በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ሥኬትን የማያልማት ማን ነው? ከውድቀት ለመሸሽ የማይሻስ? በሥኬት አደባባይ ላይ ከወጡት ጎን ለመቆም የሚያፍርስ ማን ነው? በሽንፈት መድረክ ላይ አብሮ መገኘትን ልምዱ ያደረገስ? የሁሉም ጥያቄዎች መልስ “ማንም” የሚል ነው ።
እውነታው ሥኬት በሁሉም የተፈለገች መሆኗ ነው ። እውነታው ከውድቀት መሸሽ የሁላችንም ፍላጎት መሆኑ ነው ።ከእዚህ ቀጥተኛ የሥኬት እና ውድቀት እይታ ባሻገር ግን በሥኬት ውስጥ ውድቀት አለ፤ በአግባቡ ባልተገራ የውድቀት ድባብ ውስጥ ደግሞ መጥፋት አለ። ይህንንም ዛሬ እናያለን። በሥኬትም ሆነ በውድቀት ውስጥ ስላለው ኪሳራ በጥሞና እንድናስብ የተዘጋጀ ጽሁፍ ነው። በሥኬት የወደቁ፤ በውድቀት ከጠፉት ዛሬ ትምህርት መውሰድ ለእኛ የተገባን ስለሆነ ።
ሁለቱንም ሃሳቦች በአጭሩ እንደሚከተለው እንተርጉማቸው፤
- በሥኬት መውድቅ – በትላንት ጥረት ዛሬ ሥኬት ሆኖ እጃችን የገባ ነገር ወይንም የእኛ የሆነ ነገር ለነገ የውድቀት ምክንያት ሲሆን እርሱ በሥኬት መውደቅ ነው፡፡
- በውድቀት መጥፋት – በትላንት ጉዟችን ውስጥ በገጠመን ውድቀት አማካኝነት ውድቀቱን በአግባቡ ካለመያዝ የተነሳ የሚመጣ ጥፋት እርሱ በውድቀት መጥፋት ነው፡፡
በሥኬት መውደቅ ማለት
ከአሸናፊነት መድረኮች የሚሰማ አንድ የተለመደ ንግግር አለ ።በሩጫው መድረክ የመጀመሪያውን መስመር የያዘው ሰው ድሉን አስመልክቶ በሚናገርበት ጊዜ የሚናገረው የዛሬው ድሉ የነገ የቤት ሥራው እንደሆነ ነው። በሻምፒዮን ሊጉ ዋንጫውን ከፍ ያደረገው አሰልጣኝ ከድል በኋላ የሚያስደምጠው የዛሬ ድል ለነገ ጥረት ቀብድ መሆኑን ነው ።ሁሉም የዛሬ ሥኬታቸው የነገ ትልቅ የቤት ሥራ መጀመሪያ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ ። የዛሬው ድል ብዙ መስራት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ቀብድ አድርገውም ያቀርባሉ። የዛሬ አሸናፊነት ትርጉም የዛሬ ብቻ ይሆንና ስለ ነገ እንደ መነሻ ይቆጠራል ።ይህን ጤናማ አመለካከት አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ለነገ የተሻለ ስራ እንደ መነሻ ሊሆን የተገባው መነሻ ነጥብ በመሆኑ ።ችግሩ ግን የዛሬ አሸናፊው የዛሬ ስኬቱን መሸከም አቅቶት የውድቀት ምእራፍ በርን በራሱ እጅ ከፍቶ ሲገባ ሲታይ ነው ።ሃሳቡን በቀላሉ ለመረዳት ከሥኬት ማዶ ያለውን የውድቀት ፈተናን ለማየት በሚከተሉት የህይወት ምእራፍ ገጠመኞች ውስጥ እንመልከት ።
ህይወት በተማሪነት ወቅት – የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከቤተሰብ ጋር ሆኖ ሲከታተል የነበረ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያውን ውጤት ሲያመጣ ቤተሰብ በታላቅ ደስታ የልጁን ሥኬት ይቀበላል ።ተማሪውም ቤተሰብም ስለ ተገኘው ሥኬት በደስታ ድባብ ውስጥ ይቆያል። የልጁ የዛሬ ሥኬት ግን ሙሉ የሚሆነው ልጁ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ሥራ ተሰማርቶ ራሱን ችሎ መኖር ሲጀመር እና ለሌሎችም መትረፍ ሲችል በመሆኑ በነገ ውስጥ ሊታይ የተገባ ቀሪ ሥራ መኖሩ ግን ለሁሉም ግልጽ ነው። ተማሪው ግን የዛሬው ሥኬት ላይ ከቆመ ከሥኬቱ ማግኘት የገባበት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በገናው ማዕበል ተመቶ ወደ ቤተሰብ የማይመለስበት ምንም ምክንያት የለም። ወደ ቤተሰብ ከዩኒቨርሲቲ ተባሮ መመለስ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ካለማምጣት አንጻር የሚፈጥረው የሥነ-ልቦና ተጽእኖም ቀላል አይደለም። በእዚህ መሰል የተጠባቂነት ቀውስ ውስጥ የገቡ ወደ ቤተሰብም ሳይመለሱ ተንከራታች ሆነው የቀሩ ተማሪዎችን ቤቱ ይቁጠራቸው፤ በተለይም ሴት እህቶቻችን። ዩኒቨርሲቲዎች ባሉባቸው አካባቢዎች በወጣቶቹ ገላ የሚነግዱ ደላሎች የበዙበትም አንዱ ምክንያት ይህ መሆኑን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገርም አድምጠናል ።
ህይወት ሥራ በመፈለግ ወቅት – ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ልጃቸው አንድ ምዕራፍ ላይ ደርሶ የተመለከተ ቤተሰብና ወዳጆች ሁሉ በደስታ ይከርማሉ ።ደስታውን ያጣጠመ የተመራቂው ቤተሰብ ልጃቸው ወደ ሥራው ዓለም ተሰማርቶ ሲንቀሳቀስና ወደ መዳረሻው ላይ ደርሶ ሊያዩት ይሻሉ ።ይህ መሆን ሳይችል ሲቀር ግን የጠባቂነት እና የተጠባቂነት የሥነ-ልቦና ቀውስ ይፈጠራል ።ተመርቆ አሁንም በወላጆች ድጋፍ እየኖረ ያለ ወጣት አስቀድሞ የተገነባ ባህሪ ከሌለው በስተቀር አቅም ኖሮት የሥነ-ልቦናው ጦርነት ተቋቁሞ መቆም ይቸገራል ።
ህይወት ሥራ በመሥራት ወቅት – ተመርቆ ወደ ሥራ መቀላቀል የቻለው ምሩቅ እና ቤተሰብ ስለ ልጃቸው ሥራ ማግኘት እና ወደ አንድ ምዕራፍ መድረስ አሁንም ይደሰታሉ። ወደ ሥራው የተቀላቀለው ወጣት ደግሞ የሥራው ዓለም እንደሚጠብቀው ሳይሆን ሲቀር በሚያገኘው ደሞዝ እንኳን ለሌሎች ሊተርፍ ለራሱም በተገቢው ሁኔታ እየኖረ አለመሆኑን ሲረዳ የድል ማግስት የሥነ-ልቦና ጫናው ይጋፈጠናል ።
ከእዚህ በላይ በተነሱት የሕይወት ምዕራፎች ውስጥ የሚያልፉ እና ሥኬትን ከማክበር ማግስት በውድቀት ውስጥ ራሳቸውን የሚያገኙ ሰዎች ምን ያህል ይሆኑ?
