አስመረት ብስራት
ዶክተር ዳዊት ከበደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና የውስጥ ደዌ የሳንባና የፅኑ ህክምና ስፔሻሊሰት ሀኪም። ላለፉት ስምንት ወራት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የኮቪድ ህክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ኮቪድ ከቁጥጥራችን ውጭ እንዳይወጣ በሽታው ሲጀመር የነበረውን አይነት ጥንቃቄ ህብረተሰቡ ማስቀጠል አለበት ይላሉ። በተለይም በአዲስ አበባ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ በመሆኑ ቸልተኝነቱ እንዲያበቃ አደራ እያሉ ስለቫይረሱ እንዲህ ነግረውናል።
ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ 19 ምንድነው?
ኮቪድ ሳርስ ኮቭቱ በሚባል ቫይረስ ምክንያት የሚመጣ የበሽታ አይነት ነው። ሳርስ የሚባሉ ቫይረሶች በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰቱ ቆይተዋል። እስከዛሬ ሰባት የሚሆኑ የሳርስ ቫይረስ አይነቶች በዓለማችን ተከስተዋል። ኮቪድ የመጣውም ከዘሁ የሳርስ ዝሪያ ውስጥ ሳርስ ኮቭቱ የሚባል ነው። ይህ ቫይረስ የሚለየው በጣም ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በመያዘ ነው። ከተያዘው ሰው ወደ ሌሎች የመተላለፍ እድሉ ከሌሎች የሳርስ አይነቶች ጋር ሲነፃፀር በጣም ሰፋ ያለ ነው።
የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡ በሽታው በጠናባቸው ታማሚዎች ላይ ደግሞ እንደ ሳንባ ምች፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚያሳይ ሲሆን የኩላሊት ስራ ማቆምና ሞትን ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው።
ምልክቶች ምንድናቸው?
የኮሮና ቫይረስ ሁለት ዋነኛ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ወደ ትንፋሽ ማጠር ይወስዳሉ። ደረቅ ሳል ሲባል በጣም ጠንካራ የሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ነው። ከፍተኛ ትኩሳት የሚባለው ደግሞ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ37.8 ዲግሪ በላይ ሲሆን ነው። ይህ ትኩሳት ሰውነት እንዲግል ወይም ደግሞ ከፍተኛ ብርድና መንቀጥቀጥ እንዲሰማን ያደርጋል።
በተጨማሪም ራስ ምታትና ተቅማጥ አንዳንድ የበሽታው ታማሚዎች የሚያሳይዋቸው ምልክቶች ናቸው። የማሽተትና የመቅመስ አቅም ማጣትም ምልክቶች ሲሆኑ በአብዛኛው ሳርስ ኮቭቱ የልብና የኩላሊት ችግሮችን ማስከተሉን ለመገንዘብ ተችሏል። ይህ ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ በኋላ አብዛኛው ሰው ምልክት ያልታየበት ነው።
ይህም የታወቀው ምልክት ባይተይባቸውም ከቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የተገናኘ ሰውን የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ ለማድረግ የመመርመር ስራ ተሰርቶ ነበር ያን ጊዜ ያለምንም ህመምና ምልክት በሽታው ይዞ ሊለቃቸው ይችላል። በምርምሩም 80 በመቶው በሽታው በደሙ ውስጥ ኖሮ ምንም የህመም ምልክት ያልታየበት ነበር። የተቀሩት ደግሞ በከባድ ህመምና ሞት ውስጥም የነበሩ ናቸው።
ህክምናው ምን ይመስላል?
