ሀገር በደስታ ጊዜ ማሸብረቂያ በኀዘን ጊዜ መደበቂያ ሰገነት ነች፡፡ ደስታም ሆነ ኀዘን የሚያምረው በሀገር ነው። ለዚህም ነው የሀገርን ክብርና ልዕልና የተረዱ ጀግኖች አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከውስጥ ቦርቧሪ ከውጭ ወራሪ ለመጠበቅ በዱር ገደሉ የተዋደቁት፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያን ታላቅነት የተረዱ፤ በትውልድ ቅብሎሽ የተከፈለውን መስዋዕትነት ያወቁና ለነጻነትና ሉዓላዊነት ቀናኢ የሆኑ ዜጎች ለሀገራቸው ክብር ወድቀው ተነስተዋል፡፡
ደማቸውን አፍሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ነች፡፡ ዛሬም የሚሞቱላት ፤ የሚቆስሉላትና የሚሰዉላት ሚሊዮኖች እንዳሉ እያየን ነው፡ ፡ የጁንታው ቡድን የኢትጵያውያን ሀገራዊ ስሜት ተዳክሟል፤ በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለዋል በሚል የተሳሳተ ስሜት የሀገር መከላከያን ሰራዊት ከኋላ በወጋበት ወቅት የታየው የጋለ ሀገራዊ ስሜትና አንድነት ብዙ ሴራ የተሸረበበት ኢትዮጵያዊነት ዛሬም በከፍታ ማማ ላይ እንዲሚገኝ ያሳየ ነው፡፡
የሀገሩ መደፈር፤ የመከላከያ ሰራዊት መወጋት ያስቆጨው ህዝብ ደሙን በመስጠት፤ ገንዘቡን በመለገስ፤ ለዳር ድንበሩ ለመዋደቅ ቁረጥኝነቱን በማሳየት ለህግ አስከባሪው አካል ጠንካራ ደጀንም መሆኑን አሳይቷል፡፡ ዛሬም እያሳየ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ግን ሁል ጊዜ ትችትና ነቀፋን የሚያስቀድሙ፤ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በመንግስትና በጸጥታ አካላት ብቻ እንደሚጠበቅ የሚያምኑ፤ ዳር ቆመው የሩቅ ተመልካችና ፈራጅ የሆኑ፤ ሀገር ስትታመም የማይታመሙ፤ የወገኖቻቸው መፈናቀል፤ ጉዳት ሞት የማይሰማቸውን ሰዎችን እየተመለከትን ነው፡፡ ይባስ ብሎም በሰዎች ጉዳት፤ መፈናቀልና ሞት ለሚነግዱ የፖለቲካ ቡድኖች መነገጃ በመሆን የሀገሪቱን ሸክም ሲያከብዱ የታዩ ብዙዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በአዲስ ተስፋ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የሀገራዊ ስሜት መዳበር፤ የፖለቲካ ምህዳር መስፋትና የአሳዳጅና ተሳዳጅ ትርክ ተቀይሮ ሁሉም ለሀገሩ እኩል አስፈላጊ መሆኑ የታመነበት ነባራዊ ሁኔታ መፈጠር፤ በሀገር በቀል
የኢኮኖሚ አቅጣጫ ዜጎች በሀገራቸው ሀብት የሚጠቀሙበትና ሰርተው የሚለወጡበት መሰረት መጣሉ፤ በሉዓላዊነቱ የማይደራደር መንግስት የለውጡ ዋነኛ ሞተር መሆኑ የሀገሪቱ ተስፋ ብሩህ መሆኑን አመላካቾች ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ሲሸረብባት በቆየው ሴራ፤ አይን ያወጣ ሙስናና አምባገነናዊ አገዛዝ ቆዳዋ ሳስቷል፡፡ ትከሻዋ ጎብጧል፡፡ በስልጣን ላይ የነበረው ቡድን ለረጅም ዘመናት ያህል ሲከተለው በነበረው ጸረ ኢትዮጵያ ፖሊሲ የብሄር ግጭት፤ የድንበር ውዝግብ ፤ የጥቅመኝነትና የአደርባይነት ስንክሳሮች፤ የውጭ ብድር ጫናና የኑሮ ውድነት አሁንም ፈተናዎች ሆነው እየተገዳደሯት ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በጋራ ተጋፍጦና የተጀመሩትን ተስፋ ሰጪ የልማትና የፖለቲካ መንገዶችን አጠናክሮ ሀገሪቱን ማሻገር ሲገባ ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች በመቀፍቀፍ ላይ የተጠመዱ ወገኖችም በዚያው መጠን በየስርቻው ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ወገኖች በጊዜያዊ የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ጥቅም ተጠልፈው ወይም በምንቸገረኝ አባዜ ተተብትበው የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ሀገሪቱ የጀመረቻቸው ተስፋ ሰጪ የልማት ውጥኖች ከዳር እንዳይደርሱ ከማድረጉም ባሻገር በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብን በማንገስ ያልተረጋጋች ሀገር እንድትኖረን ተግዳሮት እየሆኑ ነው፡፡ በእነሱ ምክንያት ንፁኃን ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና የአገር ሰላም ሲታወክ ለጊዜው ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጡም፣ ከታሪክ ተጠያቂነት የሚታደጋቸው ግን የለም፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከጎኗ የሚቆሙ ልጆቿን ትፈልጋለች፡፡
ቁስሏን የሚያክምላት ፤ የጎበጠ ትከሸዋን የሚያቃናላት፤ የተፈናቀሉ ዜጓቿን የሚያበላላት፤ የሚያለብስላት፤ የተጋረጠባትን የሉዓላዊነት ፈተና የሚጋፈጥላት የቁርጥ ቀን ልጅ ትፈልጋለች፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉ ልጆቿ ክንዳቸውን አስተባብረው ከጸብና ሁካታ ይልቅ ለልማት እንዲነሱ፤ አባገዳዎችና አደስንቄዎች በትግራይ እንዳደረጉት አንዱ ለአንዱ አለኝታነቱን እንዲያሳይ፤ ሞት፤ መፈናቀል፤ ጦርነት ቀርቶ በምትኩ ፍቅርና መከባበር እንዲሰፍን ፤ በአካባቢያዊነትና በዘር ያለው መጠራጠዝ ተወግዶ ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ ሁሉም የዜግነትና የትውልድ ሃላፊነት አለበት፡፡
በውጭ ያለውም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከዳር ተመልካችነት ፤ ከተችነትና ከነቀፌታ ወጥቶ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን እሾህና አሜካላ ሊነቅልላት ይገባል፡፡ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶችን በሃሳብ፤ በገንዘብና በዕውቀት በመደገፍ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ሸክም ይቀላል፡፡ ነገም ብሩህ ቀን ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 08/2013