በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
በታክሲ ላይ ተሳፍሮ በሃሳቡ የሄደ አንድ ሰው በምናባችን እንሳል። በሃሳብ ጭልጥ ያለው ሰው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ነው። የሞከረው ሁሉ አልሳካ ብሎት እጁ ያለው ተበትኖ በድካምና በዝለት ውስጥ ሆኖ በሃሳብ ፈረስ ተሳፍሯል።
ይህ ሰው በታክሲው አሻግሮ እየሄደ ካለበት የሩቅ ጉዞ የመለሰው መንገድ ላይ “በርታ” የሚል ቲሸርት የለበሰ ሰው ጽሁፍ ነው። ግለሰቡ ቲሸርቱን ለብሶ በእግሩ እየተጓዘ ሲሆን ከሃሳብ ፈረስ ላይ የተቆናጠጠው በታክሲ እየተጓዘ ያለው ሰው ከሰመመኑ ነቃ።
ከሃሳብ ሰመመን። በመቆዘምና ተስፋ መቁረጥ ከተቃኘው ሰመመን። ግለሰቡ “በርታ” በሚለው መልዕክት ውስጥ ከገባበት የተስፋ መቁረጥ የሚያወጣ አቅም ያገኘ እንደሆነ ተሰምቶታል።
እኒህ ሦስት ቀናት ያለፈባቸውን ሰላሳ አመታት ሸክም የተሸከሙ ያህልም ተሰማው። ለራሱም እጅ ከመስጠት መበርታት አስፈላጊ እንደሆነ ተናገረ። ለነፍሱም፤ ነፍሴ ሆይ በርቺ ሲል መከራት።
ባለንባት ምድር ውስጥ የተስፋ መቁረጥ ምክንያት መሆን የሚችሉ አያሌ ምክንያቶች አሉ። ከምክንያቶቹ በላይ መሄድ የቻሉ ሰዎች ታሪክ የመስራት እድላቸው ሰፊ ነው።
ታሪክ ሰሪነት የግድ ወደ ታዋቂነት የሚያመጣ ታሪክ መሆን የለበትም። ታሪክ ሰሪነት እንደ ሁኔታው ልንተረጉመው እንችላለን።
ያለ አባት ብቻዋን ጉሊት እየነገደች ልጆችን ማስተማር የቻለች እናት ታሪክ ሰሪ ነች። ያለ እናትና አባት የህይወትን ፈተና ተቋቁማ በጽናት ለፍሬ የበቃች ሴት እህታችን ታሪክ ሰሪ ነች።
ጾታዊ ትንኮሳና መደፈር ገጥሟት ተስፋ ከመቁረጥ ወጥታ ወደ ውጤታ የደረሰችው እንዲሁ ታላቅ ባለታሪክ ወይንም ታሪክ ሰሪ ነች። አካል ጉዳተኝነት ሳይበግረው ያሰበበት ላይ ለመድረስ የጣረና ያንንም ማሳካት የቻለው ሰው እንዲሁ ታሪክ ሰሪ ነው።
ታሪክ ሰሪነት በጦር ሜዳ ውሎ በመግደል ውስጥ ብቻ እንዲሆን ያደረገው ማንነው። የሕይወት ጉዞ ፈተናን ገጥሞ አሸንፎ መውጣት መቻል እርሱ ታሪክ ሰሪነት ነው። በዙሪያችን እንዲህ አይነት ታሪክ ሰሪዎችን ብንፈልግ በብዛት እናገኛለን።
ታሪካቸው ሳይሰማ ታሪክ ሰርተው ያለፉ እልፍ ሰዎች አሉ። አንተም የታሪክ ሰሪነት ገጾች ላይ ትገኛለህ። አንቺም እህቴ ዛሬ ያለሽበት የትኛውም ሁኔታ ለታሪክ ሰሪነት እድል ሆኖ በእጅሽ አለ። የትኛውም ሁኔታ ማለት የማይመቸውንም እንደሚጨምር ልብ ሊባል ይገባዋል።
በዙሪያችን የበዙት እኒህ ታሪክ ሰሪዎች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸውን ነጥቦች ለማውጣት ብንሞክር በእርግጠኝነት ሁሉም ነገን የሚመለከቱ መሆናቸው አንድ ያደርጋቸዋል።
ነገን መመልከት በመቻል ውስጥ ዛሬ ላይ ይተጋሉ። እናቶች በልጆቻቸው ውስጥ ነገን በማየት ስለ ልጆቻቸው ዋጋን ለመክፈል ይወጣሉ ይወርዳሉ። ለሥራ እድሜ የደረሰ ወጣት ተጧሪ ቤተሰቦቹ ውስጥ እናትነትና አባትነትን እያየ ነገን በእነርሱ ውስጥ ያያል።
ታላቅ ልጅ በታናሽ ወንድሞችና እህቶች ውስጥ ነገን በማየት የዛሬው ትጋት ምክንያት ይሆናል።
እግዚአብሔርን በማየት ውስጥ ደግሞ ከሰው ጋር አብሮ በመኖር ውስጥ ተስፋ ስራውን ይፈጽማል። ነገን መመልከት መቻል በሁሉም ሰው ውስጥ ያለ ቢሆንም፤ የምንመለከትበት አመለካከት ግን የዛሬን እርምጃችንን ይወስነዋል። የዛሬ ጽሁፍም በነገ ውስጥ የምናየው እኛን የሚያየን እንዲሆን ስለሚያደርገው ራዕይ እንመለከታለን።
ነገን መመልከት
ነገን መመልከት ማለት ራእይ ያለው ሰው መሆን ማለት ነው። ራእይ ያለው ሰው ማለት ደግሞ ነገን እየተመለከተ ዛሬ ላይ ወደ ነገ በሚያደርሰው መንገድ ላይ የሚራመድ ማለት ነው።
እያንዳንዱን ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ እግሩ ወደመራው የሚሄድ ቢሆን ምድር ምን ልትመስል እንደምትችል ማሰብ ተገቢ ነው።
እውነታው ግን ከእዚህ ተቃራኒ ብዙ ሰው ነገን እያየ የሚራመድበት ነገር አለው። ነገን የሚያይበት አተያይ ጥራት ያለው ይሁንም አይሁንም፤ ጠንካራ ይሁንም ደካማ ነገን ያያል።
በተወሰነ ደረጃ ነገን ለማየት መሞከርና ነገን እያዩ መራመድ ተፈጥሯዊም ይመስላል። ነገን እያየ የማይራመድ ግለሰብ ቢኖር በምን እንመስለዋለን? ጆን ማእክስዌል የተባሉ ሰው እንዲህ አይነቱን ሰው በክብ/circle ውስጥ የሚጓዝ ተጓዥ ብለው ይመስሉታል። እዚያው የሚሽከረከር።
ባለበት እየረገጠ ነገርግን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚቆጠር። የሚጨመሩት ቀናት ትርጉም የሌላቸው የሆኑበት ሰው።
ነገን መመልከት መቻል እዚያው ከመርገጥ ህይወት የሚያወጣ፤ ታሪክ ሰሪነትን የጉዞችን አካል የሚያደርግ ነው። ታሪክ ለመስራት ተነሳ፤ እርሱም ነገን በመመልከት ውስጥ ታገኘዋለህ። ነገን መመልከት ነገን ወደ መተለምም ያመጣሃል።
ነገን መተለም ልቦናችን ውስጥ ድምጽ አለ። ውስጣችንን ለማዳመጥ በሞከርን ቁጥር በለሆሳስ የሚሰማን ነገን የሚያሳየን ድምጽ አለ። በግርግር ውስጥ ይህን ድምጽ ማዳመጥ አንችል ይሆናል።
በጥሞና ውስጥ በእርጋታና በማረፍ ውስጥ ከውስጣችን የሚሰማ ድምጽ አለ። ልጆቿን አሳድጋ ለወግ ለማእረግ ማብቃትን አሻግራ የምታይ እናት፤ መጻፍና ማንበብ ባትችልም ነገ ላይ የምታደርገውን ትተልማለች። ለልጆቿ መልካም እንዲሆን ያሰበችውን ሁሉ ለማሳካት ትተልማለች። ትልሟም እንዲሰምር ትተጋለች።
