የእግረኛ መንገዱ በጡብ ንጣፍ አምሯል። መንገደኛው በጭቃ ከመቡካት ተላቅቆ ምቹ በሆነው መንገድ ላይ ይጓዛል።ይሄ የእግረኛ ምቾት ብዙም አልዘለቀም፤ በግራና በቀኝ በሰልፍ በተደረደሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች መገፋፋቱ ሌላ ችግር ሆኖ ቀጠለ።ያ ሳያንስ ደግሞ አሁን በጡብ ከተነጠፈው የእግረኛ መንገድ አብዛኛው በብሎኬት ታጠረ።በበሃ ላይ ቆረቆር ማለት ይሄኔ ነው። በዚህም ምክንያታ በአንድ ወገን በቀኝና በግራ መኪና መተላለፍ እያቃተው ተጠባብቆ የሚያልፍ ሲሆን፣ ጠበብ ባለበት ቦታ ደግሞ እግረኛውም ከመኪናው ጎን ለጎን እየተገፋፋ ለመጓዝ ተገዷል። ቦታው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት በተለምዶ ሾላ የሚባለው አካባቢ ሲሆን፣ የዚህ ችግር መንስኤ ደግሞ ግንባታ ለማካሄድ በሚል ካለማንም ፈቃድ የእግረኛው መንገድ ተዘግቶ በመታጠሩ ነው።
የወረዳ ስምንት የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር እሸቱ ፀጋው የችግሩን አሳሳቢነት ይናገራሉ። በተደጋጋሚ እርምጃ ቢወሰድም በቂ ለውጥ አለመምጣቱን ያክላሉ። የእግረኛ መንገድ መዋል ያለበት ለእግረኛ ብቻ ነው የሚሉት ኃላፊው በየትኛውም ቦታ ካለ ፈቃድ የሚሰራ ማንኛውም ነገር ካለ የማስቆም እና የተሰራውንም በአፍራሽ ግብረ ኃይል እስከማፍረስ የሚደርስ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን ይናገራሉ። በብሎኬት መንገድ ዘግተው ያጠሩት ለመኪና ማቆሚያ (ለፓርኪንግ) ህንጻ በቦታው ሊገነባ በመሆኑ ለግንባታ ዕቃ ማስቀመጫ የእግረኛውን መንገድ በማይዘጋ መልኩ ሥራቸውን እስኪያጠናቅቁ እንዲሰሩ አስተዳደሩ በደብዳቤ ፈቀደላቸው ይላሉ ።
«በከተማ ደረጃ ለሚገነባው የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ሙሉ ለሙሉ ስለምንቆፍረው በሚል መንገድ ውስጥ ገብተው ያጠሩ አሉ፤ህብረተሰቡ ቅሬታ በማቅረቡ አስቁመናቸው በድንበራቸው ተወስነው እንዲሰሩም ትዕዛዝ ተሰጥቷል» የሚሉት ደግሞ የወረዳው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደምሴ ገብረወልድ ናቸው። «ከአስተዳደሩ በደብዳቤ ተፈቅዶላቸዋል» በማለት ከደንብ ማስከበር የተሰጠው ምላሽም ሀሰት መሆኑን ይገልጻሉ።
ኃላፊው እንደሚሉት ግንባታው ትልቅ በመሆኑና ቦታ ስለማይበቃ ግንባታውን እስክንጀምር ንብረት ማስቀመጫ ያስፈልገናል በሚል አጥሩን ማጠራቸውን ተናግረዋል። ጥያቄያቸው አንደኛዋን መንገድ ለመዝጋትም ነበር ይሄንንም ቢሆን ከራሱ ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር መነጋገር ስለሚጠይቅ በእኛ በኩል ግን የመንግሥትም ሆነ የግል ግንባታ በዚህ መልኩ መከናወን እንደማይችል በመግለፅ ፈቃድ ይዘው እንዲመጡ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አስቁመናቸዋል። በአሁኑ ወቅት ምንም ሥራ እየሰሩ አይደለም። ከዚህ በፊትም በዚህ መልኩ ፈቃድ የሰጠነውም የከለከልነውም የለም ፤ይሄ የእኛ ሥራ አይደለም ፤ ህብረተሰቡ ግን በአብዛኛው ግንባታ ሲያካሂድ ለግብዓት ማስቀመጫ ለግንባታ ማካሄጃ ብሎ ቦታ ከማዘጋጀትና የሚመለከተውን አካል ከመጠየቅ ይልቅ መንገድ መዝጋትና መንገድ እያበላሹ መስራት ነው የሚመርጠው።
በዚህም በአካባቢው ህጋዊ ግንባታ የሚያካሂዱ ሆነው አርማታ ሲያቦኩና ተረፈ ምርት ሲያስቀምጡ በእግረኛና በተሽከርካሪ መንገድ ላይ ብዙ ችግር ይከሰታል። ለዚህም በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየሰጠን እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን። ነገር ግን በአካባቢው በርካታ ግንባታዎች የሚካሄዱ በመሆኑ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች የእግረኛውንም ሆነ የተሽከርካሪውን መንገድ በሚያበላሽ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ይናገራሉ። በእነዚህም ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የሰሜን አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሰይድ በአጠቃላይ ችግሩ ሰፊ መሆኑን ያምናሉ። በህገወጦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም ተጨባጭ ለውጥ አለመምጣቱን ይናገራሉ።አቶ እስማኤል እንደሚያብራሩት ማስጠንቀቂያ ደርሷቸው ያልተመለሱትን ከደንብና ከፖሊስ ጋር በግብረ ኃይል አጥር የማስፈረስ ፣መንገድ ዘግተው የተቀመጡትን ደግሞ ቁሳቁሶችን የመውረስ ሥራ ይሰራል። ችግሩ ግን ሲቀንስ አይታይም፤ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው እሺ ብለው ተመልሰው ወደዛው ሥራ ይገባሉ። በእኛ በኩልም ተናቦ መስራት ላይ ክፍተት በመኖሩ ጭምር የሚፈጠር ችግር ነው ።
የህንፃ ግንባታ ፈቃድ ሲሰጥም የት ተቀምጦ ነው ግንባታው የሚካሄደው የሚለው ስለማይታይ በበርካታ ሚሊዮን ብር የተሰራ መንገድ በቀላሉ ለብልሽት ሲዳረግ ይታያል። ለተቆረጠና ለተበላሸ መንገድ ግምት የሚከፈል ቢሆንም ለመንግሥትም ለመንገዱም በቅድሚያ እንደመቆጣጠሩ አይሆንም። መቀጫውም አምስት መቶና አንድ ሺ በመሆኑ ህግን ለሚጥሱት አስተማሪ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