አስመረት ብስራት
ወጣትነት ጉልበት የሚሆንበት እድሜ ነው። የብዙ ነገር መጀመሪያ ቀሪውን የእድሜ ዘመናችንን መስሪያም እንደሆነ ይነገርለታል። ይህ ፍፁም ነፃነት የሚሰጠው እድሜ፣ ብዙ ነገር መሞከሪያም ነው። አለም ለወንዶች ሚዛኗን ባደላችበት ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ግን በአብዛኛው በወንዶች የመደገፍ ዝንባሌ ይታይባቸዋል።
በራሳቸው እንኳን ተፍጨርጭረው ከህልማቸው ጫፍ ለመድረስ ቢተጉም በተለያዩ ተፅዕኖዎች ውስጥ መደናቀፋቸው አይቀርም። ሌሎቹ ደግሞ ካለእድሜያቸው የቤተሰቦቻቸውን ችግር በሀላፊነት ለመሸከም በአፍላ ጫነቃቸው ላይ ይጭናሉ። ያኔ ነው እንግዲህ ያልጠናው የልጅ ገላ ሊሰበር፤ ለወደቅ፤ ሊንኮታኮት የሚዳዳው።
የዛሬ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሴቶች አመድ እንግዳችንም በአፍላ እድሜዋ የቤተሰቧን ችግር ለማቃለል ደፋ ቀና ከሚሉት መካከል የምትመደብ ሴት ናት። ገና በልጅነቷ የቤተሰቧን ችግር አላቅቅ ብላ ባላሰበችው የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ የገባች ከራሷ የህይወት ውጣ ውረድ ተነስታ የሌሎችን ሴቶች ችግር ለመቅረፍ ደፋ ቀና የምትል ሴት ናት።
ቀላ ደልድል ያለች ሳቂታ ሴት ናት። በእድሜ ወደ ጉልምስናው የተጠጋች ብትመስልም ሩህሩህ ፊቷ የውበት ፀዳልን የተላበሰ ነው። በምትሰራው ስራ ልበ ሙሉነት የተሰማት የምትመስል የስራዎቿን ውጤቶች ማለትም ከጎዳና የሰበሰበቻቸውን ሴቶች ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ናት። መሰረት በውቢቷ ባህርዳር ብትወለድም እድገቷም ኑሮዋም የሀገራችን መዲና አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ሆኗል።
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሴት ልጅ ተላልካ የቤት ስራ ሰርታ ተጫውታ ነበር ያደገችው። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አያለች ነበር አባቷ ወደ ወህኒ በመግባታቸው የተነሳ ልጆቿን ጥሩ ቦታ ለማድረስ ብቻዋን የምትንገላታ እናቷን የመደገፍ ሀሳብ የመጣላት። የእናቷ ችግርና ጉስቁልና አላስችል ቢላት ለችግር ማምለጫ መላ ብላ ያሰበችው ገና በመጀመሪያዎቹ የወጣትነት አመታት ወደ ትዳር መግባት ነው።
እሷ ባሰበችው ልክ ሳይሆን ነገሩ የተገላቢጦሽ ይሆንና ባገባች ልክ በአመቱ ባለቤቷም በራሱ ምክንያት ወደ እስር ቤት ይገባል። ያኔ ነው እንግዲህ ብቻዋን የቤተሰብ ሀላፊነትን በጫንቀዋ ተሸክማ ብቻዋን መታተር የጀመረችው። በብዙ መከራዎች ውስጥ በማለፏ የተነሳ የሌሎች ሴቶች ስቃይ የራሷ የሆነ ያህል ያማት ጀመር።
̋የተለያዩ ሴቶች መንገድ ላይ ልጆችን ይዘው ስመለከት የእኔ ህይወት ትዝ እያለኝ በጣም አዝን ነበር። ከእለታት አንድ ቀን እነዚህ ሴቶችን ሰብሰበ አድርጌ ህይወታቸውን የሚቀይር ስራ ብሰራ የሚል ሀሳብ በውስጤ ይመላለስ ገባ” ትለናለች ወይዘሮ መሰረት። በችግር መካከል መማርንና መለወጥን የዘወትር ተግባሯ ያደረገችው ወይዘሮ መሰረት የዘወትር ህልሟ እውን የሚሆንበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የመጀመሪያ ተቀጥራ የገባችበት የስራ ቦታዋ በቀይ መስቀል ውስጥ ሆነ። በዚህ ድርጅት ውስጥ የበጎ አድራጎት ስራን የመስራት እድል ሲገጥማት የተቸገሩ ወጣቶችን የመሰብሰብ ሀሳቧን ለማሳካት መስራት ጀመረች።
