ዘላለም
ጀምበር ምሥራቅ አድማስ ላይ ስቃለች። ሀጫ ጥርሷን ለዓለም ገልጣ ስትታይ ጎረምሳ ለማማለል የተላከች ሳቂታ ጋለሞታ ትመስል ነበር። ከሆዷ የሚወጣው ቀይ የብርሃን ፍንጣቂ ምሥራቃዊውን መንደር አፍክቶታል።
ሲራክ ቁርጭምጭሚቱ ድረስ የረዘመ የታራሚ ልብሱን እንደለበሰ መስኮቱ አጠገብ ቆሟል። ፈገግ እንዳለ ነው። ክርክም ጥርሶቹ ከከንፈሩ አምልጠው ሜዳ ላይ ናቸው፤ ፀሐይ እየሞቁ።
ሩቅ አያየ ሩቅ እያሰበ ሳቅ፣ ደሞ ኮስተር፣ አፈር፣ ደፈር፣ እንዲህ እያለ የሞትን ያህል በሚያስፈራ ጽሞና ውስጥ ውድቋል። የማለዳዋ ፀሐይ ፈገግታው ላይ አርፋ ሌላ ፈገግታዋን አጎናጽፋዋለች።
አራስ ንፋስ እየተጋጨው ይመለሳል። እዚህ ቦታ ከማለዳዋ ፀሐይ ጋር እያወራ፣ከንፋሱ፣ከአእዋፋቱ ጋር እያወጋ ቆሞ ያውቃል። ብዙ መከራዎችን ብዙ ትዝታዎችን መስኮቱ ጋ አሳልፏል። ከስምንት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳቁ ነው።
ነገ ከእስር ይፈታል። ወደሚያፈቅራት ሚስቱና ወደናፈቀው ልጁ ይሄዳል። ነገ የምጻትን ያህል ራቀችው። ጭራሽ ነገ የሚባል ቀን የሌለ መሰለው። በህይወቱ ውስጥ የባከኑ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል። ለምን እንደ ታሰረ አንኳን ሳያውቅ የህይወቱን አስቀያሚ ጊዜ በእስር አሳልፏል።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ የሚስቱ መጥፋት ነው። የታሰረ ሰሞን በየቀኑ እየመጣች ትጠይቀው ነበር። ለሁለት ዓመታት ያህልም እየተመላለሰች ጠይቀዋለች። ከሁለት ዓመት በኋላ ግን መጥታ ጠይቃው አታውቅም። ለምን እንደጠፋች ዛሬም ድረስ አያውቅም። ግን ትናፍቀዋለች። ባሰባት ቁጥር … ትዝ ባለችው ጊዜ ይበላዋል።
እሷ በእሱ ውስጥ ደምቃ የተጻፈች ፊደል ናት። የሁሉም ነገር መጀመሪያው ናት። ከእሷ ቀጥሎ ጓደኛው ሳሙኤል ነው። ከሁለቱ ሌላ ዓለም የለውም። ሄዶ ሄዶ መቆሚያው እነሱ ጋ ነው። ግን ሳሙኤል መጥቶ ጠይቆት አያውቅም። መጀመሪያ ሰሞን አንድ ሁለት ጊዜ መጥቶ ጠይቆት ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን የውሃ ሽታ ሆነበት። የሆነ ነገር ሆኖ ካልሆነ እንዲህ እንደማያጠፋ ያውቃል።
አምላክ የእሱን ክፉ እንዳያሳየው ብዙ ጊዜ ጸልዮአል። እሱ ጓደኛው ብቻ አይደለም። ወንድሙም ጭምር ነው።
አብረው ብዙ ታሪክ ሠርተዋል። የሚያስቁ የሚያሳዝኑ የልጅነት ትውስታዎች አሏቸው። ብዙ ሳቆችን አብረው ስቀዋል። አብረው ተክዘው ያውቃሉ። ለሁለት ጎን ለጎን በርበሬ ታጥነው ያውቃሉ። በጓደኝነት ዓለምን በአንድ እግሯ አቁመዋት ያውቃሉ። ይሄ ብቻ አይደለም ሜላትን ሲያገባም አንደኛ ሚዜው ነበር። ይሄ ብቻል አይደለም….
የማያውቀው የሆነ ፊት በሃሳቡ መጣ። ትንሽዬ ፊት… ደግነት የሞላበት …ቅንነት የሚቦርቅበት ፊት። ልጁ ነው … የማያውቀው ልጁ። ልጁን ሲያስብ ብሩህ ነገ ፊቱ ድቅን ይላል። ከነገ በኋላ ከልጁና ከሚስቱ ጋር የሚኖረውን ህይወት ሲያስብም ራሱን በደስታ ለመሳት ሁሉ ይደርሳል።
ግን የሚስቱን መጥፋት ሲያስብ የጓደኛው መሰወር ትዝ ሲለው ሁሉንም ረስቶ መሳቅ ይጀምራል። ሁሌም ግን የሚስቱና የልጁ ነገር ያሳስበዋል። ከእነሱ ጋር ብዙ ህልም አለው። ሚስቱ አለሙ ናት፤ ልጁ ደግሞ ለቀሪ ዘመኑ የተሰጠው ስጦታ። ስልጣን ቢኖረው ከህይወቱ ውስጥ የሚሰርዛቸው በርካታ ቀኖች ነበሩ። ከስምንት ዓመት በፊት በእለተ እሁድ ምን እንደ ተፈጠረ ሳያውቅ ራሱን ቃሊቲ አገኘው። መስኮቱ ጋ እንደቆመ ሃሳብ ወሰደው።
ስምንት ዓመት ወደ ፊት ሄደ። እሁድ ሠርጉ ነው። ሜላትን ሊያገባ ሽርጉድ ላይ ነበር። ማክሰኞ እለት ከሜላት ጋር ቀጠሮ ነበረው ፤ግን ከከተማ ውጪ ቤተሰቦቼ ጋ ደርሼ እመለሳለሁ ብላው ሄደች።
ድንገት ተነስታ የሆነ ቦታ ልሄድ ነው ብላው ታውቃለች። ወይም ደግሞ የት ነሽ እንገናኝ ናፍቀሽኛል ሲላት ከከተማ ወጣ ብያለሁ ብላውም ታውቃለች።
ስለሚያምናት ከማ ጋር… የት ብሏት አያውቅም። ብዙ ጊዜ ሳትነግረው ሄዳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ ስልኳ ዝግ ሆኖበት ያውቃል፤ ግን አታድርም ፤ማታ ከእሱ ጋር ናት። በብዙ ነፃነት ውስጥ ነው የሚያኖራት።
በጣም የሚገርመው እሷ ስትጠፋ የጓደኛውም የሳሙኤል አብሮ መጥፋት ነበር። ማክሰኞ ማታ ከሄደችበት መጣች። እንደወትሮው እየሳቀ እንደተቀበላት ትዝ ይለዋል። እሮብ ጠዋት ከሚዜዎቿ ጋር ቬሎ እመርጣለሁ ብላው ወጣች።
በጣም ስለደበረው ሳሙኤል ጋ ሲደውል ስልኩ ጥሪ አልቀበልም አለው። ተኝቶ ይሆናል ብሎ ቤቱ ሲሄድ ትናንት ጠዋት ጀምሮ ቤት እንዳልመጣ እና ከአንተ ጋር ይሆናል ብለን አሰብን ነበር ብለው ነገሩት።
ሀሙስ እለት ሦስቱም ምሳ እየበሉ ስለ ሠርጉ ሲያወሩ ቆዩ። እለተ ዓርብ አመሻሽ ላይ ከአንደኛ ሚዜው ሳሙኤል ጋር ሱፍ እየመራረጡ ቦሌ አካባቢ ከሚገኝ ከአንድ ሱቅ ውስጥ ነበሩ። ድንገት የማያውቀው አንድ ስልክ ተደወለለት። ‹‹ሳምሶን እባላለሁ የሪል ስቴት ባለቤት ነኝ፤ጥሩ አርክቴክት እንደሆንክ ሰምቼ ነው የደወልኩልህ።
ድርጅታችን በጥሩ ገንዘብ ሊያሰራክ ይፈልጋል፤ ዛሬ ማታ ራት እየበላን ማውራት ብንችል ደስ ይለኛል። አለው።በሠርጉ ማግስት የመጣ ዕድል መሰለው። ከሁለት ቀን በኋላ ሠርጉ ነው። ሚስቱ የሰባት ወር እርጉዝ ናት ብዙ ነገር የሚፈልግ ሌላ ሦስተኛ ሰው ወደ ቤታቸው እየመጣ ነው።
‹‹ መገናኘት እንችላለን›› ደስ እያለው መለሰ። ‹‹አንድ ጀማሪ ባለሙያ ያበላሸው ሕንፃ አለ። እሱን ካየን በኋላ ራት እየበላን ስለቀረው እናወራለን።›› ጎርናናው ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰማው። ‹‹ምንም ችግር የለም›› በቅድሙ የደስታ ድምፅ መስማማቱን ገለጸለት።
አመሻሽ ላይ ደስ እያለው ነበር ወደ ቀጠሮው ቦታ የሄደው። ሲመለስም በጥሩ ደሞዝ ጥሩ ሥራ በማግኘቱ ደስ እያለው ነበር።
በማግስቱ በሠርጉ ዋዜማ ሳምሶን በተከፋ ድምጥ ደወለለት። በቃ ይሄን ብቻ ነው የሚያስታውሰው። ማታ ሁለት ሰዓት ላይ በሠርጉ ዋዜማ በፖሊስ ተይዞ ተወሰደ። ስምንት ዓመት ተፈረደበት።
