አስመረት ብስራት
ዶክተር ተስፋዬ ሙላት በኢትዮዽያ ኪዩር የህፃናት ሆስፒታል የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ሀኪም ናቸው። በሆሰፒታሉ በከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ህፃናትን፤ በሰው ሰራሽ ማለትም በቃጠሎ ምክንያት የተጎዱ ልጆችን፤ በተፈጥሮ የተለያዩ የአካል መጎዳት የገጠማቸው ልጆችን በማስተካከል ስራ ላይ ይገኛሉ። ለዛሬ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላይ ተወያይተናል። መልካም ንባብ።
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ እንዴት ሊከሰት ይችላል?
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ በእርግዝና ጊዜ ጽንሱ ላይ በእናቱ ማህጸን ውስጥ እያለ የሚከሰት ትክክለኛ ቅርጽ ይዞ አለመፈጠር ነው። የከንፈር መሰንጠቅ የላይኛው ከንፈር ሳይገጣጠም ወይም ለሁለት ተከፍሎ የሚፈጠር ሲሆን የላንቃ መሰንጠቅ ደግሞ የላይኛው የአፍ ጣሪያ ለሁለት ሲሰነጠቅ ነው።
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ከላይ ወይም ከታችኛው የአፍ ክፍል አሊያም በሁለቱም ሊከሰት የሚችል የተፈጥሮ የአካል ጉዳት ነው። ይህ አይነት ችግር ያለባቸው ልጆች በንግግር እና በመመገብ ጊዜ ችግር ይገጥማቸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ላይ የመስማት፣ የጆሮ መቁሰል እና የጥርስም ችግር ሊገጥማቸው ይችላል።
የችግሩ መንስኤዎቹ ወይም አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?
በብዛት የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ይህ ነው የተባለ ትክክለኛ መንስኤዎቹ አይታወቁም። በብዛት እንደ አጋላጭ መንስኤ ተደርገው የሚጠቀሱት ከዘር ወይም በቤተሰብ ተመሳሳይ ችግር ካለ እና ከአካባቢው ተጽእኖ እንደሆነ ይጠቀሳል። እናት በእርግዝና ጊዜ የምትወስደው መድኃኒት ከነበረ በተለይም የሚጥል በሽታ ያላቸው ሴቶች የሚወስዱት አይነት ለረጅም ገዜ የሚወሰድ መድሀኒት ካለ ችግሩ ሊከሰት ይችላል።
ሕጻኑ በማኅጸን ውስጥ በነበረበት ጊዜ በእናትየው አማካኝነት ለቫይረስ ወይም ለአደገኛ ኬሚካል የተጋለጠ ከነበረ ለከንፈርና ለላንቃ መሰንጠቅ መጋለጥ ምክንያት ይሆናል። በእርግዝና ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓት አለመጠበቅ፣ ማጨስ፣ መጠጥ አብዝቶ መጠጣት እና የስኳር በሽታ ያለባቸው ሴቶች የሚወልዱአቸው ልጆች ለዚህ ጉዳት የመጋለጥ እድላቸው በጣም የሰፋ ነው። እናቲቱ የምግብ እጥረት ካጋጠማት በተለየም የፎሊክ አሲድ እጥረት ያጋጠማት ከሆነ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
እንደዚህ አይነት ልጆች ሊያጋጥማቸው የሚችለው ችግር ልጆቹ በመጀመሪያ የሚገጥማቸው የምግብ አወሳሰድ ችግር ስላለባቸው ማለትም መጥባት ስለሚቸገሩ የመጥባት ችግር፣ ጡት ሲጠባ ወደ አፍንጫ የመግባት ትንታ፣ በቂ እድገት በወቅቱ አለማሳየትና የክብደት መቀነስ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። ትን ስለሚላቸው የሳንባ ኢንፌክሽን ይገጥማቸዋል። የላንቃና የጆሮ ቱቦ በመቀራረቡ የተነሳ ተደጋጋሚ የጆሮ ቁስለትና መናገር አለመቻል የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው።
ልጆቹ በጊዜ ህክምና አለማግኘታቸውና በወቅቱ አለመሰራቱ የስነልቦና ጫና እንዲኖርባቸው ያደርጋል። ንግግራቸው የሚነፋነፍ ማለትም በአፍንጫ የሚወራ አይነት ድምፅ ሲያወጡ የንግግር ስርአት የሚያስተካክሉ ባለሙያዎች በሚሰጡ ስልጠና ሊስተካከልላቸው ይችላል። ቀዶ ህክምናው ከተደረገላቸውም በኋላ ከንፈርን በትክክል መግጠም አለመቻል የአፍንጫ ቅርጽ መለወጥ ሊገጥማቸው ይችላል።
ህክምናው ምን ይመስላል?
እነዚህ ህፃናት ሲወለዱ በሀገራችን ብዙ ህክምና ባይኖርም ይህንን ስራዬ ብለው የሚሰሩ የተቀናጀ ህክምና ወደ ሚሰጥበት እንደ ኪዩር የህፃናት ሆስፒታል ያለ ቦታ መምጣት ይኖርባቸዋል።
ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ይህን ችግር መፍትሄ ለመስጠት የተዘጋጁ ነርሶች ይኖራሉ ያንን ተመልክተው እንዴት ምግብ እንደሚወስዱ፣ ጡጧቸው ምን አይነት መሆን እንዳለበት የምከር አገልግሎት ይሰጣቸዋል። በዘህ መልኩ ክብደታቸው የተስተካከለ ሲሆን የከንፈር ኦፕሬሽን የሚደረግለት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሲሆን የላንቃው ደግሞ ከ9 ወር እስከ 2 አመት ህፃኑ መነጋገር ሳይጀምር ስለሚሆን ህፃኑ ኦፕሬሽን እንዲደረግለት ቅድመ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ ይሰራል ማለት ነው።
ህክምናው በጊዜ እንዳይሰጥ ዋናው ችግር የሚሆነው ልጆቹ ምግብ በትክክል ስለማይወስዱ ክብደታቸው የቀነሰ ይሆናል። በሆስፒታሉ ግን የምግብ አወሳሰድ ችግር ላለባቸው ልጆች በስነ ምግብ ባለሙያ እየተረዱ አመጋገባቸው እንዲስተካከል የሚያደርጉበት ሁኔታ ይኖራል። ከዚህም በተጨማሪ የጥርስ አበቃቀል ችግር ላለባቸው የጥርስ ሀኪሞች የሚከታተሏቸው ሲሆን የንግግር ችግር ለገጠማቸው ደግሞ የንግግር ባለሙያዎች እርዳታ ያደርጉላቸዋል።
ወላጆች ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄ ምን መምሰል ይኖርበታል?
መጀመሪያ ሁልጊዜ ወላጆች እንደዚህ አይነት ልጅ ሲያጋጥማቸው ይደነግጣሉ፤ ነገር ግን በመረጋጋት እንደዚህ አይነት አገልግሎት የሚሰጥባቸው የህክምና ተቋማት በመሄድ እርዳታ እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህ ሲባል በተለይ የላንቃ ክፍተት ያላቸው ልጆች የአመጋገብ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ሁለተኛ የሚወስዱት ምግብ ወደ ሳንባ ይሄዳል፤ ትንታም ይኖራቸዋል፤ ምግቡ ወደ ሳንባ በመግባቱ ብዙ ህፃናትን ለሞት የሚያደርስ የሳንባ ምች ላይ ይጥላቸዋል። ይህን ለመከላከል ወላጆች ህፃናቱን ሲያጠቡ ቀና አድርገው ጡጦው እየተጨመቀ እንደማንኛውም ልጅ ባይሆንም ረዘም ላለ ጊዜ ከመገቡ በኋላ ማስገሳት የግድ በመሆኑ ወላጆች ይሄን ተረድተው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሌላው ልጆቻቸውን መደበቅ ምግብ በተገቢው አለመስጠት አይነት ሀሳቦችን ትተው በህክምና ተቋማት በመረዳት ህፃናቱ በደንብ ጠብተው አድገው በጊዜ ወደ ህክምና እንዲገቡ በማድረግ በህክምና ባለሙያዎች መረዳት ይኖርባቸዋል።
ከቀዶ ህክምና በኋላስ ልጆቹ ሊገጥማቸው የሚችል ችግር ምንድነው?
ልጆቹ ከቀዶ ህክምና በኋላ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አነዚህም የአፍንጫና የአፍ መዛባት ሊሆን ይችላል። ይህም በአራት አመታቸው ላይ የማስተካከያ ህክምና ይደረግላቸዋል።
ልጆቹ አስራ ስምንት አመት እስከሚሞላቸው ድረስ የተወላገደ ጥርስ ካላቸው የጥርስና የድድ ህክምና ይደረግላቸዋል። የመናገር ችግር ያላቸው ልጆች እስፒች ሰርጀሪ ተደርጎ ንግግራቸው እንዲመለስላቸው ይደረጋል። ቀጣይና ተከታታይነት ያለው ህክምና ይደረግላቸዋል። ልጆቹ ህይወታቸው ተስተካክሎ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ የጋራ ሀላፊነት ነው።
ማህበረሰቡ መገንዘብ የሚገባውማህበረሰቡ ማወቅ የሚገባው እሰታንዳርዱን የጠበቀ ህክምና ስለሚሰጥ ቤተሰብ ልጆቹን ወደ ህክምና ማምጣት ይኖርባቸዋል። ስራውም እስከ አስራ ስምንት አመት እድሜያቸው ድረስ የሚቀጥል ስለሆነ አንዴ ተሰርቶ አለማለቁን ተረድተው ልጆቹን ለተከታታይ ህክምና ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ህክምናው በኮቪድ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ መምጣቱ በርካታ የጤና ተቋማት ላይ ተጨማሪ ስራ ፈጥሯል። በተመሳሳይ ጫናውም ይህን ሆስፒታልም አጋጥሞታል፤ ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ በየወሩ ህክምና የሚሰጡት ሰራተኞች ይመረመራሉ፤ ታካሚዎችም ወደ ሆስፒታሉ በሚገቡበትም ወቅት በምርመራ ወደ ውስጥ ይገባሉ።
በቀዶ ህክምና ወቅት ፊልተር የሚያደርግ መሳሪያ በአንስቲዥያ ማሽን ውስጥ ይቀመጣል። ልጆቹ ለዚህ ህክምና መጥተው እንዳይያዙ ሁሉም የህክምና ባለሙያ ማስክ ያደርጋል። ከሚደረገው ጥንቃቄ በዘለለ ባሳለፍነው አመት 115 የሚደርሱ ህፃናት ህክምናውን አግኝቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013