ሃላፊነቱ የሁላችንም ነው !
ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረውን ፀረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በማስመልከት ከኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተላለፈ መልዕክት
የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ በሴቶችና ሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት የማስቀረት ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ እንዲውል እ.አ.አ በ1996 በወሰነው መሠረት ቀኑ በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም ታስቦ ይውላል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል አንዱ የሆነው ጾታዊ ጥቃት በዓለማችን ላይ ካሉትና በስፋት የተሰራጨ፣ ሥር የሰደደና ከፍተኛ ደረጃ አጥፊ የሆነ ግንባር ቀደም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚገልጹት ከሶስት ሴቶች መካከል አንዷ አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ በዓለም ላይ በሚታየው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ሰባ አንድ በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡
በእያንዳንዱ አገር፣ በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሆነ መደብ ከሶስት ሴቶች አንዷ በሕይወቷ ውስጥ የዚህ ጥቃት ሰለባ ትሆናለች፡፡ በ2012 መረጃ መሠረት ከሁለቱ ሴቶች ውስጥ አንዷ በትዳር አጋሯ ጥቃት የተነሳ ህይወቷ ያልፋል፡፡ ያሳቅቃል፡፡
በሃገራችን ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ጾታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በአስከፊነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በሴቶችና ሴት ልጆች የሚደርሰው ጥቃት መሠረቱ ሴቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው የተዛባ ቦታ ነው፡፡ የችግሩ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የነበረው ቀዳሚ ትኩረት ሰለባ ለሆኑትና ሕይወታቸውን ላዳኑት ድጋፍ መስጠት ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን አሰቃቂ ጥቃት ለማስቆምና ዳግም እንዳከሰት መረባረብን ይጠይቃል፡፡
ይህ ሃላፊነት የሁላችንም ነው፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆም ቆርጦ መነሳት ይጠበቅበታል፡፡ በያዝነው ክፍለ ዘመን ጾታዊ ጥቃትን ዝም ብለን ለማለፍ አንችልም፡፡ ዝምታ ቦታ የለውም፤ መናገር ያስፈልጋል፤ መናገርም አይበቃም፤ ወደ ተጨባጭ ተግባር መሸጋገርን ይጠይቃል፡፡
በዚህ ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው ለልጆቻችን የምንመኘው የተሻለ ነገን መፍጠር የሚቻለው? እንዴትስ ተደርጎ ነው ነገ በእርግጥም ዛሬን እንደማይመስል እርግጠኛ መሆን የምንችለው? ሁኔታው ብዙ ዋጋን እያስከፈለን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ለዚህም ነው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ያዘጋጀውና በሴቶችና ሴት ልጆች ላይ የሚፈፀም ጾታዊ ጥቃትን የማስቆም የ16 ቀናት ንቅናቄ ፕሮግራም በመላ አገራችን ዛሬ ዕለት የሚጀመረው፡፡ ማንኛውም የአስተዳደር እርከንና መላው ሕብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡
16ቱ ቀናት የችግሩን መጠን ከማስገንዘብ፣ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ጠቃሚነታቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ጥረታችን ዓመቱን በመሉ በእያንዳንዱ ቀን ሳይላላ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ምንም ዓይነት ጥረት ቢደረግ የሕብረተሰባችን ግማሽ የሆኑት ሴቶችና ሴት ልጆች ከሚያሸማቅቃቸው፣ ሕይወታቸውን ከሚቀጥፈው፣ አካላቸውን ከሚጎዳው፣ ከእድሜ ልክ ጭንቀትና አእምሮአቸውን ከሚያውከው ጾታዊ ጥቃት እስካለተላቀቁ ድረስ መራመድ ይቀርና ሙሉ በሙሉ በሁለት እግራችን ቆመናል ለማለት አንችልም፡፡
የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት