ልጆች! ታላቁ የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ሰማችሁ አይደል? በሰማችሁት ሰበር ዜና በጣም እንደተደሰታችሁ እገምታለሁ። ሁሉም ሰው በጣም መደሰቱን በተለያየ መንገድ እየገለጸ ይገኛል። «ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያለን» በመባባል ላይ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የእናንተ የልጆች ሚናም ቀላል አልነበረም፡፡ በርካታ ሕፃናት በወላጆቻቸው አማካኝነት ቦንድ ገዝተዋል፡፡ አንዳንድ ልጆች የልደት ስጦታቸው ቦንድ እንዲሆንላቸው በማድረግ ለግድቡ ትልቅ አበርክቶት አድርገዋል፡፡ በግጥምና በዘፈን በተለያዩ ጊዜ ቅስቀሳ በማድረግ ተጨማሪ ጉልበት ፈጥረዋል፡፡ በትምህርት ቤታቸው ገንዘብ በማዋጣት ደግፈዋል። ይሄ ሁሉ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ሁላችንም ተባብረን ባደረግነው ድጋፍ በተሰራው ሥራ ደግሞ አሁን የመጀመሪያውን ዙር ውሃ ለመሙላት ተችሏል።
ተማሪ ናትናኤል ግርማ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ከግድቡ በላይ እየፈሰሰ አባይ ሲጎማለል በማየቱ መደሰቱን ገልጾልኛል። ተማሪ ናትናኤል በምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ «አባይ የሁላችን ሀብት ነው፡፡ ወደፊት በቀላሉ እድገት ለማምጣት ይጠቅመናል፡፡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የአራት መቶ ብር ቦንድ አስገዝቻለሁ፡፡ እህትና ወንድሞቼም ቦንድ ገዝተዋል፡፡ በ8100 ኤ ላይም በየቀኑ በመላክ አስተዋፅኦ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቁን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡» በማለት ዜናውን ሲሰሙ በቤት ውስጥ በመጮህ በደስታ መተቃቀፋቸውን ነግሮናል፡፡
ግድቡ የታሰበለት ቦታ ደርሶ ጥቅም እንዲሰጥና ወደ ሌላ ፕሮጀክት እንድንዞር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የውሃ ሙሌቱ ገና መጀመሩ ነው የሚለው ናትናኤል ከምን ጊዜውን በላይ ድጋፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጫፍ ማድረስ አለብን ይላል፡፡ ከ50 ብር ጀምሮ ቦንድ መግዛት ስለሚቻል ሁሉም ሕፃናት ከሚገዛላቸው ልብስና ጫማ እንዲሁም መዝናኛ ቀንሰው ቦንድ ሊገዙ ይገባል ብሏል፡፡ ልጆች እናንተም እንደ ተማሪ ናትናኤል በደስታ እንደፈነደቃችሁ አምናለሁ። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የታሰበለትን ጥቅም እስኪሰጥ ድረስ መደገፍ አለባችሁ። ቦንድ በመግዛት አሁንም አጋርነታችሁን አረጋግጡ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
በሞገስ ጸጋዬ