ኢትዮጵያ የታሪክ ደሃ አይደለችም፡፡ አያሌ ዘመናትን የተሻገሩና ዛሬም ህያው ሆነው ለዓለም ምስክር የሆኑ የታሪክ አሻራዎች አሏት፡፡ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት ታሪክ ሲዘክረው ከኖረው የአክሱም ሃውልት ጀምሮ የጎንደር ቤተመንግስት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርሶቻችን የአንፀባራቂ ታሪኮቻችን ማስታወሻዎች ናቸው፡፡
ከጀግንነት አንጻርም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጥቁር ህዝቦች ጭምር የሚተርፍ ታሪክ አላት፡፡ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላም በርካታ የውጭ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ቢሞክሩም አንድም ጊዜ ድል አልተቀዳጁም፡፡ ይልቁንም ጠላት ዳግም ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመልስ ያደረጉ ጀግኖችን በየጊዜው አፍርታለች፡፡
እነራስ አሉላ አባነጋ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ ወሌ እና መሰል ጀግኖች የአድዋ ኩራቶቻችን ናቸው፡፡ እነ አብረሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶምም የአልበገር ባይነት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ በስፖርት ዘርፍም ቢሆን በነጭ ወራሪዎች ፊት በባዶ እግር ሮጦ ነጮችን በአደባባይ ከዘረረው አበበ ቢቂላን ጀምሮ፤ እነ ምሩፅ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና የመሳሰሉት ጀግኖች አትሌቶች ሁሉ የጀግንነትና የአልበገር ባይነት ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡
በሌሎች የተለያዩ ዘርፎችም አያሌ ጀግና ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ለመረዳት የታሪክ ድርሳናትን ማገላበጥ ብቻ በቂ ነው፡፡ በየዘመኑም የኢትዮጵያ ማህፀን ጀግና ማፍራቱን አቋርጣ አታውቅም፡፡ በቅርቡም ማህፀነ ለምለሟ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ጀግኖች ያንኑ የተለመደና የቀደመ የጀግንነት ታሪክ የሚያድስ ሌላ አዲስ አንፀባራቂ ድል ተጎናጽፈው የመላ ኢትዮጵያውንን የአሸናፊነት ወኔ አድሰዋል፡፡ ለዓመታት በጉያዋ ተወሽቆ ህዝቦቿን
ሲከፋፍልና እንደመዥገር ደሟን ሲመጥ የኖረውን የህወሓት ጁንታ ቡድን በአጭር ጊዜ በማፈራረስና ትግራይን ነፃ በማውጣት ለመላው ኢትዮጵያ ምቹ የልማትና የእድገት ጉዞ መደላድል እንዲፈጠር መንገዱን አመቻችተዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን ይህንን ታሪክ ያስመዘገበው ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላው የጀግንነት ጥበብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድም ዜጋ ሳይጎዳ በጥንቃቄ ጠላትን ነጥሎ በመምታትና በአጭር ጊዜ ድልን በመጎናፀፍ መሆኑ ድሉን ይበልጥ ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡ ድሉም ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ለጠላት እጇን እንደማትሰጥና በገሃድ ያስመሰከረችበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ጀግኖች የመኖራቸውን ያህል ለዘመናት ያልተፈቱና በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንዳንሄድ ያደረገን፤ እየተገዳደረን ያለ ጠላት ከፊታችን ተደቅኗል፤ ይህም ድህነት ነው፡፡
ይህ ጠላት በተለይ መሰሪ የሆኑ ጠላቶቻችን በሸረቡት ሴራና የአልጠግብ ባይነት የዘረፋ ተግባር በየጊዜው አብሮን ኖሯል፡፡ በተለይ አሁን የተወገደው የህወሓት ጁንታ ኢትዮጵያን ያለርህራሄ በመዝረፉና ሃብቷንም በማባከን በሰራው ክፉ ስራ ድህነት አብሮን እንዲኖር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህ ቡድን ሃብት መዝረፍ ብቻ አልነበረም ሲሰራ የቆየው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በርስ በጎሪጥ እንዲተያዩና አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር፣ ከዚያም አልፎ የስራና የትጋት መንፈስ እንዳይዳብርና የጠባቂነትና የስራ ጠልነት መንፈስ በሃገሪቱ ላይ እንዲነግስ ጭምር በመስራት ለዘመናት የማይሽር ክፉ ቁስል አኑረው ሄደዋል፡፡
ስለዚህ ከጁንታው መወገድ በኋላ የሚቀጥሉት የቤት ስራዎች ይህንን ማስተካከልና ማረም ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡ በተለይ አሁን የተዋቀረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በአንድ ፓርቲ ስር ሆኖ አንድ አይነት እይታ ብቻ እንዲኖረው የተፈረደበት የትግራይ ህዝብ በነፃነት ሃሳቡን እንዲያራምድና በክልሉ በሚካሄዱ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶች የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ በተካሄደው የሰላም ማስከበር ሂደት ጁንታው በርካታ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙ ይታወቃል፡፡
የፌዴራል መንግስትም እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት እና ለከፋ ችግር የተዳረጉ ነዋሪዎችንም ለመደገፍ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በሃይል አቅርቦትና በቁሳቁስ አቅርቦት ረገድ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቀጣይም የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌዴራል መንግስት ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠል ትግራይን ለማልማት ሊረባረብ ይገባል፡፡ አዲስ የተመረጡት የክልሉ የካቢኔ አባላትና አመራሮችም ለዓመታት በጁንታው አፈና ስር የቆየውንና የመልካም አስተዳደር እጦት ሰለባ የነበረውን የትግራይ ህዝብ ለማገልገል በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2013 ዓ.ም