(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
ጥበቃው የላላው የሕዝብ አንጡራ ሃብት፤
ባለሃብቶቹ ባስተዋወቁን ስያሜ ሪል እስቴት እያልን መግባባት ከጀመርን ዓመታት ነጉደዋል:: በግሌ ግን ከባዕድ ስያሜው ይልቅ “አንጡራ ሃብት” የሚለውን አቻ ትርጉም ብንለማመድ ይበልጥ ከልባችን የሚደርስ ይመስለኛል:: “አንጡራ” የሚለውን ቃል መዛግብተ ቃላት የሚፈቱት “የነጠረ የራስ ገንዘብ” በማለት ነው::
አንጡራ ሃብት በሥራ ትጋት “ከደምና ከላብ ውስጥ ነጥሮ” የሚወጣ የድካም ፍሬ እንጂ ከሌላው ወዝ ተመጦ የሚቀዳ “የጉልበት መቅኒ” አይደለም:: የዘርፉ ባለሃብቶች ይህንን ሀገርኛ ስያሜ “አሜን!” ብለው ቢቀበሉ በአዕምሮ ፈጠራ ባለቤትነት መብት እንደማልከራከራቸው አረጋግጥላቸዋለሁ:: ብቻ እነርሱ ባደረጉት::
የጹሑፌ ርዕስ የብሶት ድምጸት እንዳለው አልጠፋኝም:: ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግ- ሥታዊ ተቋማትም “ኃላፊነታችንና ሥራችን እንዴት ይጠፋናል?” በማለት ቅሬታ እንደማይሰማቸውም ተስፋ አደርጋለሁ:: አልሚዎቹ ከሚፈጽሙት አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ተነስተን መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ያሉትን ሪል እስቴቶች በሙሉ የአደባባይ ውሏቸውን ካልሆነ በስተቀር የጓዳ ገመናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል ለማለት እጅግም አያስደፍርም::
እርግጥ ነው የእንያንዳንዱ ሪል እስቴት የሥራ ፈቃድ፣ የቢሮ አድራሻና የሳይቶቹ አካባቢ ለፈቃጁና ለተቆጣጣሪ መንግሥታዊ ተቋማት ይጠፋቸዋል ማለት ድፍረት ጭምር ይመስለኛል:: የክንውናቸውን ሪፖርትና ይፈጸምልን የሚሉትን የማያቋርጥ ጥያቄዎቻችውን ጭምር ጥራዝ በጥራዝ እያነባበሩ ለሚመለከተው ክፍል ሳይታክቱ እንደሚያቀርቡም አይጠፋኝም::
መንግሥት ይጠፋው ይሆን ወይ ብዬ የምሞግተው ግን ዜጎች አንጡራ ሃብታቸውን ሆጨጭ አድርገውና ኪስና ማጀታቸውን አራቁተው ለገዙት መኖሪያ ቤታቸው ኃላፊነት ወስዶ “ለመሆኑ ከምን ደረሰ” ብሎ የጊዜና የጥራት ቁጥጥር ያደርጋል ወይ ነው? በግሌ አይመስለኝም:: ሆኖም ከሆነ ማስረጃ እያቀረብን ብንወያይ አይከፋም::
መቼም እያንዳንዱ ሪል እስቴት በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያዎቹን የሚያስነግረው የሚገነባቸው የመኖሪያ አፓርትመንቶች አዳምና ሔዋን ከኖሩበት ገነት ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ አእምሮን በመስለብና በማማለል ጥበብ እየተጠቀመ ነው::
እውነታው ግን የሚገነቡት አፓርትመንቶች በሠዓሊያን ሥራዎች ውስጥ እንደምናስተውላቸው የጥበብ ወጤቶች ካልሆኑ በስተቀር በገሃዱ ዓለም ይገኙ ከሆነ ዕድሉ ደርሶኛል የሚሉ ምስክሮች ቢያስጎመጁን አይከፋም::
ከሚዲያ ማማለሉ ባልተናነሰ ሁኔታና በተጨማሪነት በዋና ዋና አደባባዮችና ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በሚያሰማሯቸው “አፈ ቅቤ” ደላላዎች (እነርሱ የሽያጭ ባለሙያ ይሏቸዋል) አማካይነት ማስተዋወቅ ብቻም ሳይሆን እንዴት ስሜትን ሰርስረው እንደሚገቡ ለመመስከር አይገድም:: በማስታወቂያዎቹና በአፈ ቅቤዎቹ ሽንገላ የተማረኩ ብዙዎች ግዢ ከፈጸሙ በኋላ በጸጸት ላይ መውደቃቸውን ደጋግሜ አድምጫለሁ::
ጥረትና ድካማቸው ባልከፋ:: በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተጽእኖ መፍጠራቸው አይካድም:: በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ብቻም ሳይሆን “መጦሪያቸውን” ሀገራቸው ውስጥ ለማድረግ ለጓጉ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ማረፊያ መሆናቸውን አልዘነጋም:: ዘርፉ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ እያሳረፈ ያለው አሻራም ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል::
ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል እንደፈጠርም አይካድም:: መንግሥት ግራ ለተጋባበት የመኖሪያ ቤት ፍላጎትም በጎ ምላሽ መስጠቱ እርግጥ ነው:: ለከተማችን ገጽታ ማማር ጥቂትም ቢሆን አስዋጽኦ ማድረጋቸውን ሸምጥጦ መካድ ከባለ ሃብቶቹ ጋር ማቀያየም ብቻም ሳይሆን ከራስ ኅሊና ጋርም ክፉኛ ያጋጫል::
ችግሩ የሚስተዋለው አልሚውና ቤት ገዢው በጋራ የተስማሙበት ቃል እየተሻረ፣ መሃላ እየፈረሰና ውል እየተጣሰ የቤት ባለቤቶቹ ሃብታቸውን ካፈሰሱ በኋላ ተከታዩ ውጤት በልቅሶና በእንባ መታጀቡ ላይ ነው:: በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብታቸውን ያፈሰሱ የመኖሪያ ቤት ተስፈኞች በተባለው ጊዜና ጥራት ቤቱን ሳይረከቡ መቅረት ብቻም ሳይሆን ተስፋቸው ጭልም እያለ ሲመክን ምን እንደሚሰማቸው ለመገመት አይከብድም::
ባለ ሃብቶቹ ምክንያት ደርድሩ ቢባሉ ከዶላር “ወርቅነት” እስከ ግብዓቶች እጥረት እንደሚተርኩ ጠፍቶኝ አይደለም:: “ያልገነቡትን እንደማይሸጡ” በመሃላ ጭምር አረጋግጠው ገንዘቡን ኪሳቸው ካስገቡ በኋላ “ታገሱ! ምን ያስቸኩላል! ከቸኮላችሁ ግንባታው ባለበት ሁኔታ ፈርማችሁ ተቀበሉ!” ወዘተ. በሚል ምክንያትና ማስፈራሪያ ደንበኞቻቸውን የስኳር፣ የደም ብዛትና የጨጓራ በሽታዎችን ከአፓርትመንታቸው አስቀድመው “የሸለሟቸው” ሪል እስቴቶችን ቁጥር ከማሰስ ቤታቸው ይቁጠረው ማለቱ ይቀላል:: “የቤት ያለህ!” እያልኩኝ “ቤቱ ይቁጠረው” ማለት የብዕር ወለምታ መሆኑ ይታወቅልኝ::
ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ዱቄትና መሰል መሠረታዊ የዕለት ፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የዋጋ፣ የጥራት ቁጥጥርና ክትትል የሚደረገውን ያህል ለመሠረታዊ መጠለያ ለምን ትኩረት እንደተነፈገ አልገባኝም:: በቢሊዮን ብሮችና ዶላሮች በሚንቀሳቀስ የሪል እስቴቶች ላይ መንግሥት ዓይኑን በቅርበት ጥሎ ለምን ክትትል እንደማያደርግም በግሌ ይገርመኛል:: የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ጩኸትም ወደ መንግሥት ጆሮ ጠልቆ የማይገባበት እንቆቅልሽ እጅግም አይገባኝም::
በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን አንጡራ ሃብት ሙልጭ አድርጎ ከዘረፈ በኋላ ከሰርኩ፣ ነጣሁ፣ አጣሁ፣ በሚል ምክንያት ክህደት የፈጸመ አንድ የሪል እስቴት ኩበንያ ሲቀጣና ኃላፊዎቹም ተጠያቂ ሆነው አደባባይ መቆማቸውን በተመለከተ የሀገሬ የፍትሕ ሥርዓት ሲመሰገን ሰምቼ አላውቅም:: ከመንጫጫት ያላለፉ አንዳንድ ብሶቶች በመገናኛ ብዙኃን መደመጣቸውን ግን አልዘነጋሁም::
የሪል እስቴት ዘርፉ ምንም ጠንካራ ጎን የለውም በማለት ድምዳሜ እንዳልሰጠሁ ይታወቅልኝ:: “ቤት ለእምቦሳ!” በማለት በጊዜውና በሰዓቱ ደንበኞቻቸውን አርክተው ያስደሰቱ እንደማይጠፉ ይገባኛል:: ያልፈረጠው የዘርፉ ሕመም ግን መልካም ጎኑን ፓራላይዝድ አድርጎ ያስነከሰው ይመስላል::
እውነት እውነቱን እንመስክር ካልንም የዘርፉ ችግር ለመንግሥት ይጠፋዋል ማለትም አይደለም:: ችግሩ ያበጠውን የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር በጥቂቱም ቢሆን ስለሚያስተነፍስ፣ ተቆንጥሮ የሚከፈለው የታክስና የግብር “አሞሌም” ስለሚጥም፣ የቤት አቅርቦቱን ፈተናም በጥቂቱም ቢሆን ስለተጋራው መንግሥት የዘርፉን ችግር ጠልቆ ለማስወገድ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ያለ ይመስላል:: ይህ የጸሐፊው ግምት ነው:: እውነታው ሌላ ከሆነ ይመለከተኛል የሚለው ክፍል የራሱን ማብራሪያ ሊሰጥ ይችላል::
እንኳን ጆሮዬን ዳባ ላለብስ ቀርቶ ዓይኔን ከዘርፉ ላይ መች ነቅዬ የሚልም ከሆነ ስለ ድፍረታችን በማስረጃ ያሳምነንና በአደባባይ ንሰሃ ያስገባን:: ያለበለዚያ ግን መንግሥት ባለበት ሀገር የቤት ተስፈኞች ከሪል እስቴቶች ጋር የገቡት የባለቤትነት ኪዳን የሚመክንና ገንዘባቸው እየተነገደበት እነርሱ ግን ለእንባ የሚዳረጉ ከሆነ “የመንግሥት ያለህ!” ጩኸት ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም::
ከሴፕቴምበር 5 – 9 ቀን 2016 ዓ.ም አንድ ታላቅ ጉባዔ እዚሁ ሀገራችን ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚከ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዶ ነበር:: የጉባዔው አስተናጋጅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ህንጻ ግንባታ እና ከተማ ልማት ተቋም ሲሆን AfRES (African Real Estate Society) የተባለ አህጉራዊ ማሕበር በየዓመቱ የሚያዘጋጃው የምክክር መድረክ ዓመታዊ ጉባዔ ነበር::
የዚህን ጉባዔ መርሐ ግብር በስኬት ያስፈጸመው ይህ ጸሐፊ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ይመራው የነበረው የግል ኩባንያ ስለነበር ብዙ ትምህርቶችን ለመቅስም ችሏል:: ስለ ሀገራችን ብቻም ሳይሆን ስለ መላው አፍሪካ ሀገራት የሪል እስቴት ዘርፍ ለማወቅም ጥሩ ዕድል ፈጥሮለታል::
ከአፍሪካ የዘርፉ አልሚ ባለሃብቶችና ምሁራን ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶችና ሃሳቦች፣ ከመስክ ጉብኝቶችና ውይይቶች መረዳት እንደተቻለውም ሀገራችን በሪል እስቴት ዘርፍ አበረታች ደረጃ ላይ መገኘቷ ተመስክሮላታል::
ዘርፉን ተብትበው የያዙት ማነቆዎችም እንዲሁ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል:: በተለይም ለማሳያነት በተመረጡ የከተማችን ሪል እስቴቶች ተገኝተው ተሳታፊያኑ ባደረጉት ጉብኝት ለመረዳት የተቻለው ከነችግሮቹም ቢሆን የሀገራችን የሪል እስቴት እንቅስቃሴ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት አርአያ ሊሆን እንደሚችል መጠቀሱን ሳላስታውስ አላልፍም::
የሀገራችን የሪል እስቴት አልሚዎች የራሳቸው የብሶት ኡኡታ ስላለባቸው በራሳቸው ድምጽ ብሶታቸውን ቢያሰሙ የተሻለ ይሆናል:: ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ለማድረግ የሞከርኩት የቤት ባለንብረት ለመሆን እየጓጉ ፍጻሜው እንደ ጅማሬው ላላማረላቸው በርካታ ዜጎች ድምጽ ለመሆን በማሰብ ነው::
ለሪል እስቴት አልሚዎች የማስተላልፈው መልዕክትም “ ቃል ይከበር! ተስፋ አይደፍጠጥ! ጥራትና ተያያዥ አገልግሎቶችን በተመለከተም የደንበኝነቱ ንጉሥነት እንኳ ቢቀር እንደ ሀገር ዜጋ ሰው በሰውነቱ ይከበር” የሚል ነው:: ጥራትና መሠረታዊ አገልግሎቶችም በውሉ መሠረት ይፈጸሙ ካልሆነም በህግና በኅሊናቸው ይዳኙ ብዬ አጽንኦት ሰጥቼ ማለፍ እፈልጋለሁ::
ከተለያዩ ሪል እስቴቶች መኖሪያ ቤት የገዙ ባለንብረቶችም ሰብሰብና ጠንከር ብለው በማሕበር ተደራጅተው መብታቸውን ያስከብሩ የግል ምክሬ ነው:: በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ተቋትም የቢሮክራሲያቸውን ሰንሰለት አሳጥረው የማደራጀቱን ሥራ ቢያፋጥኑ ጥቅሙ የጋራ ይሆናል::
በቅርቡ የሰነዶች ማረጋገጫ መንግሥታዊ ተቋም (የቀድሞው ውልና ማስረጃ) ቤት ገዢዎች የከፈሉባቸውን የባንክ ማስረጃዎች ከባንክ አስመስክራችሁ ካላቀረባችሁ የሚለውን አሳሪ መመሪያም እንደገና ቢፈትሽ አይከፋም:: ለዓመታት እየተንጠባጠቡ በባንክ በኩል የተከፈሉ ሰነዶችን በሙሉ እየለቀሙ ማሰባሰቡ ለባንኮች ሌላ የራስ ምታት እንደሆነባቸው ለመረዳት ችያለሁ::
የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ በዘርፉ ላይ የሚደመጡ የዜጎችን ጩኸት ለመረዳትና ቀረብ ብለው ለመዘገብ ዓይን አፋርነት ባያጠቃቸው መልካም ይሆናል:: ለወደፊቱም ቢሆን ይህ ጸሐፊ ዝርዝር ችግሮችን ቀረብ ብሎ እየተከታተለ እንዲታረሙ የድርሻውን ለመወጣት ይሞክራል:: ያበጁትን ማመስገን፣ ያጠፉትን መገሰጽ ሰብዓዊ መታወቂያ ነውና “ከዱላ ምክቶሽ” ይልቅ የዘርፉ አልሚዎች ራሳቸውን ፈትሸው ቀድመው ቢታረሙ አይከፋም::
ቢሆንማ . . .
ሥልጣኔ የሀብትና የዕውቀት መትረፍረፍ ብቻም ሳይሆን ቃልና ተስፋን በመጠበቅና በማስጠበቅ ጭምር አርአያ ሆኖ መገኘት ነው:: በተለይም የቤተሰብ ያህል ለሚቀራረብ ቤት ገዢ ደንበኛ በሪል እስቴቶች በኩል ተገቢው አክብሮትና ለጥያቄውም ፈጣንና ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ቢሰጠው ያስከብራል እንጂ አያጎልም:: በምሳሌነትም ያስወድሳል እንጂ ለነቀፋ አይዳርግም:: በዚህ ረገድ አንድ የግሌን ገጠመኝ ባስታውስ ለሃሳቤ ማጠቃለያ ጥሩ ግብዓት የሚሆን ይመስለኛል::
በውጭ ሀገር በትምህርት ላይ በነበርኩበት አንድ ወቅት በጣም የማከብረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ወዳጄ ወደ አንድ ቦታ አጅቤው እንድሄድ ጋበዘኝ:: አብረን እንድንሄድ የጋበዘኝ አካባቢ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የሀገሪቱ ዜጎች (ወዳጄም የዚያው ሀገር ዜግነት ነበረውና) ቤት የሚሰራ አንድ የተራድኦ ድርጅት ለዚህ ጓደኛዬ ቤት ሊሰራለት ተስማምቶ ኖሮ የቦታውንና የፕላኑን አተገባበር አስመልከቶ በቦታው ላይ ተገኝቶ ሊያብራራለት ስለፈቀደ ነበር:: እኔም በአጃቢነት የተፈለግሁት ለዚሁ መሠረታዊ የወዳጄ ጉዳይ በአስተያየት ሰጭነትና በታዛቢነት ከጎኑ እንድቆም ነው::
አጅግ የተገረምኩበት አንዱ ነገር “በጎ አድራጊው ድርጅት” ያንን ወዳጄን እንዴት በአክብሮትና በትህትና ያስተናግደው እንደነበረ ነው:: “አካባቢውን ወደድከው? አየሩስ እንዴት ነው? ኮሚኒቲው የደስታ ምንጭህ ሊሆን ይችላል? ቤተሰቦችስ ደስተኛ የሚሆኑ ይመስልሃል?” አቤት አክብሮት! አቤት ለሰው ልጅ ደስታ መጠንቀቅ? ይታደሉታል እንጂ አይታገሉት! እጅግ ያስገረመኝ ጉዳይ ኃላፊነት ተሰጥቶት የተላከው የድርጅቱ ተወካይ ግለሰብ በመጨረሻ ላይ የተናገረው ንግግር ነበር::
እንዲህ ነበር ያለው፤ “ደስታችን የአንተን ቤተሰብ ደስ ማሰኘት ነው:: በቀጠሯችን መሠረት አንድም ደቂቃ ሳናዛንፍ ቤትህን ሠርተን እናስረክብሃለን::” እንዳሉትም አደረጉ:: ይመስለኛል ለወዳጄ የተደረገለት በጎነት ካሰበውም በላይ ከፍ ያለ ይመስለኛል:: ያ ድርጅት “Habitat International” እየተባለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው::
ይሄው ድርጅት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ጉለሌ አካባቢ ሸጎሌ እየተባለ በሚታወቀው ልዩ ስፍራ 60 ያህል ሰዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ ሲል በ1983 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ምክንያት ሥራው ተስተጓጉሎበት እንደቀረ ትዝ ይለኛል:: ያ በጎ አድራጊ ድርጅት ምነው ዛሬ በሀገሬ ኖሮ በሕዝብ አንጡራ ሃብት እየነገዱ ባለገንዘቡን ለሚያማርሩ ሪል እስቴቶች ትምህርት በሆናቸው እያልኩ እቆጫለሁ:: መቼስ ምኞት አይከለከልም አይደል? ለማንኛውም ቸር አምላክ ቅን ልብና መተሳሰብን ይስጠን:: ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013