትር ዲኤታዋ አመልክተው፣ በተለይም የአገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛነት፣ ህክምናውን የሚሰጥ የሰው ኃይልና የመድሃኒት እጥረት መኖር አሁንም የካንስር ህመም ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የካንሰር ህክምና ማዕከላትን የማስፋትና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቁጥር የማሳደግ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ መሠራት እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
በአስናቀ ፀጋዬ