ተገኝ ብሩ
ከእንቅልፍ እርቆ ያደረውን ዓይኔን እየጠራረኩ ከአልጋዬ ላይ ወረድኩ። መድረሻዬን ባላውቅም ከቤት ለመውጣት ቸኩያለሁ። ሣር ቅጠሉ በሚያጌጥበት መስኩ በሚደምቅበት በዚህ ቀን ችግር ድሩን ያደራበት የኔ ቤት ፈፅሞ ከአውዳመት ድባብነት ርቋል። ቤቱን ትቼ የምወጣውም ይህንኑ ፈርቼ ነው፤ ሽሽት የተያያዝኩት።
ባለቤቴ አውዳመት መሆኑ ጠፍቷታል መሰለኝ ገና ከእንቅልፍዋ አልነቃችም። ለነገሩ በዓል መሆኑን ብታውቅስ ምን ይፈይድላታል። እንደ ሌላው ዶሮ በሎሚ ዘፍዝፋ አታጥብ፤ የበጉን ስጋ ለጥብስ ለወጥ ብላ አትለይ ነገር አላደላት። በዚህ ሰዓት መንቃት ምን ያደርግላታል። ወግ ደርሷት በዓሉን ለማድመቅ ለመደገስ ጉድ ጉድ ማለት ላትችል ነገር። አዎ ይህን ጊዜ ለሽ ብላ ብታሳልፈው ነው ሚሻላት።
ማታ በስራም በጭቅጭቅም ደክሟት ነው የተኛችው። እንደምትወደኝ አውቃለሁ። ለዚያ ነው ምንም ሳይኖረኝ ተጠግታ የባሰ ምንም ሳሳጣት ያልራቀችኝ። ውድዋ፤ ሚስኪንዋ የልጆቼ እናት ማታ አስከፋኋት። ጠዋት ከቤት ስወጣ ለበዓል መዋያ ይሆን ዘንድ ከወርሀዊ ገቢዬ ቀንሼ እስዋ ጋር አስቀምጪው ያልኳት 1000 ብር ወትውቼ ተቀብያት መንገድ ላይ ስንቀዋለል ሌባ መንትፎኛል፤ አልነገርኳትም። ምን ብዬ ልነግራት እችላለሁ።
ለልጆቼ ከ1000 ብሩ ላይ ቀንሼ የሆነ እራፊ ጨርቅ ነገር ልገዛላቸው አስቤ ሰልባጅ ተራ ገበያ መሀል ገባሁ። ይሆናቸዋል ያልኩትን ሸሚዝ መርጬ ዋጋ ተከራክሬ ከተስማማሁ በኋላ ኪሴ ስገባ ጠዋት ያስገባሁት ብር የለም። በድንጋጤ ስሜት አላበኝ። ሊሸጥልኝ አጠገቤ የቀረበኝ ነጋዴ እጁን ዘርግቶ እየጠበቀኝ የማደርገው ሳጣ ልብሱን ጥዬለት ወደኋላ ፈንጠር ብዬ ከገበያው መውጣት ጀመርኩ። ከእጅ ወዳፍ በሆነው ገቢዬ ለብዙ ወራት ለባለቤቴ እየሰጠሁ የቆጠበችው ለዓውዳመት ይሆነናል ያልነውን ብር ጣልኩት፤ ሌቦች ወሰዱብኝ።
ማን ወስዶብኝ፤ ቅድም ወደ ገበያው መግቢያ በር ላይ የዓመት በአሉን ግርግር ሰበብ አድርገው ቀርበው የፈታተሹኝ ሳይሆኑ አይቀሩም። አዎ የዛኔ ነው የወሰዱት። የትኛው ጨካኝ ሌባ ኪሴን አራቁቶብኝ ይሆን? አዬ የልጆቼ ምን ይለው ምን ይቀጣው ይሆን? ከኔ ይሰረቃል? ከጎደለበት ይነጠቃል? ምን አይነቱ ጨካኝ ሌባ ነው። የባለቤቴ ጌታ በምን ይቀጣው ይሆን? ወደቤቴ ለመመለስ ተሳቀቅሁ። ሌቦቹን ደጋግሜ ረገምኳቸው።
እንደ ምንም አምሽቼ እቤት ስመለስ ባለቤቴ በር ላይ አግኝታኝ ሰላም ካለችኝ በኋላ አትኩራ ተመልክታኝ እንዲህ አለችኝ። “ውዴ ከምንበላው ላይ ትንሽ ቀንሰህም ቢሆን ለእነዚህ ልጆች ክናቴራ ነገር ይዘህ አትመጣም ነበር። እነሱ እኮ ገና ልጆች ናቸው፤ አዲስ ነገር እላያቸው ላይ ካላዩ አመት በዓል አይመስላቸውም። የጎረቤት ልጆች እያዩ እንዳያለቅሱብን እንደዚያ ብታደርግ ይሻል ነበር ጌትዬ።” ብላኝ ወደ ውስጥ ስትገባ ይበልጥ ግራ ተጋባሁ።
አዬ እናትዬ፤ የሆንኩትን ባወቅሽ፤ ገና በአውዳመት ምድር ፆምሽን ላውልሽ አይደል። አልኩ በልቤ። እቤት ስገባ ልጆቼን ሳያቸው ይበልጥ ፈራሁ። ደግነቱ እኔም እነሱን ሽሽት አርፍጄ መግባቴ ጠቅሞኛል መሰለኝ ደካክሟቸው ለመተኛት እየሞከሩ ነበር። የቀረበውን እራት ቀማምሼ ጎኔን ላሳርፍ ወደ አልጋዬ አመራሁ።
አልጋ ላይ በሀሳብ ቁልጭ ቁልጭ ስል ቆየሁ። ባለቤቴ ስራዋን አጠናቃ ልጆችዋን አባብላ አስተኝታ ጎኗን ለማሳረፍ እኔ ወዳለሁበት ተጠጋች። “ፍቅር ዋዜማ ነው፤ ከወዲሁ እንኳን አደረሰህ” አለችኝ። “እንኳን አብሮ አደረሰን” አልኳት።
አንድ ጥፋት አጥፍቻለሁ፤ ፊትዋን ደፍሬ በሙሉ ዓይን ማየት አቅቶኛል። ሌላ ምንም ሳትጠይቀኝ ወደ እንቅልፍዋ እንድትገባ ተመኘሁ፤ ፀሎት ማድረግ ምንም አልቀረኝም። ፀሎቴ አልተሳካም አንድ ነገር አለችኝ።
“ጠዋት በጊዜ ውጣና አንድ ሁለት ኪሎ ስጋ ይዘህ ና! ቢያንስ ልጆቼ በበዓል ምድር ከሰው ቤት ያለው ምግብ እንዳይሸታቸው ጠባብሼ አጎርሳቸዋለሁ።” ስትል የሆነውን ነገርኳት። ፍረሹ ላይ አሳርፋው የነበረው አካሏን ከፍረሹ አላቃ ትክ ብላ እየተመለከተችኝ “እየቀለድክ ነው አይደል ? ስትለኝ የሆነው ባልሆነና በቀለድኩ አልኩ ለራሴ። እውነታው ደግሜ ስነግራት ድርጊቴ አበሳጭቷት ከኔ ጋር ስትጨቃጨቅ አርፍዳ ነው የተኛችው። እና አሁን ብትነቃ ምን ታደርጋለች ብትተኛ ይሻላታል።
ፍራሽ ላይ እራፊ ጨርቅ ላያቸው ላይ ጣል ተደርጎባቸው ለሽ ብለው የተኙት ሁለቱ ልጆቼን እንዳልቀሰቅስ ተጠንቅቄ አልፌያቸው በሩን ከፍቼ ወጣሁ። የአካባቢው ድባብ ከወትሮ ተለየብኝ። ወደ ላይና ወደ ታች የሚተላለፍ ሰው፣ አዳዲስ ልብስ የለበሱ ዋንኛው መንገድ ላይ እየተሯሯጡ የሚጫወቱ ህፃናት፣ ወዳ አፍንጫ ሲማግ ልዩ የሆነ መዓዛ ያለው አካባቢውን የወረሰው የዓወዳመት ልዩና ደስ የሚል መአዛ ዓውዳመት መሆኑን በብዙ ይናገራል። ከሩቅ አንድ ድመፅ ጎልቶ ይሰማል። “አውዳመቱ ሲመጣ በየ አመቱ ድመቀታችን ስንኖር ባገሪኛ በወጋችን…”
እንደ ቤቴ አይደለም፤ ሁሉ ነገር ደመቅመቅ ብሏል። በዓውዳመት ሰማይ ምድሩ የሚደምቅለት ሳር ቅጠሉ የሚያሸበርቅለት አገር እንደ ኢትዮጵያ ይኖር ይሆን? እንጃ! ዓውዳመት እንደ አበሻ የሚደምቅለት መኖሩ። ቅዝቅዝ ካለው ቤቴ በጠዋት ያስወጣኝ እግሬን እየጎተትኩ የአውራ ጎዳናው የመጀመሪያ ጠርዝ ታጥፌ ቁልቁል ወረድኩ። እገሬ ወደፊት መሄዱን እንጂ መድረሻውን አያውቅም። ሲደክመኝ አንዱ ጥግ ላይ አረፍ አልኩኝ። ስለራሴ፣ ስለ ልጆቼና ሚስቴ እያሰብኩ በአውዳመት እንዲህ መሆናችን እያስታወስኩ ስቅስቅ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ። ሁሉ ነገር አስጠላኝ። አለምን አምርሬ ጠላኋት። ማልቀሱም ሲደክመኝ አቆምኩ።
የቀኑ ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ ጃኬቴን አወለኩ። ከፊት ለፌቴ ከጃኬቴ ኪስ ውስጥ አንድ ነገር ሲወድቅ ተሰማኝና ወደ መሬት ሳይ ደነገጥኩ። የሆነ የተጠቀለለ ብር ተመለከትኩ። በፍጥነት አፈፍ አደረኩት፤ 1000 ሺህ ብር ነው። ብሩ ትዝ አለኝ። ትላንት ከባለቤቴ ተቀብዬ ከቤቴ ስወጣ እንዳይጠፋብኝ በማሰብ የጀኬቴ የውስጠኛው ደረት ኪስ ላይ አድርጌው ነበር። እንደ አዲስ ሳቅ ፊቴ ወረረኝ፤ ደስታ ተሰማኝ። ቅድም በተስፋ መቁረጥ የራኩት ቤቴ ቶሎ ልደርስ ስፈልግ ራቀኝ። ወደ ባለቤቴና ልጆቼ ሮጥኩ።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013