በአንድ አገር ዴሞክራሲን ለማስፈንም ሆነ ለማጎልበት አብዛኞቹ ዜጎች ከዴሞክራሲ ጋር አብሮ የሚሄድ ወይም የሚስማማ ክህሎት፣ እሴቶች እና ባህርያት ሊኖራቸው ይገባል። ከዚህም ባሻገር ዜጎች በመሰረታዊ የዴሞክራሲ ባህርያት ዙሪያ በቂ እውቀት መጨበጥ፣ በመሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆዎችና እሴቶችም ማመን ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በአካባቢያዊና ሃገራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ ፍላጎትና ተሳትፎኣቸውም ስለዴሞክራሲ ስርዓቱ ቀጣይነት አስፈላጊ ነው ብለው ማመን አለባቸው። እነዚህን ከላይ የተጠቁሰትን እውቀቶች፤ ክህሎቶችና እሴቶች ለማዳበር ደግሞ የተለያዩ አካላት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።
ከዚህ እንጻር በተለይ ትምህርት ቤቶችና ትምህርት የማይተካ ሚና አላቸው። ከሳይንስና ቴክሎጂ ትምህርት ጎን ለጎን የአንድ ሃገር ትምህርት ዜጎች የማህበረሰባቸውን እና የዴሞክራሲ እሴቶችን እንዲረዱ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ስሊሚኖራቸው ሚናና ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ስርዓተ ትምህርቶቹና ትምህርት ቤቶች በየወቅቱ ለሚቀያየሩ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ተገቢውን ግንዛቤ የሚያስጨብጡና ለለውጥ የተዘጋጁ ዜጎችን የማፍራት ሃላፊነትም አለባቸው።
የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ምንነት
ዜግነት በአንድ አገር በዜጎችና በመንግስታቸው ወይም በሃገራቸው መካከል እንዲሁም በዜጎች መካከል የሚኖርን ወይም ሊኖር ስለሚገባቸው ግንኙነቶች የሚያመለክት እሳቤ ነው። በሌላ አገላለፅ ዜግነት ማለት እኛ ማነን፣ እንዴትስ አብረን መኖር አለብን፣ ቀጣዩ ትውልድስ ምን መምሰል አለበት፣ የሚሉትን ጉዳዮች አጠቃሎ የያዘና የሚመልስ ጽንስ ሃሳብ ነው። ስለዚህ የዜግነት ትምህርት ዜጎች በንቃትና በኃላፊነት መንፈስ በአገራቸው የዴሞክራሲ እንዲሁም በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሳተፉ የሚያዘጋጅ ነው።
የስነዜጋና የስነምግባር ትምህርት ከማህበራዊ ትምህርት ዘርፎች አንዱ ሲሆን ዋና ትኩረቱም በአንድ የፖለቲካ ማህረሰብ ውስጥ የዜጎች መብትና ግዴታ ምን እንደሆነ ማሳወቅ፣ ዜጎች በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ተሳትፎ ፣ ከሌሎች ግለሰቦች ፤ ከማህበረሰቡና ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ወዘተ ማስተማር ነው።
ስለዚህ ከብያኔዎቹ ተነስተን ስናየው የስነዜጋ ትምህርት እውቀትን፣ ክህሎትንና እሴቶችን ከተግባር ወይም ከባህርይ ጋር ማጣመር አለበት ማለት ነው።
የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት አስፈላጊነት
ዜጎች መሠረታዊ የዜግነትና የመልካም ስነምግባር እሴቶችን ያውቁ ዘንድ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት መማር እንዳለባቸው ሁሉም ምሁራንና መንግስታት ይስማማሉ። ዋና ዋና የዜግነትና የስነምግባር እሴቶችን የተገነዘበና ያዳበረ ዜጋ ከሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር የሚጋራቸው ፍላጎቶች እንዳሉትና ይህም ከራሱ ፍላጎት ጋር የማይጻረር እንደሆነ መገንዘብ ይችላል። ተግባራዊ ውጤቱም ስልጡንና ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር ይሆናል።
በተመሳሳይ መልኩ የዜግነት ኃላፊነትና ግዴታዎችን በተመለከተ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት የተማሩ ዜጎች በምርጫ መሳተፍ፣ ግብር መክፈል፣ የአካባቢያቸውን ህዝብ በቀጥታ በሚመለከት የፖለቲካ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ተሳትፎ ማድረግ አስፈላጊና ከአንድ ዴሞክራሲያዊ ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ካልተማሩት እጅግ በተሻለ መልኩ ያምናሉ። እንዲሁም በዴሞክራሲ ስርዓቱ ሂደት ያላቸው እርካታ ፣ ዴሞክራሲ ወደፊት እየተሻሻለ ስለመሄዱ ያላቸው እምነትም ከፍተኛ ይሆናል።
ዴሞክራሲ በዳበረባቸውም ሆነ ገና በጅምር ላይ ላሉ ሀገሮች ዜጎች ሊኖራቸው የሚገባው የአንድ ጥሩ ዜጋ የዜግነት ባህርያትና ብቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዜጎች በተለይም ወጣት ዜጎች የመልካም ዜግነት መገለጫዎች የጎደሏቸው ጉልህ የሆነ የዜግነት ባህርያት ጉድለት ያለባቸው ናቸው በማለት ሶስት ጉድለቶችን ያስቀምጣሉ።
- መሰረታዊ የሆነ የዜግነት እውቀቶች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ በቂ መረጃ የሌሏቸውና እንዴት እንደ አንድ ዜጋ መኖርና መስራት እንዳለባቸው በሚገባ የሚያውቁ፤
- ለፖለቲካ ጉዳዮች ባይተዋር የሆኑና ከማህበረሰባቸውና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ራሳቸውን የነጠሉ እንዲሁም፤
- ጨለምተኝት የተጠናወታቸውና በማህበረሰቡና በዴሞክራሲ ዋና ዋና ስሌቶች ላይ እምነት የሌላቸው ናቸው።
ለዚህ ችግር ደግሞ መፍትሄው የዜግነትና የስነምግባር ትምህርትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስተማር ነው። ስለዚህ የስነዜጋ እና የስነምግባር ትምህርት አስፈላጊነት ከነዚህ መሰረታዊ የማህበረሰቡ ችግሮችና ማህበራዊ እውነታዎች የሚመነጭ መሆን አለበት ማለት ነው።
የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ዓላማ
የአንድ ሀገር ትምህርት ዓላማ በገበያ ተፈላጊ የሆነ የሰው ሀይል ማዘጋጀትና ማቅረብ ቢሆንም የትምህርቱ ዋና ይዘት ግን ተማሪዎች በተለያዩ ማህበራዊ እውነታዎች ወይም ሁኔታዎች ውስጥ ትምህርት መቅሰምና መስራት የሚችሉ፤ ምክንያታዊነትን የሚማሩበት፣ የህግ የበላይነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን፣ ችግሮችን መለየትና መፍታት የሚያስችል በህብረት ወይም በጋራ መስራትን፣ ከሌሎች ጋር መተባበርን፣ ኃላፊነትን መገንዘብ የሚያስችል፣ የአመራር ጥበብን የሚያስጨብጥ፣ ታጋሽነትንና ቻይነትን ፣ አብሮ መኖርን ፣ መከባበርን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን አለበት።
በሊበራል ርዕዮተዓለም እይታ መልካም ዜጋ ማለት አንድ ዜጋ በማህበረሰቡ ውስጥ ግለሰባዊ ህይወቱን ለመምራትና ግላዊ ፍላጎቱን ለማሳካት በሚያስችለው አኳሃን የማህበረሰቡን ደንብና ልማድ መገንዘብ መቻል ነው። ስለዚህ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ትኩረት ዜጎች ግለሰባዊ ጥቅሞችን በተቻለ መጠን ሊያሳዩ የሚችሉበት ክህሎትና ባህርይ ማስተማር ነው።
በሌላ መልኩ በሌሎች የዴሞክራሲ ርዕዮት ደግሞ የሚታሰበው በማህበረሰቡ አባላት መካከል የጠበቀ መስተጋብርና የጋራ እሴቶች ያሉና በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የቡድንም የግለሰብ ዜጎችም መብት ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚችል ነው። ስለዚህ የርስ በርስ ግንኙነቶች የመደጋገፍ ማህበረሰባዊ ስሜትና ለፖለቲካና ማህበራዊ ሃላፊነት እውቅና የሚሰጡ ዜጎችን ማፍራት ዋናው ትኩረት ነው።
በዚህም መሰረት የስነዜጋና የስነምግባር ትምህርት ግብ መቼም ይሁን የት ዜጎችን በተለይም ወጣቶችን በሃገራቸው ጉዳዮች ላይ በያገባኛልና ተቆርቋሪነት ስሜት የበኩላቸውንና የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል ነው። ስለዚህ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎኣቸውን የሚያዳብሩበት እሴት፣ እውቀትና ክህሎት የሚገበዩበት ትምህርት ነው።”
አንድ ዴሞክራሲያዊ ዜጋ እውነትን ከሃሰት፣ ተጨባጭ ሁነቶችን ከፕሮፓጋንዳ መለየት የሚችል ቢያንስ ለመለየት ጥረት የሚያደርግ መሆን ይገባዋል። እንዲሁም ጽንፈኝነትንና ጭፍን ጥላቻን የሚነቅፍና የሚጸየፍ መሆን ይገባዋል። በተጨማሪም ምክንያታዊ፣ ሳይንሳዊና በማስረጃ የተደገፈ የአተናተን ሂደትን የሚከተል መሆን አለበት። ሌላው የትምህርቱ ዓላማ ሁል ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ለመማርና በተለመደው አስተሳሰብና ልማድ በምክንያታዊነት ለመላቀቅ ዝግጁ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ነው።
በአጠቃላይ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ዓላማ መልካም ዜጎችን ማፍራት ነው። መልካም ዜጋ ማለት ደግሞ የአካባቢውንና የሃገሩን ችግሮች በሚገባ መገንዘብ የሚችል፤ በመልካም ስነምግባርና ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ታንጾ የዜግነት ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣና መብቶቹንም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ የሚጠቀም ማለት ነው። እንዲህ አይነት ዜጎችን ማፍራት ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ በመፈተሽ በመልካም ስነምግባር የታነጸና የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ ትውልድ ማዘጋጀት ለነገ የማይባል ስራ የቤት ስራ ነው። ምንጭ በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ በትምህርት ተቋማት የስነዜጋና ስነምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በሚል የተዘጋጀ መጽሃፍ፤ ግንቦት 2009 ዓ.ም።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ወርቁ ማሩ