በዛሬይቱ ዓለማችን በድንበር ይገባኛል፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በፖለቲካ ሽኩቻ፣ በስልጣን ጥምና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ግጭቶችን ማየት፣ ስለጦርነቶች፣ አንዱ አንዱን ሲያወግዝና ሲራገም . . . መስማት ለማንኛችንም እንግዳ ደራሽ ወግ አይደለም፤ የዕለት ተዕለት ክስተት እንጂ፤
በተለይ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች፣ የቅኝ ግዛት፣ አፓርታይድና ሌሎች ዓለም አቀፍ እኩይና ፀረ-ሰብዕ ክስተቶች ቀድሞውኑ ያደረሱት ቀውስና ውድቀት አንሶ ጦሳቸው በዚህም ሆነ በዚያ ዛሬም እቺኑ ዓለም ጤና እንደነሳት ይገኛል። ዛሬ በዚህ ፅሁፍ አማካኝነት የምንመለከተው የሩሶ-ጃፓን አታካሮም ከዚሁ የቀውስ ማዕቀፍ ውጪ አይደለም። ለምን ቢሉ የግጭቱን ሰበበ-ነገር በተመለከተ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ያ አሰቃቂው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነውና ነው፡፡
ሩሲያና ጃፓን ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸው ትብብርና አጋርነት፤ ባጭሩ ግንኙነታቸው ጠንካራና ለሁለቱም አስፈላጊ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ይህ ወዳጅነትና ግንኙነታቸው ሳይጠራና ውል ሳይኖረው፤ እንደተረበሸ እስካሁን አለ። የደሴት/ቶች “ይገባኛል/አይገባሽም” ጉዳይ እያወዛገባቸው 70 ዓመታትን መዝለሉ ለዚህ በቂ ማስረጃና ተጭባጭ ማሳያ ነው፡፡
ይህ ሩሲያንና ጃፓንን ከቃላት ወንጨፋ አልፎ ወደ ሚሳኤል ማምዘግዘግ ካልተሸጋገርኩ እያለ የሚንደረደረው ከ70 ዓመት የዘለለ ውዝግብ ሰሞኑን የሁለቱ አገራት መሪዎች በጉዳዩ ላይ ለመምከርና ‘’የመጨረሻ’’ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በሞስኮ ተገናኝተው መምከራቸውን ተከትሎ መነጋገሪያነቱን ያጎላው ሲሆን፤ በተለይ ዓለም በሰነቀው የስምምነት ተስፋ ላይ ውሃ የቸለሰ መሆኑ ነው፡፡
አወዛጋቢዎቹ ደሴቶች
በ“Kuril Islands” ጥቅል መጠሪያ የሚታወቁት አራት ደሴቶች ሁለቱም አገራት የየራሳቸውን ቋንቋ መሠረት በሚደረግ “ተቀራራቢ” በሚባል ደረጃ በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሯቸው ሲሆን፤ ዓለም ግን በእንግሊዝኛው በ“Kuril Islands” ስያሜ እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡
ከሩሲያ በስተደቡብ፤ ከጃፓን በስተሰሜን የሚገኙት እነዚህ ደሴቶች በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ በሩሲያ ግዛትና ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጃፓን የተዋጠላት ጉዳይ አይደለም፡፡ “Northern territories” የምትላቸው ደሴቶች ሙሉ በሙሉ የጃፓን ግዛቶች የነበሩ ሲሆን፤ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በወቅቱ በሩሲያ መንግሥት በግፍ የተወሰዱ ናቸው፡፡ በመሆኑም፤ እንደጃፓን ዘመንን የተሻገረ አቋም “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊመለሱ ይገባል”። ሩሲያም ይህን ዕውነት ልትቀበል የግድ ነው፡፡
ለ”ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ” ባዩ ፑቲን ይህ ጉዳይ ከቶም ሊነሳ የማይገባው፣ ከቀልድም በታች የወረደ ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። የ1855ቱን ዬናም ስምምነት/“Yenam Treaty” በታሪካዊና ትክክለኛ ሰነድነት የሚጠቅሱት የሩሲያው ፕሬዚዳንት፤ ጉዳይን ለሚያነሳባቸው ሁሉ ጣታቸውን የሚጠቁምበት ወደዚሁ “ትክክለኛ” የስምምነት ሰነድ ሲሆን፤ ጃፓንም ይህንኑ እውነት መለስ ብላ ልታጤነው ይገባል ባይ ናቸው፡፡ የውጪ ጉዳዩም ሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሮቻቸው ይህንኑ ሀሳብ የበለጠ አጠናክረው ሲገልፁት ነው የሚሰማው፤ እንደሚኒስትሮቹ አቋም ይህ ከቶም ሊሆን የማይቻል ጉዳይ ነው፡፡ ሰሞኑን ሲኤንኤንን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤
የሩሲያ የድንበር ኤጀንሲ እንደገለፀው፤ ይህ 199.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው አካባቢ ከጃፓን ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነጥብ ቦታ የለም። በመሆኑም ውዝግቡ ከጉንጭ ማልፋት የዘለለም ፋይዳ የለውም። “አራቱም ደሴቶች የማንም ሳይሆኑ የቻይና ናቸው” የሚሉት የመልክዓ-ምድር ጠበብት ውዝግቡ ላም ባልዋለበት . . . ነው ባይ ናቸው፡፡ በአካባቢው ምንጫቸው ከጃፓን የሆኑ የአይኑ ብሄረሰብ (Ainu Tribes) አባላት የሚኖሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓትም 19ሺህ ያህል ሕዝብም ይኖርበታል ሲል የዘገበው የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን፤ ነዋሪዎቹም ሆኑ አካባቢው የሩሲያ ነዋሪዎችና የሩሲያ ግዛት መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያሉት የብሄረሰቡ አባላትም ይህንኑ ነው ሲደግፉ የሚታዩት፤
የህዝብ አስተያየቶች
የደሴቶችን የይገባኛል ውዝግብ በተመለከተ በሁለቱም አገራት በኩል ያለው የህዝብ ስሜት ልዩነቱን እንደያዘ በተካረረ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የሁለቱንም አገራት ህዝቦች አስተያየቶች ያሰባሰበው ተቋም እንደገለጸው፤ በሁለቱም በኩል ገመዱ የተወጠረ ሲሆን ሁለቱም “የኔ ነው” ከሚለው አቋማቸው ሲላሉ አይስተዋሉም፡፡ ይህ ከሚዲያ አስተያየት ባለፈ ማህበራዊ ሚዲያን ተሻግሮ በጐዳና ሰልፍ እየተገለጸ ያለው የሁለቱም ህዝቦች ስሜትና አቋም በመሪዎቹ ላይ ውጥረት እስከመፍጠር እየደረሰ ይገኛል፡፡ ሩሲያውያን በመፈክሮች በታጀበ ሰልፋቸው “ደሴቶቹ የኛ ናቸው፤ አገራችንን የሚደፍር ካለ አንደራደርም፤ ፑቲን በዚህ ጉዳይ መደራደሩን በአስቸኳይ ያቁም . . .” እና መሰል አቋማቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ ያገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንኑ የህዝብ አቋም እየተጋሩት ይገኛሉ፡፡ እንደተቃዋሚውና የዴሞክራሲ ፓርቲው መሪ የከረረ አቋም፤ ሩሲያ ባስቸኳይ በአገር ጉዳይ ላይ መደራደሯን እንድታቆም፤ ፑቲንም ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለው ውይይት እንዲርቁ ከማሳሰብ ባሻገር፤ የሩሲያ ጦር ቶኪዮ በመሄድ ክንዱን ማሳየት አለበት እስከማለትም ደርሰዋል፡፡
