ቆጮ በአብዛኛው በሀገራችን በደቡቡ ክልል በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍል ተወዳጅና የተለመደ የምግብ አይነት ነው። ምግቡም የሚዘጋጀው ከእንሰት ሲሆን ኃይል ሰጭ ከሚባሉ የምግብ አይነቶች ሁሉ በጣም የበለጸገ እንደሆነ ይነገርለታል። ነገርግን ምግቡን ለማዘጋጀት በጣም አድካሚና ሰፊ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፤ ማህበረሰቡ በሚፈልገው መጠንና ጥራት አዘጋጅቶ ለመጠቀም ይቸገራል።
ወጣት አለምነህ ተሻለ ይህን የማህበረሰቡን ችግር በቅርበት በማየቱ ለችግሩ አይነተኛ መፍትሄ የሚሆን የፈጠራ ስራ ይዞልን ብቅ ብሏል። እኛም ወጣቱን ስለፈጠራ ስራው አነጋግረነዋል።
ወጣት አለምነህ ተሻለ ተወልዶ ያደገው በሆሳዕና ከተማ ነው። ዋገበታ ቅድስት መስቀልና ሆሳዕና ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። የካቲት 25/67ና ዋቻሞ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ሀብትና በአካባቢ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2003 ዓ.ም አግኝቷል። የከፍተኛ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በሀገሪቱ በሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተቀጥሮ በመስራት ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ለመቅሰም ችሏል።
“አርሶ አደሩ የቆጮን ምርት በባህላዊና ኋላቀር በሆነ መንገድ በማዘጋጀቱ ከእንሰቱ ማግኘት የሚገባውን ያክል ምርት የማያገኝ ሲሆን፤ እንሰቱ የሚቆረጥበት፣ የሚጨመቅበትና የሚያደርቅበት ዘዴም በጣም አሰልቺና አድካሚ ነው። በመሆኑም ሴቶች ለማዘጋጀት በሚያደርጉት ውጣ ውረድ ለተለያዩ ችግርና እንግልት ይጋለጣሉ።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ « የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ፣አንዲት ነፍሰጡር እናት ወደ ኋላ ወድቃ ህይወቷ ያልፋል። በዚህም የሟቿ ልጆች በህይወት አባታቸው ባለመኖሩ የሟች እህት ከራሷ ልጆች ጋር ጨምራ ይዛ በማሳደግ ብዙ መከራና ችግር ስታሳልፍ በቅርበት ሁኔታውን አውቅ ነበር። ሁኔታውን በቅርበት ላየው ሰው፤ ለሰሚውም በጣም ልብ የሚነካ ነው። እኔም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የገጠሩ ማህበረሰብ ቆጮን ሲያዘጋጅ ከሚደርስበት እንግልት፣ድካምና ችግር በምን መንገድ መታደግ እችላለሁ? በዘመናዊ መንገድ የቆጮን ምርት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በቆጠበ መልኩ አምርተው ማግኘት የሚገባቸውን ምርት በምን መንገድ ማግኘት ይችላሉ? እያልሁኝ ሁሌም በአዕምሮየ አወጣና አወርድ ነበር፡፡
«በዚህም የመሰናዶ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስገባ፤ ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ሀሳብና እውቀት የማገኝበት የትምህርት መስክ ምን ሊሆን ይችላል ብየ ሳሰብ፤ ብቸኛው አማራጭ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ስለገባኝ ትምህርቴን በቴክኖሎጂውና በምህንድስናው የትምህርት ዘርፍ ልከታተል ችያለሁ»ሲል ለፈጠራ ስራው መነሻ የሆነውን በቁጭት ይናገራል። ።
