ጌትነት ተሰፋማርያም
አቶ ግርማይ ሀደራ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት ወይም ኢዲዩ ፓርቲ ታጋይ ናቸው። በትጥቅ ትግል በኢትዮጵያ እና በሱዳን አካባቢዎች ለበርካታ አመታት ተሳትፈዋል። ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ምርጫቸው አድርገው መሳተፍ ከጀመሩ በኋላ በሶስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ላይ ተወዳድረዋል።
ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው። ኢዲዩን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነውን የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር(ኢፍዴኃግ) ሊቀመንበር በመሆን እያገለገሉ ይገኛል። ከሰፊው የትግል ታሪካቸው ጥቂቱን እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል።
አዲስ ዘመን:- በ1960ዎቹ በትግራይ ክልል የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– የአፄ ኃይለስላሴን መንግስት የጣለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ ሰራዊቱ እና ህዝቡ አንድ ሆኖ ስርዓተ መንግስቱን ገርስሶታል። ጥያቄው የነበረው መሬት ላራሹ ይሁን፣ የብሄሮችና ብሄረሰቦች እኩልነት ይከበር፣ ዴሞክራሲ ይከበር የሚል ነበር። ደርግ በመሃል ገብቶ ወታደራዊ መንግስት አቋቋሞ ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም በሚል ማስመሰያ ቃል መንቀሳቀስ ሲጀምር ተቃዋሚ ፓርቲዎች በትግራይ መቋቋም ጀመሩ።
በትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው በ1967 ዓ.ም አካባቢ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ቀደም ብሎ በትግራይ አካባቢዎች ይንቀሳቀስ ነበር። በ1967 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ ተጋድሎ ሀገርና ህዝቢ ትግራይ ጠረናፊት ኮሚቴ የሚባለው ፓርቲ ተቋቋመ። ጠረናፊት የሚለው ቃል መልዕክቱ ከትግራይ ውጪ ያሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ታጋዮችንም ለማቀፍ እና አብሮ ለመጓዝ እንዲቻል የተሰጠ ስም ነው።
በወሎ፣ በጎጃም፣ በሸዋ በወለጋ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች አምጸው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን እንሰበስባቸዋለን ለማለት ነው ጠረናፊት ኮሚቴ የተባለው። ከዚያም ከአንድ ዓመት እንቅስቃሴ በኋላ ጠረናፊት ኮሚቴ 1968 ዓ.ም ላይ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት(ኢዲህ) ወይም በተለመደው የአንግሊዘኛ አጠራሩ ኢዲዩ ተብሎ ትግሉን ጀመረ።
ህወሓት ደግሞ ከጠራፊት ኮሚቴ ምስረታ አራት ወራት በኋላ በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም ላይ ነው የተመሰረተው። ገድሊ ግንባር ትግራይ የሚባል ፓርቲም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። ይሁንና በወቅቱ ህወሓት ውህደት እናድርግ ብሎ ጠርቶ በአንድ ሌሊት የቡድኑን አባላት በመፍጀት ፓርቲውን አከሰመው።
አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያምን በመሆኑ ደርግን ጥለው ህዝቡ ሰላማዊ ህይወት እንዲኖረው ይታገላሉ ብሎ የሚያምናቸውን ፓርቲዎች ይደግፍ ነበር። በወቅቱም በርካቶች በትጥቅ ትግል ይንቀሳቀሱ ስለነበር ጾታ ሳይለይ ወጣቶች ሰፊ ተሳትፎ ነበራቸው። እንደአጠቃላይ መመልከት ከተቻለ ግን በትግራይ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ አብዛኛውን ህዝብ ያሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እቅዳቸውን እያሳወቁ ትግል ማድረግ የጀመሩበት ወቅት ነው።
አዲስ ዘመን:- የኢዲዩ ፓርቲ ከህወሓት ጋር የነበረው የፖለቲካ ግንኙነት ምን መልክ ነበረው?
አቶ ግርማይ ሃደራ:- በመሰረቱ ኢዲዩ እና ህወሓት አብረው ለመስራት ህጋዊ ስምምነት አድርገው አያውቁም። ይሁንና በሚገናኙበት ወቅት አብረው ለመታገል ጥረት ያደረጉበት ወቅት ነበር። ኢዲዩ ደርግ ቢወድቅ እንኳን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መስራት እንደሚችል የሚያስብ እና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ነበር። በቅድሚያ ኢዲዩ ከህወሓት ጋር በመተባበር ደርግን መጣል ይቻላል የሚል እምነት የነበረው ፓርቲ ነው።
ከህወሓቶች ጋር በየበረሃው በምንገናኝበት ወቅት ግን ምንድነው አላማችሁ ይሉናል። እኛም ዲሞክራቲክ ስርዓት በኢትዮጵያ እንዲነግስ፣ ህዝባዊ መንግስት እንዲኖር፣ በህዝብ ተመርጦ በህዝብ የሚወርድ ስርዓት እንዲኖር ነው የምንታገለው እንላቸዋለን።
ህወሓት በአንጻሩ ትሀህት የሚል ስያሜ የነበረው እና በአጥፍቶ መጥፋት የሚያምኑ እንዲሁም ስለአንድነት የማያስቡ ሰዎች ስብስቦ የያዘ ነበር። ትሀህት ማለት የትግራይ ነጻ አውጪ ነው። ህዝቡ ደግሞ በኢትዮጵያ አንድነት ከማንም በላይ የሚያምን በመሆኑ ከማነው ነጻ የምንሆነው እያለ ይጠይቃቸዋል።
ህወሓቶችም የትግራይ ህዝብ ስለአንድነት እንዳያወራ እና ስለዴሞክራሲ እንዳይናገር ውስጥ ውስጡን ማስነገር ጀመሩ። በዚህ ምክንያት በወረቀትም ባይሆን በንግግር አብረን እንሰራለን በሚሉ በኢዲዩ እና በህወሓት መካከል በርካታ ግጭቶች ተፈጠሩ።
ኢዲዩ እና ህወሓት 46 ጊዜ ጦርነት ገጥመዋል። እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድም ደብዳቤ ተጽፎ ህወሓትን እናጥፋ የሚል ደብዳቤ ለኢዲዩ ታጋዮች ደርሶ አያውቅም። ሁሌም ኢዲዩ ከህወሓት የሚደርስበትን ትንኮሳ ለመከላከል በሚወሰድ እርምጃ ነበር ግጭቶች ውስጥ ተሳትፎ የሚደረገው። በመሆኑም የኢዲዩ እና የህወሓት ግንኙነት አብዛኛው በግጭት እና በአለመግባባት ነው የተቋጨው።
አዲስ ዘመን:- ህወሓት ከኢዲዩ ጋር ሲነጻጸር ፍጹም ተቃራኒ ነበር፤ የትግራይ ህዝብ አንድነትን ይፈልግ ከነበረ ህወሓትን እንዴት ይመለከተው ነበር?
አቶ ግርማይ ሃደራ:- በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ኢዲዩ ዲሞክራቲክ ስርዓት ነው የሚከተለው። ከዚህ ባለፈ ሀገር አቀፍ እና ህብረ- ብሔራዊነትን ይቀበላል ። ከቡድን ይልቅ በቅድሚያ የአንድ ግለሰብ ነጻነት መከበርን ያምናል ። የፓርቲው መግቢያ ቃልኪዳናችን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔዋና ገናንነቷን ማስመለስን መሰረት ያደረገ ነው።
ህወሃቶች ደግሞ ስማቸውን ሳይቀይሩ ትሀህት በሚባሉበት ወቅት ኮሚኒስት ከመሆናቸው ባለፈ ጠባቦች እና በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑ ናቸው። ህወሃቶች ቀድሞ ትሀህት ብለው የተነሱበት አላማ እና ትግራይን ነጻ እናወጣለን ብለው የተነሱበት ቃል ይዘው በቀድሞው የአድዋ አውራጃ እና የተንቤን አውራጃ አዋሳኝ ላይ የሚገኘውን ወርሂ የተሰኘውን ወንዝ እንኳን መሻገር አልቻሉም።
ነጻ አውጪ የሚለውን ቃል የትግራይ ህዝብ ልክ እንደአባጨጓሬ ሰውነቱን ይኮሰኩሰው ጀመር። በዚህ ወቅት ድሮ በአባቶቻችን በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን የነበረ ቀዳማይ ወያኔ የሚባል የትግል እንቅስቃሴ ነበራቸው። ያ ትግል በትግራይ ህዝብ ስሜት ውስጥ ነበርና ይህን እድል ለመጠቀም ስሙን በማቀላቀል ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ ብለው ህወሓት የሚለውን ስያሜ ያዙ።
ስለዚህ ወያኔ የሚለውን የቀደመ ስም ነጻ አውጪ ከሚለው ጋር አቀናጅተው አላማቸውን ሳይለቁ በ1968 መውጫ ላይ ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት አደረጉ። ህወሓት ስሙን ይያዝ እንጂ በውስጡ ግን አሽአ የሚል ልዩ ኮድ ነበራቸው። አሽአ ማለት አድዋ፣ ሽሬ እና አክሱምን የሚያጠቃልል ልዩ ታማኝነት የሚሰጣቸው ሰዎች ስብስብ ነው። እናም አሽአዎች ድርጅቱን መምራት አለባቸው ብለው ማስቀመጥ ጀመሩ።
የእንደርታ ሰዎች ደግሞ በፖለቲካው ሰፊ እንቅስቃሴ የነበራቸው ስለሆኑ ይህንን አሽአ የሚለውን ኮድ አወቁባቸው። እናም ለምን አስፈለገ የሚለውን ጥያቄ በሰፊው አነሱ። ህንፍሽፍሽ የሚለው የእርስ በእርስ የህወሓት አባላት ግጭት የተነሳው በዚህ ወቅት ነው። አንዱ ሌላውን ቀድሞ እየመታ ብዙዎች ያለቁበት ታሪካቸው ነው።
ለአንድ ዓመት ያክል ይህ ህንፍሽፍሽ በርካቶችን ህይወት እያሳጣ ቀጠለ። በመጨረሻም የእንደርታ፣ አጋመ፣ ተንቤን እና ራያ የነበሩ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ጥለዋቸው እየወጡ ለስደት ተዳረጉ።
የቀሩ ህወሃቶችም በቤተሰብ እየተሰባሰቡ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ህዝብ ውስጥ ለመደበቅ በሰፊው መንቀሳቀሳቸውን ቀጠሉ። በክህደት እና በውሸት አጠገባቸው ያለውን ሁሉ ተቀናቃኝ እያዳከሙ እነሱ ብቻ የትግራይ ህዝብ ወካይ አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል። ህዝቡንም ሲያታልሉ እና ሲጠቀሙበት በመኖራቸው ትክክለኛ ማንነታቸው እየቆየ ነው እየታወቀ የመጣው።
አዲስ ዘመን:- ኢዲዩ አቅሙ እንዲዳከመ ብሎም እንዲጠፋ የህወሓት አባላት ዋናውን ድርሻ እንደተወጡ በሰፊው ሲገለጽ ቆይቷል ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– ኢዲዩ ውስጥ ከአርሶአደር ጀምሮ እስከ ሚኒስትሮች የደረሰ ሰፊ አባላት ይሳተፉ ነበር። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች ተሳትፎ ያደረጉበት ፓርቲ ነው። የኢዲዩ ታጋይ ታጣቂዎች ብቻ ከ30ሺ በላይ ናቸው። ሽሬ፣ አድዋ፣ አክሱም፣ ተንቤን እና እንደርታ የሚገኙ ወረዳዎችንም ይዞ የትግራይ ግማሽ አካባቢዎች የኢዲዩ ነጻ ቦታዎች ነበሩ። አብዛኛው የሱዳን ድንበር አካባቢዎች ነጻ መሬት ነበረን።
ኢዲዩን ግን እንዲዳከም አሊያም ህወሃቶች እንደሚሉት የጠፋው በህወሓት ሴራ አይደለም። ይልቁንም በኢዲዩ ውስጥ የነበሩ አመራሮች ግልጽ ያልሆነ ሴራ ነው ችግሩን የፈጠረው። ህወሓት ግን በትምህርት ስርዓት ጭምር አስገብቶ ለትውልዱ ሲነግር የኖረው እራሱ ኢዲዩን ደምስሼ አጥፍቼዋለሁ እያለ ነው።
በዚህ የሃሰት ትምህርት ተቀርጸው የወጡ ጋዜጠኞች ጭምር ከዚህ ቀደም ከኢዲዩ ነኝ ስላቸው ኢዲዩማ በህወሓት ተደምስሶ ጠፍቶ የለ እያሉ ሲናገሩ ስሰማ አዝኛለሁ። እውነታው የኢዲዩ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ጄኔራል ነጋ ተገኝ የተባሉ ሰው የፓርቲው ሊቀመንበር ልዑልመንገሻ ስዩም ሳያውቁ ሁሉም የኢዲዩ ታጋይ ወደሱዳን ድንበር እንዲሄድ በደብዳቤ በማዘዛቸው ነው ፓርቲው የተበተነው።
ሴራው ለምን እንደሆነ ባላውቀውም ለስብሰባ በሚል የሃሰት መረጃ ሁሉም አካባቢ ያለው የኢዲዩ ታጋይ ከነመሳሪያው ሱዳን ድንበር እንዲሰባሰብ ታዘዘ። ሱዳን ከገቡ በኋላ ደግሞ ጄኔራሉ እና ተከታዮቻቸው መልሰው የነልዑል መንገሻ ሰራዊት የአፄ ዮሐንስን ደም ለመበቀል መጥቷል ብለው ለሱዳኖች የሃሰት መረጃ አቀበሉ።
30 ሺህ የሚገመተው የኢዲዩ ጦር ሱዳን ሲገባ ሱዳኖች ምን ሆናችሁ በማለት ትጥቅ እንዲፈታ መጠየቅ ጀመሩ። ሱዳኖች በወቅቱ ከውጭ የሚመጣውን እርዳታ ለኢዲዩ ያቀብሉ የነበሩ እና ትልቅ ድጋፍ ያደርጉ ስለነበሩ ማንም እነሱን ለመውጋት ያሰበ አልነበረም። እናም ታጣቂው ሁሉ ግራ ተጋብቶ ትጥቅ አልፈታም ቢልም በመጨረሻ በድርድር ተመልሶ ይሰጣችኋል በሚል ሰበብ በ1972 ዓ.ም ትጥቅ እንዲፈታ ተደረገ ፤ ጥቂቶች ግን አንፈታም በሚል እየተታኮሱ ወጡ።
ትጥቅ የፈታው የኢዲዩ አብዛኛው ሃይል ግን ወደስደተኛች ካምፕ እንዲገባ ተደርጎ ለሰባት ዓመታት ያክል በዛው በመታጎሩ ፓርቲው ተዳከመ የያዛቸውም ቦታዎች ነጻ ሆኑ። ኢዲዩ እያለ ይታገልበት የነበረው መሬት ነጻ በመሆኑ ምክንያት ህወሓት እድሉን ተጠቅማ ማንም በሌለበት ቦታው ላይ መሸገ ።
ህወሃቶች ለ15 ዓመት ሙሉ አንድም የትግራይ ወረዳ ነጻ ሳያወጡ ነው ኢዲዩ የለቀቃቸውን ቦታዎች ላይ ሰፍረው ሲነግዱ እና የቢዝነስ እቅዳቸውን ሲነድፉ የኖሩት። ለኢዲዩ ትግል መዳከም የኢዲዩ አመራር ሴራ ብቻ ሳይሆን የደርግ፣ የህወሓት እና የሻዕቢያም ሴራ እንዳለበት አምናለሁ። ይሁንና ሙሉ ለሙሉ ኢዲዩ አልተደመሰም ወደውጭ ሀገራትም የሄዱ ሀገር ውስጥም ያሉ ሰዎች ፓርቲውን በድጋሚ ለማቋቅም ጥረት አድርገዋል።
አዲስ ዘመን:- ህወሃቶች ወደ ስልጣን ሲወጡ በኢዲዩ አባላት ላይ የፈጠሩዋቸው ችግሮች ሰፊ እንደነበሩ ይነገራል ፤ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– ህወሓት በቅድሚያ የኢዲዩ አባላት የነበሩ ሰዎች ሁሉ በትግራይ ምድር ላይ መሬት እንዳያገኙ በገሃድ አውጇል ። ደርግ የወረሳቸውን ቤቶች ሁሉ ሲመልሱ ከስልጣናቸው እስኪነሱ ድረስ የኢዲዩ አባላት የተወረሰባቸውን ቤቶች ለመመለስ ፍቃደኛ አልነበሩም።
እስከፌዴራል መንግስት ድረስ በወቅቱ ኡኡ ብለው ቢጠይቁም ያፌዝባቸው ነበር። ለክልሉ ሲጠይቁ ጥያቄያችሁ በዞን ይመለሳል ፣ ዞን ሲጠይቁ ክልል ጠይቁ እየተባሉ ሲንከራተቱ ቀይተዋል። ለአብነት የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ የነበረው ገበሩ አስራት ጋር አባላቱ ተሰባስበው ቤቶቻችን ይመለስልን ብለው ሲጠይቁ የሽሬ ዞን አስተዳዳሪው ኪሮስ ቢተው ጋር ጠይቁ ተባሉ። ኪሮስ ጋር ሄደው ሲጠየቁ ደግሞ ክልሉ ነው መልስ የሚሰጥ አላቸው። በዚህ መልኩ ያፌዙባቸው ነበር። የኢዲዩ አባላት ሞራላቸው እንዲወድቅ እና ማንነታቸውን እስኪጠሉ እንግልት ደርሶባቸዋል።
የኢዲዩ አባላትንም ሆነ በፖለቲካ የተቃወማቸውን ሰው ንብረት ከወረሱ በኋላ ከባለቤቱ አፋተው ህይወቱን ያጠፉታል። ከፈለጉ ከባለቤቱ አፋተው ለሚስትህ ግማሹን ንብረት ይሰጡና ለሌላ ያጋቧታል። ይህ አረመኔያዊ ተግባር ከበረሃ ጀምሮ ይሰሩበት የነበረ ነው። በአጠቃላይ የህወሓት አመራሮች በሰው ስቃይ የኮሩ እና የሰለጠኑ በሰው ስቃይ ያደጉ ሰዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን:- ህወሓት በተለይ የፊውዳል ቤተሰቦችን እና ከባላባቶች ጋር ግንኙነት ያላቸውን የማደን እርምጃ ነበረው የሚል ሃሳብ ይነሳል፣ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ምን አለ?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– ህወሓት ሲፈጠር ጥንታዊነት፣ አባታዊነት እና ታሪካዊነት የማይፈልግ ፓርቲ ነው። የድሮ አባቶች ባይማሩም እንኳን በተፈጥሯቸው የአዕምሮ እድገታቸው እና ስለሀገር አንድነት ያላቸው ግንዛቤ ከፍተኛ ነው። ህወሃቶች ደግሞ እነሱ በሚቃኙት መንገድ ዝምብሎ የሚጓዝ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር፣ የቀደመ ታሪክ እና ተጨባጭ ሁኔታ የሚያውቁ እንዲሁም ያለፉት መንግስትታት የሰሩትን ቀን እና ሰዓት እንኳን ሳያዛቡ የሚናገሩ አባቶችን ማጥፋት እንዳለባቸው ወስነዋል።
እናም ባላባቶች እና ታሪክ አዋቂዎችን ልቅም አድርገው አድነው ነው ያጠፏቸው። በዚህ ምክንያት ከዚያ በኋላ የመጣውን የትግራይ ወጣት ትውልድ ትግራይ ማን ነች ብለህ ብትጠይቀው ትክክለኛውን ነገር አይነግርህም፣ ትክክለኛ ታሪኩንም አያውቅም ፤ የታሪኩ ድሀ አድርገውታል። ከዚህ ይልቅ ትግራይ ታምረኛ ሀገርና ህዝብ ፣ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ መኖር የማይፈልግ እንዲሁም ሁሉን አዛዥ ሆኖ የሚኖር አድርገው ነው በተሳሳተ ትርክት የቀረጹት።
በአንጻሩ የኢትዮጵያን ታሪክ ስታነሳ ”ሀ” ብሎ የሚጀምረው ከትግራይ ነው። የአክሱም ስርወ መንግስት፤ ንግስተ ሳባ እንዲሁም የየሃ ጥንታዊ ታሪኮች የሚነሱት ከትግራይ ነው። ታሪኩ እስከ ጎንደር እና ላሊበላ እንዲሁም ሸዋ ድረስ ሄዶ ይተሳሰራል። በስነጽሁፉም ሆነ በስነህንጻ ጥበብ ሙያ እና ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ቀይባህር እና ላሊበላ እንዲሁም ጣና ውስጥ ውስጥን ዋሻ ፈልፍለው የሚሄዱ አባቶች ነበሩን።
ይህን ታሪክ ግን ወጣቱ ትውልድ እንዳያውቅ፣ በዚህ ታሪክ አንድነቱን እንዳያጠናክር በማሰብ ህወሃቶች ታሪክ አዋቂዎችን እና ባላባቶችን አድነው ሲያጠፉ ኖረዋል። ወጣቱንም በእነሱ ትርክት ለመያዝ ታሪክና ታሪክ አዋቂዎችን ማጥፋት ላይ ተጠምደው ነበር።
አዲስ ዘመን:- ህወሓት ከማህበረሰቡ አባላት በተለይ ቤተክህነት ላይ የተለየ ጫና ያሳድር እንደነበር የሚገልጹ ሰዎች አሉ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– በተለይ የህወሓት አመራሮች ከትግል ወቅት ጀምሮ ሳውቃቸው ሃይማኖት የላቸውም። በበረሃ እንኳን ስለሃይማኖት ሲነሳ የህወሓት ሰዎች በማፌዝ እና ሃይማኖት ምን ያደርጋል በሚል ስሜት ነው ህይወታቸውን የሚገፉት። ሃይማኖት መያዝ እና መጸለይን ልክ እንደኋላ ቀርነት ነው የሚያዩት። በኋላም ወደስልጣን ከመጡ በኋላም ቤተክርስቲያን ላይ ጉዳቶች አድርሰዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ እና አንድነት ማፍረስ ከፈለግክ ዋና ሞተሩ ያለው ቤተክርስቲያን ላይ ነው። ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ባለውለታ መሆኗ ይታወቃል። ልክ እንደትምህርት ሚኒስቴር በርካቶችን አስተምራለች ፣ እንደወታደር ደግሞ ታቦታትን ይዛ ነው ጠላት ሲመጣ የተዋጋችው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅርስ አላት፣ ታሪክም አላት ህወሃቶች ደግሞ ከሁለቱም ጋር የተጣሉ ናቸውና ቤተክርስቲያኗ ላይ ግልጽ ተጽእኖ አድርገዋል። የኦርቶዶክስ ጳጳስ የሆኑት አቡነ መርቆሬዎስን እንኳን ብንመለከት የህወሓት አመራሮች ሽጉጥ ይዘው ይቀድሳሉ የሚሉ እና ሌሎችንም አሉባልታዎች በመንዛት ህዝብ እንዲጠላቸው ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ህዝቡ ግን ሊሰማቸው አልቻለም።
በመጨረሻም በህወሓት የደህንነት ሰው በነበረው ክንፈ ገብረሚካኤል ተገደው ከሀገር እንዲወጡ መደረጉን የህወሓት ታጋይ የሆነው ታምራት ላይኔ ጭምር የመሰከረው ሃቅ ነው። ከዚያም ሌላ ጳጳስ ሾሙ።
ዶክተር ዐብይ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ አቡነ መርቆሪዎስም ወደሀገር የገቡት። እንደዚህ አይነት በተመሳሳይ በርካቶች የህወሓት ጫና የደረሰባቸው የሃይማኖት ሰዎች መኖራቸው ሲታሰብ ህወሓት ከሃይማኖታዊ ስርዓት የራቀ እና ቤተክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጫና ቀላል እንዳልነበር መገመት አይከብድም። በህግ ማስከበሩም ቢሆን መስጂዶች እና ቤተክርስቲያኖችን ለጦር አላማ በመጠቀም ሰፊ ጥፋት አድርሰዋል።
አዲስ ዘመን:- እንደአጠቃይ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው ሴራዎች እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ ግርማይ ሃደራ:- ህወሃቶች የትግራይ ህዝብን 46 ዓመት ሙሉ አስረዋል ፤ ገድለዋል ፣አሰቃይተዋል። መላ ኢትዮጵያን ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት አጭበርብረው በሀይልና በሴራ ገዝተዋል። ወደስልጣን ሲመጡ እኮ የትግራይን ህዝብ ትግራይን በወርቅ እንቁ እናደርግልሀለን ፣ተደላድለህ ትኖራለህ ብለው ነው የቀጠፉት።
የትግራይ እናት ግን በአዲስ አበባ ትራፊክ መብራት አካባቢ ልጅቿን አዝላ ምጽዋት ስትጠይቅ ልታገኛት ትችላለህ። በአጠቃላይ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመው ሴራ እና በደል ተቆጥሮ አያልቅም።
እነሱ እኮ በትግል ላይ ባሉበት ወቅት ስልጣን ከያዝን ግብር አትከፍሉም እያሉ ህዝቡን ሲዋሹት ነበር። ኋላ ስልጣን ሲይዙ ግብሩ እንደማይቀር ያወቀው ህዝብ ከሃዲነታቸውን የበለጠ አወቀው። ግብር ለአንድ ሀገር የገቢ ምንጭ መሆኑን እያወቁ ለአላማቸው ማሳኪያ እንዲሆን ግን የፖለቲካ መጠቀሚያቸው አድርገውታል።
በሌላ በኩል ህወሃቶች የሚያምኑት በመግደል እና በማግለል ነው። ስልጣን ላይ እያሉም ህዝቡን ጠርተው ስብሰባ ያደርጉና የፈለጋችሁትን ተናገሩ ይላሉ። አንድ ሰው ዳር ተቀምጦ ማሳሰቢያ የሚሰጠውን እና ይህን አስተካክሉ የሚለውን እየለየ ይጽፋል። በስብሰባዎች የሚናገሩ የትግራይ ልጆች በቀጣዮቹ ቀናት ተገድለው ነበር የሚገኙት።
ህወሃቶች ፀአዳ ማሽላ የሚሉት ቦታ አላቸው፤ ነጭ ማሽላ እንደማለት ነው ትርጉሙ። አበርጌሌ የተባለ ቦታ ላይ ነው ፀአዳ ማሽላ ያለው። ወደእዛ አካባቢ የሚልኳቸው በርካታ የትግራይ ወጣቶች በህይወት አልተመለሱም። በትግሉ ጊዜ እንኳም በፖለቲካ አመለካከታቸው የሚጠረጥሯቸውን እና ያልተመቻቸውን ታጋዮች ከደርግ ጋር ተገናኝተዋል፣ ከነራስ መነገሻ ስዩም ጋር ታሪካዊ ፍቅር አለላቸው በሚል ወደ እዛ አግዘው ገድለው ቀብረዋቸዋል።
በኢኮኖሚውም ቢሆን በህዝቡ ስም የኤፈርት ድርጅቶችን አቋቁመው ለግል ጥቅማቸው እና ለቤተሰባቸው ኑሮ ማደላደያ ሲዘረፉ እና ሲያከማቹ ኖረዋል። አርሶ አደሩ ግን የባሰ ድህነት ውስጥ ነው ያለፈው።
አርሶአደሩን ካለው ላይም እየቀነሱበት የስጦታ ቀን በማለት ካለው ከብቶች ላይ በግዴታ እንዲለግስ ሲያደርጉት ቆይተዋል። ካልሰጠ ደግሞ የሚደርስበትን በደል ያውቃልና ይሰጣል። ለእርሻው የሚሆን ማዳበሪያ ወስዶ እህሉ ባይበቅልለት እንኳን ካልከፈለ በሬውን ከመንገድ ወስዶ ስለሚያስቀርባቸው ለቀጣዩ እርሻ በሬውን እንዳያጣ ተበድሮም ቢሆን የእነሱን እዳ በቅድሚያ የሚከፍለው ።
የትግራይ እናትም ልጆቿን በደረቷ አቅፋ እና በጀርባዋ አዝላ ድንጋይ ስትሸከም እንዲሁም አፈር ስተቧጥጥ ትውላለች። እናቶች ከሰሩ በኋላ ምግብ ይሰፈርላቸዋልይህም ምግብ ለስራ አሊያም ሴፍቲኔት ብለው ሰይመውታል። የህወሓት አመራሮች ግን ግማሽ ኢትዮጵያን ሊያለማ የሚችለ ሃብት የያዙ ትላልቅ የኤፈርት ድርጅቶችን ሃብት እየተቀራመቱ ነው ኑሯቸውን ያደላደሉት።
አዲስ ዘመን:- ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የህወሓት አባላት በሰላም እንዲንቀሳቀሱ የቀረበላቸውን እድል እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– ሰይጣን በሰው ሆኖ ከመጣ በጣም ጸረ ሰላም ተዋጊ ነው። ህወሃቶችም የሰይጣን መሳሪያ ነው የሆኑት። ድሎታቸው እና ጥፋታቸው እያዩ እንዳያዩ ጆሯቸውም እንዳይሰማ ነው የተዘጋው። 27 ዓመት ኢትዮጵያን በጉያቸው ይዘው እንደፈለጉት ሲያዙበት እና በየክልሉ ልዩ ጽህፈት ቤት አቋቁመው ሲመሩ የነበሩበት ወቅት አስበው ለውጡን ሊቀበሉት አልቻሉም። ይህን ሁሉ አድርገው አልጠገቡም።
እድሉ ተመቻችቶላቸው በሰላም የሚኖሩበት ሁኔታ ነበር ይሁንና ህዝብ ለማስጨረስ በመፈለጋቸው እድሉን አልተጠቀሙበትም። በወቅቱ ለሰላም ሳይሆን ለጸብ ነበር ሲመኙ የከረሙት።
የህወሓት አባላት እኮ 27 ዓመት ሲመሩ ትግራይ እንኳን አያድሩም። ስብሰባ ቢኖርባቸው እንኳን ጨርሰው ወደአዲስ አበባ ነው የሚመጡት። በለውጡ ጊዜ ግን የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ ለማድረግ ወደመቀሌ ሄዱ። ጥፋታቸው እየበዛ በመምጣቱ ግን መጨረሻቸው አላማረም። እድሉን ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ እንሱም ህዝቡም በሰላም እንዲኖር በር ይከፍቱ ነበር።
አዲስ ዘመን:- የህወሓት አመራሮች መከላከያ ላይ የፈጸሙት ጥቃት እና በደል ሲመለከቱ ምን ተሰማዎት?
አቶ ግርማይ ሃደራ:– ህወሃቶች ወደስልጣን ሲመጡም እኮ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን አፍርሰዋል። በወቅቱ የደርግ ሰራዊት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰራዊት ነበር የነበረው። ይሁንና የእራሳቸውን አላማ ለማስፈጸም እንዲመቻቸው የራሳቸውን ታጋይ ነው ያስገቡበት።
አሁንም መልሰው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ትልቅ ነውረኝነት ነውና በጣም አሳዝኖኛል። መከላከያዎች እኮ የሚወዷቸው ልጆች እና ባለቤት አላቸው ይሁንና ለሀገር ህልውና እና ክብር ብሎ ነው በየዋሻውና በረሃው የሚያድሩት።
ይህ ብቻ አይደለም ለየአካባቢው ህብረተሰብ በእርሻ እና በችግር ጊዜ እየረዳ የሚኖር ነው። ይህን ሰራዊት ለመደምሰስ መነሳት ማለት ኢትዮጵያን ለመደምሰስ መነሳት ነው። ይህ ታዕምራዊ ክህደታቸው ግን በመንገድ ላይ ከሸፈ። ይህ ክህደት የትግራይን ህዝብ የማይወክል እና አሳፋሪ ጉዳይ ነው።
በዚህ ዓለም ይደረጋል ብለህ የማትገምተው ነውረኛ ድርጊት ነው ህወሃቶች የፈጸሙት። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በአንድነቱ አይደራደርም እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስልጣናቸው አሰናብቷቸዋል። ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ እንደሚባለው የማይነካውን በመንካታቸው ባዷቸውን እንዲቀሩ አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን:- አሁን ላይ በትግራይ ለተፈጠረው ሰብአዊ ችግር ተጠያቂው የሚሆነው አካል ማን ነው ይላሉ? መፍትሄውስ ምንድን ነው?
አቶ ግርማይ ሃደራ:- በአጭሩ ለዚህ ቀውስ ተጠያቂዎቹ የህወሓት መሪዎች ናቸው። በእያንዳንዱ የትግራይ አካባቢዎች የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ተጠያቂዎች ጦርነት ጎሳሚዎቹ የህወሓት ሰዎች ናቸው።
አንደኛ በሀገሪቷ ህግ አንገዛም በማለት መንግስት ሽረው መንግስት እኔ ነኝ ብለው ነበር። ያለህገ መንግስት ፍቃድ ምርጫ አካሂደዋል። መንግስት የሰየማቸውን ሃላፊዎች ከኤርፖርት ሲመልሱ ተስተውለዋል። የመንግስት ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሰዋል። መንግስት ደግሞ ከዚህ በኋላ ለዚህ ጁንታ እድል መስጠት አያስፈልግም በማለት እርምጃ ወስዷል። ህዝቡ እኮ የታጠቀውን መሳሪያ ለመከላከያ እያስረከበ ከህወሃቶች ጎን አለመሆኑን በማሳየቱ ጉዳቱም ቀንሷል።
ይሁንና በጦርነቱ ሳቢያ ውድመት ቢያጋጥም እና ሰብአዊ ቀውስ ቢከሰት ተጠያቂው ጦርነት ያስነሳው ህወሓት እራሱ ነው። ለመፍትሄውም በተባበረ ስሜት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መርዳት እና አንድነትን አስጠብቆ ለመቀጠል መተባበር ነው ። ሀገርን በመተጋገዝ እና በፍቅር ማስተዳደር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነት እንዲጠናከር በማድረግ ህወሓት የረጨውን ዘረኝነት እና ጸብ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ግርማይ ሃደራ:- እኔም ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013