ነገን መተለም ውስጥን በማዳመጥ የተመለከትነው ነገ ላይ ለመድረስ የሚያደርገንን መንገድን መቀየስ ተግባራትንም ማከናወን ማለት ነው። ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው እንደሚባለው እንዲሁ ተቀምጦ የሃሳብ መዓት ከማግተልተል በተግባር ሜዳ ውስጥ ገብቶ በመጫወት ፍሬን ማፍራት ይገባል።
ፍሬውም እውን እንዲሆን ያየነው ነገ ላይ ለመድረስ ዛሬ መራመድ ያለብን መንገድን መለየት ያስፈልጋል።
በጦር ሳይንሱና በንግዱ አለም ይህ ሃሳብ ስልት (strategy) ተብሎ ይቀመጣል። ስለ አንድ ነገር መማርና ማወቅ አሻግረህ ነገ ላይ ያየኸው ነገር ቢሆን እርሱን ለማሳካት የምትሄድበት መንገድ ግን አማራጩ ብዙ ሊሆን ይችላል። ትልምህን በማስቀመጥ በትልምህ መሰረት መጓዝና ወደ ውጤት መድረስ እንዲቻል ውስጥን ማዳመጥ ተገቢ ነው።
በእጅ ያለውን ሃብት በአግባቡ መተንተን እና ትርጉም ሰጥቶ ያሰቡት ጋር ለመድረስ መተለም ይጠይቃል። በንግዱ አለም የጥንካሬና ድክመት ዳሰሰ በማድረግ ውስጥ ስልት እንደሚነደፈው ማለት ነው።
ውስጥን በማዳመጥ ውስጥ የራስን የነፍስ መሻት፣ ጥንካሬና ድክመትን በጸጥታ ሆኖ በማሰብ ትልምን መቅረጽ ተገቢ ነው። እናቶች ያደርጉታል ያልተማሩ ቢሆኑም። ታዳጊዎች ያደርጉታል እድሜያቸው ለሃላፊነት እድሜ የበቃ ባይሆንም።
የትልሙ ውስንነት ባለን እውቀትና መረጃ የሚወሰን ቢሆንም መተለም መቻል እያለፍንበት ያለ ሊሆን ይችላል። የትልሙን ውስንነት ለመቀነስ በዙሪያችን ያሉትን ልዩ ልዩ ድምጾች ለማድመጥ መፍቀድ ተገቢ ይሆናል።
ድምጾችን ማድመጥራእይን መሰነቅ የሚያስችሉን ድምጾችን ለይቶ መስማት አስፈላጊ ነው። ልቦናችን ውስጥ ድምጽ አለ። ውስጣችንን ለማዳመጥ በሞከርን ቁጥር በለሆሳስ የሚሰማን ድምጽ አለ። ከእዚያ ያለፈም ድምጽ በዙሪያችን አሉ።
እውቁ ተናጋሪና ጻሃፊ ጆን ማእክስዌል ራእይ የሚመጣው ከየት ነው? የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ ነገን አሻግሮ ለማየትና ለመተለም የሚረዱ ድምጾችን ይተነትናሉ። ጥሩ አድማጭነት ጥራት ላለው ራእይ እና ራእይውን ለማሳካት ለምንተልመው ትልም ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ይዘረዝራሉ። እኒህን ድምጾች ሲዘረዝሯቸው፤
1. የውስጥን ድምጽ ማድመጥ/The Inner Voice
አሻግሮ ማየት የውስጥ እይታ ነው። አስቀድሞ ለማለት እንደተሞከረው ራእይ ከውስጥ የሚጀምር ነው። እንደ ግለሰብ የህይወትህን ተልእኮ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ልብህ የሚያንቀሳቅሰውን ጉዳይ መረዳትም።
ህልምህን አጥርተህ ማየት። ይህ ሁሉ ከውስጥ ጋር የሚገናኝ ነው። የምታልመው ነገር ከውስጣዊ እምነትህ ወይንም ከውስጥህ ሊወጣ የሚገባ ነው፤ ካልሆነ ግን ልትፈጽመው ይቸግርሃል። በውስጣዊ ድምጽህ ውስጥ ያለው ይህ ነው።
