የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ትናንት አንድ ልዩ እንግዳ ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡ በህግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው እንዲሉ፤ ቃል በተግባር ታይቶበታል፡፡ የክበበ ጸሃይ ህጻናት ማሳደጊያ ተቋም ተወካይ እንዲሁም ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተወካይ ችሎት ቀርበው በህግ ስርዓቱ መሰረት ሕጻን ሚሊዮንን በጉዲፈቻ ወስደው ለማሳደግ የጠየቁት ውል እንዲጸድቅ ችሎት ቀርበዋል፡፡
አመልካቾቹ ቤተሰቦች ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ሕጻን ሚሊዮንን ልጅ አድርገው ለማሳደግ የተፈራረሙትን ውል ለማጸደቅ ጠይቀው ነበር፡፡ የክበበ ጸሃይ ህጻናት ማሳደጊያ ተቋም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ቤተሰቦች ህጻን ሚሊዮንን እንዲያሳድጉ ውል የፈረሙት ለህጻኑ መልካም አስተዳደግ እንደሚበጅ በማመን እንደሆነ በማመልከቻቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ህጻን ሚሊዮን ዕድሜው ከሁለት ዓመት በታች በመሆኑ በውሉ ላይ ያለውን አስተያየት እንዳልሰጠ እንዲሁም ውል እንዲጸድቅ የተለያዩ ማስረጃዎች መቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የቀረቡለትን ማስረጃዎችም መርምሯል፡፡ በኋላም ህጻኑን ወስደው ቢያሳድጉት ለመልካም አስተዳደጉ የበለጠ የሚበጅና ጠቃሚ መሆኑን መገንዘቡን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ በአመልካቾች መካከል ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም የተፈራረሙት የጉዲፈቻ ውል በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ዓ.ም 194/1 መሰረት እንዲጸድቅ ወስኗል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ ጉዲፈቻ የተቀበሉትን ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ፤ ትልቅ ስጦታ ቤተሰቡን መቀላቀሉን ተናግረዋል፡፡ ተግባሩ አርአያነት ያለው መሆኑን ልጆች ማሳደግ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ዶክተር ዐቢይና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ህጻን ሚሊዮንን ለማሳደግ መወሰናቸውን በበጎነት ያነሳሉ፤ ይህን ማድረግ ሰፊ ልብ የሚጠይቅ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አጋጣሚው የተመቻቸ ኑሮ የሌላቸውን ህጻናት ወስዶ በማሳደግ ባሉበት ለመደጎም ምክንያት እንደሚሆን ነው ወይዘሮ መዓዛ የተናገሩት፡፡ ባደጉት አገራት ትልቁ ሃብት የሚፈስሰው ህጻናት ላይ መሆኑን በማስታወስም፤ ህጻናትን በጤና ለማሳደግ፣ በእውቀትና በምግብ ለመገንባት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ወሳኝ መሆናቸውን በማንሳትም፤ የአገር መሰረት ህጻናት በመሆናቸው በኢትዮጵያም ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ በቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽና በዶክተር ዐቢይ የተደረገው ነገር ትልቅ ነው፡፡
በሦስት መንግሥታት ማለፋቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ መዓዛ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የአገር መሪዎች ቤተሰቦቻቸው ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማንኛውም ዜጋ ጉዳይ ሲያስፈጽሙ እንዳልተመለከቱ ያስታውሳሉ፡፡ የትናንቱ ቀን ለአገሪቱ የፍትህ ስርዓት አዲስ ቀን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለ ሰው፣ ማኅበራዊ ደረጃው ከፍ ያለ ዝቅ ያለም ቢሆን በህግ ፊት እኩል መሆኑን ቀዳማዊት እመቤት ትናንት ትምህርት እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡
በህግ ጉዳይ ህጻናት ላይ በርካታ ሥራ መሰራት አለበት፣ በፍርድ ቤት ብቻ በሚሰራው ሥራ የፍትህ ስርዓቱን መለወጥ አይቻልም፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ በህዝቡ ላይ የሚሰራው ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ህግ ምን እንደሆነ ህጻናትን ለማስተማር ሥራዎች ተጀምረዋል ይላሉ፡፡
የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ በየቤቱ ህጻናት የሌላቸው ህጻናትን የሚፈልጉ ቤተሰቦች በርካቶች ናቸው፡፡ በተለያዩ ማሳደጊያ ቦታዎች የሚገኙ ህጻናት እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ህጻናትን ማሳደግና መታገድ የሁሉም ሰው ኃላፊነት መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ እስካሁን የተሻለ አማራጭ ባለመገኘቱ በርካታ ህጻናት በተቋም እያደጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ወስዶ ማሳደግ ባህል እንደመሆኑ አቅሙ የፈቀደ ኅብረተሰብ ህጻናቱን ወስዶ እንዲያሳድግ፣ በተቋማት በመገኘት የመጎብኘትና ፍቅር የመስጠት ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ በህጋዊ መንገድ ህጻናትን ወስዶ ማሳደግና መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ቀዳማዊ እመቤትና ዶክተር ዐቢይ በህጋዊ መንገድ ህጻኑን ወስደው ማሳደግ መጀመራቸው ለኅብረተሰቡ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን በመጠቆምም፤ ጉዲፈቻ ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን፣ ዜጎች ህጻናትን ወስደው ማሳደግና መንከባከብ እንዳለባቸው የሚያመለክት ትልቅ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ዘላለም ግዛው