አዲስ አበባ፡- በቅርቡ በመንግሥትና እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መካከል በአምቦ በተደረገው ስምምነት መሠረት እርቁን ተግባራዊ ለማድረግ የተዋቀረው የቴክኒክ ኮሚቴ ሥራውን በተግባር መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የእርቁ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት አቶ ጀዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ትናንት ማምሻውን ለመገናኛ ብዙኃን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚቴው የእርቁን ተግባራዊነት ለማሳካት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና ከመንግሥት ጋር በመወያየት አስፈላጊው ትብብር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በእስካሁኑ ሂደትም ተስፋ ሰጭ ስራዎች መኖራቸውን በመጠቆም በ20 ቀናት ውስጥ የኦነግ ሰራዊት ወደ ካምፕ እንደሚገባና መንግስትም ለዚህ ድጋፍ እንደሚያደርግ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴው ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በተቀሩት ቀናት ውስጥ በተመረጡ ስምንት ቦታዎች በመዘዋወር ሠራዊቱን በማነጋገርና ቀጣይ ሰላም እንዲረጋገጥ ይሰራል፤ ለሰራዊቱም አቀባበል ይደረግለታል ብሏል፡፡
በመግለጫው፤ በተለይ እርቁ ተግባራዊ እየተደረገ ባለበት ወቅት በመንግሥትና በኦነግ በኩል የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉና ግጭት አላስፈላጊ በመሆኑ ኮሚቴውም ጉዳዩን በትኩረት በማየት እርቁንና ስምምነቱን ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በጫካ ውስጥ የሚደረገው ብቻ ሳይሆን በሚዲያው በኩል የሚታየው ግጭትም መቆም እንዳለበት አሳስበው እርቁ ከተፈጸመ ወዲህ ሚዲያዎች ነገሩን ለማብረድ እየተወጡ ያለውን ሚናም አድንቀዋል፡፡ ሁለቱንም ወገን በማወያየት ነገሩን የማለዘብ ሥራው ቀጣይነት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም በአምቦ ከተማ በተዘጋጀ የእርቅ መድረክ የኦዴፓ እና የኦነግ አመራሮች፣ አባገዳዎች የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም አካላት በተገኙበት በመንግሥትና በኦነግ መካከል የእርቅ ስነስርዓት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
አዲሱ ገረመው