ያ ሀሳቧ ሞልቶ ድርጅቱ ሲመሰረት 25 ወጣት ሴቶችን ማለትም ያለ አባት ልጅ የሚያሳድጉ ወይም ያለእድሜያቸው የወለዱ ሴቶችን በመያዝ ነበር። በተጨማሪም ሀምሳ ህፃናትንም ከእናቶቻቸው ጋር በማድረግ የመጀመሪያው የእርዳታ ስራ ተጀመረ። ̋ስራው ሲጀመር ብዙዎች ችዬ የማሳካው አይመስላቸውም ነበር።” የምትለው ወይዘሮ መሰረት በየጊዜው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የተለያዩ ሴቶችን ህይወት የመቀየር ስራ ሰርታለች።
ወይዘሮ መሰረት ሴቶችን ጎዳና ሳይወጡ በቤታቸው እየሰሩ የሚለወጡበት ሀሳብ በማመንጨት የበርካቶችን ህይወት ቀይራለች፡፡ ልጆቻቸውን ማስተማሪያ ያጡትን በመደገፍ፣ ስራ በመስጠት የተሻለውን ነገር እንዲያዩ የሚደረግበትን ምቹ ሁኔታም ፈጥራለች።
የአሁኑን ፕሮጀክት ጎዳና ላይ ልጆችን ወልደው የሚያሳድጉትን በመሰብሰብ ህይወታቸውን ሲቀይሩ፤ የመቋቋም አቅም ላይ ሲደርሱ ወደ ትክክለኛ የህይወት መስመር የሚሸኙት እነዚህ ሴቶች የድሆች እናት የሆነችውን መሰረት እንደ ደረጃ ተጠቅመው ወደ ከፍታ ይራመዳሉ።
በበጎ አድራጎቱ ቅጥር ጊቢ በተገኘችበት ወቅት በርካታ ህፃናትና እናቶቻቸው በፀዳ ቤት ውስጥ የተመቻቸ ህይወትን በሚለማመዱበት ሁኔታ ሲኖሩ አግኝተናቸዋል። የተለያዩ የእደጥበብ ውጤቶችን እያመረቱና እየተዝናኑ ስለወደፊት ህይወታቸው ለማሰብ የሚችሉበት እድል አግኝተዋል።
ጎዳና ላይ የነበሩ እናቶች ከነልጆቻቸው በዚህ ቤት ገብተው ተረጋግተው ከገቡበት ሱስ ለመላቀቅም ይሞክራሉ። ስለ ወደፊት በደንብ ካሰቡ በኋላ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ በፈለጉት የትምህርት ዘርፍ ስልጠና አግኝተው የተወሰነ ማቋቋሚያ ገንዘብ ይዘው ወደ ህብረተሰቡ የሚቀላለቀሉበት ፕሮጀክት ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር በመተባበር የሚሰራ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ሀምሌ ወር ላይ ነው የተጀመረው። በፕሮጀክቱ አሁን ላይ ሀምሳ ሴቶች እየተገለገሉበት ሲሆን የታቀደው ግን አንድ መቶ ሰባ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የነበረ መሆኑን ወይዘሮ መሰረት ትናገራለች።
መንገድ ላይ እየወለዱ የምትጣልላቸውን ሳንቲም መለቃቀም የለመዱት እነዚህን ሴቶች በፍቃደኝነት ከጎዳና ላይ መሰብሰበ እጅግ ከባደ መሆኑን ነው ወይዘሮ መሰረት ያስረዳችው።
ከዚህ ቀደም በርካታ የተለያዩ አይነት ሴቶችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ነድፋ በርካቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራች መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ መሰረት በአሁኑ ፕሮጀክትም ሴቶቹ መንገድ ላይ እየወለዱ ጎዳና ላይ ህፃናትን እያሳደጉ ወደማይወጡበት አዘቅት ውስጥ እንዳይገቡ የተሻለ ህይወት ለመስጠት ያሰበ ነው፡፡ ሴቶቹ ይህ ፕሮጀክት በሚሰጣቸው የገንዘብና የሞራል ድጋፍ እውነተኛ ህይወታቸውን መምራት የሚያስላቸውን ስልጠና ወስደው እንዲቋቋሙ እያደረጋቸውም ይገኛል።
ህብረተሰቡ በተናጠል መንገድ ላይ ከመርዳት ወደ ዘላቂ ህይወት ለማስገባት የሚደረገው ጥረት ውስጥ በፍቃደኝነተ ከመሳተፍ ይልቅ የጎዳናው ነፃነት የሚገኘው ሳንቲም የእለት ከእለት ኑሮን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ደግነት በልክ፣ በስርዓት ቢሆን ሀገራችን ካለችበት ማህበራዊ ችግር ለማላቀቅ ጠቀሜታ ይኖረው ነበር የምትለው ወይዘሮ መሰረት የሁሉም ህብረተሰብ የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ ስራ መሆኑን ነው የገለፀችው።
