በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ክፍል አንድ )
የሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ በርካታ ሺህ ዓመታትን ወደ ኋላ ቢመልሰንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙ ፈቀቅ ያላለ ነው ። ይሁንና በሰራተኛ ማህበር ፣ በሙያ ማህበራት ፣ በተማሪዎች ማህበራት ፣ በመረዳጃ ማህበር ፣ በልማት ማህበር ፣ በተወላጆች ማህበር ፣ ወዘተረፈ ስም የፍትሐዊነት ፣ የተጠቃሚነት ፣ የውክልና ፣ የእኩልነት ፣ የነጻነት ፣ የመብት ጥያቄዎች ላይ መምከርና መወያየት የተለመደ ነው።
በነጻነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ስላልነበር እነዚህ ማህበራዊ አደረጃጀቶች ለፖለቲካዊ ትግል ሽፋን በመሆን አገልግለዋል። በ 1960ዎቹ እንደ እንጉዳይ የፈሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እርሾ በመሆንም አገልግለዋል። ሜጫና ቱለማ መረዳጃ ለኦነግ /ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ ፤ የሀገር ቤትና የውጭ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለኢህአፓ/ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ / ፤ ለመኢሶን/ የመላው ኢትዮጽያ ሶሻሊስት ንቅናቄ / ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) ለህወሓት/ለሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ / መመስረት ጥንስስ ሆነው አገልግለዋል።
በተማሪዎች የ1960ዎች እንቅስቃሴ ከእነ ግርማቸው ለማ ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስሙን የወረሱት ) ፣ ሰለሞን ዋዳ ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም ፣ በክፉም ስሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው ።ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ / ኮርጆ / ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ ተደጋግሞ ቢወቀስም ፤ አንዳንዶቹ ዋለልኝ የተማሪዎች ማህበር መሪዎች ያሳለፉትን ውሳኔ አነበበ፣ ጻፈ እንጂ የብሔር ጥያቄን ቀድሞም ሆነ ለብቻው አላነሳውም በማለት ጥያቄው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለደው ስለሆነ ከዋለልኝ ጫንቃ ውረዱ የሚሉ ወገኖች አሉ።
ያም ሆነ ይህ በፈጠራ ትርክትና በግልብ ትንተና መታገያና ማታገያ ሆኖ የመጣው የብሔር ጥያቄ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል እና አጣብቂኝ መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር ፤ ሀገር ፣ ሕዝብና የባህር በር አሳጥቶናል ።ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያባላና እያጨቃጨቀ ይገኛል ። በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች ተጠምዷል ።
የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል ።እዚህ ላይ በህወሓት ፣ በኦነግ እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ይስተዋሉ የነበሩ ልዩነቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል ።
ሆኖም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለትህነግ ፣ ለኦነግና ለሌሎች የብሔር ድርጅቶች መፈጠር እርሾ ሆኖ ማገልገሉ አይካድም ።የጋራ ሀገር ፣ ታሪክና ጀግና እንዳይኖረን አድርጓል ።ጥላቻ ፣ ልዩነትና ጎሰኝነት እንዲጎነቁል ለም አፈር ሁኗል ።የሀብት ብሔርተኝነትን /resource nationalism /ተክሏል፡፡
የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ ም በ11 ሰዎች በምዕራብ ትግራይ ቆላ በሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በተባለ ስፍራ የተመሰረተው እና የቀዳማይ ወያኔ ቅርሻ የሆነው “ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ “ / ተሓህት / ወደ አማርኛ ሲመለስ የትግራይ ሕዝብ አርነት ግንባር፤ የዛሬው ትህነግ/ህወሓት ባልጠራ ርዕዮተ ዓለም የትግራይ ሕዝብ ጭቆና መደባዊና ብሔራዊ ነው በሚል ግልብና እንቶፈንቶ ትንታኔ እንዲሁም አንድን ሃይማኖትንና ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ የተጠነሰሰው በተማሪዎች እንቅስቃሴ እርሾነት ነው ።
ደርግን ለ17 ዓመታት በነፍጥ ታግሎ በ1983 ዓ.ም ለስልጣን ቢበቃም ።የብሔር ጥያቄን ለከፋፍሎ መግዣነትና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ለማሳደድ ስላዋለው የብሔር ጥያቄን በሀቀኝነት ሙሉ በሙሉ አልመለሰውም ።የመደብ ቅራኔውንና ልዩነቱን ከመፍታት ይልቅ ዘራፊና ስግብግብ መደብ ፈጠረ ።ቁጭት ፈጥሮ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አደረገው እንጂ ታገልሁለት ያለውን የብሔር ጥያቄ በልኩ አልመለሰውም ።
ለዚህ ነው ጥያቄው የብሔሩ ልሒቃን በአቋራጭ ስልጣን መያዣ እንጂ የተራው ሕዝብ ጥያቄ ተደርጎ የማይወሰደው ።በግሌ ከትህነግ የብሔር ጥያቄ ይልቅ የኦነግ የብሔር ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ በቅንነትና በእውነት/ጄኒውን / ሆኖ የተነሳ ሆኖ ይሰማኛል ።ይህን ስል መስራች ልሒቃኑ ስልጣን ኮርቻ ላይ ለመቆናጠጥ እንደ እርካብ አይጠቀሙበትም ወይም ትግሉ አልተጠለፈም ማለት አይደለም ።
የታላቁ መፅሐፍ ወንጌል ተመስርቶ ፤ “ በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን ፤ በሌሎች ላይ አታድርግ ፤ “ በሚል በ1950ዎች አጋማሽ የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ፤ ትምህርትን ፣ ጤናንና ሌሎች የልማት ስራዎች በኦሮሞ አካባቢዎች ለማስፋፋት ቢቋቋምም የወቅቱን የፓሊስ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ታደሰ ብሩን ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ በሥርዓቱ በጥርጣሬ እንዲታይ እንድርጎት እያለ ፤ በንጉሱ ላይ በተሞከረ የግድያ ሙከራ አመራሮቹ ተጠርጥረው ዘብጥያ በመውረዳቸውና በመሰደዳቸው መረዳጃ ማህበሩም በመታገዱ ቆይቶም ጄነራሉ በደርግ በመገደላቸው ህቡዕ የገባው መረዳጃ ማህበሩ እና የኦሮሞ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተጋምዶ በ60ዎቹ መጨረሻ የኦሮሞ ነጻነት ግባር /ኦነግ/ን ይዘው ሊወጡ ችለዋል ።
በድቡሽት ላይ በተመሰረተ ግልብ ትንተና የመደብ ጭቆናን ከብሔር ጥያቄ አፋልሰውና አጣርሰው የፈጠሩት ትህነግ መጨረሻውን እየተመለከትን ነው። ከጅምሮ ተሓህት በስሁት ትንታኔ የተመሰረተ ቡድን መሆኑን የድርጅቱ መስራችና ነባር ታጋይ አይተ ገብሩ አስራት” ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ “ በሚለው መፅሐፋቸው ገፅ 38 ላይ እንዲህ አረጋግጠውልናል ።“ የማገበት /ተሓህት / መስራች አባላት ትግሉ መደባዊ ይሁን ብሔራዊ የጠራ ግንዛቤ ባይኖራቸውም ፤ የብሔር መብት እስከ መገንጠል የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዱ የነበረ ሲሆን በዚህ ዙሪያ ብዙ ውዝግብ አልነበረም ።“ ይሉናል።
ትህነግን ጨምሮ የሀገራችን ፖለቲካ ድርጅቶች ለምን ይከሽፋሉ ? ይወድቃሉ ? የሚለው ጥያቄ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም ፤ ይህን ጥያቄ ባንሰላሰልሁ ቁጥር ሶስት ገዥ ነጥቦች ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።
1ኛ . ፖለቲካዊ ትንተናው በአመክንዮና በተጠየቅ ሳይሆን በስሜትና በግዕብታዊነት የተቃኘ መሆኑ፦ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን /መስራች አባል አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በዚያ ሰሞን “ አርትስ “ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው “ ትናንትም ሆነ ዛሬ እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ የገጠሙንን ፈተናዎች ለመሻገር ሳይንሳዊ ጥልቅ ትንተና ያስፈልጋል። ትንተናው ግን በግዕብታዊነትና በስሜት ሊሆን አይገባም ።“ ብለዋል ።
ዛሬ ለምንገኝበት ውርክብ የዳረገን የ60ዎቹ ትውልድም ሆነ እሱን ተከትለው የተቀፈቀፉ ነፃ አውጭ ፓርቲዎች በስሜትና በደም ፍላት ተመስርቶ የተደረገ ትንተናና የደረሰቡት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው ማለት ይቻላል ።በተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ተንጠልጥሎ የሚሰጥ የመፍትሔ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ለውጥ ውጤቱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው።
የመደብ ትግልን በማንነት ጥያቄ አሳክሮ የተወጠነው ዘውጌ’ዊ ፌዴራሊዝምም ሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተዘፈቅንበት አዘቅት ሊያወጣን ይቅርና ለከፋ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ዳርጎን አርፎታል ፡፡
