የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን የድንበርና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅ የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም”_ በማለት በክልሉ ተግባራዊ እንዳይሆን በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ማስተላለፉ ኢ-ህገመንግስታዊ መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡ የክልሉ ምክር ቤቱ በበኩሉ፤ አዋጁ ህገ መንግስቱ በህጋዊ መንገድ ሳይሻሻል፣ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በአዋጅ የሚሽር፤ በክልሎች ጣልቃ ገብቶ መብታቸውን የሚቃረን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን የሚነጥቅ ነው፡፡ የድንበርና የማንነት ጉዳይ በህገመንግስቱ ተፈትቶ ሳለ፤ የድንበር ኮሚሽኑ መቋቋሙ ትርጉም የለውም፡፡ በፌዴራልና በክልል መንግስታትም መካከል ያለውን የስልጣን ከፍፍል የሚያደፈርስና በክልሎች መካከል መቃቃርን የሚፈጥርም ነው ሲል ይገልጻል፡፡
የትግራይ ክልል ምክር ቤት የተጠቀሱትን ምክንያች በማቅረብ አዋጁ በትግራይ ክልል ተግባራዊ እንዳይሆን ወስኗል፡፡ የፌዴሬሸን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበትም ጠይቋል፡፡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚም በህገ መንግሥቱ ላይ የተፈጸመውን ጥሰት ትርጉም እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እንዲያቀርብ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
የህግና የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ብረሃነ መስቀል አበበ እንደሚሉት፤ የክልሉ ምክር ቤት አዋጁ በክልሉ ተግባራዊ አይሆንም ሲል ያስተላለፈው ውሳኔ ህገመንግሥቱን የሚጻረር ነው፡፡ በህግ ቅደም ተከተል የፌዴራል ምክር ቤትን አዋጅ በክልል ምክር ቤት ውሳኔ ተግባራዊ አይሆንም በማለት ውሳኔ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ አዋጁ ህገመንግሥቱን የሚጻረር እና የክልልን ስልጣን የሚነጥቅ ከሆነ፤ ክልሉ ለፌዴሬሸን ምክር ቤት አጣሪ ጉባኤ ጥያቄውን በማቅረብ ውሳኔ ማሰጠት ይችላል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እሰኪሰጥ ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አዋጅ የመፈጸምና የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህግና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ አቶ ሙልዩ ወለላው፤ የአዋጁ ዓላማ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ህዝብ ሀሳቡን እንዲሰጥ በማድረግ የአስተዳደር ወሰንን፣ ከማንነት ጋር የተያያዘ ግጭትን አጥንቶ ለፌዴሬሸን ምክር ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች፣ለመንግሥትና ለህዝብ ማቅረብ ነው፡፡ ተግባርና ስልጣኑም በህገ መንግሥቱና በሌሎች ህጎች ለፌዴሬሸንም ሆነ ለክልሎች የተሰጠው ስልጣን እንደተጠበቀ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች፣ የፖለቲካ ቡድኖችን፣ ባለድርሻ አካላትንና ህዝብን በማሳተፍ ጥናት አድርጎ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብም ኃላፊነቱ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም አዋጁ ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚያጋጨው ነገር የለም ይላሉ፡፡
ህገ መንግሥቱ ተጣሰ የሚባለው በተግባር ሲጣስ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በአዋጁ የተሰጠው ኃላፊነት ጥናት አድርጎ ሀሳብ ማቅረብ የሚል ነው፡፡ ኮሚሽኑ ጥናት አድርጎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማይስማማበት ከሆነ የመጨረሻን ውሳኔ የሚሰጠው ምክር ቤቱ ስለሆነ ውድቅ ማድረግ ይችላል፡፡ እናም በዚህ አዋጅ ለፌዴሬሸን ምክር ቤት በህገመንግሥቱ አንቀጽ 48፣ 84 እና 62 የተሰጠው ኃላፊነት አንዱም አይነካም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ባለሙያው አያይዘውም፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ህገ መንግሥቱን ይጥሳል ብሎ ካመነም የውሳኔ ሀሳብ ማሳለፍ፣ መወያየት ሳያስፈልገው ሂደቱን ጠብቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡ አሁን ግን ምክር ቤቱ አዋጁ በክልሉ ተግባራዊ አይሆንም ማለቱ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ በህገመንግሥቱ አንቀጽ 74 እና 77፤ እንዲሁም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠውን ኃላፊነት የሚከለክል መሆኑንም ያመላክታሉ፡፡ ይህም ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚጻረር ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሙልዩ፤ እንደሚሉት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች አገሪቱን በመኖርና ባለመኖር መካከል አድርገዋታል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በጋራ ከመስራት ይልቅ እንቀበላለን አንቀበልም ማለት ተቀባይነት የለውም፡፡ ከመሸሽ ይልቅ ወደ ጨዋታ ሜዳ ገብቶ ትክክለኛ አለመሆኑን ማሳየት ነው የሚገባው፤ ለዚህም አዋጁ ሁሉንም የሚያሳትፍ ሜዳ አለው፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት በበኩላቸው፤ የሚቋቋመው ኮሚሽን የአማካሪነት ሚና ኖሮት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሚና አልተነካም ማለት ነው፡፡ የድንበርና የማንነት ጉዳዮችን በሚመለከት የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ እናም ኮሚሽኑ ያጠናውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፤ ምክር ቤቱም ከፈለገ ይጠቀምበታል፡፡ ካልፈለገም አይጠቀምበትም፡፡
አያይዘውም፤ ኮሚሽኑ ውሳኔ መስጠት እንደማይችል አዋጁ ግልጽ አድርጓል ያሉት ባለሙያው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቱ እነዚህ ችግሮች እልባት እያገኙ እንዳልሆነ የተገነዘበው አስፈጻሚው አካል አገሪቱን ለማስተዳደር ስለተቸገረ በራሱ በኩል የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማቅረብ የሚያግዘውን ተቋም ቢመሰርት የሚከለክለው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አዋጅ ሕገመንግሥታዊ አይደለም የሚያሰኘው ምክንያት የለም ማለት ይቻላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ክልሎቹ ተስማምተው ነጻና ገለልተኛ ድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወሰናቸውን ስላልለዩ ወይም ደግሞ ወሰናቸውን ለይቶ የሚያሳውቅ ኮሚሽን ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ባለመወሰኑ ቀድሞ ያልተሠራውን ተግባር የሚሠራ ኮሚሽን ቢቋቋም ለአገር ይጠቅማል ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
አጎናፍር ገዛኸኝ