አስመረት ብስራት
እናትነት ታላቅ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ይህ ፀጋ ሲመጣ ከከባድ ሀላፊነት ጋር ነው። ህፃናት ሲወለዱ ምንም እንኳን ደስታ ቢሰጥም በተለይ ለመጀመሪያ እናት ግን ከባድ ነው። እንቅልፋቸው፣ ትንታቸው፣ ፈገግታቸው፣ ደስታና ስጋት የተቀላቀለበት ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ ሁሉ ግን ካለምንም የጤና ችግር የተወለዱ ልጆች ሲያጋጥሙ ነው። በተቃራኒው ከተለያዩ የአካልም ሆነ የአእምሮ እክል ጋር የተወለዱትን ህፃናት ለማሳደግ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ ከባለቤቱ በላይ ማን ሊረዳ ይችል ይሆን።
̋ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” አይደል የሚባለው ከነተረቱ። ይሄንን ከባድ ፈተና በድል የተሻገሩት የወለዷቸውን ልጆች እንደ ስጦታ ተቀብለው ነጋቸውን ብሩህ ለማደረግ ከሚታትሩት መካከል ለዛሬ ሁለት ጠንካራ እናቶችን ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ መልካም ንባብ።
ወይዘሮ ስምረት አስራት በሰላሳዎቹ እድሜ እኩሌታ የምትገኝ ሴት ናት። በፈገግታ የበራ ፊቷን ለተመለከተ የምትናገረውን ያህል መከራን ያለፈች አትመስልም። የሶስት ልጆች እናት ስትሆን፤ የእናትነት ወሰኗን የፈተነችው ሶስተኛ ልጇ ስትወለድ የገጠማትን እንዲህ ታጫውተናለች።
‹‹ሶስተኛ ልጄን ሳረግዝ ባልጠበኩት አጋጣሚ ስለነበር ቅር ብሎኝ ነበር። ነገር ግን ለህፃናት ያለኝ የተለየ ፍቅር አሜን ብዬ እንድቀበል አስገደደኝ። ለዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሳደርግ ነበር። አንድም ቀን ከቀጠሮዬ ቀን አልፌ አላውቅም። የታዘዘልኝንም መድሀኒት ሳልውጥ የቀረሁበት ቀን አልነበረም።›› ትላለች።
በስተመጨረሻ ቀኑ ደርሶ ስትገላገል ልጇን የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ከሚባል ችግር ጋር ነበር የወለደችው። በወቅቱም በጣም ነበር የደነገጠችው። ዶክተሮቹም እጅግ ቀላል እንደሆነ ቢነግሯትም ለመስማት ምንም ዝግጁ አልነበረኝም። ከሆስፒታል እንደወጣች ወደ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል እንደሄደች ታስታውሳለች።
በሆስፒታሉ ይህን ችግር በቅርበት የሚከታተል ክፍል ስለነበር በትህትና ተቀብለው ከችግሩ ጋር የሚወለዱ ልጆች በብዛት መኖራቸውን በአጭር ጊዜ ከተስተካከለ የሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚቀንሱ መሆኑን አስረድተው ለዚሁ አላማ የተዘጋጀ ጡጦ ሰጥተው እንዴት ልጇን በጥንቃቄ ማሳደግ እንዳለባት ነግረው እንደሸኟት ትናገራለች።
እንደ ወይዘሮ ስምረት ገለጻ፤ በሚገርም ሁኔታ የቅርብ የሚባሉ ሰዎች በሙሉ በወላጆቿ ሀጥያት ልጅቷ እንደዚህ አይነት የጤና ችግር እንደገጠማት ያስቡ ነበር። ሰው እንዳያያት የሚመክሩም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ከሰው ወሬ ባለፈ ልጅቷ የጠባችውን በሙሉ በአፍንጫዋና በአፏ ሲወጣ በየቀኑ ይሄንን ማስተናገድ እጅግ ፈታኝ ሆነ። ለአፍታም እንቅልፍ ካሸለባት ትንታው መጥቶ ልጇን የሚገልባት እየመሰላት አይኗን ከልጇ ላይ አትነቅልም ነበር።
