ለምለም መንግሥቱ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን ከመሬት ወረራ፣ ህገወጥ ግንባታና ከጋራ የመኖሪያ ቤት ጋር ተያይዞ ፍትሐዊ የዜጎች አጠቃቀም ላይ የታዩ ክፍተቶችንና ግኝቶችን ለህዝቡ ይፋ ማድረጉ ብዙዎችን እንዳስደሰተና በተለይም በመኖሪያ ቤት ዕጦትና በኪራይ የሚበዘበዙትን ዜጎች የበለጠ ተስፋ የሰጠ እንደሆነ እገምታለሁ::
14 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው አንድ ሺ 338 ሄክታር መሬት፣ከ21ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤት መስተዳድሩ ጥናትን መሠረት አድርጎ በህገወጥ ጥቅም ላይ የዋሉ እንደነበር ማረጋገጡን አስታውቋል::15ሺ891 የሚሆኑት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ መረጃ አልቀረበባቸውም ብሏል::
ይህ ለምን ሆነ ሲባል የኋላ ታሪክ ማንሳት ተገቢ ነው::ባለፈው ሥርዓትም ቢሆን ከግንባታና ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸውንና የተወሰዱ እርምጃዎችም በማሳያነት ሲቀርቡ ነበር:: መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በገቢ ዝቅተኛ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል እጠቅማለሁ ብሎ ትልቅ አጀንዳው ያደረገውን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እንኳን ምን ያህል ለመገንባት እንዳቀደና በዕቅዱ መሠረት ስለመፈጸሙ ትክክለኛው መረጃ ህዝብ ጆሮ ደርሶ አያውቅም::ጥፋተኛው ማን እንደሆነም አይገለጽም:: ብቻ በድፍኑ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ነው የሚባለው:: ግን ሲፈጸም አናይም::
የሚገርመው የጋራ መኖሪያ ቤት ቆጠራ ሲካሄድ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው:: ለማንና መቼ እንደተሰጠ ቀድሞ መታወቅ ሲገባው ሰፊ የሰው ኃይልና ገንዘብ ወጥቶ የተካሄደው ቆጠራ በአግባቡ ሳይደራጅ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ነዋሪው ጊዜውን አባክኖ ለፎቶ ኮፒ ወጪ አውጥቶ ነው ቆጠራ የተካሄደው:: አንዳንዴ ይገርመኛል::
ለሆነ ሰው ሲባል ህዝቡ ወጪ እንዲያወጣ የሚደረግ ይመስለኛል::በቆጠራው ወቅት ፎቶ ኮፒ ቤቶች ተጨናንቀው ነበር::ወዲያው ደግሞ የይዞታ ካርታ ይቀየራል ተብሎ ፎቶ ቤቶች እንዲሁ ተጨናንቆ ሰነበተ:: ፎቶ ያልነበረው ካርታ ፎቶ እንዲኖረው ተደርጎ ከተጠበቀው በላይ ወጪ ነበር የተጠየቀው::
አንድ ሰው ህጋዊነቱ ተረጋግጦ ካርታ ሲሰጠው ካርታው ፎቶግራፍ እንደሚያስፈልገው የሚነገረው በቤቱ ውስጥ አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ከኖረ በኋላ ነው? ደግሞ ካርታውን ለማስቀየር በጥሩ ሁኔታ የሚያስተናግድና የእጅ መንሻ የማይፈልግ ከተገኘ ቢያንስ ለሁለት ቀናት መመላለስ ግድ ነበር:: ይሄን የማነሳው የማጣራት መንገዱ ትክክል መስሎ ስለማይታየኝ ነው::አገልጋዩ በሚፈጥረው ክፍተት ሁሌም ተገልጋዩ ነው በጊዜና በገንዘብ የሚጎዳው::
እኔም እንደ አንድ ዜጋ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ እያጠሩ መሄድ አስፈላጊ እንደሆነ እስማማለሁ:: ነገር ግን ዝርክርክ አሰራር እየተበረታታ ዜጋው አላግባብ መንገላታት የለበትም:: መንግሥት አሰራሩን መፈተሽ አለበት:: ያለፈው ሥርዓት የፈጠረው አሰራር ነው እየተባለ እስከመቼ:: አሁንም በከተማ አስተዳደሩ ይፋ የሆነው ግልጽነት ይጎለዋል::
