አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደመጠለያ የማጓጓዙ ዝግጅት ተጠናቅቆ በዛሬው እለት የመጀመሪያው ዙር ጉዞውን እንደሚጀምር ተገለፀ።
በአዲስ አበባ መስተዳድር የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሁሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዛሬው እለት የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ወደተመደቡበት መጠለያ ጣቢያ ይሄዳሉ።
በኤጀንሲው የልዩ ድጋፍ ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሀሰን በማጓጓዙ ተግባር ላይ ለሚሳተፉ በጎ አድራጎት ሰጪ ወጣቶች ትናንት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር በከተማዋ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደመጠለያ በመውሰድ አስፈላጊውን ተሀድሶና ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደመደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ ባቀደው መሰረት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት የመጀመሪያው ዙር ተጓዦች ጉዟቸውን ይጀምራሉ።
ይህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደመጠለያ የማጓጓዙ ሂደት ቀደም ባሉት ጊዜያት ሲደረግ ከነበረው በአፈሳ መልክ የመውሰድ ሁኔታ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው የገለፁት አቶ መስፍን፤ ይህ የአሁኑ እንቅስቃሴ ሁሉንም እንደየሁኔታቸው የሚያስፈልጋቸውን በመለየት እርዳታ፣ድጋፍ፣ ስልጠና፣ ልዩ ክትትል በማከናወን ወደመደበኛ ህይወታቸው መመለስ ዋና አላማው መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከሚገኙት 10 ክፍለ ከተሞች አራት ክፍለ ከተሞች በጥናት ተለይተዋል ያሉት ኃላፊው፤ ክፍለ ከተሞቹም አራዳ፣ ጨርቆስ፣ ልደታ፣ እና አዲስ ከተማ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዛሬው እለት በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማጓጓዝ ሥራው የሚጀመር ሲሆን፤ አሰራሩ እየተገመገመ እና ልምድ እየተወሰደበት የሌሎቹ ክፍለ ከተሞችም ይቀጥላል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ተመዝግቦ በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበረው ወጣት ሀየሎም ሞናናው የዚህ ተግባር ተሳታፊ በመሆኑ ደስታውን የገለፀ ሲሆን፤ የጉዞውም ሆነ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ አያያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ሲል አሳስቧል።
እንቅስቃሴውን ለማገዝ ለተመዘገቡ 300 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ሲካሄድ እንደተገለፀው፣ ለሚንቀሳቀሱት የጎዳና ተዳዳሪዎች ከመጠለያ ጀምሮ አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቷል። ከተጓዦቹ መካከል ህፃናት፣ አረጋውያን እና ነፍሰጡሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ዝግጅቱ እነዚህን ሁሉ ያካተተ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ከ50 ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ በግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሙ ላይ ከተሰጠው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ግርማ መንግሥቴ