ቅድመ-ታሪክ…
የጥንዶቹ ሰላም ማጣት እያደር ብሶበታል። ጠዋት ማታ በጭቅጭቅ የዘለቀው ኑሮ ተስፋ ያለው አይመስልም። ባልና ሚስቱ ለመለያየት ወስነው ፍቺን ካሰቡ ቆይተዋል። በትዳር ሲኖሩ ያፈሩት ወንድ ልጃቸው አፉን በወጉ አልፈታም፣ እግሮቹ ጸንተው አልቆሙም። ከመታዘልና ከመታቀፍ ያልወጣ ጨቅላ ነው።
ባልና ሚስት ትዳራቸውን በፍቺ ሲቋጩ የህጻኑ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ሆነ፤ እናት የባሏን እጅ አይቶ ከማደር ያለፈ ገቢ የላትም። ልጁ ምግብና ልብስ ያስፈልገዋል። የቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን ማሟላትም የግድ ነው። እናት ደግሞ ጨቅላ ልጇን ለአባቱ መስጠት አይቻላትም።
መቂ ላይ የተገነባው ትዳር እንዳልሆነ ሲሆን ወይዘሮዋ ህጻኑን ታቅፋ ሻሸመኔ ገባች። የአቅሟን እየሰራችም ልጇን ማሳደግ ጀመረች። ህጻኑ ጎበዜ በእናቱ እቅፍ ሆኖ ያሻውን አገኘ። ዕድሜው ከፍ ሲልም ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት ገባ። አንድ… ብሎ የጀመረው ክፍል ሲጨምር ግን የእናቱ አቅም ተዳከመ። ልጅን ያለአባት ማሳደጉ ይከብዳት ያስጨንቃት ያዘ።
ድህነትና የዕለት ችግር ጎጇቸውን ሲፈትን እናት በትካዜ አንገቷን ደፋች። ባላት አቅም እየታገለች አራተኛ ክፍል ያደረሰችው ልጅ የወደፊት ዕድሉ አሳሰባት። ይህን ሁሉ እውነት በቅርበት የሚያየው ጎበዜ ከእናቱ በላይ ማሰብ ጀምሯል። ከዚህ በኋላ በችግር መፈተኑን እያመነበት አይደለም። በትንሽ አይምሮው ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ ከጀመረ ቆይቷል።
አንድ ቀን ማለዳ ጎበዜ ማልዶ ከዕንቅልፉ ተነሳ። ሰሞኑን ሲያስብበት የከረመው ጉዳይ እንደሚሳካለት እርግጠኛ ሆኗል። ከመኪናው መንገድ ወጥቶ የሩቅ ተጓዥ መኪኖችን ጠበቀ። ሁሌም በጎዳናው ከሚያልፉት ከባድ መኪኖች አንዱ ካሰበበት እንደሚያደርሰው ተማምