እፀገነት አክሊሉ
የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ ገና ነው፡፡ የገና በዓል አከባበር በየአገሩ መጠነኛ ልዩነት ቢኖረውም በየዓመቱ አዳዲስ መሻሻሎች እየተደረገበት ደማቅነቱን እንደጠበቀ ቀጥሏል፡፡
አውደአመት ሲመጣ ሁሉም እንደ አቅም እንደቤቱ ዝግጅት አድርጎ በደመቀ ሁኔታ ለማሳለፍ ይሞክራል። በተለይም እንደ እኛ ኢትዮጵያውያን በዓልን አድምቀን ለመዋል ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት እናደርጋለን። ወንዶችም የወንድ በሚሉት ጎራ ሴቶችም እንዲሁ ይመለከተናል ቤታችንን በዓል ያስመስልልናል ብለው በሚያስቡት ነገር ሁሉ ዝግጅት ያደርጋሉ።
በዓል ላይ በብዙ መልኩ ኃላፊነት ከሚበዛባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ግንባር ቀደሙን ተርታ ይይዛሉ። ተፈጥሮም ይሁን ኃላፊነት ብቻ ሴቶች ለቤታቸው ራስ እንደዚህ በዓል ሲሆን ደግሞ ድምቀት ናቸው። ይህንን ደግሞ ሁላችንም በቤታችን የምናየው ሃቅ በመሆኑ ለመመስከር አንቸገርም።
በዓል ደረሰ ሲባል ቤት ከማጽዳት ጀምሮ በእለቱ ለምግብነትና ለመጠጥነት የሚውሉትን ግብዓቶች እስከማዘጋጀት አዘጋጅቶም ለቤተሰቡ ብሎም ለዘመድ ጎረቤት እስከማቅረብ ድረስ ያለባቸው ኃላፊነት በትንሹ የሚታይ አይደለም።
እነዚህ ሴቶች ደግሞ በሌሎች ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት ውስጥ ሲሆኑ እንኳን በዓል ቤታቸውን ማየት የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ቤታቸውንና ቤተሰባቸውን በሚገባ በመምራት በኩል አሁንም ችግር አይስተዋልባቸውም።
ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደግሞ የሁሉም ብሔር እንዲሁም ጾታ ተዋጽዖ ያለው እንደመሆኑ ሴቶች በጀግንነቱም ቤተሰብ በመምራቱም ቆራጥ ስለመሆናቸው ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው።
እኛም ውትድርናና ሴትነት አልፎም በዓል አከባበር ምን መልክ አለው? ስንል ለሴት ጀግና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥያቄዎችን አቅርበናል።
ብርጋዴር ጀኔራል እርጎ ሺበሺ መከላከያ ሰራዊትን የተቀላቀሉት በ1982 ዓም ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እንደ ሴትም እንደ ወታደርም የአገርን ዳር ድንበር በመጠበቅ አልፎም ቤተሰብን በመምራት ውጤታማ ጊዜን አሳልፈዋል።
«ሴትነት በምንም መልኩ ቢሆን የሚከብድ አልያም ትልልቅ ኃላፊነቶችን ከመወጣት የሚያግድ አይደለም፡፡ ዋናው እወጣዋለሁ ብሎ ራስን ማሳመን ነው»፤ የሚሉት ብርጋዴል ጀኔራል እርጎ በዚህን ሁሉ ዓመት የመከላከያ አገልግሎት ጊዜም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ ጎን ለጎንም ቤተሰብ መስርተው ልጆች ወልደው ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረሳቸውን ይናገራሉ።
