አዲሱ ገረመው
ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት የሦስተኛ ዓመት የቋንቋ ተማሪ ነበርኩ ልበል እንጂ ነኝ ማለት እንኳን ቀርቷል። ነበር በተባለው የኋላ ትውስታዬ እጅግ በጣም ደስ የሚል የሁልጊዜም የህሊና ስንቅ የሆነ የዩኒቨርሲቲ ህይወት አሳልፌያለሁ። ዘለቄታቸው ዛሬ ድረስ የሆነ ተወዳጅ ጓደኞችን አግኝቻለሁ።
የመጨረሻው ዓመት የግቢ ቆይታዬ ግን ከሁሉም ይለያል። ምክንያቱም ያ ወቅት ከሄዋኔ ጋር የተዋወቅኩበት ዓመት ነበር።እንዴት እንደምታምር ቃላት ካልተሞሸሩ በቀር መግለጽ አይቻልም። ፈገግታዋ ከምታወራቸው ቃላት ጋር ተደምሮ ልብ ያቀልጣል። ጎላ ጎላ ያሉ ማራኪ አይኖቿን ስመለከት ከእርሷ ጋር የተዋወቅኩበትን ቀን ሳይሆን ሰው የሆንኩበትን ቀን አመሰግናለሁ።
ፊት ለፊቷ ቆሜ ተልባ ድቅል የሚመስለውን ጸጉሯን ስዳብስ ያለ ክንፍ እበራለሁ። በፍቅሯ አድማስ ያለ ስስት እከንፋለሁ። አንድ ላይ በሆንን ቁጥር ውስጤን ሰላም ይሞላዋል። በፍቅሯ ጠብታ ልቤ ይርሳል። ሄዋኔ የኔ እናት እንዴት እኮ እንደምወዳት። እወዳት ነበር ልበል እንጂ አሁንማ ሁሉ ነገሬ ፈርሷል። አካሏ ርቆ ትዝታዋ ብቻ ቀርቷል።
በቃ ከትውስታ ውጭ ምንም የሚዳሰስ የሌለው ባዶ፤ ዞር ብዬ የመለያየታችንን ጽንስ ሳስበው ያመኛል። አንድ ቀን ከሄዋኔ ጋር ምሳ ከበላን በኋላ «ዎክ» ማድረግ ጀመርን። ከዚያ በፊት እኮ ቀን ላይ «ዎክ» አድርገን አናውቅም ነበር።
ምናለ የዛን ቀን ዎክ ማድረግ አፈልግም ባልኳት! ምናለ እሽታዬን በሰበርኩት!ከሄዋኔ ጋር ደስ የሚሉ ጊዜ እያሳለፍን ነበር። እጄን አንገቷ ላይ ጠቅልዬ፤ በገላዋ እንፋሎት ልቤ እየቀለጠ በፈገግታዋ እኔነቴ እየታደሰ፤ ሳምኳት! ሳቀች። ጥግ የሌለውን ደስታ ፊቷ ላይ ጻፈች። አነበብኩት። ሳቋ ግን ብዙምአልቆየም። (እዛው) እጄ አንገቷ ላይ እንዳለ ጥል ተጀመረ። ሳቋን እያነበብኩ ተጣለን። ሙሉነቴን እያሰብኩ ተጣላን። እጄ ከአንገቷ ላይ ወረደ። ሳቋ ወደ ሀዘን ተመለሰ።
በላይሁን ነው ስሜ። በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን የበላይነቴን ማሳየት ነበር የምፈልገው። ማንም ሲበልጠኝ ቆሜ ማየት አልችልም። ግልፍተኛ ነበርኩ። የእልኸኛ ጥግ ማለት እኔ ነኝ። ስምን መልዐክ ያወጣዋል የተባለው ስሜ ከእኔ ጋር ያለው ዝምድና ታይቶ ይመስለኛል። ነገረኛም ቢጤ ነበርኩ።
ዘሬን ስቆጥር ዘሯን ስዘረዝር ዘሬን ከፍ ሳደርግ ዘሯን ሳኮሰምን ጸባችን ከረረ። ይህ የፍቅረኛሞች የግለሰብ ጥል ቀስ በቀስ የቡድን ጸብ ሆነ። የልብ የልብ ተሰማኝ። አለንልህ አይዞህ ሲሉኝማ ማን ይድረስብኝ። ግቢውን በአንድ እግሩ አቆምኩት። ጸባችን ሲያይል የጸጥታ አካላት መጥተው አፋፍሰው ወሰዱን ጸቤም ወደ እነርሱ ዞረ።
ከመሃላቸው ፈርጣማ ሰውነት ያለው ጸጥታ አስከባሪ ተንደርድሮ በያዘው ዱላ ጀርባዬን ሲለኝ ራሴን ሳትኩ። (አሁን በግራ እጄ እንደልብ እቃ ማንሳት አልችልም። ይህ የጤና መጓደል የዛ ጸብ ትርፍ ነው) ኋላ ሁኔታው እስኪጣራ ብለው ማረፊያ ቤት አስገቡን።
ገላዋን መንካት የሚያሳሳኝን ሄዋኔን በተዘጋ ቤት ውስጥ ሆኜ ሳስብ፣ እግሯን አጣጥፋ አንገቷን ቆልምማ ለመተኛት ስትቸገር፣ እንቅልፍ አጣሁ። አንድ ሳምንት ሙሉ በተዘጋ ቤት ውስጥ ሆኜ በስቃይ አሳለፍኩ። እንኳን ሞቴ እንቅልፌ ናፈቀኝ። ወቅቱ የማጠቃለያ ፈተና የምንወስድበት ጊዜ ስለነበር በዋስ ተለቅቄ ፈተናውን እንድፈተን ብለምናቸው አሻፈረን አሉኝ።
