የቱን?
ለውጥ የምንለው እንደ 1983 ዓ.ም አይነቱን በስልጣን ላይ የነበረውን ኃይል ሁሉ ጠራርጎ ወደ ወህኒ መወርወር ከሆነ እውነት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የለም። ለውጥ የምንለው እንደ አምባገነን መንግሥታት የቀደመውን አመራር በሙሉ ከምድር ማስወገድ ዓይነቱን ከሆነ ትክክል ነው ለውጥ መቼ አለና። ለውጥ የምንለው እንደ ዝምባብዌ ዓይነቱን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተመራውን ለውጥ ከሆነ እውነት ነው በኢትዮጵያ ለውጥ የለም።
ለውጥ የምንለው እንደ ግብጽ ጀኔራል ስልጣን ይዘው ሲያበቁ፤ ዘግየት ብሎ ደግሞ “ሲቪል ሆኛለሁ” በማለት ፕሬዚዳንት መሆንን ከሆነ እርግጥ ነው ለውጥ የለም። እንደ ጥቂት የአፍሪካ አገራትም ለውጥ የምንለው በምርጫ ስም ቅርጫ አካሂዶ ስልጣን ላይ መውጣትን ከሆነም ለውጡ ገና ነው። ለውጥ የምንለው ከተማ ተረብሾ፣ ንብረት ተዘርፎ፣ ሰው በአደባባይ ተገድሎ፣ ወታደሩ ከካምፕ ወጥቶ በጎዳና ሰፍሮ፣ ኢኮኖሚው ጋሽቦ መቶ ብር 10 ሳንቲም ሆኖ፣ ባንክም ባለባንክም ተዘርፎና ተገድሎ፤ ሚሊዮኖች አገር ጥለው ተሰድደው፣ ፖለቲከኞች ሁሉ ወህኒ ተወርውረው፣ ሚዲያው ታፍኖ የሚመጣውን ለውጥ ከሆነ እውነት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የለም።
ለውጥ የምንለው ባሰርንበት፣ በገረፍንበት፣ በገደልንበት፣ ዝርፊያን አይተን እንዳላየን ቸል ባልንበት አገርና መንግሥት መልሰን በገፍ ካልታሰርን፣ ካልተገረፍን፣ የተዘረፈውም ካልተወረሰ የምን መደመር? የምን ይቅርታ? ከሆነ ስሌቱ አዎን ለውጥ የለም። ለውጥ የምንለው በቀደመው መንገድ ብቻ መጓዝ ከሆነም እውነት ተብሏል ለውጥ የለም።
ለውጥማ አለ!
አዎን ለውጥማ አለ። በአገራችን የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው ለውጥ ከቅርብም ከሩቅም ያሉ አገራት ያደነቁት፤ በአገር ውስጥም በየከተማው እልፎች ያለቀስቃሽ ሰልፍ የወጡለት፤ እንኳንስ ወዳጅ ጠላትም ያጨበጨበለት ለአፍሪካ ሞዴል የሚሆን ለውጥ ነው። እንደ አገር ይቅር እንባባል፤ እንደመር ያለፈውን እንርሳ፤ የቂም በቀል ፖለቲካ በቃህ ይባል፤ ያለፈውን ለመርሳት ጊዜው አሁን ነው፤ በሚል መርህ የተጀመረውን ለውጥ አይንን ጨፍኖ “ለውጥ የለም” ማለት ምክንያታዊነት አይደለም።
እነሆ ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው እርካቡን ከጨበጡና ለውጡን መዘወር ከጀመሩ ዛሬ 300 ቀን ሞላቸው። እነዚህ 10 ወራት ወይንም 300 ቀናት የተስፋም የስጋትም ሆነው አልፈዋል። ተስፋው እንደ አገር ያጣጣምናቸው ድሎችን ስናስብ ነገም ይበልጥ ይሆናሉ የሚለው ነው። ስጋቱ ደግሞ መልካም ድሎች ይቀጥላሉ ወይንስ ይጨናገፋሉ የሚለውና በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በስፋት የሚታዩት መፈናቀሎች፣ የጸጥታውና ሰላሙ ጉዳዮች ናቸው። በግራም ይሁን በቀኝ እይታ አገሪቷ በለውጥ ምህዋር ውስጥ ገብታ መጓዝ ከጀመረች እነሆ 300 መዐልት እና 299 ሌሊት ተቆጥሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ 300 ቀናት ለ20 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮ-ኤርትራ የገነገነ የጸብ ግድግዳ ያለሸምጋይ የተናደበት፤ ከ20 ዓመት በላይ ልቡ በአገሩ መንግሥት ላይ ሸፍቶ የኖረው የዳያስፖራ ልብ የተማረከበትና ለመጀመሪያ ጊዜም የአገሩን መሪ አበባ ይዞ የተቀበለበት፤ አንድም ጋዜጠኛ በእስር ቤት የለም ተብለን እንደ አገር የተወደስንበት፤ በስም እንኳን የማይታወቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይቀር “ተፎካካሪ” ተብለው ተከብረውም ጭምር በቦሌ ገብተው አዲስ አበባ የከተሙበት፤ በየቤተ እምነቱ የነበረው የጸብ መጋረጃ ተቀድዶ አንድ የሆኑበት፤ በሽብርም በብርም ተከስሰው ማረሚያ ቤት ለከረሙ ሁሉ በሩ ያለ ገደብ የተከፈተበት፤ መንግሥት በግልፅ አሸባሪ ነን ብሎ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በምክር ቤት ያመነበትና ይቅርታ የጠየቀበት፤ በመንግሥት ሥር የተመዘበሩ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ እውነታው ተፍረጥርጦ የተነገረበት ሆነው አልፈዋል። እነዚህ እሰዬው የሚያስብሉ እርምጃዎች ስለሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመንግሥታቸው ምስጋና ይገባቸዋል። ለውጥማ አለ ማለታችንም ለዚሁ ነው!
ያለፉት 300 ቀናት አልጋ በአልጋ የሆኑና ድል ብቻ የተመዘገቡባቸው አይደሉም። ትልቁ ስዕል ድሉ ሆኖ እንጂ መንግሥትን የሚገዳደሩ ችግሮች እዚህም እዚያም ታይተዋል። በተለይም የሰላምና የፀጥታው ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ነው። የመንጋ ፍትህ፣ ዜጎችን ከኖሩበት ቀዬ በስህተትም በስሌትም ማፈናቀል፣ በውሃ ቀጠነ ሰበብ አደባባይ መውጣትና ንብረት ማውደም፣ የኑሮ ውድነትና የዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መስተጓጎል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ300 ቀናት ፈተናዎች ናቸው።
እነዚህን ፈተናዎችን በፍጥነት ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ላይ መንግሥት ባለፉት 300 ቀናት፤ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ ከልክ ያለፈ ትዕግስት አሳይቷል። ህዝቡም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምስል ወታደራዊ ዩኒፎርም እያለበሰ ሳይቀር ኮስተር ያለ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ሲወተውት ታይቷል። ይሄ መዘግየት መታረም እንጂ መደገም የሌለበት ስህተት ነው።
ምናልባትም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል መልኩ ዜጎች ይኖሩበት ከነበረው ቀዬ በብዛት የተፈናቀሉት አሁን ላይ ነው። ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ300 ቀናት ጉዞ አንድ እንከን ስለሆነ በፍጥነት መታረም አለበት። “ለውጥ ውስጥ ባለ አገር ላይ የሚያጋጥም ችግር ነው” ተብሎም ብቻ በቀላሉ መታየት የለበትም። የዚህ አይነት ችግሮች ስር ከሰደዱ አደገኝነታቸውን መተንበይ ዛሬ ቀኑ ዓርብ መሆኑን የመናገር ያህል ቀላል ነው። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኒያቸው ብሎም በየደረጃው ያለ አመራር ሁሉ በርትቶ መስራት ይገባዋል።
አገራዊ ለውጡን ከግለሰብና ከቡድን ጥቅምና ጉዳት አንጻር ብቻ እየመዘኑ “ለውጥ የለም” “ለውጥ አለ” ማለትም ተገቢ አይደለም። “እኔ የሌለሁበት ጸሎት በመንግስተ ሰማያት አይሰምር” አይነት አካሄድም መቆም አለበት። ሁሉም በልኩ ሁሉም በሚዛኑ ይታይ። ለውጡ ይቀጥል፤ እዚህም እዚያም የሚታየው ስርዓት አልበኝነትና ነውጥም በፍጥነት ይቁም።
ጥር 24/2011