መርድ ክፍሉ
ሰው ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አዕምሮ ባለቤት መሆኑ ነው። ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች የሚያደርገው ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጥሩ ባህልና እንደጽድቅ የሚቆጠር በጎ ተግባር ነው። ብዙ ሰው እርዳታን ለፈጣሪው ይበልጥ የሚቀርብበት መንገድ አድርጎ ስለሚቆጥረው በተለያዩ አካባቢዎች ድሆችን መርዳት የተለመደ በጎ ተግባርም ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት ከተወሰኑ ወቅታዊ ሁኔታዎችና ምክንያቶች ጋር እየተያያዙ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚሉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች አገራት የምንሰማቸው የራስ ወዳድነትና ግለኝነት ባህርያት ተዛምተውብን ከመተዛዘን ይልቅ መጠፋፋት፤ ሌሎችን ከመርዳት ይልቅ ለራስ ብቻ እስከመኖር የደረስንባቸው አጋጣሚዎችን እንመለከታለን። የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ህጻናትና አረጋውያን ባሉባት አገር በብዙ ሚሊየን ብር የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ የማስገባትና ለልደትና ለሌሎች የደስታ ዝግጅቶች ብዙ ሺህ ብር የማውጣት አባዜ የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት ስለመኖራቸው በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ረጂና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ወገኞች በዘመቻ መልክ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።መንግስትም የእለት ቀለብ ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችንና ቁሳቁሶችን ለግሷል።የደሴ ከተማ ነዋሪዎቹ ዘላለም ካሳሁንና ጓደኞቹ ‹‹እናትዬ ደሴ የአረጋውያን መርጃ ማህበር›› በተባለ ማኅበራቸው በኩል ለአረጋውያን እንክብካቤና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።ማህበሩን የመሰረተው ወጣት ዘላለም ካሣሁን ቢሆንም ከተመሰረተ በኋላ በርካታ በጎ ፈቃደኞች አግዘውታል።ማህበሩ ተመስርቶ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ ዘጠኝ ወራትን አስቆጥሯል።
ወጣት ዘላለም እንደሚናገረው፤ መጀመሪያ ከሆቴል ምግብ ተከራይቶ አቅመ ደካሞችን መመገብ ጀመረ። በመቀጠል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ገንዘብ እንዲሰበሰብ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ከ250 በላይ አረጋውያንን የመመገብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።ከቤት መውጣት ለማይችሉ 50 አረጋውያን ደግሞ ቤታቸው ድረስ ምግብ እንዲቀርብላቸው ይደረጋል። በተጨማሪም የስኳር ህመም ላለባቸው አረጋውያን ቁርስ፣ ምሳና እራት ወደ ቤታቸው ይወሰድላቸዋል።
ማህበሩ ሲመሰረት ተግባሩ ምግብ ማግኘት የማይችሉ አረጋውያንን ምግብ እንዲያገኙ ማስቻል እንደነበር የሚናገረው ወጣት ዘላለም፤ መንገድ ላይ ወድቀው የሚገኙ አረጋውያንን ለመርዳት ቅድሚያ ሻይ በዳቦ እንዲበሉ በማድረግ ስራው እንደተጀመረ ያስታውሳል። በመቀጠል ምሳ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻቸ። ከዚያም አሁን አረጋውያኑ በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ይጠቅሳል።