2ኛ . ለችግሮች ሀገርኛ መፍትሔ አለመሻት፦ ላለፉት 50 ዓመታት እንደ መስኖ ውሃ እነ ሌኒን ፣ ስታሊን ፣ ማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ማኦ ፣ ማኪያቬሊ ፣ ወዘተ . በቀደዱልን የርዕዮተ ዓለም ቦይ መፍሰሳችን አልያም ሲገድቡን መገደባችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ። ሆኖም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬም ጥያቄዎቻችን አለመመለሳቸው ችግሮቻችን አለመፈታታቸው ሳያንስ ይበልጥ ተወሳስበው ውላቸው ጠፍቷል ።
ለዚህ ነው ለአንደኛው ችግር መፍትሔ ስናበጅ ሌላው እንደ እንቧይ ካብ ከጎን የሚናደው ።ከሌኒን ኮርጀን የብሔር ጥያቄን እንደፈታን ስናስመስል ሀገራዊ ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀው ።ከሶቪየት ገልብጠን የዕዝ ኢኮኖሚን
ስንተገብር ፈጠራ የኮሰመነው ኢኮኖሚው የደቀቀው ።ከደቡብ ኮሪያ ፣ ከጃፓንና ከቻይና እንዳለ ቀድተን ልማታዊ መንግስት ስናነብር ሀገር የጥቂቶች ሲሳይ ሆና ያረፈችው ።ለነገሩ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ተቋማት በሌሉበት ልማታዊ መንግስት አይታሰብም ።እነዚህ ማሳያዎች ችግሮቻችንን በተናጠል እና በተኮረጀ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖሊሲ ለመፍታት ያደረግነው ሙከራ መክሸፉን ያሳጣሉ ።
ለዚህ ነው ሀገር በቀል ወደ ሆነና ዙሪያ መለስ እይታ ማተኮር የሚያስፈልገው ።ለዚህ ነው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “መደመር “ ቁጥራቸው ቀላል ባልሆነ ልሒቃን ሀገርን ፣ ትውልድንና ዘመንን የዋጀ ምላሽ ተደርጎ የተወሰደው ።ፅንሰ ሀሳቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ በ” ቲንክ ታንክስ “ ፣ በሙያ ማህበራት ፣ በዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ፣ ወዘተ . ሲተች ሲሔስ ደግሞ ይበልጥ የጋራ አካፋይ ሆኖ ሊወጣ ይችላል ተብሎ የታመነው ፡፡
3ኛ . የተረክና የታሪክ ምርኮኛ መሆን ፦ ሰለሞን ሥዩም የተባሉ ፀሐፊ በፍ-ት-ሕ መፅሔት ከአንድ ዓመት በፊት ባስነበቡት መጣጥፍ ታሪካችን ሶስት የትርክት ዘውጎችን መፍጠሩን ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡን ጠቅሰው አትተዋል ።አክሱማዊ ፣ ሴም ኦሪየንታላዊ እና ስር – ነቀላዊ ናቸው ።ሶስተኛው የስድሳዎቹ ትውልድ የፈጠረው ነው ።የታሪኩንም የፖለቲካውን ትርክት ከስሩ ለመቀየር ፣ ለመንቀልና ለመፈንቀል ነው የሰራው ።
ትርክት ቀድሞ በተቀመጠ ድምዳሜና ብያኔ ላይ የሚዋቀር መሆኑ የውርክቡ መግፍኤ ነው ።የዚህ ትውልድ ቅርሻ የሆኑ “ ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጭዎች “ በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ታሪክን በሸውራራ ትርክት ለመቀየር ያደረጉት ጥረት በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸው ነበር ማለት ይቻላል ።በእነዚህ የፈጠራ ትርክቶች በዜጎች መካከል ጥላቻን ፣ መጠራጠርንና ልዩነትን ጎንቁለው በማሳደግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል ።
በተዛባ ትርክት ለቆሙ የጥላቻ ጣኦታት እንድንሰግድ መስዋዕት እንድንገብር አድርገዋል ።ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለይ ለውጡ ከባተ ወዲህ ሰሞነኛውን ጨምሮ የተስፋዋን ምድር ወደ አኬልዳማ ቀይረው ዳግም ቅስማችንን ሰብረው አንገታችንን አስደፍተውናል።
ሆኖም ዛሬም ከዚህ የጥላቻ አዙሪት ለመውጣት ተረካችንን እንደገና መበየን እና ቂም በቀል የሚያወርሱ ጣኦቶቻችንን ከአእምሮ ጓዳችን አውጥተን ማንከባለል በየከተሞች ያቆምናቸውን የጥላቻ ሀውልቶች እንደገና ስለፍቅር ስለይቅርታ መቅረፅ አለብን። ከዚህ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ሳይሸራረፍ የማረጋገጥ ጉዳይ አጠናክሮ የመቀጠል ግዴታም አለብን ።
የሰላም ሚኒስቴርና የታሪክ ልሒቃን ታሪካችንን መቧቀሻ ጓንት ከማድረግ ይልቅ የወይራ ዝንጣፊ መያዥያ እንዲሁም የሰላምና የመግባቢያ ድልድይ መገንቢያ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው እያልሁ በክፍል ሁለት መጣጥፌ ደግሞ ከፍ ብዬ ካነሳሳኋቸው ማንጠሪያዎችና ሚዛኖች ጎሎ ስለሞተው ትህነግ አረዳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን ።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013