«የከፍተኛ ትምህርቴን ከጨረስኩኝ በኋላ ይህን የማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችለኝ በተግባር የተደገፈ ልምድና ክህሎት ለማግኘት እና የተማርኩትን ጽንሰ ሀሳብ ወደተግባር ለመቀየር እንድችል በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መስራት ስለነበረብኝ፤ በግልገል ጊቤ ሶስት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክቶች በቢሮ መሀንዲስነት ተቀጥሬ በመስራት፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ህልሜ የነበረውን ፕሮጀክት ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችለኝን በተግባር የተደገፈ እምቅ እውቀትና ክህሎት ከነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ማግኘት ቻልሁኝ።
«ከዛም ከ2008ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ያክል ሙሉ ጊዜዬን በፕሮጀክቱ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ፤ ይህን የማህበረሰቡን ችግር የሚያቃልል የቆጮ ማጠቢያና ተረፈምርት ማጠራቀሚያ ማሽን ለመስራት ችያለሁ” በማለት ይገልፃል።
የፈጠራ ስራውን ከሰሩ በኋላ ብዙ ማካተት የነበረበትን ነገሮች በተግባር በማየቱ፤በተለያየ መንገድ ተጨማሪ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ሀሳቦችን በመጨመር የፈጠራ ስራውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል አሻሽሎ መስራት እንደቻለ ይናገራል።
“አሜሪካን አድቫንስመንት ኦፍ ሳይንስ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር በ134 የገበሬዎች ማሳላይ ጥናት አካሂዶ እንዳወጣው መረጃ፤ በአንድ ሄክታር በአማካይ10 ቶን የቆጮ ምርት ማግኘት ይቻላል። ይህን የቆጮ ምርት በባህላዊው መንገድ ቢመረት በሄክታር ወደ 144 የሚደርስ እንሰት ምንም ጥቅም ሳይሰጥ ይጣላል። የቆጮ ምርቱንም ለማዘጋጀት 40ሺ ያክል ሊትር ውሃ በየሰፈሩ ይባክናል። እንዲሁም ከአንድ ሄክታር የሚወጣውን ምርት ለማዘጋጀት የሚወስደው ጊዜና ጉልበት የትየለሌ ነው። በባህላዊ መንገድ ረዥም ጊዜ በመው ሰዱ፤ ቆጮው ተፈጥ ሯዊ ጣሙን አጥቶ ጥቅም ላይ ሳይውል የሚጣልበትና ሰዎችን ለበሽታ የሚያጋል ጥበት አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው።
ይህ የፈጠራ ስራ ጊዜን፣ ወጭን፣ ጉልበ ትንና ተፈጥሮ ሀብትን ቆጥቦ በአጭር ጊዜ ምርትና ትርፋማነትን የሚጨምር ነው። ማለትም በሰዓት 180 ኪሎ ግራም የቆጮ ምርትን የሚያጣራ ሲሆን፤ የተጣራው ውሃ መልሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ያስችላል። ተረፈ ምርቱንም መልሶ ለማዳበሪያነት እንዲውል በማድረግ ምንም የሚባክን የተፈጥሮ ሀብት እንዳይኖር የሚያስችል የፈጠራ ስራ ነው።
በምግብ ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ድርጅቶች በጥናታቸው እንዳረጋገጡት፤ እንሰት በሚሰጠው ምርት መጠን ከማንኛውም ተክል የተሻለ እንደሆነ በጥናታቸው አሳውቀዋል። ስለዚህ ይህ መሳሪያ ገበሬው ከእንሰት የቆጮ ምርትን ተፈጥሯዊ ጣዕሙንና ቃናውን በጠበቀ መልኩ በተፈለገው መጠንና ጥራት በማምረት የሚገባውን የምርት መጠን እንዲያገኝ በማስቻል፤ ከራሱ የምግብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማውጣት በገቢ ተጠቃሚም የሚያደርግ ነው። ከእንሰቱ አልሚ ምግብ በማዘጋጀት ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያስችላል። በአጠቃላይ የቆጮ ምርትን የማምረቱን ሂደት ቀላልና ምርታማ በማድረግ በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱና ለመቀንጨር የሚጋለጡ ህፃናት ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ የሚያስችልና የገበሬውን ድካምና እንግልት የሚያስቀር ፕሮጀክት ነው” በማለት የፈጠራ ስራው ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን ፋይዳ በመረጃ አስደግፎ ገልፆልናል።