ግኝቱ ጥናትን መሠረት ያደረገ ነው ይባል እንጂ ችግሩን የፈጠረው ማን እንደሆነና ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድበት አልተገለጸም:: መቼም የገነባውም ሆነ መንግሥት በሰራው ቤት ውስጥ ገብቶ የሚኖረው ሰብሮ ገብቶ አይሆንም:: ፈቃድ የሰጠው አካል አለ::መቼም ጉቦ ተቀብሎ የሰጠው የመንግሥት አካል አሁን ይገኛል ማለት ዘበት ነው::
ለዓመታት በቤቱ ውስጥ የኖረውን ሰው ወይንም የሀገር ሀብት የፈሰሰበትን ግንባታ በቀላሉ ማፍረስም የህግ ሂደቶች የሚኖሩት ይመስለኛል:: የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን የሚያጋጥሙ ክፍተቶች እንዴት ሊፈታው እንደተዘጋጀም አብሮ ይፋ ቢያደርገው እነርሱ ልማዳቸው ነው ከሚባለው ትችት ይወጣል ብዬ እገምታለሁ::
የከተማ አስተዳደሩ ይፋ ያደረጋቸው ክፍተቶች የቆዩና ተንከባለው የመጡ ችግሮች እንደሆኑ ፀሐይ የሞቀው ነው::
እርሱ ባካሄዳቸው ጥናት ውስጥ ያላካተታቸው አሁንም የህዝብ ችግር የሆኑ ግንባታዎች አልተቀረፉም:: በተለይ ማስፋፊያ በሚባሉ አካባቢዎች ግንባታዎች በቅለው ነው የሚያድሩት:: አስተዳደሩ የኋለኛው ችግር ላይ ሲያተኩር ከፊቱ ያለውን ህገወጥ ተጋባር ጎን ለጎን ማስቆም ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት::
ሌላው ቢቀር የመንግሥት መሠረተ ልማት በተገነባበትና የነዋሪ መውጫዎች በጉልበተኞች በቆርቆሮ ታጥረው ህዝብ ጥበቃ እስከማቆም የደረሰባቸው ማን ይነካናል ብለው ወራት ያስቆጠሩ ህገወጥ ተግባራት በየአካባቢው ይገኛሉ:: ህዝብ ሲታገል የሚረዳው ባለመኖሩ ህዝቡ ቢጮህም የሚሰማው እንደሌለ ስለሚታወቅ ጉልበተኞች የልብ ልብ ተሰምቷቸዋል::
ሀገሪቱ የአልባሳት መሸጫ ሱቅ ችግር ያለባት ይመስል የበሬ ግንባር የሚያክል ሱቅ እየተገነባ በነፍስ ወከፍ እንዲዳረስ የተባለ ይመስል በየቦታው የሚታየው ግንባታንስ የከተማ አስተዳደሩ እንዴት አየው:: የከተማ አስተዳደሩ የአልባሳት መሸጫ ሱቆችን ለማስፋፋት ቆርጦ የተነሳ እስኪመስል ድረስ በላስቲክ በተወጠሩና ትናንሽ ግንባታዎች ሥራ ተወጥሯል::
ተጠቃሚዎቹ በህገወጥም ይስሩት በህጋዊ መንገድ ያግኙት ማረጋገጫ ባለመኖሩ የከተማ አስተዳደሩን ከተወቃሽነት አያድነውም:: የሚገርመው ደግሞ ባለሱቆቹ ከይዞታቸው አልፈው የመንገደኛውን መተላለፊያ ጭምር በመያዝ እንደመብት ዕቃቸውን ይደረድሩበታል:: የጎዳና ላይ ንግድ ተጨምሮበት መንገደኛው መብቱን ተነጥቆ ከመኪና ጋር እየተጋፋ ለመሄድ ተገዷል:: የከተማ አስተዳደሩ ይሄንንስ እንዴት እያየው ነው?
አሁንም የተጀመረው ሥራ ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይሆን እሰጋለሁ:: ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ መሆን ይኖርበታል:: አስተዳደሩ የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው በፍትሐዊነት የሚጠቀሙበትን መንገድ ካላመቻቸ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው የሚሆነው:: የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ የመሬት ወረራ ተስፋፋ ማለቱ ተገቢ አይመስለኝም::
በመሬቱ ላይም ግንባታ ሲካሄድ እስኪያልቅ ጠብቆ በማፍረስ የሀብት ብክነት ማስከትልና ሀገርን መጉዳት ነው:: አስተዳደር በተለዋወጠ ቁጥር የተፈጠሩ ችግሮችን ብቻ በማስተካከል ላይ ማተኮሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዳይኖረው ስለሚያደርግ አሰራርን ዘርግቶ የሚታዩ ችግሮች በማያዳግም መልኩ እንዲቀረፉ መስራት ይገባል::
ማንም ይሾም አሰራሩ ቀጣይነት ያለውና ያንን መሠረት አድርጎ የሚተገበር መሆን ይኖርበታል:: ይህንን የሚያስፈጽሙ ጠንካራ ተቋማትን ማደራጀት ደግሞ የጊዜው ጥያቄ ሊሆን ይገባል:: አዲሱ የከተማዋ አስተዳደርም በጀመረው መንገድ ለዘላቂ መፍትሄዎች መሰረት ጥሎ ቢሄድ ስሙም ዘላለማዊ ይሆናል::
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013