ወንጀሉን ሲጠየቅ ከአንድ ወንጀለኛ ጋር በመተባበር በአንድ ሕንፃ ውስጥ ከባድ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽመሃል ተባለ። ነገ ሠርጉ ነበር… የሰባት ወር እርጉዝ ሚስቱ ከእሱ ጋር ልትሞሸር እየጠበቀችው ነበር። በማያውቀው ወንጀል ስምንት ዓመት ተፈረደበት።
ከስምንት ዓመት በኋላ ራሱን መስኮቱ ጋ በደስታ አገኘው። ነገ ወደ ሚስቱ ይሄዳል። ልጁም አድጎ ትልቅ ሆኖ ይጠብቀዋል። ወደ ተወው ታሪኩ ይመለሳል።
ከርቀት ቅርንጫፎቻቸውን ያንጨፈረሩ ረጃጅም ዛፎች ይታዩታል። አበባ የሚቀስሙ ንቦች….. ጎጇቸው ውስጥ የሚንሾካሻኩ ….የሚዘምሩ አእዋፋት፣ብሩህ ሰማይ … በሩህ ዓለም። ከማለዳዋ ጀምበር እኩል የፈገገ ፊቱን እንደያዘ ወደ ኋላው አፈገፈገ።
እስኪመሽ ከፊቱ ስላለው ብርሃናማ ነገ ሲያስብ ነበር። ወደ መኝታው ሲያቀና ከለሊቱ 9 ፡00 ሰዓት ሆኖ ነበር።
እይነጋ የለ ነጋ።
ወደ መስኮቱ ሄደ። አይቶት የማያውቅ ማለዳ …. ታይቶት የማያውቅ ብርሃን ተቀበለው። የሚስት ንፋስ… እስክስታ የሚወርዱ እጽዋቶች ተቀበሉት። ሰማዩ ላይ ትልቅ እውነት ያየ መሰለው። በደመና የተሳለ፣በክዋክበት የተለቀመ አንጸባራቂ ሀቅ።
ገጹን ፈገግታ ሞላው። ዓለም ውብ ሆና ታየችው። በሃሳቡ በመንፈሱ ታደሰ። ከእንግዲህ እንዲህ ይኖራል አለ ፤እየሳቀ እየተፍለቀለቀ።
ጓደኞቹን ዞሮ አያቸው። በአስቂኝ አተኛኘት ተኝተዋል። ሌላ ሳቅ መጣበት። ጓደኞቹ የቀሪ ዘመኑ ትዝታዎቹ ሆነው ይኖራሉሉ። አይረሳቸውም።
ረፋድ ላይ 4፡00 ሰዓት ላይ ስሙ ተጠራ። እግዜር የጠራው ይመስለዋል። እንደ ዛሬ ስሙን ከሰው አፍ ደስ ብሎት ሰምቶት አያውቅም። ከሲኦል የሚመጣ ይመስለዋል። ወደ ገነት… ወደ አርያም የሚሄድ አንዲህም ይመስለዋል። እንደ ገናም እየተፈጠረ…ለዘላለም እየተባረከም።
በለቅሶና በእንባ… በደስታም ወዳጆቹን ተሰናብቶ ለዓመታት የቆየበትን እስር ቤት ለቆ ወጣ።
ከእንግዲህ ወደ ኋላ አይመለስም። ከሚስትና ልጁ ጋር ብዙ ነገዎችን … ብዙ ዘላለሞችን ሊኖር እያሰበ ተጓዘ።
ፀሐይ ምድር ወገብ ላይ ስታቅላላ የድሮ ሰፈሩ ደረሰ። ሁሉም ነገር ተቀይሮ አዲስ ሆኖ ነበር የጠበቀው። ሚስቱን ለማየት ትንሽ ልጁን አቅፎ ለመሳም የቸኮለ፤ ምን ያህል ለምንም ነገር ተቻኩሎ አያውቀም።
ከጥቂት ርምጃዎች በኋላ ከቤቱ ደረሰ። የሚያውቀው ቤቱ የዱሮ ገጽታውን አጥቶ በግንብ ታጥሯል። ቤታቸው በር ላይ የሆነ መኪና ቆማ አየ። የውጪው በር እንደተዘጋ ነው። የሚወጣም የሚገባም ሰው አልታይህ አለው። ሁሉም ነገር ግራ ገባው። በርካታ ጥያቄዎች ተፈጠሩበት።
ቤቱ አንዲህ አልነበረም። እንዴት እንዲህ ሊያምር ቻለ? ሚስቱ ምን ሆና ይሆን?… ልጁስ? ተጨነቀ።
ከውስጥ በኩል የትንሽ ልጅ ድምፅ ሰማ። ራሱን ስቆ አገኘው።
ስለሚስቱና ልጁ የሚነግረውን ሰው ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲል የተዘጋው በር ተከፍቶ ሁለት ወንድና ሴት ታቃቅፈው ሲወጡ አየ።
ያየውን ማመን አልቻለም። መሳሪያ የጮኸበት ያህል ክው ብሎ ደነገጠ። ሜላትን አያት….. ከጓደኛው ሳሙኤል ጋር ተቃቅፈው። ከድንጋጤው ሳያባራ ከኋላቸው ሌላ አንድ ሰው ተመለከተ። ከስንምት ዓመት በፊት የሚያውቀውን ሳምሶንን።
እየተሳሳቁ በመኪና ገፍተውት ሄዱ።
በግራ መጋባት ውስጥ ሁሉም ነገር ገባው።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013