
ሞገስ ተስፋ
አዲስ አበባ፡- በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የቀብር ሥነስርዓት በዛሬው ዕለት በቅድስት ስላሴ ካቴዴራል ተፈፀመ።
ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ከአባታቸው ከአቶ ወግደረስ ወንድምተካሁ እና ከናታቸው ከወይዘሮ አበቤቴ አርጋው በአዲስ አበባ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሐምሌ ሰባት ቀን 1937 ዓ.ም እንደተወለዱ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስም በቀጨኔ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ፊደል የቆጠሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በእንጦጦ ተራራ ግርጌ በሚገኘው የቁስቋም ተምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ ሀገራቸውን በውትድርና ለማገልገል ካላቸው ፅኑ ፍቅር የተነሳ በ1954 የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በመቀላቀል የአውሮፕላን ጦር መሳሪያ ኤሌክትሮኒክስ ትምህርት በመማር በአጥጋቢ ሁኔታ ፈፅመዋል። በ1958 ዓ.ም ለከፍተኛ የሙያ ስልጠና ወደአሜሪካ በመሄድ አሪዞና በሚገኘው የአንድሪው አየር ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ በዘመኑ ዝነኛ የነበሩ ኤፍ-5 ለተባሉ ተዋጊ ጄት አውሮፕላኖች ተስማሚ የጦር መሳሪያና የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ስልጠና ለስድስት ወራት ተከታትለው ወደሀገራቸው በመመለስ በከፍተኛ የሃገር ፍቅር ስሜት ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ፍቅረ ስላሴ ወግድረስ በአየር ኃይል የዕጩ መኮንኖች ትምህርት ቤት የስድስተኛ ኮርስ ተወዳዳሪ በመሆን ለሰባት ወራት ያህል ስልጠና ወስደው በአጥጋቢ ውጤት በማጠናቀቅ በ1961 ዓ.ም የምክትል መቶ ዕልቅና ማዕረግ አግኝተዋል። በ1966 ዓ.ም ህዝባዊው የኢትዮጵያ አብዮት ከዳር እስከዳር ሲቀጣጠል በአብዮቱ መለዮ ለባሹን በመወከል ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ፣ አስተባባሪ ኮሚቴው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተብሎ መንግሥት ሆኖ ሲሰየም ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ወታደራዊ ዘርፍ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት አገልግሎት ተሳታፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በ1973 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ በመሆን ኃላፊነታቸውን ፍፁም በሆነ የሀገራዊ ፍቅር አገልግለዋል።
ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ በደርግ ዘመን በነበራቸው ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ መሬት የሌለው መሬት እንዲያገኝ፣ አርሶ አደሩን፣ ምሁሩንና መለዮ ለባሹን በመያዝም ድሃው አርሶአደር ከጭሰኝነት እንዲወጣ የበኩላቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል። ከጳጉሜ 5 ቀን 1979 ዓ.ም ጀምሮም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።
በ1983 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስና በርካታ ጓዶቻቸው ለእስር ተዳርገው ለ20 ዓመታት ያህል በእስር ቤት ያሳለፉ ሲሆን፤ ከእስር ሲፈቱ ያለፉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ‹‹እኔ እና አብዮቱ እና እኛ እና አብዮቱ›› የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል።
በእስር ቤት በነበረው የእስረና አያያዝ ምክንያት ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በተደጋጋሚ ይታመሙ እንደነበር በህይወት ታሪካቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፀና ታመው የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ በተወለዱ በ75 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም በትላንትናው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል።
ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ባለትዳር እና የአንድ ወንድና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት እንደነበሩም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2013 ዓ.ም