የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 38ኛ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ በጅቡቲ ተካሂዷል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በጉባኤው ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎንም ከኢጋድ አባል አገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽና የተናጠል ውይይቶችን አካሂደዋል።
በውይይቶቹ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ እየሰወደች ያለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ዋነኛው ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያ እየወሰደችው ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ከሀገሪቱ ህልውና ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው የተገለጸበት ነበር።
የኢጋድ መሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ሕጋዊነት በመረዳታቸውና እውቅና በመስጠታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን በመግለፃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።
ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ሕግንና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተረዳ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን በማሰማራት ቀዳሚ ከሆኑት አገራት መካከል ነች። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው።
ለአብነትም በደቡብ ሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛቶች እንዲሁም በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ከክልሎቹ የፀጥታ መዋቅር ጋር ተባብራ በመስራት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህም የኢጋድ አባል ሀገሮች የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ስለከፈሉት መስዋዕትነትና አስተዋጽኦም ዕውቅና ሰጥተዋል።
የሱዳን ሰላም የኢትዮጵያም ሰላም ነው፤ የኢትዮጵያ ሰላም ለደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ሰላም ነው፤ በሶማሊያም ያለው ሰላምና መረጋጋት በቀጥታ የሚገናኝ ነገር ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም ልብ ሊባል ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕግ የማስከበር ዘመቻ በታሪክ አጋጣሚ መንግሥት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሀገር ያስተዳደረውን እና ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንዲሁም ጅምላ ጭፍጨፋ የፈጸመውን ጽንፈኛ ቡድን መስመር ለማስያዝ እና ሕግና ሥርዓትን ለማስጠበቅ የተደረገ ነው።
ይህ ቡድን ደግሞ በሥልጣን ዘመኑ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የራሱን ቡድኗዊ ፍላጎት ለማሳካት በየኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቀማት ውስጥ የሰገሰጋቸው ቅጥረኛ ዲፐሎማቶች ነበሩት። እነዚያ የዲፕሎማሲ ካባ የለበሱ ሰዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ላይ አሳሳች ዲፕሎማሲያቸውን ለመጫን ጥረት አድርገዋል። እነዚህ አሳሳች ዲፕሎማቶች መንግሥት እየወሰደው ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ የጦርነት መልክ እንዲይዝ ለማስመሰልም ሙከራ አድርገዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያላ ት ተደ ማጭነት ከፍተኛ በመሆኑ ውሃ ሳይዝ ቀርቷል ።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የውስጥ ጥንካሬዋና ሰላሟ ለጎረቤቶቿ ሰላምና ደህንነት ትልቅ ትሩፋት እንደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያ ሰላም በሆነችባቸው ጊዜያት ብቻ ሳይሆን በውስጧም አለመረጋጋት ሲኖር የጎረቤቶቿ ደህንነት ያስጨንቃታል። ከባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በፊት ኢትዮጵያን ሲመራ የነበረው መንግሥት ሲከተል የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት የነፈገ ከመሆኑም ባለፈ ሀገራትን በጠላትነት በመፈረጅ የዘለቀ በመሆኑ በቀጣናው አለመተማመን እንዲሰፍን ተሰርቶበታል።
ነገር ግን ለውጡን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ማሻሻያ ተደርጎበታል። በዚህም ፖሊሲው ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት ከመስጠት በዘለለ ቀጣናዊ ትስስር እንዲኖርና እንዲጠናከር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላት ተፅዕኖ ከፍ እንዲል ያደረገው አንዱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ምንጩ ከውስጥ ችግሯ ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራትን ችግር ያገናዘበ ሆኖ እንደገና በመቀረፁ ነው።
ፖሊሲው ከዚህ ቀደም በጎረቤት ሀገራትም ሆነ በውስጥ የተቀሰቀሱ ግጭቶችን በማርገብ ረገድ መንግሥት ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ከመሆኑ ባለፈ ትልቅ ድልም እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል።
በህወሓት ጁንታ ላይ የተካሄደው ዘመቻም የሕግ የበላይነትን በማስከበር፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በማስጠበቅ ሀገራዊ ግብ ያነገበ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። ይህም የሀገሪቷን ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት ከማስቀጠል ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም ሰላምና መረጋጋት ሚናው ከፍ ያለ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ ለሌሎች አፍሪካውያን ወገኖች ሰላምና መረጋጋት የሚቆረቆር ሰራዊት የገነባች ሀገር በመሆኗ ከዓለም አቀፉ የሰላም አስከባሪዎች ጋር በጋራ በመስራት የራሷንም ሆን የጎረቤቶቿን ሰለምና ደህንነት ታስከብራለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2013