ወታደርነት ብዙ ውጣ ውረድ ያለው እንኳን ለሴት ለወንድም ፈታኝ የሆነ የሙያ ዘርፍ ቢሆንም ወታደር መሆን በራሱ ሕይወትን ቀላልና ዘመናዊ አድርጎ ለመምራት ያስችላል። ይህም በእኛ የአኗኗር ሁኔታ በተግባር ታይቷል ይላሉ።
«ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሙሉ ወታደር ሆነው በዚያ መንገድ ማለፍ ቢችሉ በሥነ ምግባር ታንጸው፣ አገራቸውን ወዳድ ሆነው፣ ለአገር ክብር ዝቅ የሚሉ፣ ለቤተሰብ አዛኝ፣አገራቸውን ከልባቸው የሚወዱ ይሆኑ ነበር» ብለዋል።
በዓልና ውትድርና ምንም የሚቃረኑ አይደሉም፤ ወታደሩ ባደገበት ማህበረሰብ አካባቢ በዓል እንዴት እንደሚከበር ያውቃል፡፡ በዚያ መልኩ እንዲያውም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ሆነን ደስ በሚል ሁናቴ እናከብራለን። እዚህ ላይ ግን ወታደር ከሌላው ማህበረሰብ የሚለየው ዛሬ በዓል ነው ሥራ አልገባም አልያም ካለበት ግዳጅ በዓልን ላክብር ብሎ ወደቤተሰቡ የሚሄድ አለመሆኑ ነው።
ወታደሩ ግንባርም ቢሆን ማድረግ ያለበትን ነገር አድርጎ ሴቶቹም ወንዶቹም በአንድ ላይ ተሰባስበን በደስታ በዓልን በበረሃ በምሽግ ሳይቀር በሁሉም ቦታ ያከብራል።
«የወታደር ልጅ ቤተሰብ መሆን በራሱ በሥነ ምግባር ታንጾ ለመሄድ ከፍተኛ የሆነ አቅም አለው፤ በመሆኑም የእኔ ልጆች የወታደር ልጆች ናቸው፤ እናታቸው ምን እንደምትሰራ ያውቃሉ፤ ይረዳሉ፤ ለበዓል ትታን ሄደች ብለው የሚያዝኑበት ሁኔታ የለም። አብሬያቸው ካለሁ በጣም ደስ ይላቸዋል፤ ከሌለሁ ደግሞ ተከፍተው የሚውሉበት ነገር የለም፤» ብለዋል።
«ለበዓል ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ ልጆቼን ለሠራተኛ ጥዬ ወደግንባር እሄዳለሁ» የሚሉት ብርጋዴር ጀነራል እርጎ ልጆቹም እነሱም እንደወታደር ስለሚያስቡ ይህንን ሁኔታ አምነው ይቀበላሉ፤ ምንም ችግርም ገጥሟቸው እኔንም አስጨንቀውኝ አያውቁም ይላሉ።
«እኔ የእነሱ እናት ብቻ ሳልሆን ለአገሬም ዘብ የምቆም ድንበሯን የማስከብር ወታደር መሆኔን ያውቃሉ» የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራል እርጎ በዓልን ከእኛ ጋር አልዋልሽም ብለው ብዙም የሚከፉበት ነገር የለም፤ እንዲያውም ቤት ያፈራውን እራሳቸው ሰርተውና አቅርበው ይውላሉ፤ ዛሬ ላይ እንዲያውም ስልክ አለ፤ ቀድሞ ስልክ እንኳን እንደልብ በማይገኝበት ወቅት ያን ያህል አልተቸገርንም፤ ዋናው የአገር ፍቅር ቆራጥነት ነው ይላሉ።
ወታደር ባለው ነገር ሁሌም ደስተኛ ነው፤ በዓልንም ባለው ነገር ስቆ ተጫውቶ ዘፍኖና ጨፍሮ የሚያሳልፍ በመሆኑ በወታደር ቤት እንደውም በዓል ልዩ ገጽታ እንዳለውም ይናገራሉ።
በ1978 ዓም መከላከያ ሰራዊትን እንደተቀላቀሉ የሚናገሩት ደግሞ ኮሎኔል ሁለአገርሽ ድረስ ናቸው። እርሳቸውም ሴትነት ጌጥ ነው፤ ሴትነት አስደሳች ነገር ነው፤ ምናልባት ውትድርናን ለሴቶች ከባድ የሚያደርገው ተፈጥሯዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እርሱም ቢሆን ሴቶች እጅግ ጎበዞች እንዲሁም ቆራጦች በመሆናችን ሁሉንም ተወጥተን እዚህ ለመድረስ ችለናል በማለት ይገልጻሉ።