̋የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተገባ ደግነት ለስራችን እንቅፋት ሆኖብል” የምትለው ወይዘሮ መሰረት ለሀገር የሚያስብ ሰው በየቀኑ የሚሰጠውን ሳንቲም ሰብሰብ አድርጎ በአንድ ቦታ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ በሚያሰጥ መልኩ ቢሰጥ መልካም መሆኑን መክራለች፡፡ እጅን ለምፅዋት መዘርጋት ሰዎች ስራ ሰርተው ኑሯቸውን እንዲመሩ፣ በላባቸው ጥረው ግረው እንዲበሉ ካለማስቻሉ በተጨማሪ በየመንገዱ ገንዘብ መስጠት የባሰ ዜጎችን የሀገር ሸክም እንዲሆኑ ማበረታታት ነው ትላለች።
ይህ የበጎ አድራጎት ስራ ሲጀመር በከባድ ችግር ውስጥ የነበረ ሲሆን አሁን በተወሰነ መልኩ ችግሮች መቃለላቸውንም ነግራናለች። ̋በፊት ቤት ተከራይተን ሰዎችን ስናገለግል የነበረ ሲሆን አሁን መንግስት ቃሊቲ አከባቢ ቦታ በመስጠቱ የሚረዱ ሴቶችን በራስ ግቢ ለመሰበሰብ መቻሉ አንድ እመርታ ነው።” ትላለች ወይዘሮ መሰረት። በሰዎች እርዳታ ላይ የተመረኮዘው ይህ በጎ ስራ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይበታል።
ፕሮጀክቱ ደግሞ ለአንድ እናት አንድ ሺ አምስት መቶ ብር በማሰብ የሚደገፍ ሲሆን ልጆች ያላቸው ሴቶችም ቢሆኑ የገንዘቡ መጠን በገቡት ሴቶች ልክ ብቻ የሚለቀቅ ስለሆነ ድጋፉ ውስን እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ፕሮጀክትም እንደቀድሞዎቹ የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትም እገዛቸውን ባያቋርጡ የሚል መልእክት አስተላልፋለች።
ስራው እጅግ ፈታኝ እንደሆነ የምትናገረው ወይዘሮ መሰረት ሴቶቹን አሳምኖና ለውጦ ወደ ትክክለኛ ማንነታቸው መመለስ መቻል እጅግ ከባድና ፈታኝ ነው። ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ታቅፈው የትላንት ታሪካቸውን ለመቀየር የቻሉትን መመልከት ደግሞ ትልቀ አቅም የሚፈጥር እጅግ ተስፋ ሰጪ ተግባር እንደሆነ ነው የገለፀችልን።
የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና በኮሮና ወቅት ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሰባሰበ የንፅህና መጠበቂያ፣ የምግብና የተለያዩ ድጋፎችን ለበርካታ ቤተሰቦች ድጋፍ ማድረጋቸውንም በማስታወስ «እያለኝ አልራብም» በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ለወገን የመድረስ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ወይዘሮ መሰረት አስረድታናለች።
መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ 1079 ወላጅ አልባ ህጻናትንና ለችግር የተጋለጡ 711 ሴቶችን እየደገፈ ሲሆን በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ረገድም አምስት ሺ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም በተለያዩ ጊዜያት ችግር ላይ ያሉ ሴቶችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ስራ ተጠናክሮ
የሚቀጥል መሆኑን ወይዘሮ መሰረት አስገንዝባለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013