ከዚህ ችግር ጋር የተወለዱ ህፃናት የጆሮ ኢንፈክሽን ሊገጥማቸው ስለሚችል ክፍተቱ ከሚፈጥረው የንግግር ችግር በተጨማሪ መስማት የተሳናት ልጅ እንዳትኖራት በሰቀቀን ነግቶ እንደሚመሽ ትናገራለች። የምትጠባው ወተት በአብዛኛው ስለሚወጣ ኪሎዋ እየቀነሰ መሄዱም እጅግ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደነበርም ታስረዳለች።
ከእለታት አንድ ቀን ጎረቤታቸው ሊጠይቃቸው መጣ። ጎረቤትየው ወደቤታቸው መምጣት የልጇ የዛሬ ላይ ጤናማ መሆን ምክንያት ነው ብላ እንድታስብ አድርጓታል። የጓደኛው ልጅ እንደዚህ አይነት ችግር የገጠማት መሆኗንና በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ የሚገኝ አንድ ኪዩር የሚባል የህፃናት ሆስፒታል ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዳለው ስለነገራት የጨለመ ተስፋዋን እንዳበራላት ትጠቅሳለች። ያን በሰማችበት ቅፅበት ነበር ልጇን አዝላ ወደ ሆስፒታሉ የገሰገሰችው። አስመዝግበሽ ሂጂ እንጠራሻለን ሲሏት ልጇን አገላብጠው ስላላይዋት ቅር ተሰኝታም ቢሆን ወደ ቤቷ መመለስዋን ትገልፃለች።
ልክ ልጇ ከተወለደች በሶስተኛ ወር ከሆስፒታሉ ደውለው ከውጭ የመጡ ዶክተሮች መኖራቸውን ስለነገሯት ወደ ሆስፒታሉ አቀናች። በዚህም የመጀመሪያው ቀዶ ህክምና ማለትም ከንፈርን መልሶ የማስተካከል ስራ ተሰርቶ የውስጠኛውን የላንቃ ክፍተት ለመስራት ለአመት ተቀጥራ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
የፊት ገፅታዋ ቢስተካከልም ላንቃዋ እስካሁን ክፍት በመሆኑ ትንታው፣ ምራቋን አለመሰብሰብና የተለያዩ ችግሮች አልተወገዱም ነበር። ሙሉ ለሙሉ ስራዋን አቁማ ልጇን መንከባከብ ላይ ብቻ ትኩረት አደረገች። በከባድ ጭንቀት ውስጥ ስለነበረችም ለጥቂት ወራት የቀጠለ የአእምሮ መታወክ ገጥሟት እንደነበር ትናገራለች።
ሆስፒታሉም ቃል በገባው መሰረት ከአንድ ዓመት በኋላ የውስጡን ክፍተት ደፍነው፣ ልጇን ወደ ጤንነቷ መልሰው ያለምንም የገንዘብ ክፍያ አሁን ላለችበት ጤንነት ስላበቁላት አመስግናለች። የእያንዳንዷ ቀን መከፋትና ጭንቀት በእነዚህ ደግ እጆች ስለተፈወሰ ዛሬን ያንን ክፉ ቀን አልፋ ወደ መደበኛ ህይወቷ ለመመለስ በቅታለች። ልጇም ዘንድሮ አራት አመት ይሞላታል። ምንም አይነት ተጓዳኝ የጤና ችግር ስለሌለባት ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ አቅዳለች።
ሌላዋ ባለታሪካችን ወይዘሮ ማህደር ግርማ ትባላለች። እሷም በሰላሳዎቹ እድሜ እኩሌታ ትገኛለች። የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ማህደር ሁለተኛ ልጇ ከተደራራቢ የጤና ችግሮች ነበር የተወለደችው። የዚህች ሴት ችግር የሚያበቃበት ቀን በውል አለመታወቁም መከፋቷ እንዳይቋረጥ አድርጎታል።
ወይዘሮ ማህደር ሁለተኛ ልጇን ወልዳ እንዳቀፈች ምንም የተለየ ሁኔታ ይኖራል ብላ አለሰበችም ነበር። ሁለተኛ ልጅ እንደመሆኗ ግን ህፃኗ እያደገች ስትሄድ ችግሮቹ በግልፅ መታየት ጀመሩ። ሲዠር ወይም ማንቀጥቀጥ ያለበት አይነት የሚጥል ህመም፤ የተወሰነ የእይታ ችግር፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላት ለእነዚህ ሁሉ የጤና ችግሮች የተለየዩ ህክምናዎች የሚያስፈልጋት ልጅ ሆነችባት።
የህክምና ባለሙያዎቹ በእርግዝና ወቅት በተከሰተ ኢንፌክሽን ምክንያት የመጣ ችግር እንደሆነ ያስባሉ። እስካሁን ድረስ መፍትሄ አለመገኘቱም እለተ ከእለት በሚያባንን ድንጋጤ ውስጥ እንድትኖር አስገድዷታል። ‹‹ህፃን ልጅ በቀን ለብዙ ጊዜ እራሱን እየሳተ ሲንቀጠቀጥ ከማየት የበለጠ ሰቀቀን ምን አለ።›› ስትልም ትጠይቃለች።
ልጇን በአግባቡ ተረድቶ ችግሯን በምን መልኩ ልቀርፈው እችላለሁ ከሚለው አንስቶ እውነታውን ተጋፈጦ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ መሞከር በራሱ እጅግ ከባድ ሆኖባታል። በየቀኑ ሀኪም ቤት መመላለስ፣ ከዚኛው ሀኪም ይሄኛው ይሻል ይሆን እያሉ በየቦታው መርገጥ እና የእናትነት ጭንቀት ከልክ በላይ በመብዛቱ ምክንያት ያላዳረሰችው ሆስፒታል እንደሌለ ትናገራለች።
የቤት ሰራተኛ ማጣት፣ ደጋፊ አይዞሽ ባይ በሚፈለገው ልክ አለመኖሩ፣ በየእለቱ ለህክምናና ለመድሀኒት የሚወጣው ወጪ ስቃይዋን እንዳበዛባት ትጠቅሳለች። ልጇ ፌስታል ሙሉ መድሀኒት ተገዝቶ ስትውጥ የተገዛው መድሀኒት ልጅትዋ ሰውነት ውስጥ እንደገባ ማሰብ እጅግ የሚያም ነገር መሆኑን ትገልፃለች።
‹‹እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋን በአንክሮ እየተከታተልኩ ለሁለት አመታት ሙሉ ለሙሉ ስራ አቁሜ ልጄን ለመንከባከብ ብሞክርም ነገሮችን መሸከም ቀላል አልሆን ስላለ ቢያንስ የገንዘበ ችግሩን በጥቂቱ ለመቅረፍ ስራ ጀመርኩ። ስንት ጊዜ ለመወሰን እንደፈጀብኝ። ለመቁረጥ እንዴት እንደተቸገርኩ ነፍሴ እንደተጨነቀች ማሰብ ይከብደኛል። ነገር ግን ለሌሎቹም ልጆቼ እናት መሆን ስላለብኝ ከመረጋጋት በስተቀር ምንም አማራጭ አልነበረኝም።›› ትላለች።
አንድ ቀን የመጀመሪያው ወንድ ልጇ የእናቱን ጭንቀት፣ ድካምና ምሬት ተረድቶ ‹‹እማ በጣም እየተቸገርን ነው አይደል የምንኖረው›› አላት። ከትንሽ ልጅ ይህ ጥያቄ የማይጠበቅ በመሆኑ መደናገጧን ታስታውሳለች። ለምን እንደዚህ እንዳለም ስትጠይቀው ‹‹ሲዠር›› የሚል መልስ ሰጣት። የህመሙ ስም ተደጋግሞ ከመጠራቱ የተነሳ ህፃኑ ልብ ውስጥ ቀርቷል።
ታናሽ እህቱ ዘወትር እየወደቀችና እየተንቀጠቀጠች እናትየው የልጇን በሞትና በህይወት መካከል ያለ የሰቆቃ ፊት እየተመለከተ ትንሽ ልቡ በጭንቀት ተወጥሮ መናገር እስኪከብደው ድረስ መቆየቱን እናት ተረዳች። ያን የጭንቀት ሰአት በወይዘሮዋ ጥንካሬ መታለፍ እንዳለበት ወሰነች። የተቀሩትም ልጆች እናት ያስፈልጋቸዋል። በምንም አይነት ሀሳብ ያለተዋጠች እናት ይፈልጋሉ። ቢያንስ ወጥታ ስትገባ የተሻለ መንፈስ ይዛ ስለምትመለስ ፍቅር የመጋራቱ ስራ ቤት ሙሉ ጊዜዋን ከታማሚ ልጇ ጋር ከምታሳልፍበት የተሻለ ሆነ።
‹‹ልጄ ቃል ማውጣቷ፣ መቆሟ፤ ሌላው ይቅር ምግብ እንኳን በደንብ መብላቷ ሁልጊዜ ብርቅ ይሆንብኛል። የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያላቸው ልጆች ደግሞ ነገሮችን ለመረዳት ድግግሞሽ የግድ በመሆኑ ፍፁም ትእግስትን ይጠይቃል። ይህንን ድግግሞሽ ለማድረግ የሷን ስሜት መከተል የግድ ይላል።›› ትላለች።
ሲዠሩ ከመከሰቱ የተወሰነ ደቂቃ፤ ሰዓት ወይንም ቀን በፊት የሚሰሙ የመረበሽና የፍርሃት ስሜቶች እንዳሉ የምትናገረው ወይዘሮ ማህደር፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጡንቻ መሳሳብ የሰውነት መገታተር እና መንቀጥቀጥ እንዲሁም ራሷን እንደሳተች መቆየት፤ ሽንት መልቀቅ፤ አረፋ መድፈቅ እንደሚከሰቱ ትገልፃለች። ህመሙ ሲነሳ የምትወድቅበት ቦታ ጉዳት እንዳያደርስባት አይኗን ከሷ ላይ ማንሳት ከባድ የሚሆንበት ጊዜ ከመኖሩም በላይ ከህመሙ በኋላ የሚሰማት ስሜት ይበልጡኑ ነገሮችን እንድትገነዘብ የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ እንደሚጎትተውም ትናገራለች።
ሌላው ወይዘሮ ማህደር የምታስታውሰው ‹‹ልጄ በር ከፍታ እንዲቆምላት ማስደገፊያውን አስጠግታ ለማቆም ትታገላለች። ሁልጊዜም ትሞክራለች። ሞክራ ሳይሳከላት ሲቀር በጣም ታለቅስ ነበር። አንድ ቀን ግን ያ ጥረት ተሳክቶ በእግሯ ማስደገፊያውን ገፋ አድርጋ ስታቆመው የተደሰትኩትን ደስታ ማሰብ ይከብዳል።” እያንዳንዱን ልጇ አውቃ የምታደርገው ነገር ልቧ ውስጥ ትናንሽ ተስፋዎች እየጫረ ያለፈ ነገር ነው።
ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ ሶስተኛ ልጇን ለመውለድ ለመወሰን ሰባት አመታትን እንደወሰደባት ታስታውሳለች። ሶስተኛ ልጅ ስትወልድ ሁለተኛ ልጇ በይበልጥ የተሻለ መነቃቃት እንዲኖራት ማድረጉን ትጠቅሳለች።
ሌላው ከባዱ ፈተና ልጅቷ እድሜዋ እየጨመረ በመሄዱ ትምህርት ቤት ማስገባት የግድ ሆነ። በወቅቱ ትምህርት ቤት ሲጠየቅ አምጧት ይሉና ለምን ስራችሁን ትታችሁ አትንከባከቧትም ወይም ሌላ ደስ የማይሉ መልሶችን መስማት ግድ እንደነበር ትናገራለች። ትምህርት ቤቱ ተገኝቶ ለማስተማርም በወር ስደስት ሺ ብር እየተከፈለ ለሁለት አመታት ቢሞከርም በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንድታቋርጥ መደረጉን አጫውታናለች።
ለአንድ አመት ከአራት ወራት ያህል የሚጥል ህመሙ ቆሞ ስለነበር በታላቅ ተስፋ ውስጥ ቢቆዩም ልጅቷን የሚጥላት ህመም በድጋሚ በመመለሱ ድጋሚ ወደ ሀዘን መግባቷን ትጠቅሳለች። በሚፈጠሩ ሁኔታዎችም ተስፋ ላለመቁረጥ እየታገለች እንደምትገኝም ትገልፃለች።
‹‹እኔ የምችለውን በእኔ አቅም ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ሁሉ ቢገጥመኝ እያልኩ አስባለሁ። ማንም ሴት፣ ማንም እናት እኔ የደረሰብኝ አይድረስባት፤ የኔን መከፋት ማንም አይሸከመው።›› ትላለች።
ይህን ሁሉ እየተናገረች ብቻ ተመስገን የሚለው ቃል ከአፏ የማይጠፋው ወይዘሮዋ የተሻለ ስራ ብትሰራም፤ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችም በተለይ የመድሀኒት ወጪ ላይ እገዛ ቢያደርጉላትም፤ በተቻላት አቅም ብትደክምም የልጇን የወደፊት ህይወት ለማቃናት ግን ደፋ ቀናው ከጫንቃዋ በላይ ከብዶ አስጎንብሷታል።
ሁለቱ ባለታሪክ እናቶች ምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ችለው የማለፍ አቅም ቢኖራቸውም ረዳት ግን የግድ ያስፈልጋቸዋል። የወይዘሮ ስምረት ልጅ ከውጭ በመጡ ደግ ልቦች ቢጠገንም የወይዘሮ ማህደር ችግር ድርብርብ በመሆኑ ዙሪያዋ ያሉ ሰዎች ሁሉ ቢያግዟትም ከሸክም በላይ ሆኗል። በጎ ልብን ለማግኘት ችግሮችን ለመሸካከም የግድ ከባህር ማዶ ረዳት ሊመጣልን አይገባም።
ሰው በተሰማራበት መስክ ለእንደነዚህ አይነት ልጆች ድጋፉን ቢለግስ፤ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነውና ሸክሞችን ተከፋፍሎ እንደጥንቱ ባህላችን እየተጋገዝን እንለፍ እላለሁ። ደግና ሩህሩሁ የእናት ልብ አይሰበር የእናት ፊትም በእንባ እንዳይታጠብ ምኞቴ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013