ከድምጾች ሁሉ ጎልቶ ለመሰማት ቅርብ የሆነ፤ በጥሞና ውስጥ ጎልቶ የሚሰማ የውስጥ ድምጽ።
2. ያለመደሰት ድምጽን ማድመጥ/The Unhappy Voice
ለትልልቅ ሃሳቦች ያለ መነሳሳት የሚመጣው ከየት ነው? በአግባቡ ሊሰራ ያልቻለ ነገርን ከመረዳት ይመጣል። ባለህበት ነባራዊ ሁኔታ እረክቶ አለመቀመጥ ለራእይ መቀጣጠል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።
ለውጥን የሚከላከል ታላቅ መሪ በምድራችን ላይ የለም። ታላቅ መሪ የለውጥ መሪ ነው ደስታ የራቀውን ድምጽ ሰምቶ የሚቀይር። ነገን አሻግሮ መመልከት በዛሬው ነገር ተረጋግቶ ካለመቀመጥ የሚነሳ በመሆኑ ዛሬ ላይ በዙሪያህ ያለው ያለመደሰት ድምጽ ትልምን መተለሚያ የመሆን እድሉን ማየት አስፈላጊ ነው።
3. የስኬታማነት ድምጽን ማድመጥ/The successful voice
ማንም ሰው ታላቅ ነገርን ብቻውን ማሳካት አይችልም። ትልቅ ራእይን ለማሳካት ጥሩ ቡድን ያስፈልግሃል። በተጨማሪም በአመራርነት መንገድ ውስጥ ያለፈ ሰውም ምክር ያስፈልግሃል።
ሌሎችን ወደ ታላቅነት ለመምራት ግለ-መካሪ/Mentor ሊኖርህም ያስፈልጋል። ራእይህን ቅርጽ ለመስጠት የሚረዳ አማካሪ አለህ? ይህ ጥያቄ የስኬታማ ድምጽ ነገን ለመተለም የሚሰማ ወሳኝ ድምጽ መሆኑን ያሳይሃል።
4. ከፍተኛውን ድምጽ ማድመጥ/The Higher Voice
ዙሪያችንን በምናዳምጥበት ጊዜ የሚገባን አንድ ነገር አለ፤ እርሱም በውስንነት የምንቀሳቀስ መሆናችንን። ምንም እንኳን ራእይህ ከውስጥህ የሚወጣ ቢሆንም በአንተ ውስንነት ምክንያት እንዲጨማደድ ማድረግ ግን የለብህም። በዛሬ ውስንነት አሻግረን ያየነውን ነገን ማጨማደድ ተገቢነት የለውም።
እይታችንን ማስተካከል እንጂ፤ እይታን አጨማዶ ትልም አልባ የሆኑ ቀናትን መግፋት ተገቢ አይደለም። እውነተኛ ዋጋ ያለው ራእይ ፈጣሪ ውስጡ ሊኖር ይገባዋል። እርሱ ብቻ ሙሉ አቅምህን ያውቃልና። ከራስህ በላይ፣ ከአንተ እድሜ በላይ የሆነን ራእይ ውስጥህ ሲያልም ያገኘዋለህ? እንግዲያውስ እርሱ ከፍተኛው ድምጽ ነውና በሁኔታህ ሳትወሰን ይህን ድምጽ አስተናግደው፤ ትልምህን ለመተለምም ተጠቀምበት።
የተግባር እርምጃውበመግቢያችን ላይ በምናባችን የያዝነው ግለሰብ ከታክሲው ወርዶ ወደ ፊት ሲራመድ በመበርታት እንዲሆን በርታ የሚል መልእክት አስፈልጎት ነበር። በዙሪያችን ባሉ ነገሮች ውስጥ አይናችንን ከፍተን ብንመለከት መበረታታትን የሚሰብኩ ድምጾችን እናገኝ ይሆናል።
በተጨባጭ በእኛ ባህል ውስጥ መበረታታት በጠንካራነት የሚነሱ ባይሆንም ማህበራዊ ትስስራችን ውስጥ ያለው መበረታታት ትርጉም ላቅ ያለ ነው። የተግባር እርምጃችን ራሳችንን በማበረታታት መጀመሩ የግድ ነው።
በፍጹም ከተስፋ መቁረጥ ክልል ውስጥ ወጥተን ማሰብ ተገቢ ነው። ተስፋ መቁረጥን በተስፋ መሰነቅ በመተካት የተግባር እርምጃን መራመድ ይገባናል።
ይህም ታሪክ ሰሪ የሚያደርግ የባለራእይነት ጉዞ ነው። እርምጃችንንም ነገን በመመልከት ነገን መተለም በመቻል የራእይ ጉዞ መሆን እንዲችል የሚከተሉትን የተግባር እርምጃዎች መኖር ጆን ማእክስዌል ይመክራሉ።
• ራስህን መዝን – ራእይህን አስቀድመህ አውቀህ ከሆነ እንዴት እንደያዝከው መዝን። ከተለያዩ ቁልፍ የህይወትህ አካላት ማለትም ከትዳር አጋርህ፣ ቅርብ ጓደኞችህ፣ ቁልፍ ሰራተኞችህ ጋር ራእይህ ምን እንደሆነ ጠይቃቸው። እነርሱም በሚገባ ማስቀመጥ ከቻሉ እየኖርከው ነው ማለት ነው።
• ጻፈው – ስለ ራእይህ አውቀህ ነገርግን በጽሁፍ ያላስቀምጥከው ከሆነ ዛሬውን አድርገው። መጻፍ አስተሳሰብህን ግልጽ ያደርገዋል።
ከጻፍከው በኋላ የህይወትህ ራእይ ልታደርገው የሚገባ መሆን አለመሆኑን መዝን። ከተቀበልከው ራእይህን ለመፈጸም ተራመድ።
• መነሳሳትህን መዝን – በራእይ ዙሪያ አስፈላጊ ተግባራትን የምታከናወን ሰው ከሆንክ በቀጣይ ሳምንታትና ወራት ስለእዚህ በማሰብ አሳልፍ። የመነሳሳት ደረጃህ በምን ተጽእኖ እንደሚደረግ ግምት ውስጥም አስገባ፣
ምን ያስለቅስሃል?
ምን ህልም እንድታልም ያደርግሃል?
ምን ሃይልን ይሰጥሃል?
በአጠግብህ ያለው አለም ውስጥ ምን ተቀይሮ ማየት እንደምትፈልግም አስብ። ምንስ መቀየር ያለበት ነገር አለ? ሃሳብህን ለራስህ ግልጽ ካደረከው በኋላ ጻፈው ደግሞም ከግለ-መካሪህ ጋር ተወያይበት።
የምታየው ሲያይህ
ነገን በማየት ውስጥ የሚደረግ ጉዞ ስታየው የነበርከው ነገር ወደ መሆን መጥቶ በተራው አንተን ወደ ማየት ይቀየራል።
እናት በልጆቿ ውስጥ ነገን እያየች ስትራመድ ያሰበችው ጋር ስትደርስ ልጆቿ ደግሞ እርሷን ሲያይዎት ታገኛለች። ዛሬ አሻግረህ የምታየው ነገር፤ ዛሬ አሻግረህ ላየኸው ነገር የተለምከው ትልም ተሳክቶ ከፊትህ ሲሆን እርሱ በተራው አንተን ማየት ይፈልጋል። አንተን ማየቱ በብዙ መንገድ ሊተረጎም ይችላል።
ነገርግን መዘንጋት የሌለብን ነገር ዛሬ አሻግረን የምናየው ነገር ነገ እኛን ዞሮ የሚመለከት ከሆነ እርሱ ራእይ መሆኑን ነው።
ለፖለቲካ ስልጣንና ለህዝብ ለውጥ ራእይ አድርጎ የታገለ ትግሉ ሰምሮ ህዝብን ለማገልገል የሚችልበት ስፍራ ሲደርስ ህዝቡ እርሱን ያያል።
በውስጡ ያለውን ተሰጥዖ ተጠቅሞ ኩባንያ መስርቶ አገልግሎት ሊሰጥ የተመለከተ ሰው በተጨባጭ ያየው ጋር ሲደርስ ያየው መልሶ እርሱን ያየዋል። ይህ የራዕይ ባህሪ ነው። ነገ ላይ አሻግረህ የምታየው ስለ እዚያም ዛሬ ትልም ያለህ ጉዳይ እርሱ ምንድን ነው? የምታየውስ እንዴት እንደሚያየህ ትወዳለህ? በመቃብርህ እለት ሰዎች እንዲያወሩት የምትፈልገው ነገር እርሱ ራእይህ ነው? ዛሬ አንተ አሻግረህ የምታየው፤ በሆነ ጊዜ ግን እርሱ መልሶ የሚያይህ።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013