አሁን በሆስፒታሎች እየተሰጠ ያለው ህክምና በከባድ የህመም ደረጃ ያሉትን ብቻ ነው። በህመሙ ከተያዙት ሆስፒታል መሄድ የሚያስፈልጋቸው ከ10 በመቶ በታች ናቸው። በእድሜ የገፉ ሰዎችና የተለያየ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች ሆስፒታል መሄድ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ቤት እንዲሆኑ ይመከራል።
በተለይም የህክምና መስጫ ተቋሞች ሁሉንም ሰው ማስተናገድ በማይችሉበት ወቅት ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ እንደሚደረግ መደረግ ይኖርበታል። ቤታቸው ሆነው እንዲያገግሙ የሚጠበቁ ሰዎች ሌላ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸው ለራሳቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንዲያደርጉ ይመከራል። ትኩሳት እና ሳል የሚያስታግስ ነገር በቤታችን ማድረግ ሀኪሞች ላይ የሚፈጠረውንም ጫና ይቀንሳል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ
በአገራችን አሁንም ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። ̋ኮቪድ የለም ለምትሉ ከኛ ከህክምና ባለሙያዎቹ የበለጠ የሚመሰክር አይገኝምና በየቀኑ ከምንመለከተው ስቃይ ራሳችሁን በአግባቡ በመጠበቅ ገላግሉን ” ይላሉ።
ፅኑ ህሙማን ተለይተው የሚታከሙበት ክፍል አይሲዩ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። እዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ለመተንፈስ እንዲረዳቸው ኦክስጅን ይሰጣቸዋል። ቬንቲሌሽን የተሰኘው ቁስ የሚገጠመው በጣም ለታመሙ ሰዎች ብቻ ነው።
መሣሪያው በርከት ያለ ኦክስጅን ለታማሚው ያቀርባል። ምንም እንኳን ይሄ ማሽን ፅኑ ህሙማንን በመርዳት ረገድ የማይናቅ ሚና ቢጫወትም አሁን ግን በሀገራችን የኮቪድ ህክምና እየሰጡ የሚገኙ የህክምና ተቋማት በሙሉ ይህ መሳሪያ ተይዟል።
ሌሎችም ይህን ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ። የፅኑ ህሙማን ደረጃ ውስጥ ከገቡ ሰዎች አብዛኞቹ የህይወት ማለፍ ይገጥማቸዋል። የጤና ሚኒስትሯም እንዳመለከቱት ፅኑ ህሙማንን የማከም አቅም ያጠረው በርከታ ተማሚዎች በመኖራቸው መሆኑን አመልክተዋል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ተገቢውን ነገር ከማድረግ መቦዘን የለበትም።
ምንም እንኳን በሽታው የተፈራውን ያህል የሰው ህይወት ባያጠፋም የሞት ምጣኔ ዝቅ ያለ ቢሆንም ወትሮም በቂ ህክምና የማዳረስ ጉዳይ ራስ ምታት የሆነባት ሀገራችን ወረርሽኙ ከዚህ በበለጠ ቢከሰት ምን ሊመጣ እንደሚችል ሰው መገመት ይኖርበታል።
መደረግ ያለበት ጥንቃቄ
ራስን ከዚህ ወረርሽኝ ለመጠበቅ የበሽታው ምልክቶች ካለባቸው ሰዎች መራቅ፣ ቢሚያስነጥሱና በሚያስሉበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ ከሌሎች ሰዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅና እና ከማህበራዊ ግንኙነቶች ለጊዜው መራቅ ያስፈልጋል። እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥንቃቄዎች በማድረግ እራስን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የቫይረሱን ስርጭትም ለመግታት የሚረዳ ነው። ካልሆነ ግን የቫይረሱ ስርጭት ጠንካራ የጤና ሥርዓት የዘረጉትን ያደጉ ሀገሮች ሳይቀር የሚያሽመደምድ ነው።
በአጠቃላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ልክ ቫይረሱ መኖሩ የተሰማ ጊዜ ያሳየውን አይነት የጥንቃቄ ሁኔታ አጠናከሮ መቀጠል ካልተቻለ ቀላል የማይባል የሰው ህይወት ሊያሳጣ እንደሚችል ዶክተር ዳዊት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013