በጃፓን በኩል ያለውም ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ ገንዘብ እስከማሰባሰብ ድረስ ተሄዷል፡፡ የአንድ ግለሰብ የቢዝነስ ተቋም ብቻ በሚሊዮን ዶላር መለገሱ ህዝቡ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ለመግለፅ በማሳያነት እየቀረበ ይገኛል፡፡
በተለይ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ “እየተለሳለሰ ነው፤ ህዝቡን በቃላት ይደልላል፤ ትክክለኛ አቋሙን ሲገልፅ አይሰማም፤ ስልጣኑን ለማራዘም እየተጠቀመበት ነው…” የሚለው አስተያየት ከፍተኛውን የህዝብ ስሜት የያዘ ሲሆን የጠ/ሚኒስትሩንም አስተዳደር እጅጉን እያሳሰበ ይገኛል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች የጃፓን ምሁራንም እያስተላለፉት ያለው መልእክትም ከዚህ የተለየ ሆኖ አልተገኘም። በተለይ የጠ/ሚኒስትሩን አቋም ከመጠራጠርና መሆንና መውሰድ ያለባቸውን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ውሳኔዎች ከመሰንዘር አኳያ የከረረ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ይገኛል፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች
ከደሴቶች ጋር በተያያዘ ያለው ውዝግብ በይፋ ታውቆ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከተጀመረ 70 ዓመታት ያስቆጠረ ይሁን እንጂ፤ አጠቃላይ እድሜው ሲሰላ ጊዜው ረጅም ነው (ከ1855ቱ “Borders of Shimoda Treaty” የሚጀምሩ አሉ)፡፡ በዚህ ረጅምና አታካች የውዝግብ ወቅት 10 የተለያዩ ስምምነቶች የተፈረሙ ሲሆን፤ በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ የሁለትዮሽ ውይይቶች፤ ድርድሮችና የመሪዎች የግንባር ለግንባር ንግግሮች ተካሂደዋል፡፡ አሁን ያሉት መሪዎች እንኳን 22 ጊዜ በግንባር ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ ተወያይተዋል፡፡
የተደረጉት የሰላም ስምምነቶችም ይህንኑ ስር የሰደደ ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ በነዚህ ስምምነቶች ወቅት ችግሮች የሉም ማለት ግን አይደለም፣ አሉ፡፡ በተለይ፤ በሩዝቬልት የተመራው የሳን ፍራንሲስኮ (1951) ስምምነት አሜሪካ የያዘችው /ለጃፓን ይገባል/ አቋምና እሱን ተከትሎ የሩሲያ ስምምነቱን አለመፈረም፤ ከሁሉም ጐልቶ የወጣና ሩሲያ የከረረ አቋም እንድትይዝ ያስገደደ መሆኑ በብዙዎች ታምኖበታል፡፡
በአሁኑ የሁለቱ መሪዎች የሞስኮ ውይይት (Jan.22/2019) ፑቲን ወደውይይቱ ከመግባታችንና ስለደሴቶቹ ከመነጋገራችን በፊት “ጃፓን የሩሲያን ሉዓላዊነትና ግዛቷን ልታከብርና እውቅና ልትሰጥ ይገባል” የሚል አቋም መያዛቸው የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
ከዚሁ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጋር በተያያዘ በተቋም ደረጃ አቋም የያዙ መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፤ የአውሮፓ ፓርላማ (ጁላይ 7/2005) ያሳለፈው “ለጃፓን ይገባል” ውሳኔ አንዱ መሆኑን ከሰነዱ መረዳት ተችሏል፡፡
ወታደራዊ ፍጥጫ
በደሴቶቹ ዘመንን የፈጀ የ”ይገባኛል ውዝግብ” ምክንያት የተነሳው አተካሮ ከቃላት መወራረፍ አልፎ ወደጦርነት እንዳይሸጋገር የተፈራበት ጊዜ ቢኖር አሁን ይመስላል፡፡ የሁለቱ አገራት በግንባር ከሚያደርጉት ውይይት፣ ድርድር፣ ስምምነት . . . በስተጀርባ ጦርነት እየደገሱ ነው የሚለን “The Diplomats” መፅሄት፤ በተለይ ሩሲያን በድርጊቱ ባለቤትነት፤ ጃፓንን ደግሞ በድርጊቱ ተቃዋሚነት በመመደብ በቀጣናው ውጥረት መንገሱን ይነግረናል፡፡ ዘ ዲፕሎማት ጉዳዩ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይራመድ ሦስተኛና ገለልተኛ ወገኖች ሊገቡበት ይገባል ሲልም ይመክራል፡፡
ይህ እሰጥ አገባ አዲሱ ዓመት /2019/ ከገባ ወዲህ በከፍተኛ የአነጋጋሪነት አጀንዳነቱ እያወያየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን “አወዛጋቢ” ሚና እየተጫወቱ ስለመሆኑም እየተነገረ ይገኛል፡፡ በተለይ የአሜሪካ ደሴቶቹ የጃፓን ናቸው በሚል አቋም መፅናት፤ እንዲሁም ከጃፓን ጋር ብቻ በመስማማት በአካባቢው የጦር ሰፈር ማቋቋሟ በአወዛጋቢ ምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ በሳን ፍራንሲስኮ የሰላም ስምምነት ላይ ባለመፈረም ያፈነገጠችውና ከጃፓን የወገነችው አሜሪካ በአካባቢው ወታደራዊ ኃይል ማሰማራቷ በሩሲያ በኩል የገጠመው ነገር ቢኖር የከረረ ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን፤ የዩ.ኤስ ጦር በአስቸኳይ ከአካባቢው ለቅቆ መውጣት ያለበት መሆኑንም የሚያሳስብ ነበር፡፡ አሜሪካ ግን የፓስፊክን አጠቃላይ ሰላምና ደህንነት ለመቆጣጠር ነው በሚል ሰበብ የሩሲያን አቋም ልትቀበለው አልፈለገችም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሩሲያ ከፍተኛ የምድር ጦርና የባህር ኃይል ተቋማትን (Military Barraks) በአካባቢው ያደራጀች ሲሆን፤ 3 ሺህ 500 ጦርም አስፍራለች፡፡ ምክንያቷንም “ደህንነቴን ለመጠበቅ” በማለት ትገልፃለች፡፡ ይህ ደግሞ ለጃፓንም ሆነ ለአሜሪካ ራስ ምታት በመሆን ውጥረቱን እያባባሰው ይገኛል፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ በውልብታ እንዳየነው ጉዳዩ ውስብስብና ረቂቅ ነው። በተለይ ጉዳዩ በኃያላን መካከል መሆኑ በቀላሉ እጅ የመሰጣጣት ሁኔታ ይኖራል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ሊቋረጡ የማይፈልጓቸው በርካታ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች አሏቸው፡፡ ግን ደግሞ ሁለቱም “የኔ ነው፤ ስትራቴጂካዊ አካባቢዬ ነው . . .” በሚሏቸው ደሴቶች እየተወዛገቡ ነው፡፡ የችግሩ ስፋት ሁለቱ ሀገራት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይደገምና ጥላቻ እንዲቆም የሚያደርገውን፤ አገራት የፈረሙትን የሰላም ስምምነት እንኳን እነርሱ እስካሁን ሳይፈራረሙ እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል፤ ብዙዎችንም ያሳዘነው ይሄ ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ለሚለው የተለመደውን “በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱት ይገባል” ከማለት ውጪ የተለየ ሀሳብ ለመሰንዘር ለብዙዎች ከበድ ያለ ጥያቄ ሆኗል። ማን ያውቃል፤ ቻይናም አንድ ቀን “በጂኦግራፊ ምሁራን ጥናት መሠረት ደሴቶቹ የኔ ናቸው” ብላ ትነሳ ይሆናል፡፡ መቼም ዘመኑ የ“ጠብ ያለሽ በዳቦ አይደል?”
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
ግርማ መንግሥቴ