በአሁኑ ወቅት በበጎፈቃድ የሚሰሩ 78 ወጣቶች ያሉ ሲሆን ወጣቶቹ በማብሰል፣ በማብላት፣ እቃዎችን በማጠብ፣ እንጀራ በመጋገር እና ወጥ በመስራት እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። አረጋውያኑን ለመርዳት ከግላቸውና ከአካባቢው ማህብረሰብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያመለክታል። ‹‹የመንግሥት አካላት እስካሁን ምንም አይነት እገዛ አላደረጉም›› የሚለው ወጣት ዘላለም፤ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠቀሙበት ብሎ የሰጠውን ሀብት የከተማ አስተዳደሩ ለመስጠት በመዘግየቱ ሀብቱ ለአራት ወራት መጋዘን ውስጥ ታሽጎ እንዲቀመጥ መደረጉን ይናገራል።
የተቸገረን መርዳት ላይ ክፍተት መኖሩ ማህበሩ እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች መካከል ይጠቀሳል። ከባለሀብቱ የሚደረገው ድጋፍ መደበኛና ቀጣይነት ያለው አለመሆኑም በድጋፍ አሰራሩ ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም ይጠቁማል። ማኅበሩ በሰራቸው ስራዎች ተዝካር፣ ልደት፣ ሰርግ እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ከአረጋውያን ጋር እንዲያከብሩ እየተደረገ ነው። በህብረተሰቡ ድጋፍ የቆርቆሮ ቤቶች ተሰርተው መጠለያ ለሌላቸው አረጋውያን ተሰጥቷል። በሌላም በኩል ወጣቶችን በማስተባበር በየሳምንቱ የአረጋውያኑን ገላ የማጠብና ፀጉራቸውን የማስተካከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ወጣት ዘላለም ይገልፃል።
በቀጣይ ማህበሩ እውቅና እንዲያገኝ ህጋዊ ሰነዶች እየተዘጋጁ ነው። የከተማው አስተዳደር ለማህበሩ የሚሆን ቦታ ሰጥቷል። ከከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው ቦታም አረጋውያኑ አንድ ቦታ ሆነው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ያግዛል። በተጨማሪም ማኅበሩ ህፃናትንና ሴቶችንም የማገዝና የመርዳት እቅድ አለው።ነገር ግን ማዕከሉን ለመገንባት የአቅም እጥረት ፈተና ሆኗል። በዚህም በቀን ሁለት ጊዜ የማብላቱ ሁኔታም እየቀነሰ መጥቷል። መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ወጣት ዘላለም ያመለክታል።
እስካሁን አረጋውያኑን ለመርዳትና ለመደገፍ በህጋዊ መንገድ ባለሀብቶችን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በአካባቢው የሚገኙ ባለሀብቶች የማህበሩ አባል እንዲሆኑ ተደርገዋል። በደሴ ከተማ የሚገኙ ንግድ ሱቆች በየወሩ መዋጮ እንዲያዋጡ የማሳመን ስራዎች ተሰርተው የንግድ ሱቅ ያላቸው ሰዎች በየወሩ መቶ ብር ለማዋጣት መስማማታቸውን ወጣት ዘላለም ይገልፃል።
‹‹መልካምነት ለራስ ነው። አረጋውያን የአገር ሀብትና ታሪክ ናቸው። አረጋውያኑን መንከባከብ ለአገርና ለራስ ከፍተኛ ጥቅምና ደስታ ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ስራ የለኝም። በገንዘብ የማይገኝ ደስታን አረጋውያንን በመርዳት ማግኘት ችያለሁ። በቅርቡ የመኪና አደጋ ደርሶብኝ ነበር። ከአደጋው ያለምንም ጉዳት መትረፍ ችያለሁ። መልካም ስራ ለራስ ነው የሚጠቅመው። በመተጋገዝ አረጋውያንን መርዳት ያስፈልጋል። ደግነት በመስጠት ሳይሆን ከችግረኞች ጋር አብሮ በማሳለፍም ይገለፃል›› ይላል።
ሌላው የማህበሩ አባል የሆነው ወጣት ሚካኤል ጆርጅ በደሴ ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ደሴ አካባቢ በጎ አድራጎት ላይ ከሚሳተፉ ሰዎች ጋር ተቀላቀለ። ማህበሩ በኮቪድ 19 ወቅት ችግረኞችንና ረዳት የሌላቸውን ሰዎች ለመደገፍ ከወጣት ዘላለም ካሳሁን ጋር አብሮ መስራት ጀመረ። የእርዳታ ስራው ለተከታታይ አምስት ወራት የዘለቀ ሲሆን ምሳ በማብላት፣ ልብስ በመግዛትና በማልበስ እንዲሁም መጠለያ ለሌላቸው ደግሞ የቆርቆሮ ቤቶች እንዲሰራላቸው ተደርጓል።
ወጣት ሚካኤል እንደሚናገረው፤ መጠለያ ለሌላቸው አረጋውያን የቆርቆሮ ቤቶችን በመስራትና ከ250 በላይ የሚሆኑ አረጋውያንና ችግረኞችን ምሳ የማብላቱ ስራ እንዲሁም ወደ መመገቢያው አካባቢ መምጣት የማይችሉ ሰዎችን ደግሞ እቤታቸው ምግብ ይወሰድላቸዋል። ይህ ስራ ለወራት የዘለቀም ነበር።ስራውን ለማከናወን ከአካባቢው ማህበረሰብ በሚገኝ የእርዳታ ገንዘብና ሰዎች በሚያመጡት ምግብ በተደራጀ መንገድ ሲሰራ ነበር። አብዛኛው ሰው ልደት፣ ተዝካር፣ ሰደቃ፣ ሰርግና ፀበል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስለማያከናውን ወደ ማህበሩ በማምጣት ድጋፍ ያደርግ ነበር።
በአሁን ወቅት ግን የድጋፍ ሁኔታዎቹ እየቀነሱ በመምጣታቸው ማህበሩ ቋሚ የሚባል እንቅስቃሴ ለማድረግ መቸገሩን ወጣት ሚካኤል ይናገራል። ችግሩን ለመፍታት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ካምፓስን ለማነጋገር ሙከራ ቢደረግም ለውጥ አልመጣም። ማህበሩ የሚገኝበት ክፍለከተማም ሩዝና ዘይት እርዳታ ካደረገ በኋላ ዝምታን መምረጡን ይጠቅሳል። ማህበሩን የሚረዳ ምንም አይነት ቋሚ የሆነ የመንግሥት አካል ስለሌለ ለአረጋውያኑ የሚደረገው እንክብካቤ እየቀነሰና የማኅበሩም ችግር እየከበደ መምጣቱን ይናገራል።
አረጋውያኑ ሰዓታቸውን ጠብቀው የሚመገቡበት ሁኔታ እየቀነሰ ነው። አብዛኛዎቹ ተረጅዎች መጠለያ የሌላቸውና በየቤተ እምነቱ አካባቢ የሚኖሩ መሆናቸውን ወጣት ሚካኤል ይጠቅሳል። ከተረጅዎቹ መካከል አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን ህፃናትና ሴቶች በብዛት እንደሚገኙበት ይጠቁማል። የደሴ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤትም የማህበሩን እንቅስቃሴ ቢያውቀውም ድጋፍ አላደረገም። ማህበሩን ለማስፋት በወልድያና በቆቦ ድጋፍ ለማድረግ እቅድ ይዞም እንደነበር ወጣት ሚካኤል ይጠቁማል። በደሴ ከተማ ውስጥ በሌሎች ክፍለ ከተማዎች ላይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲጀመር የልምድ ልውውጥ መደረጉን ያስረዳል።
ይህንን የበጎ አድራጎት ስራ ክፍለከተማውም ሆነ ባለሀብቶች ሊደግፉት ባለመቻላቸው ማህበሩ እየተዳከመ መጥቷል። ድጋፍ እናደርጋለን የሚሉ አካላት ማህበሩን ቢጎበኙትም ፎቶ ተነስቶ ከመሄድ የዘለለ ስራ ሰርተው እንደማያውቁ ያመለክታል። ማህበሩ ሲመሰረት በጣም የተቸገሩ ሰዎችን ለይቶ ለመደገፍ ያለመ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ሚካኤል፤ በተጨማሪም ቤት የሌላቸውና አጉራሽ ለሌላቸው ሰዎች እስካሁን ቤት ተሰርቷል። ማህበሩ ድጋፍ ካገኘ እንደ መቄዶንያ አይነት ማዕከል ለመስራት ውጥን እንዳለው ያስረዳል።
በማህበሩ ስር ሊረዱ የሚገባቸው ሰዎችን አንድ ማዕከል ውስጥ ለማስገባት ባለሙያዎች በተገኙበት ጥናት ተደርጓል። ነገር ግን አረጋውያኑና ችግረኞቹ ቅድሚያ መመገብ መቻል አለባቸው። አረጋውያኑና ተረጂዎቹ ምሳ ለመብላት ቀደም ብለው በቦታው የሚሰበሰቡ መሆናቸውን ወጣት ሚካኤል ይገልፃል። ሚካኤል እንደሚለው፣ ድጋፉን ለማስቀጠል ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ መሳተፍ መቻል አለባቸው። በደሴ ከተማ አትርፈው የሚኖሩ ባለሱቆች፣ ባለሆቴሎችና ሌሎች ግለሰቦች ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። የደሴ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት እንደዚህ አይነት ድጋፍ የሚያደርግ ማህበር በግለሰቦች ተደራጅቶ ሲሰራ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር። ነገር ግን ከንቲባ ፅሕፈት ቤቱና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ምንም አይነት ድጋፍ እያደረጉ አይደለም። ማህበሩ የሚገኝበት ክፍለከተማ የመሬት ጥቄዎችን እየመለሰ እንደሚገኝ ይናገራል።
ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሮ ኢክራም ብርሃነመስቀል እንደሚሉት፤ ማህበሩ ሲመሰረት ዋና ዓላማ የነበረው ጎዳና ላይ የወደቁ አረጋውያንና ደጋፊና ጧሪ ያጡ ሰዎችን ለመርዳት ነበር። ስራው የተጀመረው የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ሲሆን ለተከታታይ ወራት ድጋፉ እየተካሄደ ነው።
በአሁን ወቅት ግን ማህበሩ ባጋጠመው የእርዳታ እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው። ህብረተሰቡ ቀን በቀን እርዳታ ሲጠየቅ ፊት የመንሳት ሁኔታዎች እንዳሉም ወይዘሮ ኢክራም ይጠቅሳሉ። ማህበሩ እንደተጀመረ ለተከታታይ ሦስት ወራት አቅም ስላልነበር በራሳቸው ቤት ምግብ ያበስሉ ነበር። ወይዘሮ ኢክራም ባለትዳርና የልጆች እናት ቢሆኑም አረጋውያኑን ለመርዳት በቤታቸው ምግብ እያዘጋጁ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ይገልፃሉ።
አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ እንቅስቃሴዎች በመቀነሳቸውና ድጋፍ የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመጥፋታቸው ለአረጋውያኑ የሚደረገው እንክብካቤ እየቀነሰ መጥቷል። አረጋውያኑ በቀን አንድ ጊዜ እንኳ እንዲመገቡ በዱቤ የምግብ ፍጆታዎች እየተገዙ እንደሚገኙ ወይዘሮ ኢክራም ያስረዳሉ። መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።መጠለያ ለሌላቸው አረጋውያን ጊዜያዊ ቤት ከመስራት አንስቶ ቤት ተከራይቶ እስከማስቀመጥ የደረሰ ስራ መከናወኑን ያመለክታሉ።
የማህበሩ አባላት የግል ህይወታቸውን ትተው አረጋውያኑን እየተንከባከቡ የሚገኙ ሲሆን መንግሥት ትኩረት ቢሰጥ ተጨማሪ ሰዎችን መደገፍ ይቻላል። የደሴ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤትን ለማነጋገር ሙከራዎች ቢደረጉም በስብሰባ ምክንያት ሊገኙ አልቻሉም። ነገር ግን ማህበሩ የሚገኝበት የቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ለአረጋውያኑ ምግብ መመገቢያ ቦታ መስጠቱን ወይዘሮ ኢክራም ይጠቅሳሉ።
ቀደም ብሎ ወይዘሮ ኢክራም መኖሪያ ቤት ውስጥ ምግብ በማዘጋጀት ለአረጋውያኑ ይሰጥ የነበረ ሲሆን በዚህም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገብተው እንደነበርም ይጠቁማሉ። አብዛኛው ሰው የቆሸሸ ልብስ የለበሰ ሰው ካየ የመናቅና የኮቪድ 19 ህመም ያለበት ሰው አድርጎ የመቁጠር ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ። ከክፍለ ከተማው የተሰጠውን ቦታ ለረጅም ጊዜ የማፅዳት ስራ መከናወኑንና ምግብ ማብሰያ የሚሆን ዳስ ተሰርቶበታል። በቀጣይ ቦታው ላይ ዘላቂነት ያለው ስራ ለመስራት የታሰበ ሲሆን የማህበሩ አባላት ባላቸው ሰዓት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም መጀመሪያ አካባቢ እንደነበረው አይነት ትጋት በሁሉም ላይ እንደማይታይ ወይዘሮ ኢክራም ይገልፃሉ።
በተጨማሪም ስድስት ህፃናት ማስቲካ እያዞሩ እንዲሸጡ ድጋፍ መደረጉን በመጥቀስ፤ ለአረጋውያን እየተደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ማህበሩ ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚሻና ለጋሽ ድርጅችም ከመጎብኘት ባለፈ ቋሚ የሆነ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም