ዋለልኝ አየለ
ከ2010 ዓ.ም በፊት በነበሩት ዓመታት የህዳር ወር ሙሉውን የብሄር ብሄረሰቦች ወር ነው ማለት ይቻል ነበር።ህዳር 29 ቀኑ በሚከበርበት ክልል ስቴዲየም ውስጥ የመንግስት ባለሥልጣናት ይገኛሉ። ከህዳር 29 በፊት ባሉት ሳምንታት ሁሉ የሚወራው ስለህዳር 29 ነው። የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ይሰጡት ነበር። በአንጻሩ የግል መገናኛ ብዙኃን እና የመንግስት ተቃዋሚዎች ‹‹ለፖለቲካ ፍጆታ የሚደረግ ነው›› እያሉ ይቃወሙት ነበር።
እውነት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበብ የሚያሳይ ነበር? ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበብ ስሪት ናት። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በብሄራዊ ቴአትር በተደረገ አንድ መድረክ ላይ የተናገረው ትዝ አለኝ። ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ስሪት መሆኗን በሰውነታችን ቅርጽና አቅጣጫ አመሳስሎ ነበር የገለጸው። ጭንቅላታችን በሰሜን ይገለጻል።የሰሜን ኢትዮጵያ አናት የሆነው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ጭፈራ የአንገትና የጭንቅላት እንቅስቃሴ ነው። የታችኛው ሰሜን የሆነው የአማራ ክልል አካባቢዎች ጭፈራ ደግሞ በትክሻ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው። የመሐል ኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚይዘው የኦሮሞ ጭፈራ ደግሞ በወገብ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው። የአገራችን የደቡብ ክፍል የሆኑት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ በዳሌ እና በእግር እንቅስቃሴዎች የሚታወቁ ናቸው። ኢትዮጵያ የእነዚህ ስሪት ናት።
እንግዲህ የሚያሳዝነው ነገር ‹‹ለብሄር ብሄረሰቦች ማንነት ቆሜያለሁ›› ሲል የነበረው ኢህአዴግ እነዚህን ነገሮች አለማስተዋወቁ ነው። በወቅቱ ይወቅሱት የነበሩት አካላት ትክክል ነበሩ ማለት ነው። የተጠቀመው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነበር። ለዚህ ደግሞ ግልጽ ማሳያዎች አሉ። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ይደረግ የነበረው ፖለቲካዊ ስብከት እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበብ ማስተዋወቅ አልነበረም።
በዕለቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረውን ዋናውን ዝግጅት እንኳን ማስታወስ በቂ ማሳያ ነው። በመላው አገሪቱና በመላው ዓለም በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፈው የብሄር ብሄረሰቦችን ጥበብና ባህል የሚያሳይ ጥናት ወይም ውይይት ሳይሆን የፖለቲከኞች ስብከት ነበር። ለዚያውም አንዱን አጥቂ አንዱን ተጠቂ በማድረግ አሁን ድረስ ማባሪያ የሌለው ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ንግግሮች ነበሩ ።
ፓርቲው ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ የኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን ‹‹እኔ ነኝ የፈጠርኳቸው›› ማለት ነበር የቀረው። በብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚደረገው የኢህአዴግ ስብከት መሰረት፤ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች ሁሉ የተፈጠሩት ከ1983 ወዲህ ነው፣ የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት ሁሉ የተፈጠሩት ከ1983 ወዲህ ነው ማለት ነበር የሚቀረው፤ በአጠቃላይ የብሄር ብሄረሰቦች ፈጣሪ እኔ ነኝ እያለ በተቃራኒው ግን ሲጨፈልቅ ነበር።ቀላል ምሳሌ እናንሳ።
በዕለቱ ህዳር 29 ቀን እንኳን ትርዒቱ በትክክል አይቀርብም። እዚህ ላይ ሁለት ስህተት ነበር ያለው። አንደኛው፤ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበብ በትክክል አይታይም ነበር። ሁለተኛ፤ አቅራቢዎች ትክክለኛ የባህሉ ከዋኞች ሳይሆኑ አበል የሚያመጣቸው ካድሬዎች ናቸው። በየዓመቱ ዝግጅቱ ላይ የሚታደሙት ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው።የሌላ ብሄር ተወላጅ ሆነው የአንዱን ብሄር ልብስ ለብሰው አስመስለው ያቀርባሉ። ያ! ደግሞ ትወና እንጂ ትክክለኛውን የብሄሩን ወካይ ማሳየት አይደለም። ስለዚህ ልቦልድ አሳዩን እንጂ ባህል አላሳዩንም።
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ዘንድሮ 15ኛ ዓመቱ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በቀጥታ ሥርጭት ተከታትያለሁ። አንደኛውን ደግሞ በአካል የሚከበርበት ስቴዲየም ውስጥ ሆኜ ተከታትያለሁ። ከዕለተ ቀኑ በተጨማሪም በሰሞኑ የሚዘገቡ ዘገባዎችንና የሚሰሩ ፕሮግራሞችን ተከታትያለሁ። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮችም አሉ።
በበአሉ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ትርኢቶችን ያቀርባሉ። አቀራረቡም፤ መድረክ መሪው ‹‹አሁን የእገሌ ብሔር ባህላዊ ትርዕይቱን እያሳየ ያልፋል›› ይላል። መጀመሪያ ላይ የተጠራው ምናልባት ትንሽ የመታየት ዕድል ያገኝ ይሆናል።ከዚያ ቀጥሎ ግን እያከታተለ ‹‹ቀጥሎ የእገሌ ብሄር …›› እያለ ሁሉንም ይጠራል። አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ የሚያልፈው ብሄር የማን እንደሆነ አይታወቅም። እንዲያውም መድረክ መሪው የሚሰጠው ማብራሪያና በክቡር ትሪቡኑ ሥር የሚያልፈው ብሔር ሌላና ሌላ ሊሆን ይችላል።
ቢያንስ ቢያንስ አንድ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች ብቻ እንኳን በአንድ ጊዜ ቢያልፉ። እነርሱም ገለጻ እየተደረገ ተራ በተራ እንዲያልፉ ቢደረግ መልካም ነበር። ይህ የማይመች ከሆነ መተው እንጂ እያደበላለቁ ማሳለፍ ምንም የሚገልጸው ነገር የለውም፤ ምናልባትም የሚያውቁት የዚያው አካባቢ ሰዎች ናቸው። ለእነርሱ ከሆነ ደግሞ ያን ያህል ጊዜና ገንዘብ ማባከን ለምን አስለገ? በዚህ ሁሉ ውስጥ የምንረዳው ነገሩ የፖለቲካ ፍጆታ እንደነበር ነው።
በአማተርም ይሁን በትልልቅ አርቲስቶች የሚቀርብ ትወናም አለ። ይሄ ደግሞ ቴአትር ወይም ፊልም እንጂ ትክክለኛው ባህል አይሆንም። ይሄም ይሁን ግዴለም፤ ትርዒቱን የሚያሳዩት በየዓመቱ ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው። በእዚህ አይነት ሁኔታ ቱባ ባህልን እንዴት ማሳየት ይቻላል? ለምን በከያኒያን ይቀርባል? በከያኒያን (ታዋቂ አርቲስቶች) የሚቀርብበት ምክንያት መንግስት በሚፈልገው ልክ ለማቅረብ እንዲያመች ነው። በየመሃሉ ፖለቲካዊ መልዕክቶች እንዲተላለፉ ነው የሚደረገው። በራሳቸው በባህሉ ባለቤቶች ቢቀርብ ግን ቱባውን ባህል ማየት ይቻላል።
በከያኒያኑ የተሰራው ራሱ በአግባቡ አይታይም። ለዚያ ዝግጅት ከስድስት ወር ያላነሰ ጊዜ ይባክንበታል። ለዝግጅቱ ጊዜና ገንዘብ ባክኗል። ዝግጅቱን ለማሳየት እስከ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙም አሉ። ይሄ ሁሉ ድካም ተደክሞበት ግን ዝግጅቱ አይታይም።እርግጥ ነው ማታ በዋዜማ የሚደረግ ዝግጅትም አለ፤ ያ የዋዜማው ዝግጅት ግን የታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራ የሚቀርብበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በዋዜማው ዝግጅት ላይ ባለሥልጣናትና የተለያዩ ሰዎች ብቻ የሚገኙበት ነው።
ከዚህ በፊት የነበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር ማስታወስ ያስፈለገበት ምክንያት፤ አቀራረቡ መቀየር እንዳለበት ለማሳየት ነው። በዚህ ዓመት የታሰበው የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበባት በተመረጡ አምባሳደሮች አማካኝነት ዓመቱን ሙሉ ለማስተዋወቅ ነው፤ ይህም የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች በሚገባ እንዲተዋወቁ ያደርጋል። በዚህም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ይቻላል። ስለዚህ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበባት የሚታዩበት ይሁን!
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013