ኢትዮጵያ በጤና ስትራቴጂዎቿ እና ፖሊሲዎቿ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች መካከል የነፍሰጡር እናቶችና ሕጻናት ጤና ቅድሚያውን ይይዛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ‹‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም።›› በሚል የነፍሰጡር እናቶችን ሞት ማስቀረት ይቻል ዘንድ በየትኛውም አካባቢ በሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ተገቢውን ክትትል እንዲያገኙ ይደረጋል። በተጨማሪም ቢያንስ አንድ አምቡላንስ ለዚሁ ተግባር በየጤና ተቋማቱ ተመድቦ የነፍሰጡር እናቶችን ሞት ማስቀረት እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በሚሊኒየሙ አበረታች ውጤት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች ተጠቃሽ ነው።
ይሁን እንጂ የእናቶችን ሕይወት ከሚያሳጡት ድህረወሊድ ደም መፍሰስ አሁንም በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይሄን ችግር እንዴት ማስቀረት አልተቻለም? የኮሮና(ኮቪዲ 19) ወረርሽኝ በነፍሰጡር እናቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖስ ይኖር ይሆን? በሚሉ ለነፍሰጡር እናቶች ሕይወት ጠንቅ የሆኑ ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉትን ባለሙያዎች ያብራራሉ።
አቶ ሸለመው ሁንዴሳ በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ሕጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ኬዝ ቲም ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በኮሮና ምክንያት በእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ የደረሱ የተለዩ ችግሮች የሉም። ነፍሰጡር እናቶች ክትትላቸውን እያደረጉ እንደሆነም ይገልጻሉ።
የእናቶችን ጤና የሚጎዱት ጉዳዮች በርካታ ናቸው። በአብዛኛው ግን እስከሞት የሚያደርሷቸው ልንከላከላቸው የምንችላቸውና መፍትሄ ያላቸው ችግሮች እንደሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጠዋል ይላሉ። የእነዚህን እናቶች ጤና መታደግ እንዲቻል ጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ ሦስት መቶ ሺህ የሚጠጉ እናቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሊድኑ በሚችሉባቸው ችግሮች ለሕልፈት ይዳረጋሉ። ከእነዚህም ውስጥ ወደ 99 በመቶ የሚሆኑት በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት የሚገኙ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ደግሞ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ነው። በተመሳሳይም በየእለቱ እስከ ሰባት ሺህ ጨቅላ ሕጻናት እንደሚሞቱ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ በ2016 በተሰራው የዳሰሳ ጥናት ከሚወልዱ 100ሺ እናቶች 412ቱ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ሕይወታቸውን ያጣሉ። ጨቅላ ሕጻናትም ከሚወለዱት አንድ ሺህ 29ኙ እንደሚሞቱ መረጃዎች እንደሚሳዩ አቶ ሸለመው ያብራራሉ።
በአብዛኛው የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ሞት የሚከሰተው በእርግዝና ፣በወሊድ እና በድሕረወሊድ ወቅት ነው። ከሚከሰተው ሞት ውስጥ ግማሽ ያህሉ በመጀመሪያው ሃያ አራት ሰዓታት የሚደርስ ነው ይላሉ።
ለእናቶች ሞት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ከፍተኛ ደም መፍሰስ እንደሆነ ይነገራል። ይሄን ለማስቀረት ምን እየተሰራ እንደሆነ አቶ ሸለመው ሲያብራሩ፤ ግማሽ ያህሉ የእናቶች ሞት በመጀመሪያው 24 ሰዓት በድሕረ ወሊድ በሚከሰት ደም መፍሰስ የሚከሰት ነው። ቀጥሎም በመጀመሪያው ሳምንት ከሚሞቱት እናቶች 66 በመቶውን ይይዛሉ።
ስለሆነም የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለማስቀረት የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሰረት ሁሉም እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ከወሊድ በኋላ ለ24 ሰዓታት በወለዱበት ጤና ተቋም ቆይተው እንክብካቤ እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህ መሰረት የክልል ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጎ መመሪያው ታትሞ እንዲደርሳቸው ተደርጓል። መመሪያው የሚለው አንድ እናት በጤና ተቋም እንደወለደች ወደቤቷ አትሸኝም። ሃያ አራት ሰዓት እንደሞላት ተገቢው ምርመራና ሕክምና ተደርጎላት የእናትና የጨቅላ ሕጻናቱ ጤናማነት ተረጋግጦ ምንም አይነት ችግር ከሌለባቸው እንዲወጡ ይደረጋል።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስን ለመከላከል መመሪያው ብቻ በቂ አይደለም ያሉት አቶ ሸለመው፤ሌሎች ግብዓቶችም በየጤና ጣቢያዎች ይሰራጫሉ። ለምሳሌ፡-እናቶችን ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ያህል እንዳይሞቱ የሚያደርግ ልብስ አለ። ይሄ እናቶች ሪፈራል ሆስፒታሎች እስኪደርሱ ድረስ ባለው ጊዜ ሊታደጋቸው የሚችል ነው። በሁሉም ጤና ተቋማት እንዲገኝ ተደርጓል። በተጨማሪም የሚፈሰውን ደም ለማስቆም የሚረዱ ሌሎች አዳዲስ መድሃኒቶችም ወደአገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
በሆስፒታሎች ደረጃ ደግሞ ደም የፈሰሳቸውን እናቶች ደም እንዲያገኙ ለማድረግ የደም ልገሳ ልምዶች እንዲጠናከሩ ይደረጋል። ለምሳሌ፡- በጥር ወር የሚከበር የጤናማ እናትነት ወር የደም ልገሳ ንቅናቄ አለ። በተጨማሪም በደም መፍሰስ ምክንያት እና ሕይወቷን ማጣት የለባትም የሚል ንቅናቄ ይካሄዳል። በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጭምር ‹‹ሚኒ›› የደም ባንክ እንዲቋቋም እየተሰራ ይገኛል። ጥናቶች ተካሂደው የግብዓት ግዥ እየተከናወነ ይገኛል። የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስራም እየተከናወነ ነው። ግብዓቶች በወቅቱ እንዲገኙና እጥረት እንዳይገጥም እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አያይዘው እንዳሉት፤ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰትን ከፍተኛ የእናቶች ሞት ሙሉ ለሙሉ መከላከል ይቻላል። በመጀመሪያ እናቶች በሕክምና ተቋማት መውለድ ይኖርባቸዋል። በጤና ተቋማት ሲወልዱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዓታት ከደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ሞት ለመከላከል ወሳኝ ናቸው። እናቶች ምንም አይነት ስጋት ሳይገባቸው በጤና ተቋማት በመውለድ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰትን ሞት ማስቀረት ይችላሉ። ደም ቢፈሳቸው እንኳን ለመተካትም ለማስቆምም እድል ይሰጣል። ስለዚህ የኮሮና ወረርሽኝንም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ምንም አይነት ስጋት ሊፈጥሩባቸው አይገባም። ሁሉም ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት ክትትላቸውን በማከናወን ያለ ስጋት መውለድ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ዶክተር ኑሩ መሐመድ ኡመር የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የማሕጸንና ጽንስ ክፍል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ሰዎች የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል በኩል የሚያሳዩት መዘናጋት ተባብሶ በመቀጠሉ ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል በወረርሽኙ ሊጠቃ እንደሚችል ይገልጻሉ።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የመጀመሪያው የለይቶ ማቆያ ሕክምና መስጠት የጀመረ ሆስፒታል ነው። በማሕጸንና ጽንስ ክፍል 13 የሚሆኑ ዘጠኝ ወር የሞላቸው ነፍሰጡር እናቶች ይገኛሉ። መዘናጋት እስካልቆመ ድረስ የእናቶች ተጠቂነትስ እንደምን ሊቆም ይችላል ባይ ናቸው።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት በአማካኝ እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ እናቶች አርግዘው ይወልዳሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛው እስከ 85 በመቶ የሚደርሰው ወሊድ ጤናማ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ወደ ጤና ተቋም ሄደው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በ2016 እ.ኤ.አ ወደ 28 በመቶ መድረሱን ጥናቶች ያሳያሉ። ባለፈው ዓመት በወጣው የጥናት መረጃ መሰረት ደግሞ ወደ 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች በባለሙያ የታገዘ ወሊድ እንደሚያገኙ አረጋግጧል። ይሁን እንጂ ቀሪዎቹ እናቶች ወደ ጤና ጣቢያዎች ሄደው እየወለዱ አይደለም። ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ አምቡላንሶች በየወረዳው እንዲዳረሱ ተደርጓል። በቅርቡ ከ2001 ጀምሮ እስከ አሁን ባለው መረጃ ላይ ተመስርቶ በተደረገ ጥናትም በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥር ከመቶ ሺህ እናቶች 401 እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
የነፍሰጡር እናቶች ክትትል በየትኛውም ጊዜ አልተቋረጠም። የጤና ተቋማት፣ባለሙያዎች እና ነፍሰጡር እናቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ቀጥሎም ተቋማትና ባለሙያዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡና እናቶችም እንዲገለገሉ ሲደረግ ቆይቷል፤ እየተደረገም ነው። ነገር ግን በጤና ተቋማት የመውለድ ባህሉ በበቂ ደረጃ ባለመድረሱ አሁንም ነፍሰጡር እናቶች በሚያጋጥማቸው ደም መፍሰስ የተነሳ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ቀጥሏል። ሕይወት ለመስጠት ሕይወትን እያጡ እስከመቼ?
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ሙሐመድ ሁሴን