ከህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚቀርቡባቸው የህክምና ተቋማት ውስጥ አንዱ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ከተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ወደ ሆስፒታሉ የሚጎርፉ ታካሚዎች ቁጥርም ቀላል ባለመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችም የዚያኑ ያህል በርካታ ናቸው፡፡
በቅርቡ የጤና ሚኒስቴር የ2011 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህፃናት ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥን የተመለከተ ነው ፡፡
ከህፃናት ድንገተኛ ህክምና አገልግሎትና ባጠቃላይ በሆስፒታሉ ከሚሰጡ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች በተደጋጋሚ በሚነሱ ቅሬታዎች ዙሪያና ቅሬታዎቹን ለመፍታት እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሆስፒታሉ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረሕይወት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በቀን ከ15 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት ፈልገው ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፡፡ በሃገሪቱ ከሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል ከፍተኛ የታካሚዎች ፍሰት የሚታይበትና አዳዲስ ታካሚዎቹ በየእለቱ የሚመጡበት ነው፡፡ በአመትም አስከ 500 ሺ የሚጠጉ ህሙማን በሆስፒታሉ ይስተናገዳሉ፡፡
ተገልጋዮች ወደሆስፒታሉ ሲመጡ በሌሎች ተቋሞች የሚገኙ መደበኛና በተቋሙ ብቻ የሚገኙ መደበኛ ያልሆኑ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሆስፒታሉ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ቢሆንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና ይበዛበታል፡፡ አገልግሎቱ ከስኬታማነት አንጻር የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን በአነስተኛ ክፍያ ለህብረተሰቡ ከመስጠት አኳያ ሆስፒታሉ ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም የካንሰር ህክምና አገልግሎት በዚሁ ሆስፒታል መጀመሩ እንደ አንድ ስኬት ይቆጠራል፡፡
ህክምናው በሆስፒታሉ ብቻ የሚሰጥ ከመሆኑ አኳያ በርካታ ታካሚዎች ወደዚሁ ሆስፒታል አገልግሎቱን ፈልገው ስለሚመጡ በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጫና ይታያል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከተገልጋዮች ቅሬታዎች ያቀርባሉ፡፡ የሁሉንም ፍላጎት እኩል ማሟላት ደግሞ አይቻልም፡፡
በስታንዳርዱ መሰረት አንድ የህክምና ተቋም ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የአለም ጤና ድርጅት አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ያላት ሃገር ብትሆንም ለህዝቡ ቁጥር የሚመጥን የጤና ተቋም በበቂ ሁኔታ አልተገነባም፡፡ በዚህም ምክንያትም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ከተገልጋዮች ይነሳሉ፡፡
በሆስፒታሉ የልብ ህክምና በመደበኛ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ አገልግሎቱ መሰጠት ከተጀመረ አንስቶም 530 ሰዎች የልብ ህክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ አገልግሎቱ ለነዚህ ታካሚዎች ሲሰጥ ከጥቂት ሰዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ ህክምናው የተደረገላቸው ደረታቸው ሳይከፈት አለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ህክምና መሳሪያዎችን በመጠቀም ነው፡፡
ልክ እንደ ካንሰር ህክምና አገልግሎት ሁሉ የልብ ህክምና አገልግሎትም አሁንም በቂ አይደለም፡፡ አገልግሎቱ በጣም ውድ ከመሆኑ አኳያም በሚፈለገው ልክ ለመስጠትም በቂ አቅም የለም፡፡ ከልብ ህክምና ጋር በተያያዘ የአገልግሎት ውስንነት በመኖሩ ተገልጋዩን ሊያማርር ይችላል፡፡ ሆኖም በአነስተኛ ዋጋ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠበት ያለ ሆስፒታል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ከህክምና አገልግሎቱ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በሆስፒታሉ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ተገልጋዮች ህክምና ለማግኘት ወረፋ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ችግር እንዳለም ሆስፒታሉ ያውቃል፡፡ አቅም በፈቀደ መልኩ መፍትሄ ለማምጣትም የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ሆስፒታሉ በዋናነት ስራው ለህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎት መስጠት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአመት ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ያገለግላል ሲባልም ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የደሃ ደሃ የሆነና ለአገልግሎቱ የመክፈል አቅም የሌለው ነው፡፡ ሆስፒታሉ ትርፍ የሌለው በመሆኑና በከፍተኛ ጫና አገልግሎቶችን እየሰጠ ከመሆኑ አኳያ ተገልጋዩ በአገልግሎት አሰጣጥ ቢማረር አይደንቅም፡፡
ቀደም ሲል ታካሚዎች ካርድ ለማውጣት በሌሊት ወደሆስፒታሉ መጥተው ወረፋ ይይዙ ነበር፡፡ ካርድ ካወጡም በኋላ የህክምና አገልግሎቱን በቶሎ አያገኙም፡፡ በካርድ መጥፋት ምክንያት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩም ቆይተዋል፡፡
ይህንን ችግር ታሳቢ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ የዲጂታል ካርድ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በወረፋ ምክንያት የሚኖረውን የታካሚ እንግልት ቀንሷል፡፡ የታካሚዎችን የቀጠሮ ህክምና በተመለከተም የህክምና ቀጠሮ በቀን እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡ ሁለት ቀለም ባለው ኮድ አማካኝነት የቀጠሮ ህክምና አገልግሎቱ ጥዋትና ከሰአት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ይህም በአንድ ቀን በቀጠሮ ለመታከም የሚመጣውን የታካሚዎች መጨናነቅ ለመፍታት አስችሏል፡፡
የህፃናት ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የሆስፒታሉ የህፃናት ህክምና አገልግሎት በተደራጀ መልኩና ባለሞያዎች በበቂ ሁኔታ ተሟልተውለት ህክምና የሚሰጥበት ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ሆስፒታል ውጪ በሀገር ውስጥ በዚህ መልኩ በስፋት ተደራጅተው አገልግሎት የሚሰጡ የህፃናት ህክምና ተቋማትም የሉም፡፡
ከሃገሪቱ ህዝብ 40 ከመቶው ህጻናት ይሆናሉ ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ በቂ የህፃናት ህክምና ተቋማት ባለመኖራቸው አገልግሎቱ በሚፈለገው ልክ እየተሰጠ አይደለም፡፡ በሆስፒታሉ ያለው የህፃናት ህክምና ክፍልም የሃገሪቱ ሰፊና ብቸኛ ተቋም በመሆኑ በከፍተኛ ጫናና በደከመ መልኩ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ከህብረተሰቡ ለሚነሳ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ መንስኤ ሆኗል፡፡
በህፃናት የህክምና ክፍል ውስጥ ከሚሰጡ የህክምና አይነቶች ውስጥ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ የልብ፣ የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት ካንሰር ህክምና አገልግሎቶችም ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች የሚሰጡት በቂ አቅም ኖሮ፣ የሰው ሃይል፣ በጀትና ቦታ ኖሮ አይደለም፡፡
በድንገተኛ ህክምና ክፍሉ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አግልግሎቱን ፈልጎ የሚመጣው የታካሚዎች ቁጥር ከሆስፒታሉ አቅም ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ አሁንም አገልግሎቱ በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በዚህም ምክንያት ቅሬታዎች ከታካሚዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡ ለህብረተሰቡ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የህፃናት ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ቅሬታዎች መንስኤ የአገልግሎት አሰጣጡ ዋነኛ የቅሬታ ምንጭ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው፡፡ ከፍተኛ የፍላጎት ልዩነት እንዲሁም የዛኑ ያህል የአቅርቦት ውስንነት አለ፡፡ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ቅሬታ ሲኖር ቅሬታው እንዳይባባስ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ወዲያው የሚፈቱ ችግሮች ካሉ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፡፡
በብሶት መልኩ የሚነሱ ቅሬታዎች የሚታዩት በሲስተም ኢምፒሊኬሽን ነው፡፡ ይህም ማለት ከካርድ መጥፋት ጋር በተያያዘ ተገልጋዮች የሚገጥሟቸውን ህክምና አገልግሎት ችግር ለመፍታት የካርድ አወጣጡ ዲጂታል ስርአትን እንዲከተል ተደርጓል፡፡ ህክምና ለማግኘት የሚያስፈልገው የመቆያ ጊዜ 65 ደቂቃ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ድንገተኛ አደጋ ህክምና የማግኛ ጊዜ ደግሞ ከ5 ደቂቃ በታች እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የህክምና አገልግሎቱን የማስፋት ስራዎች ሆስፒታሉ 13 ሺ ካሬ መሬት ከሊዝ ነፃ ቦታ ከመንግስት አግኝቷል፡፡ በዚሁ ቦታ ላይ 10 የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን የማስፋት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የካንሰር ህክምና ማዕከል ግንባታ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የአገልግሎት ጫና ይፈታል፡፡
ሁለተኛው የህክምና አገልግሎት ግንባታ ደግሞ ትልቅና ራሱን የቻለ የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል ነው፡፡ ይህም በተለይ የህፃናት የድንገተኛ ህክምናና የእናቶችን ህክምና አገልግሎት በይበልጥ ለማስፋት የሚያግዝ ይሆናል፡፡ በሂደትም የህብረተሰቡን ቅሬታ ይፋታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ግንባታውን ለማካሄድም በአሁኑ ወቅት የማስተር ፕላን ዶክሜንት የማዘጋጀትና የማፀደቅ፣ ቦታውን የመረከብና የማጠር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ህንፃዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንደኛው አጠቃላይ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማእከል ሲሆን፣ 324 አልጋ የሚይዝና የድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎትን በአንድ ጣራ ስር ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡
ሌላኛው ደግሞ የተመላላሽ ህክምና ክፍል ህንፃ ግንባታ ነው፡፡ ግንባታው በስምንት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በታሰበው ጊዜ ህንፃውን ገንብቶ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ በቀጣይ ግንባታው የሚፋጠን ከሆነም ክፍሉ የተመላላሽ ህክምናውን ችግር ይፈታል ተብሎ ይገመታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
አስናቀ ፀጋዬ