በዓል እንደአመጣጡ ነው የሚከበረው፤ የሚሉት ኮሎኔል ሁለአገርሽ፣ ግዳጅ በሌለ ጊዜ በቤት ውስጥ ከመላው ቤተሰብ ጋር ይከበራል፤ ግዳጅ ሲኖር ደግሞ እንደወታደው በግንባር በግዳጅ ላይ ያልፋል። ይህም ቢሆን ግን በተለይም ግዳጅ ላይ ሆነን በዓል ሲመጣ እንደማንኛዋም ኢትዮጵያዊት ሴት የሚደረጉትን ሁሉ ነገሮች አድርገን ከሌሎች ጓዶቻችን ጋር በፍቅር ተሳስቀን ነው የምናከብረው።
በእርግጥ ሴት እቤት ሆና ለበዓል የሚያስፈልጓትን ነገሮች ስታዘጋጅ እንደባህል ወጉ ጉድ ጉድ ስትል በቤተሰብም በልጆችም ላይ የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ላቅ ያለ ቢሆንም ካልተቻለ ደግሞ ከአገር የሚበልጥ ነገር ስለሌ ባለንበት ሆነን እናከብራለን፤ ይህንን ደግሞ መላው ቤተሰባችን ያውቃል፤ ይረዳልም ይላሉ።
«ልጆች እንኳን ዓመት በዓል ሆነ በአዘቦቱም ቀን እናት አጠገባቸው ሳትሆን ስትቀር ቅር የሚል ስሜት አለው፤ ነገር ግን ልጆቻችንም እንደኛው ወታደር በመሆናቸው ያን ያህል አይጨነቁም፡፡ እንዲያውም በሰላም እንድመለስላቸው ጓጉተው ነው የሚልኩኝ » ብለዋል።
ሰራዊት ጋር ሲኮን ያለው የበዓል አከባበር የጋራና በተገኘው ነገር የሚከበር በመሆኑ ትልቅ ስሜትን የሚፈጥር ነው የሚሉት ደግሞ ሜጀር ጀኔራል ጥሩዬ አሰፌ ናቸው። እንደ እርሳቸው አባባል ወታደርነት 24 ሰዓት በሰባቱም ቀን ዝግጁ መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ እንደሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በዓል መጣ ይህንን ልግዛ፣ ይህንን ልልበስ፣ እዚህ ቦታ ልሂድ፣ የሚባልበት አይደለም፡፡ ሁሌም ዝግጁ ሆኖ የሚጠበቅ ነው ይላሉ።
ከዚያ ይልቅ በያለንበት ግንባር ተሰባስበን ገንዘብ አዋጥተን ሴቶችም እንደ ባህል ወጋቸው ያለውን አዘጋጅተው ወንዶችም ከእነሱ የሚጠበቀውን አድርገው ሻይ ቡና ብለን በሳቅ በጨዋታ ነው ስናሳልፍ የኖርነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንዲያውም በወታደር ቤት በዓል ደስ የሚል ድባብ አለው ይላሉ።
አንዳንድ ጊዜ «አሁን ምንም ግዳጅ የለብኝም፤ በዓልን ከቤተሰቤ ጋር ነው የማከብረው» ብለን ከተዘጋጀን በኋላ በዕለቱ አልያም በዋዜማው ተነሱ ልንባል የምንችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፤ ይህ ደግሞ የስራው ባህርይ መሆኑን ስለምናውቅ ምንም አይፈጥርብንም፤ እንዲያውም ለተፈለግንበት ግዳጅ ጓጉተንና እንዴት ነው ውጤታማ ልንሆን የምንችለው ብለን ነው የምናስበው ይላሉ።
ሜጀር ጀኔራል ጥሩዬ እንደሚሉት ወታደር ምንጊዜም ለአገሩ፣ ለሥራውና ለተቋሙ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፤ በመሆኑም ቤተሰባችንንም በዚህ መልኩ ነው ቀርጸን የምናሳድገው በማለት አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013