አዲስ አበባ ፡- የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመንግሥት ከሊዝ ነጻ ባገኘው 13 ሺ ካሬ መሬት የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የሆስፒታሉ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ግንባታውን በማካሄድ 10 የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን የማስፋት ሥራዎች ይከናወናል፡፡
ከእነዚህ አንዱ የካንሰር ህክምና ማዕከል ግንባታ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ግንባታው ሲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የአገልግሎት ጫና እንደሚፈታ ጠቁመዋል፡፡ሁለተኛው የህክምና አገልግሎት ግንባታ ደግሞ ትልቅና ራሱን የቻለ የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል መሆኑን አብራርተው፣ ይህም በተለይ የህፃናት የድንገተኛ ህክምናና የእናቶች ህክምና አገልግሎትን በይበልጥ ለማስፋት የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል፡፡
ግንባታው በሂደት የህብረተሰቡን ቅሬታ ይፈታል ተብሎ ይታመናል ያሉት ዶክተር ይርጉ፣ግንባታውን ለማካሄድም በአሁኑ ወቅት የማስተር ፕላን ዶክሜንት የማዘጋጀትና የማጽደቅ ፣ ቦታውን የመረከብና የማጠር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ህንፃዎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ዶክተር ይርጉ ተናግረዋል፡፡አንደኛው አጠቃላይ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማዕከል መሆኑን አስታውቀው፣ማዕከሉ 324 አልጋ የሚይዝና የድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎትን በአንድ ጣራ ሥር ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው ደግሞ የተመላላሽ ህክምና ክፍል ህንፃ ግንባታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ግንባታው በስምንት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰው፣በታሰበው ጊዜ ህንፃውን ገንብቶ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ አስታውቀዋልም፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ ክፍሉ የተመላላሽ ህክምናውን ችግር ይፈታል ተብሎ መገመቱን ገልጸዋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011