ታምራት ተስፋዬ
ዩፎ UFO (Un-identified Flying Objects) የምንላቸው ከስማቸው እንደምንረዳው ያልተረጋገጡና የሰው ልጅ ተመራምሮ ምንነታቸውን በቅጡ ያልተረዳቸው ግኡዝ በራሪ አካላት ናቸው። ስለ እነዚህ ግኡዝ በራሪ አካላት ሲነሳም በሳይንሳዊ አጠራራቸው extraterrestrial life or ወይንም aliens የሚባሉት ፍጡራን አብረው ይነሳሉ። እስካሁን ባለው መላ ምት መሰረት ዩፎ የተሰኙት ያልታወቁ በራሪ አካላት የሚቆጣጠሩትና የሚያንቀሳቅሱት ልዩ ፍጡራን መሆናቸው ይገመታል።
መላምቱ እነዚህ ልዩ ፍጡራን /aliens/ ምናልባትም በአስተሳሰባቸው ከሰው ልጅ በእጅጉ የመጠቁና በስልጣኔ በመራቀቅ በእጅጉ እንደሚበልጡ ይጠቁማሉ። ፍጡራኑ ሰው ለመሰለል ወደ ምድር ይመላለሱበታል የሚባለው የጠፈር መጓጓዣ ስልታቸውም ለእውቀት ከፍታቸው ማሳያነት በቂ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።
የእውቀት ልካቸው በጣም ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚታመንላቸው እነዚህ በራሪ አካላቱም ለበርካታ አመታት የሰዎችን ትኩረት ሲስቡና ሲያወዛግቡ ቆይተዋል። አሉ ወይስ የሉም? የሚለው ጥያቄም በርካቶችን አወዛግቧል፣ አከራክሯል።
ስለመኖራቸው የሚያምኑት «ኃያላን መንግስታትና ተመራማሪዎች ምስጢሩን ደብቀው ነው እንጂ መኖራቸውማ እርግጥ ነው» ይላሉ። ካላየን አናምንም የሚሉትን ጨምሮ የተለያዩ የሳይንሱ አለም ተመራማሪዎች በአንጻሩ ከተራ ወሬ የዘለለ አይደለም ሲሉም ይሰማሉ።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት (ባእድ በራሪ አካላት) የሉም የሚለው ጥርጣሬ እየተሸረሸረ ምንድን ናቸው ወደሚለው ተለውጧል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይም የአሜሪካን ባህር ኃይል በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ቀርፆ ያስቀመጣቸውን ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮች በከፍተኛ ፍጥነት ሲበሩ የሚያሳዩ ምስሎችን ይፋ አድርጎ ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ሲሰበስብ የቆየውን ያልታወቁ በራሪ አካላት ወይም ዩፎዎችን የሚመለከቱ መረጃዎች ይፋ አድርጓል።ይፋ ከተደረጉት መረጃዎች መካከል ከ2ሺ700 በላይ ገፅ ያላቸው ከዩፎ ጋራ የተገናኙ ሰነዶች ይገኙበታል።
ታምራት ተስፋዬ
መረጃዎቹ ይፋ የሆኑት መሰል ሰነዶችን በሚሰበስበው ዘ ብላክ ቫውት የተሰኘው ጆን ግሪንዋልድ ጁኒየር ያቋቋመው ድረ-ገፅ አማካኝነት ነው። ግለሰቡም ለረጅም ጊዜያት ሲቀርቡለት በነበሩት ጥያቄዎች መሰረት ሲ.አይ.ኤ ዘ ዩፎ ኮሌክሽን የተሰኘ ሲዲ ላይ ቀድሞ በሚስጥር ተይዘው የነበሩ መረጃዎቹን አንድ ላይ በሲዲ አማካኝነት ሰብስቦ አስቀምጦ ነበር።
ጆን መረጃውን በሚመለከት በሰጠው አስተያየትም፣ ‹‹ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ችያለሁ፣ ከብዙ ድካም ተደጋጋሚ ጥረት በኋላ በመጨረሻ ተሳክቶልኛል፣መረጃውንም ማንኛውም ግለሰብ በነፃ ማግኘትና ለሌሎችም ተደራሽ ማድረግ ይቻላል›› ብሏል።
ይፋ ከሆኑት መረጃዎች መካከል በእኤአ 1976 እኩለ ሌሊት ላይ በአንድ የሩሲያ ከተማ ውስጥ የደረሰ ምስጢራዊ ፍንዳታንና በሌላ ጊዜ በአዘርባጃን መዲና ባኩ ሰማይ ላይ የታየ ልዩ በራሪ ነገርን የተመለከቱት ይገኙበታል።
በርካቶችም መረጃ በመልቀቁ ደስተኛ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።ይሁንና መረጃውን አሁንም ቢሆን ቁንፅል በመሆኑ ጉዳዩን ከህዝብና ደህነንት አንጻር በመቃኘት በልዩ ሳይንሳዊ ትኩረት መመልከትና ለህዝቧም አስፈላጊውን መረጃ መስጠት ግድ እንደሚላት አፅንኦኖት ሰጥተውታል።
በእርግጥም አንዳንድ መረጃዎችም ለማንበብም ሆነ ለመረዳት ከባድ ሆነው ተገኝተዋል። ለምን ጥቅም እንደሆነ ግን ግልፅ አልሆነም። ግሪን ዋልድም፣ ኤጀንሲው መረጃዎቹን አስቸጋሪና ጊዜውን በማይመጥን መልኩ መሰነዱንና ይህም በትክከል መረዳት መተንተን እንዳይቻል ማድረጉን ለ Vice’s Motherboard መፅሄት ገልጿል።
የጥናት ባለሙያዎች፣መረጃው በጥብቅ የሚፈልጉ ምሁራን ፣ መረጃዎች ግልፅና በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ቢሆኑ ይመርጣሉ፣ ይሁንና ኤጀንሲው መረጃው የተሰነደበት መንገድም እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሰዎች መረጃውን
በቀላሉ እንዳይመለከቱትና እንዳይጠቀሙበትና ለጥናትና ምርምር እንዳይነሱ የሚያቀርብ ነው ብሏል።
ሲ.አይ.ኤ በዩፎዎች ዙርያ አሉኝ የሚላቸውን መረጃዎች በሙሉ ይፋ አድርጌአለሁ ብሏል። ይሁንና ጆን ውድ የቀሩ ድብቅ መረጃዎች ስላለመኖራቸው ማረጋገጥ አይቻል ይሆናል፣ተጨማሪ መረጃዎች ካሉም ለማግኘት እጥራለሁ ሲል ድረ ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሁፉ ገልጿል።
አሁን ላይ ድረ-ገፁ ከ2 ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ ገፅ ያላቸው ዩፎን የሚመለከት ሰነድ መያዙ ይነገራል። እነዚህም ጆን የ15 ዓመት ታዳጊ ከነበረበት እኤአ ከ1996 አንስቶ ባቀረባቸው ከአስር ሺህ በላይ ጥያቄዎች አማካኝነት የተከማቹ መሆናቸው ታውቃል። መረጃውን ያገኘነው ከኢንድፕንደንት እና ከዘጋርዲያን ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013