« የቆጮ ዱቄትን ከሞሪንጋና ከአኩሪ አተር ጋር በመቀላቀል አልሚ ምግብ በማዘጋጀት በሀገራችን የሚታየውን በምግብ እጥረት ምክንያት የሚመጣውን መቀንጨርና የህፃናት ሞት ለመቀነስ የሚችል የፈጠራ ስራ በመስራት ላይ ነኝ። የፈጠራ ስራውንም በኢትዮጵያ አምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማስመዝገብ፤ የፈጠራ ስራው የሚዘጋጅበትን ሂደት በዝርዝር አዘጋጅቼ የባለቤትነት መብት ለማግኘት በሂደት ላይ ነኝ” ሲል ስለሁለተኛ የፈጠራ ስራው ያስረዳል።
“ይህን የፈጠራ ስራ ማህበረሰቡ በቀላሉ ሊረዳውና ሊያንቀሳቅሰው በሚችለው ቀለል ባለ ቴክኖሎጂና ቁሳቁስ የተሰራ ነው። ምክንያቱም የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች በጣም የተወሳሰቡና በቀላሉ ቴከኖሎጂውን ማህበረሰቡ ለመጠቀም የሚያዳግተው አይነት ከሆነ፤ ገበሬው መሳሪያውን ለመጠቀም ከመቸገር ባለፈ መሳሪያውን ለመጠቀም ፍላጎት አይኖረውም ማለት ነው። በመሆኑም ይህን የፈጠራ ስራ ከፍተኛ ወጭ በማይጠይቁና በቀላሉ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እንደ ባህርዛፍ፣ ጣውላ፣ ሽቦ፣ ላሜራ ቆርቆሮ፣ የፕላስቲክ ሴራሚክ፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የተሰራ ነው። ነገርግን የማምረቻ መሳሪያው በነዚህ በቀላሉ በአካባቢ በሚገኙ ከፍተኛ ወጭ በማይጠይቁ ቀሳቁሶች ቢሰራም ሳይበላሽ ለብዙ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። ማሽኑ ቢበላሽ እንኳን በቀላሉ በሀገር ውስጥ የመለዋወጫ እቃዎችን መስራት ስለሚቻል ምንም አይነት ለውጭ ምንዛሬ ችግር አያጋልጥም” በማለት የፈጠራ ስራው ከምን እንደተሰራ ገልፆልናል።
“ይህን የፈጠራ ስራ የቆጮ ምርት በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት በማድረግ፤ በተቋሞቹ መሳሪያው ዳብሮና ተሻሽሎ ተሰርቶ አንዱን መሳሪያ አምስት ሴት አርሶ አደሮችን በአንድ ለአምስት በማደራጀት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራን ነው። አንዱን ማሽን መቶ ሺ ብርና ከዛ ባልበለጠ ዋጋ እንዲዳረስ ለማድረግ ነው ያሰብነው። በዚህም ማሽኑን ወደገበያው ለማስገባት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመስራት ላይ ስሆን፤ በእንሰት ላይ ጥናትና ምርምር ከሚያደርግ አንድ ተቋም ጋር በትብብር ለመስራት በግሌ በመስማማቴ የፈጠራ ስራውን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል የግንባታ አሰራር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደስራ ለማስገባት በሂደት ላይ ነን።ፕሮጀክቱም በየዩኒቨርሲቲዎቹ እንደመነሻ ሀሳብ ተቀምጦ ጥናትና ምርምር እንዲደረግበት በማድረግ በትውልድ ቅብብሎሽ ተሻሻሎና ዳብሮ ተሰርቶ የህብረተሰቡን ችግር ከዚህ በተሻለ እንዲቀርፍ በማድረግ ላይ እገኛለሁ” በማለት የፈጠራ ስራውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተደረገውን ጥረት አብራርቷል።
«እኔ ማንኛውም አካል እገዛ አላደረገልኝም ብዬ ለመውቀስ አልፈልግም። ሞክሬ ያልተሳካልኝ ነገር ካለም በማንም ላይ ማሳበብ አልፈልግም። ዋናው ጉጉቴ የልጅነት ህልሜ ተሳክቶ ማየት ነው። ይህ ህልሜ ዛሬ ላይ እውን እንዲሆን አስተማሪዎቼ፣ አማካሪዎቼ፣ የጥናትና ምርምር ጽሁፍ የጻፉ ሰዎች፣ ከእኔ ጋር በፈጠራ ስራ የተወዳደሩ ወንድሞቼ ሁሉም የአስተሳሰብ አድማሴ እንዲሰፋ፣ እውቀትና ክህሎቴ እንዲያድግ እና በመረጃ እንዲበለጽግ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በሀሳብም በገንዘብም ስራዬ ተግባራዊ እንዲሆን አግዘውኛል።
«የፈጠራ ስራዬን ሌሎች እንዲማሩበትና እንዲመራመሩበት በማሰብ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ እንዳስተዋውቅ እድሉን ሰጥተውኛል፡፡
«ፕሮጀክቱ የረዥም ጊዜ እቅዴ በመሆኑ የፈጠራ ስራውን ለመስራት በስነ ልቦናም ሆነ በሚያስፈልጉኝ የተለያዩ ግብአቶች ቀድሜ ስለተዘጋጀሁኝ ስራውን በተሳካ ሁኔታ እንዳልሰራ ተግዳሮት የሆነብኝ ትልቅ ነገር አለ ብዬ አላምንም። ነገርግን ከአሁን በፊት በዘርፉ የተሰራ የፈጠራ ስራ አለመኖርና በቂ የጥናትና የምርምር ስራዎች አለማግኘቴ የበለጠ ስለ እንሰት አውቄ የፈጠራ ሰራውን በተሻለ መንገድ እንድሰራ አላስቻለኝም።
«የፈጠራ ስራውን ለመስራት የሚያግዙ የተለያዩ አለም አቀፍ ጥናቶችን ለማንበብ የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለማግኘቴ ስራውን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እንዳልሰራ አድርጎኛል። ቢሆንም ግን የገጠመኝን ችግር ተቋቁሜ የማህበረሰቡን ችግር ይፈታል ብዬ ያሰብኩት ስራ እውን ሆኖ በማየቴ ለኔ ከዚህ በላይ ስኬት የለም፡፡
«ወጣቱ ከድሀ ሀገርና ቤተሰብ ተወልዶ መንግስትና ቤተሰብ እርዳታ አላደረገልኝም የሚሉ እሮሮዎችን ሁሌም ያነሳል። እነዚህን የመሰሉ የተለያዩ ምክንያቶችን መደርደር ነገላይ የተሻለ እንዳንሰራራና የተሻለ ደረጃ እንዳንደርስ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ማነቆዎች ናቸው። ስለዚህ ይህ አይነት ደካማ አሰተሳሰብን አስወግዶ ሁሌም ጠንከሮ በመስራት ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ በችግር ተፈትኖ ያለፈ ዜጋ ለሀገራችን ያስፈልጋታል።
«መንግስት ጥናትና ምርምር የማድረግ አቅም ላላቸው ዜጎች የጥናትና ምርምር ተቋሞችን ክፍት ሊያደርግ ይገባል። በተለይ የተለያዩ የማሀበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች በሀገራችን እንዲሰሩ ከተፈለገ፤ በትምህርት የገፉ ሰዎች ለተተኪው ትወልድ ልምዳቸውንና ክህሎታቸውን በማካፈል መድረኩን ክፍት አድርገው ወጣቱ ትውልድ የራሱን የጣት አሻራ እንዲያኖር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
«በሀገራችን ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች የሚሰሩትን የመመረቂያ ጽሁፍ በማወዳደር የዓመቱ ምርጥ ጥናትና ምርምር በማውጣት ተማሪዎችን ማበረታታትና መሸለም ይኖርባቸዋል። እስካሁን ድረስ እንደዚህ አይነት አሰራር በተቋሞቹ ባለመኖሩ ሀገራችን በየዓመቱ ብዙ ተመራማሪዎችን እያጣች ትገኛለች።
«በሀገሪቱ የተሰሩ የተመረጡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወዳንድ ማዕከል መጥተው የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎች እነዚህን ጥናቶች በቀላሉ እንዲያገኙ በማስቻል የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዲሰሩ ቢደረግ ጥሩ ነው። መንግስት ያለምንም አድልዎ የተለያዩ የሳይንስ እና የቴከኖሎጂ ስልጠናዎችን ለወጣቱ እንዲያገኙ በማድረግ የተለያዩ ችግር ፈች የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሰሩ ማነሳሳት ይጠበቅበታል።
«በአጠቃላይ መንግስት የተማረው ኃይል በሀገሩ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለወገኑ ችግር ፈች የሆነ የፈጠራ ስራ እንዲሰራ ከአድልዎ የጸዳ ምቹ ሁኔታ፣ የስራ ቦታና ተቋም መፍጠር ይኖርበታል። ያለበለዚያ ግን በሀገራችን የሚፈልቁ ተመራማሪዎች እንደወትሮው ለምዕራባዊያኑ ሲሳይ ይሆናሉ» ሲል ለመንግስትና ለወጣቱ ኃይል ይበጃል ያለውን መልዕክቱን አስተላልፏል።
ጥር 24/2011
ሶሎሞን በየነ