በመጨረሻም ሄዋኔም እጅሽ አለበት በመባል ለአንድ ዓመት ከትምህርቷ ተባረረች። እኔም በፈጠርኩት ጸብ ምክንያት በአንደኛ ተከሳሽነት ለሦስት ዓመታት ከትምህርት ገበታዬ ታገድኩ። ሰውነቴን በመርሳቴ በሰው መሆን ህግ ባለመመራቴ ለዘር ቆጠራ በመሰለፌ በአጠቃላይ ዘረኛ በመሆኔ ምክንያት ብዙ እንቅፋቶች ገጠሙኝ። የሕይወት ብክነቱ የምወዳት ሄዋኔንም ነጠቀኝ።
የነገውን ተስፋ በራሱ ምክንያት ካጠለሸ ሰው ውጭ ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ማንም አይገባውም። ልጄ ደርሶልኝ ወግ ማዕረጉን አሳየኝ፤ ልጄ ሰው ሆነ ብላ እግሬን ጥበቃ ደጅ ደጁን ለምታይ እናት ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ማንም አይገባውም። ልጄ የአብራኬ ክፋይ በሁለት እግሩ ቆመ ብሎ ደስታውን ለዘመድ አዝማድ ነግሮ ከዚያም ከዚያም ተበዳድሮ ሰንጋውን ጥሎ ለሚጠብቅ አባት ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ማንም አይገባውም። በቃ ሰው መሆኔን ጠላሁ፤ ስሜ እኔ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ጠላሁ። የጓደኞቼን ግፊት ጠላሁ።
አባቴ የሆነውን ሁሉ ማመን አልቻለም። እናቴም ነገሩን ሁሉ ሰምታ መቋቋም ስላልቻለች፤ ተስፋዋ ስለተሰበረ፤ እኔ ልጇ የአጥንቷ ቁራሽ ባመጣሁት ጣጣ የደም ግፊቷ ተነስቶ እስከ ወዲያኛው ተሰናበተችኝ። ልጄ ብላ ላታቅፈኝ፣ በእናትነት ፍቅሯ ጸጉሬን ላትዳብሰኝ፣ በእጆቿ ላታጎርሰኝ…ላትመለስ ጥላኝ ሄደች። ልቧ እንደተሰበረ ምኞቷ ሳይሳካ አፈር ለበሰች።
አባቴም ከጊዜ በኋላ የአልጋ ቁራኛ ሆነ። መድኃኒት መግዣ እስኪያጣ አንዲት ጉርሻ ማጉረስ እስክቸገር ድረስ ችግር ቤታችንን ወረሰው። አባቴ አይኔን ማየት ከብዶት ፊቱን ትራሱ ስር ከወሸቀ ወራት ተቆጠሩ። እጄን በተስፋ ሲጠብቁ የነበሩትም ታናናሽ እህቶቼም ለመማር ያላቸውን ፍላጎት ታቅፈው ምግብ ከጨበጠ ቀናት ባለፈው እጃቸው፤ ከተበጠረ ጊዜ የማይቆጠርለት ጸጉራቸውም ውሃ ካየው ስንት ጊዜው። ቤታችንም ቤትነቱን ካጣ ሰነበተ።
ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው እኔ ነኝ። ለምን እንዲህ ሆነ ብዬ አምላኬን አልወቅስም። አልጸጸትምም፤ ምክንያቱም ስለሚመጣው እንጂ ስላለፈው ህይወቴ መጨነቅ አልፈልግም። ግን ውስጤ እልህ አለ። ትራስ ስር የተወሸቀውን የአባቴን ፊት በኩራት ቀና ለማድረግ የተነሳሳ እልህ። የእህቶቼን የመማር ፍላጎት እስከ ጥግ ለማሟላት የቆመ እልህ፤ የሞተችውን የእናቴን ነፍስ የሚያሳርፍ እልህ።
ዳግመኛ ኢትያጵያዊነቴን ጥሼ ዘርን ላላቀነቅን፤ ክብሬን አፍርሼ ዝቅ ላልል፣ ሰው መሆኔን ጥዬ ከሰው ላልለይ፤ ለእኔነቴ ስትል ለሞተችው እናቴ ስም ምዬ ቃል ገብቻለሁ። ከትምህርት ገበታዬ የታገድኩበት ገደብ አልቆ ወደ ትምህርቴ እስክመለስ ቤቴን፣ አባቴን፣ እህቶቼን ላቀና እየወደደችኝ በጥፋቴ በተለየኋት ሄዋኔ ስም ምዬ ቃል ገብቻለሁ። አገሬ እናቴ ናት። በሞተችው እናቴ ምትክ ዘረኝነትን በማስወገድ እናቴን ከፍ ለማድረግ አበላሽቶኝ በነበረው ዛሬ ደግሞ ቃል በገባው ስሜ ምዬ ቃል ገብቻለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013