ባህል በትውልድ ቅብብሎሽ፣ከጊዜ ወደ ከጊዜ እየተሻሻለ እና እየተለያየ ቢሆንም የትናንትን ማንነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የዛሬ መሰረታችንን የሚነግረን የነገ መንገዳችንን የሚጠቁመን ወዘተ… ሀብት ነው። በመሆኑም ትናትናም ሆነ ዛሬ ባለንበት ዘመን የሰው ልጅ ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስናቸውን ባህላዊም ሆነ ተፈጥሯዊ ቅርሶች የራሱ አድርጎ መያዝ ይገባል።
አገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት እና የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ በመሆኗ እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱ ወግና ባህል አለው። ከዚህ ውስጥ አንዱ የጋብቻ ስርዓት ነው። ጋብቻ በሁለት የተለያዩ ጾታዎች መካከል በፍቃደኝነት ህይወትን በጋራ ለመምራት እና ለመኖር የሚፈጸም በውል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲሆን የቤተሰቡ መሰረት እና የህብረተሰብ ዕድገት ዋስትና ነው።
በኢትዮጵያ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የጋብቻ ስነ ስርዓት አፈጻጸም አላቸው። ብሔር ብሔረሰቦች እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ እንደማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግዴታቸውን፣ደረጃ እና የራሳቸው የሆነ ባህል ወግ መሰረት ያደረጉ የበለጸጉ የጋብቻ ስነ ስርዓቶች ይፈጽማሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የአርጎባ ብሔረሰብ አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ የሆነውና የበለጸገ ባህል ባለቤት የሆነውን የአርጎባ ብሔረሰብ የጋብቻ ስርዓት ምን እንደሚመስል እናያለን። ለዚህም የተለያዩ ብሔረሰቦችን ባህል በማጥናት የሚታወቁትን አቶ ካሱ ከበደን እንግዳ አደርገናል። አቶ ካሱ መምህር ፣የቤተመጽሐፍት ባለሙያ ፣ተርጓሚ እና በኢትዮጵያ በሚገኙ ብሔረሰቦች ባህል ላይ ተመራማሪ ናቸው።
ጅማሮ
የአርጎባ ልዩ ወረዳ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካሉ 32 ወረዳዎች አንዷ ስትሆን በምሥራቅ የአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ በስተ ምዕራብ የአማራ ክልል አንኮበር ወረዳ በስተሰሜን የአማራ ክልል ጣርማበር ወረዳ በስተደቡብ የአማራ ክልል በረኸት ወረዳ ያዋስኗታል። ወረዳዋ በ13 ቀበሌ የተከፋፈለች ስትሆን ከዚህ ውስም ጋቸኔ ለወረዳው እንደ ዋና ከተማነት የምታገለግል ናት። የወረዳው አጠቃላይ የመሬት አቀማመጥ ተራራማና ተዳፋት የበዛበት የአርጎባ ልዩ ወረዳ በአብዛኛው ወይም 95 በመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ቆላ ስትሆን 5 በመቶ ደግሞ ወይና አደጋ ነው።
በአርጎባ ብሔረሰብ ባህል መሰረት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለጋብቻ የደረሰ ወጣት ካለ ለቤተሰቦቹ “እከሊትን ልቤ ፈቅዷታልና አጋቡኝ” ብሎ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት አቶ ካሱ የልጁንም ጥያቄ መሰረት በማድረግ የልጁ ወላጆች የልጅቷን ማንነት ይለያሉ፤ ቀጥሎም ልጃቸው ለማግባት ስለፈለጋት ልጃገረድ በቂ መረጃ ለማግኘት ለሙሽርነት የታሰበችው እንሰት ላይ እንድ ጓደኛ ሆና የምትሰልላት ሌላ ሴት ይልኩባታል። የተላከችሁ ሴት በድብቅ ስለ ልጅቷ መረጃ ታሰባስባለች፤ የልጅቷ አጠቃላይ ሁኔታ መታጨቷንና አለመታጨቷን ጨምር ታጣራለች። የወንዱ ቤተሰቦች አለመታጨቷን እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ከሰላይዋ ከአገኙ በኋላ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈሩ እና የተከበሩ የሀገር ሽማግሌዎችን በመምረጥ ወደ ሴት ቤት ይልካሉ፤ይህም የመጀመሪያ ሽምግልና ስርዓት ይሆናል።
አቶ ካሱ ይናገራሉ የሽማግሌዎቹን ጥያቄ ከሰማ በኋላ የልጅቷ አባት ጋብቻውን ካልተቀበለው ልጅቷ አልደረሰችም በማለት አለመፈለጉን የሚያንጸባረቁ ቃላትን በመደርደር ሽማግሌዎችን እምቢታውን እንዲያውቁ ያደርጋል። ጋብቻውን የሚፈልግ ከሆነ ግን የሽማግሌዎቹን ጥያቄ በመቀበል ከዘመድና ከቤተሰብ ጋር ልምከር በማለት ለሌላ ቀጠሮ ይጋብዛቸዋል።
አቶ ካሱ አሁንም ይነገራሉ የሴትዋ ቤተሰቦችም መረጃ ለማሰባሰብም ሆነና መልስ ለመስጠት ቀጠሮ ይይዛል። በዚህም መሰረት ማወቅ የሚፈልጉትን መረጃ ስለወንዱ ሙሽራ እና ቤተሰቦች ያጣራሉ፤ የልጅቷ ቤተሰቦች ተማክረን መልስ እንሰጣለን ያሉበትን ቀን የወንዱ ቤተሰቦች “ነገራችን የት ደረሰ” በማለት ለሁለተኛ ጊዜ ከልጁ ቤት ሽማግሌዎች በቀጠሮውም ጋብቻው ይሁንታን እንዳገኘ እና እንዳላገኘ ለመጠየቅ እነዚሁ ሽማግሌ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች በድጋሚ ይሄዳሉ። በዚህም መሰረት ልጅቱን ለልጃቸው እንደሚሰጡ ቃል ገብተው “ለቆዳ ማንጠፍ” ስርዓት ቀጠሮ የዘው ይለያያሉ።
የቆዳ ማንጠፍ ስርዓት
በቀጠሯቸው መሰረት በድጋሚ ለሦስተኛ ጊዜ ሽማግሌዎቹ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ቤት እንደሚሄዱ የሚናገሩት አቶ ካሱ ይህም ስርዓት “የቆዳ ማንጠፍ” ስርዓት ይባላል። በዚህም ስርዓት የሚነጠፈው ከከብት ቆዳ የተሠራ “ወይዶል” የሚባል ሲሆን፤ የቆዳው ቀለም ለጋብቻ የመስማማት እና ያለመስማማትን ሁኔታ ይገልጻል። ሙሉ ነጭ ቆዳ ከተነጠፈ ጋብቻውን ፈቅደናል ወይም ተስማምተናል የሚል ትርጉም ይሰጣል። ቡራቡሬ ነጠብጣብ ከለር ያለው ቆዳ ከተነጠፈ ያመጣችሁት ሃሳብ አሻሚ ነው የሚል ትርጉም ይሰጣል። ጥቁር “ወይዳል” ከተነጠፈ ደግሞ ጋብቻውን አልፈቀድንም የሚል ትርጉም ይሰጣል። ምንም እንኳን ቤተሰብ ልጃቸውን ለመስጠት ፍቃደኝ ቢሆኑም በመሀል ችግሮች ከተፈጠሩ በቆዳ ማንጠፍ ስርዓት ወቅት ጥቁር ወይዳል በማንጠፍ ጋብቻውን ሊያፈርሱት እንደሚችሉም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ካሱ ገለጻ ይሁንታ ከአገኘ በዚሁ ቀን ሽማግሌዎች፣ የሴቷ ቤተሰቦች ፣የቅርብ ዘመድ እና ጎረቤት እንዲያገኙ ተደርጎ የጋብቻው ስምምነት ይደረጋል። እንዲህ ባለ የሽምግልና ስርዓት ነገር ይፈጅበታል። ይህም ሲባል ጋብቻው መቼና፣ መቼ እንደሚሆን የሚቆረጥበት ቀን ነው። በመጨረረሻም በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ የሠርጉን ቀን ቆርጠው ይለያያሉ። የሙሽራው ቤተሰቦች እንደቤተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም የመደገሻ አቅም ለሴቷ ቤተሰቦች ይሰጣሉ።
የልጅቷንም መታጨት ለማመላከት ለተሰበሰቡ ሰዎች የተለያዩ ምግቦች ይቀርባል፤ ከሚቀርቡ ምግቦች መካከል ደግሞ በማህበረሰቡ እንደ ባህል ተደርጎ የተወሰደ እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ቀጭን “ቂጢና” ወይም የጤፍ አንጀራ በቅቤ ይቀርባል። በዚሁ ቀን በሴቷ ቤተሰቦች ቤት እርድ ይካሄዳል።
ስጦታ ”ጥሎሽ‘
በሙሽሪት ቤተሰቦች ቤት እርድ በሚከናወንበት ወቅት ቤተዘመድ ይጠራል፤የወንድ ሚዜዎችም ስጦታ ይዘው ወደ ሴቷ ቤት እንደሚሄዱ አቶ ካሱ ይናገራሉ፤የአቶ ካሱ ገለጻ ቀጥሏል ስጦታውም እንደሠርገኞች አቅም የሚለያይ ቢሆንም በአብዛኛው ሀር ወይም “ኮች” የተባለው የሙሽራዋ ቀሚስ፣ድርብ ኩታ፣የቆዳ ጫማ ወይም “ጡሙር”፣ሳሙና ለልብስ እና ለገላ የሚሆን ፣የትራስ ጨርቅ እና ሽቶ የማይቀሩ የስጦታ ዓይነቶች ናቸው። የሠርጉ ወቅቱ ደግሞ የእሸት እና የጥንቅሽ ወቅት ከሆነና በገጠር አካባቢ ከሆነ ሙሽራው ለሙሽሪት ቤተሰቦች ጥንቅሽ እና እሸት ይልካል። ሠርጉ ሦስት ቀን ሲቀረው ጤፍ፣ማሽላ እና ስንዴ ተፈጭቶ እንዲሁም በግ ወይም ፍየል ቅቤና ማር ከወንዱ ቤተሰብ ወደ ሴቷ ቤተሰብ ይወሰዳል።
በዚህ መሀል ያልታሰበ ነገር ተከስቶ ሠርጉ አንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ ከቆየ ወንዱ ሙሽራ አግብቶ እስኪወስዳት ድረስ በሚመጡት በዓላት በተለይ ለኢድ ወይም አረፋ በዓል ለሙሽሪት ቤተሰቦች ሙክት ማምጣት ባህልም ግዴታም ነው።
አቶ ካሱ ይናገራሉ በአርጎባ ባህል መሰረት በአብዛኛው ሠርግ የሚከናወነው በታኅሣሥ እና በጥር ወራት ሲሆን ይህም ምርት የሚደርስበት ጊዜ ስለሆነ ነው። እንደ አቶ ካሱ ገለጻ ለሠርግ ቀን ሙሽራዋ ጸጉሯን በቀጭኑ “ስጥቄት” የተባለ የጸጉር አሠራር በአገባች ሴት ትሠራለች፤ ቅቤን ትቀባለች፤ የወይራ ቅጠል ተቀቅሎ በውሃ ገላዋን ትታጠባለች፤ “አዝጋሮ ትሞቃለች፤ በመጨረሻም “ይፋቴ” የተሰኘውን ባህላዊ ቀሚስ ትለብሳለች ፤ችንችል፣አሸንክታብ እና ላዚም የተባሉ የአንገት ጌጦች ታደርጋለች። እንዲሁም የእጅ እዛብወይም ጥምጥም ካቴና የእግር አልቦ እና አምባር የጆሮ ጭልጥሌ ታደርጋለች። ሙሽራው በበኩሉ ወንበረቲ ሱሪ ፣ ከላይ እጀ ጠባብ ጥብቆ እና ኮት እንዲሁም ኩታ ይደርባል።
የ”ጉፍታ‘ መጫን ስርዓት
እንደ አቶ ካሱ ገለጻ የጉፍታ የመጫን ስርዓት የሚከናወነው በብዛት የተሰበሰቡ አዛውንት ወይም በዕድሜ ጠና ያሉ እናቶች ሙሽራዋ በመካከላቸው እንድትቀመጥ ከአደረጉ በኋላ ማግባቷን የሚያመላክት ቀይ በባህላዊ ጥልፍ የተጠለፈ ልብስ በራሷ ላይ ለዚሁ ስርዓት ከመጡ እናቶች ውስጥ ሌላ ያላገባች በመጀመሪያ ባሏ የጸናች ከእርሱም ጋር አብራ እየኖረች ያለች ሴት ተመርጣ ታለባብሳታለች።
ባለሙያው የዚህ ባህላዊ ስርዓት ትርጉሙ ሲያስረዱ ሙሽራዋ አግብታ እንደጉፍታ ጫኝዋ ሁሉ ረጅም እድሜ ከባሏ ጋር እንድትኖር ያለመ ነው ፤በዚህም ጊዜ የጉፍታ መጫኛ ዘፈን ይዘፈናል። ጥይት ይተኮሳል፤እልልም ይባላል፤በዚያ ጊዜ ሙሽሪት ታለቅሳለች “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ ይባል የለ” ታዲያ ሙሽሪት መሄዷ ቁርጥ ሲሆን የመጨረሻ ትግሏን ጉፍታውን ላለመልበስ ትታገላለች። የተሰበሰቡት እናቶች እጇን ይዘው በትግል ያደርጉላታል። ታዲያ ጉፍታው ሲጫን “ኦጢሾ” እየተባለ በእልልታ እና በጭብጨባ ታጅቦ ዘፈን ይዘፈናል። ይህም የጭፈራ ስርዓት “የኦጢሾ” ስርዓት ይባላል። ከዚያም ጸሎት ይደረግ እና ዳቦ ተቆርሶ የጉፍታ መጫን እየተባለ ሁሉም እንዲደርሰው ይደረጋል።
ምሽት አካባቢ ሙሽራው በአጃቢዎቹ እና በሚዜዎቹ ታጅቦ በታላቅ ሆታ እና ጭፈራ በተለይ ደግሞ መንዙማ እያሰሙ ወደ ሙሽሪት ቤት ይገባል። ሙሽራዋ በጓደኞቿ ታጅባ እንድትቀመጥ ይደረጋል። ገበታ ከመቅረቡ በፊት ሰማኒያ “ኒካህ” ይታሠራል። ከዚህ በኋላ የተዘጋጁት ምግቦች ስጋ ወጥ፣ እልበት፣ አብሽ ወሃ፣ዝልዝል ስጋ፣ ስቅስቆሽ፣ ወቃሊሞ፣ አሊጣጦ፣ የዶሮስጋ፣ እንቁላል፣ አነባበሩ የመሳሰሉ የባህል ምግቦች ለሙሽሮች እና ለታዳሚው ይቀርብና ይበላል ይጠጣል፤ ከግብዣው በኋላ ሙሽራዋን ሙሽራውና ሚዜዎቹ በበቅሎ ይዘው ይወጣሉ።
ሰንብት እና መልዕክት
ኢትዮጵያ ባለብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ባለቤት እንደሆነች አቶ ካሱ ጠቅሰው እነዚህ ብሔረሰቦች ደግሞ የየራሳቸው የሆነ ባህል አላቸው። በአገሪቱ የሚገኙ እነዚህ ውብ ባህሎችን ሊጠበቁ እንደሚገባ አሳስበዋል። እንደ አቶ ካሱ ገለጻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርጎባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ባህላዊ ክዋኔዎች እና ስርዓቶቹ የሚካሄዱባቸው ቁሶችም ሆነ ይዘቶች እየተለወጡ እንደመጡ ይናገራሉ፤ አቶ ካሱ ይናገራሉ በባህላዊ ጋብቻ ወቅት የሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦች ፣ጥሎሾ፣ባህላዊ የመዋቢያ ቁሳቁሶች በዘመናዊ እና በፋብሪካ ምርቶች እየተለወጡ ነው፤ ይህም በዘመናዊነት ስም የሚተገበሩ አዳዲስ ልምምዶች ቀድሞ የነበረውን አገር በቀል የሆነውን ባህላዊ ስርዓት እንደ ኋላ ቀርነት በማሰብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ትስስር እያላላውና ባህሉ ላይ አደጋ እየፈጠረ ነው። ስለዚህም የሚመለከተው ማንኛው አገር ወዳድ እንዲህ ያሉ ባህሎችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አቶ ካሱ አሳስበዋል።
እኛም ልክ እንደባለሙያ ትኩረት ለባህላዊ ክንዋኔዎቻችን እና ለባህላዊ ዕቃዎች እንዲሆን እናሳስባለን፤ ኢትዮጵያ የሰላም ፣የመቻቻል የደስታ እና የብልድግና ምድርነቷ ይቀጥላል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
አብርሃም ተወልደ