ልጆች ለትልቅ ሀላፊነት የሚበቁትና በየደረጃው ሀላፊነትን መወጣት የሚችሉት በስነምግባር እና በእውቀት ጎልብተው፤ እንክብካቤ አግኝተው ማደግ ሲችሉ ነው። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ሀላፊነት የሚወድቀው በወላጆች እና በአሳዳጊዎች ላይ ነው። ትምህርት ቤትና ማህበረሰብም የዚህ ሀላፊነት አካል መሆኑ ይታመናል። ሆኖም ግን ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻችን ራሳቸውን ችለው ህይወታቸውን መምራት እስኪችሉ ድረስ በእለት ተእለት አኗኗራቸው ጣልቃ እየገባን የማስተካከልና የማመቻቸት ሃላፊነት አለብን። በተለይ በዚህ በኮቪድ 19 ወረርሸኝ ወቅት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ልጆች እቤት እንዲውሉ ተገደዋል። እቤት በመዋላቸው ደግሞ መሉ ጊዜያቸውን አብረናቸው እናሳለፋለን።
በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ወላጆች የልጆቻቸውን የአእምሮ እድገትና የእውቀት ምጡቅነት እንዲሁም አጠቃላይ የስብእና ደህንነት ለማመቻቸት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውባቸዋል። ከፈተናዎቹ ጥቂቶቹ የቴክኖሎጂውን አይነት (ሞባይል፣ ኢንተርኔት ሳይት፣ ቪዲዮች፣ ወዘተ) ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ልጆቻቸው ለምን ያክል ሰዓታት ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዳለባቸው መወሰን ድረስ ናቸው። የብዙዎቻችን ውሳኔ በዘፈቀደ የሆነ እንደሆነ ለልጆቻችን ብዙም ስለማይጠቅም የሚከተሉትን አራት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መመሪያ ክህሎቶች ማዳበሩ ይረዳል።
1. ያለንና ልጆቻችን ሊገለገሉበት የሚችሉትን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ችሎታ
2. ማህበረሰባችን የሚጠብቅብንን የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን)ና የማህበራዊ እሴቶች እውቀት
3. የፈጠራና ችግር ፈቺነት ችሎታ
4. በምናገኘው የቴክኖሎጂ አቅርቦት አስፈላጊና ዘላቂ የህይወት ሙሉ ጠቃሚ ትምህርት እና እውቀትን ለይቶ የማወቅና ለልጆቻችን የሚበጀውን የመምረጥ ችሎታ ናቸው።
ብዙዎቻችን ልጆቻችን ከኛ የበለጠ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ችሎታ እንዳላቸው እናውቃለን። ይህን ለማስታረቅ ታዲያ አጠገባቸው ተቀምጠን ያልገባንን እየጠየቅን መማር ነው። ይህ ድርጊት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከልጆቻችን ጋር በመቀመጥ ሃሳብ እንጋራለን፤ በዚህም ግንኙነታችን ይጠነክራል፣ ልጆቻችንም የተግባቦትና የማህበራዊ ግንኙነት ችሎታቸውን ያዳብራሉ። የእነሱን የችሎታና የዝንባሌ ወሰን እንድንረዳም ይረዳናል፣ ወደተገቢው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማምጫ መንገዶችን እንድናስብ ይረዳናል። ልጆቻችን ሲጫወቱ አብረን መጫወትም አብረን እንድንማርና ልጆቻችን ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንደሌሎቹ የእለት ተእለት ክንውኖች ሁሉጊዜ ሊገደብለት ይገባል። ሚዛኑን የሳተ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የአካልና የአእምሮ ጤንነትን ያቃውሳል፣ በቤተሰብ መካከልም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖርን የማህበራዊ ግንኙነት ያዛባል። ልጆች የሚያዮአቸው ፊልሞች፣ የሚጫወቷቸው የቪዲዮና የመሳሰሉ ጨዋታዎች ከአኗኗር ዘዴዎቻችንና ከማህበራዊ እሴቶቻቸን ያለወጡ፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ተግባቦት የማያደናቅፉ መሆን ይገባቸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ወላጆች የሚጠበቁትን ማህበራዊ እሴቶችና የተግባቦት ዘዴዎች ማወቅ ብቻ ሳይሆን እየኖሯቸው ማሳየት ይገባቸዋል።
ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
አልማዝ ባራኪ (ዶ/ር)