የዛሬ ሥኬት ለነገ ውድቀት ምክንያት የሚሆንበትን በሁለት ነጥቦች ውስጥ ልናየው እንችላለን። አንድ በዛሬው ሥኬት ውስጥ ያለው ተስፋችን ትልቅ መሆኑ እና ሁለት ታዋቂነትን መሸከም አለመቻል። በአጭሩ ተስፋ ወለድ እና ተቀባይነት ወለድ የሥኬት ማግስት ውድቀቶች ልንላቸው እንችላለን፡፡
ተስፋ ወለድ የሥኬት ማግስት ውድቀት ዛሬ እጃችን የገባው ሥኬት ውስጥ ሆነን ነገን ስናይ የምናየው ተስፋ ነው ።ዛሬ ሪከርድ የሰበረ ሯጭ ዛሬን አሻግሮ በዛሬው ስኬቱ ውስጥ ሩቅ ይመለከትና ያን በተጨባጭ ማሳካት ሳይችል ሲቀር የሚፈጠርበት ጫና ውጤት ነው ።የሁለተኛ ደረጃ ተማሪው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ሲያመጣ የሚሰማው እና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ከሚገጥመው አንጻር የሚፈጠር እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ወደ ሥራው ዓለም በተቀላቀለ ጊዜ ከጠበቀው አንጻር የሚገጥመው ተቃርኖ የሚፈጥርበት ወዘተ ልንለው እንችላለን፡፡
ተቀባይነት ወለድ ወይንም ታዋቂነት የሚያመጣው የሥኬት ማግስት ውድቀት ሌላው ምክንያት ነው ። ተቀባይነትን በአግባቡ መሸከም ካለመቻል በሚመጣ ውድቀት በሱስ አረንቋ ውስጥ የወደቁ፤ በትላንት ሥኬት እስራት ሆነው የተቀመጡትን እንዲሁ ቤት ይቁጠራቸው።
በአርቲስቶች እና እውቅ ሰዎች/celebrities በሚባሉ ግለሰቦች ዘንድ ያለው ሥኬት ወለድ ውድቀት ለእዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ።ታዋቂ መሆን የሚያመጣው ሸክም እርሱ ሥኬት ወለድ ውድቀትን በህይወት ውስጥ ይጋብዛል ።በሙዚቃ፣ በደራሲነት፣ በፊልም ተዋናይነት፣ በፖለቲካው ወዘተ የሚመጣ ታዋቂነት ይዞት የሚመጣው ሸክም ሥኬት ወለድ ውድቀትን የሚጋብዝ ሸክም ሌላው ማሳያ ነው፡፡
በህይወታችን ውስጥ የሚገጥሙንን ፈተናዎች አልፈን ወደ ሥኬት ለመድረስ መስራት አንድ ነገር ሆኖ እያለ ሥኬትን በአግባቡ መያዝ ደግሞ ሌላው ወሳኝ ነገር መሆኑን መረዳት አለብን ።ሥኬት ወለድ ከሆነ ውድቀት ለመጠበቅ መፍትሄው ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ምላሽን ያሻል ። ምላሹም ባህሪን መገንባት በየትኛውም ጊዜ የሚል ነው ።
በውድቀት መጥፋት ማለት
በሕይወት ጉዞ ውስጥ ሁሉንም ነገር እንዳሰብነው ማድረግ እንችላለን ማለት ፍጹም ስህተት ላይ ይጥለናል። በምድር ውስጥ ሁሉንም ሰው እኩል የሚያደርገው አንድ ነገር ሁሉም ሰው ሁሉንም ያሰበውን ነገር ማድረግ የማይችልበት ቦታ መሆኑ ነው። የውስንነት ቦታ። ዛሬ አንድን ነገር ማሳካት ከቻልን ነገ ያንኑ ነገር ደግመን እናሳካለን ወይንም በሌሎች ሁሉም ነገሮች ስኬትን እናስመዘግባለን ማለት አይደለም ።
ከትንሽ ተነስቶ እስከ ትልቅ ነገሮች እንዳሰብነው ላይሄዱ ይችላሉ ።መኪና ለመለማመድ ለፈተና የቀረበ ሰው ዛሬ ፈተናውን ማለፍ አልቻለም ማለት ነገም ማለፍ አይችለም ማለት አይደለም ።ለሥራ ለመቀጠር ፈተና ወስዶ ትላንት የሞከራቸው ቦታዎች ላይ ያልተሳኩለት ሰው ሁሉም ቦታዎች ላይ አይሳኩለትም ማለትም አይደለም ።የጋብቻ ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ የሆነበት ሰው ሁሌም ውድቅ ይሆንበታል ማለት አይደለም ።በፖለቲካ ምርጫ በአንድ ዙር የተሸነፈ የፖለቲካ ማህበር ሁሌም ይሸነፋል ማለት አይደለም ።ሌሎች ብዙ እንዲህ መሰል እንዳሰቡት ያለመሆን ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል ።ዋናው ነጥቡ ግን ይህ በሆነ ጊዜ የሚኖረን ምላሽ ነው ።
ለጋብቻ ላቀረበው ጥያቄ ይሁንታን ያላገኘው ሰው ለምን አላገባሽኝም ብሎ ሞቼ እገኛለሁ ካለ ነገሮች መስመራቸውን ይስታሉ፤ በውድቀት መጥፋት ውስጥ ራሱን ይከታል ።በፖለቲካ ምርጫ ተሸንፎ ሳለ በፍጹም አሸንፌያለሁ ብሎ ግብግብ ውስጥ መግባትን የመረጠ፤ በውድቀቱ መጥፋት ውስጥ ራሱን ይከታል ።ያሰቡትን በየትም ፈጭቶ ይዞ ለመገኘት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ውድቀቱ በሌላ ውድቀት እየተባዛ ወደ ጥፋት ያመራል። ወደ ዩኒቨርሲቲ በትልቅ ተስፋ የገባች ወጣት፤ ከዩኒቨርሲቲ በውጤት መጥፋት በምትባረርበት ወቅት ለገጠማት ውድቀት የምትሰጠው ትርጉም ከውድቀት መጥፋትን ይወስናል። ከእዚህ በኋላ ተስፋ እንደሌላት በመቁጠር ገላውን ሸጦ ለማደር መወሰን እርሱ መጥፋት ነው። ውድቀቱ በዓላማ ጽናት ታጅቦ እጅ ባለመስጠት ወደ ፊት መጓዝ ይገባል እንጂ ወደ ጥፋት መሄድ መፍትሄ አይሆንም። የጋብቻ ጥያቄው ውድቅ የሆነበት ሰውም እግዚአብሔር የተሻለ ሰው ለእኔ ያዘጋጃል በሚል እምነት ራሱን መምከር ይገባዋል እንጂ ሌላ የስንፍና መንገድን ማሰብ የለበትም። በስንፍና መንገድ ገብቶ ራሱንም ሆነ ሌላ ሰውን ለመጉዳት መራመድ ሲጀመር ያኔ ውድቀት ወለድ መጥፋት ውስጥ ራሱን ያገኛል ።
በውድቀት ከመጥፋት ለመጠበቅ መፍትሄው ምንድን ነው የሚለው እንዲሁ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። ምላሹም ባህሪን መገንባት በየትኛውም ጊዜ የሚል ነው።
ባህሪን መገንባት
የዛሬ ባህሪ የብዙ ትላንቶችን ውጤት ነው ።ባህሪ በአንድ አዳር መቀረጽ የሚችልም አይደለም ።ባህሪ የእኛነታችን ማሳያ መስታወትም ነው ።ባህሪ አንዳችን ከሌላችን የሚለየን ዋነኛው መለያችን ነው ።ስለባህሪ ብዙ ማለት ይቻላል ።
ሥኬት ወለድ ከሆነ ውድቀት ለማምለጥ መንገዱ ከሥኬት በፊት የተገነባ ባህሪ መያዝን ነው ።ራስን በባህሪ መቅረጽ ትኩረት የሚያሻው መሆኑን የምንረዳው በባህሪ መዝቀጥ ምክንያት የሚፈጠረው መደበላለቅ አስከፊነቱን እኛ ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ የተመለከትን መሆናችን ነው። የፖለቲካው መድረክ የፊት ለፊት ሰዎች ከባህሪያቸው የተነሳ በሚወስዷቸው ውሳኔዎች ለሚሊዮኖች አንገት መድፋት ምክንያትም ሆነው ይታያሉ። ባህሪ በቤተመቅደስም ውስጥ እንዲሁ አስፈላጊነቱ ትልቅ ሆኖ ይስተዋላል ።የባህሪ ችግር የሰዎችን ጸጋ መካፈል እንዳንችል ፍላጎታችንን የሚዘጋም ሆኖም ይገኛል ።
ከሥኬት ወለድ ውድቀት ለመውጣት የባህሪ ግንባታ ፍቱን መድሃኒት ብቻም ሳይሆን ግዴታ አድርገን ልናየው ይገባል። ከውድቀት ወለድ ጥፋት ተቆጥቦ ረጅም ጉዞ በዓለማ ጽናት ለመሄድ የባህሪ ቀረጻ አይነተኛ መፍትሄ ነው።
ማንኛውም ሰው ስለ ባህሪ ማወቅ ያለበት ነገር ምንድን ነው?
1. ባህሪ ከንግግር በላይ ነው፤
ማንኛውም ሰው የህይወት ንጽህና እንዳለው ሊናገር ይችላል፤ ነገርግን ድርጊታችን የባህሪያችን ትክክለኛ ማሳያ ነው ።የአንተ ባህሪ ማን እንደሆንክ የሚናገር ነው። አንተ የሆንከው ነገር የምታየውን ይወስናል። የምታየው ደግሞ የምትሰራውን ይወስናል።ለእዚያ ነው የአንድን ሰው ባህሪ ከተግባር ስራው ነጣጥሎ ማየት የማይቻለው። የአንድ ሰው ድርጊት እና እሳቤ የተምታታ ሆኖ ስታገኘው ባህሪውን በመመልከት ምክንያቱን ማወቅ ትችላለህ ።
2. ተሰጥኦ ስጦታ ሲሆን ባህሪ ግን ምርጫ ነው
ታዋቂነትን ያገኙ ሰዎች ታዋቂነቱን ያገኙት በተሰጥኦቸው ሊሆን ይችላል ።ተሰጥኦ ደግሞ ስጦታ ነው ።ባህሪ ግን በምርጫችን የምናሳድገው ።በብዙ የህይወት ነገሮች ላይ በራሳችን ቁጥጥር ማድረግ ወይንም መወሰን አንችልም ።ለምሳሌ እናትም ሆነ አባት መርጠን አልተወለድንም ።የተወልድንበት ቦታም እንዲሁ ለመምረጥ አቅሙ አልነበረንም ።እኒህን መሰል ሌሎች በርካታ ነገሮችን ያለ ራሳችን ቀጥተኛ ውሳኔ አላገኘንም ።በራሳችን ቀጥተኛ ውሳኔ ላይ ከተመሰረቱ ነገሮች መካከል ግን አንዱ ባህሪያችን ነው ።ባህሪያችንን እንደሚፈለገው አድርጎ የመቅረጽ እድሉ ግን በራሳችን እጅ ላይ የሚገኝ ነው ።እርሱም ሥኬትንም ሆነ ውድቀትን መሸከም እንድንችል የሚረዳን ።
3. ባህሪ በሰዎች ላይ የሚታይ ዘላቂ ተጽእኖን ያስፈጥራል፣
ትክክለኛ አመራር ሁልጊዜ ሰዎችን አሳታፊ ነው። “መሪ ሆነህ የሚከተሉህ ሰዎች ከሌሉህ እየመራህ ሳይሆን እየተራመድክ ነው ማለት ነው” የሚባለው ታዋቂ የመሪነት አመራር የመጣው ከእዚህ አንጻር ነው። ተመሪዎች በመሪዎቻቸው ባህሪ ላይ የተመሰረተ መመራትን ይፈልጋሉ። ተመሪዎች ባህሪያቸው ጥሩ ባልሆኑ ሰዎች የመመራት ፍላጎት የላቸውም ።ባህሪ የሚከተሉህን ሰዎች እንዲያበዛ ያደርጋል ።ማስከተል መቻል ደግሞ ዓላማን ለማሳካት የሚረዳ የሥኬት መንገድ ላይ ለመገኘት የሚያግዝ ነው፡፡
4. መሪዎች ከባህሪያቸው ተጽእኖ በላይ መሄድ አይችሉም
ሰዎች በአንድ ነገር ተሰጥኦ ያላቸው ሆነው በእዚህም ምክንያት ታዋቂ ሆነው ከቆይታ በኋላ ግን ከስኬታቸው ወድቀው ተመልክተህ ታውቃለህ? ለእዚህ ዋና ምክንያቱ ባህሪ ነው ።ሰዎች እጃቸው ከገባው ስኬት በላይ ስኬታቸውን መሸከም የሚችል ባህሪ እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይገባል ። ጠንካራ ባህሪ ላይ ያልተገነባ ስኬት ለሞገደኝነት፣ ብቸኝነት፣ ቅጽበታዊ ተዓምር ፈላጊነት እና ሴሰኝነት ተጋላጭ እንደሚያደርግ በአንድ እውቅ አጥኚ የቀረበ የጥናት ሪፖርት ያሳያል ።እነዚህ ነገሮች ለደካማ ባህሪ የሚከፈሉ ትልልቅ የህይወት ዋጋዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ያልተገቡ አራት ባህሪዎች ማለትም ሞገደኝነት፣ ብቸኝነት፣ ቅጽበታዊ ተዓምር ፈላጊነት እና ሴሰኝነት በአንተም ህይወት ውስጥ የሚታይ እንደሆነ ካሰብክ ጊዜ ሰጥተህ ለማሰብ ወስን ።ስኬትህ ከፈጠረብህ ተጽእኖ በሂደት ለመውጣትም የባለሙያዎችን እገዛም ጠይቅ። ያለህበት ችግር በገንዘብ ብዛት፣ ጊዜ በረዘመ ሁኔታ ወይንም በተጨማሪ ክብር ውስጥ ይፈታል ብለህ አታስብ። በጊዜው መፍትሄ ያልተሰጠው ያልተገባ ባህሪ ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ በጊዜ ሂደት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ማሰብ ይገባሃል፡፡
በአራቱ ማሳያዎች ውስጥ አሁን እየተቸገርክ ካልሆንክ ምልክቶች መኖራቸውን ግን መመርመሩ መልካም ነው። እራስህን ጠይቅ ቃልህና ተግባርህ ሁልጊዜ አብረው የሚሄዱ መሆናቸውን ።ለልጆችህ የገባህላቸውን ቃል ለመፈጸም ትችላለህ? ሰዎች እጅህን ለስራ ውል ሲጨብጡ በቃልህና በተግባርህ እየታመኑብህ ነው?
ሰዎችን በቤትም፣ በስራ ቦታም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ስትመራ ባህሪ ትልቁ ሃብትህ መሆኑን አትዘንጋ። ባህሪን መቅረጽ እንዲሁም ባህሪን ማስተካከል ሥራን ይፈልጋል ።
ባህሪን ማስተካከያው መንገድ፣
ጆን ማእክስዌል የተሰኙ ጸሃፊና ተናጋሪ ባህሪያችን እንዴት ማስተካከል እንደምንችል ሲጽፉ የሚከተለውን ብለዋል ።
ሀ) ክፍተት ያለበትን አቅጣጫ መፈለግ፡- የህይወትህን ወሳኝ የሆኑትን ነገሮችን ማለትም ሥራ፣ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ አገልግሎት ወዘተ አካሄድ ምርምርና ክፍተት ያለበትን አቅጣጫ ለይ። በባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ዘርዝረህ ጻፋቸው ።
ለ) አካሄዱን ገምግም፡- በዝርዝር የጻፍካቸው ክፍተቶችን በመመልከት የተፈጠሩ ክፍተቶች ወይንም ተግዳሮቶች አካሄዳቸው ምን አይነት መስመር እንዳለው ለመመልከት ሞክር ።አንድ የተለየ ነገር ላይ ጎልቶ የሚታይህ ክፍተት ይኖር ይሆን?
ሐ) ስሜቱን መጋፈጥ፡- ባህሪን ለማስተካከል የሚደረገው ስራ ይቅርታ በመጠየቅ ይሁን በሌሎች ድርጊትን የተከተሉ ነገሮችን በመጋፈጥ ውስጥ ነው ።ስላደረካቸው ነገሮች ይቅርታን ልጠይቃቸው የሚገቡ ሰዎችን ስም ዝርዝር ጻፍ እናም ከልብ የሆነ ይቅርታን ጠይቅ፡፡
መ) መልሶ ማነጽ፡- ስላለፈው ነገር ልትጋፈጥ የሚገባህ አንዱ ነገር ይህ ነው። ይህ ሌላ አዲስ ነገርን የምትፈጥርበት ነው። እርሱም ትላንት የሰራኸውን ስህተት ነገ ላለማድረግ የምታደርገው በተግባር እቅድ የተደገፈ እርምጃ ነው ።
ጨረስን .. ሥኬት ወለድ ውድቀት በህይወታችን እንዳይገጥመን እንዲሁም ውድቀት ወለድ ከሆነ ከመጥፋት ለመቆጠብ ዛሬ ቀን ሳለ በባህሪያችን ላይ መስራት ይሁንልን ማለታችንን ደጋግመን እናስበው ። ባህሪያችን ላይ መስራት ምርጫችን ካደረገን ከዛሬ የተሻለ ቀን የለምና ዛሬን እንጠቀምበት። በጠንካራ ባህሪ ላይ የተገኘ ሥኬት ወደ ሌላ ሥኬት የሚያመራ ይሆናል እንጂ የውድቀት ምንጭ አይሆንም ።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጠንካራ ባህሪ ባለቤት በሆነ ሰው ላይ የሚመጣ ውድቀት ወደ ጥፋት የሚያመራ ሳይሆን በጽናት ወደ ሥኬት ለመድረስ ትምህርት ቤት የሚሆን ነው ።ቶማስ ኤድሰን እንዲህ አለ “የብዙ ሰዎች የሕይወት ውድቀት ማሳያው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ በገቡ ጊዜ ወደ ሥኬት እየደረሱ መሆኑን አለመረዳት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም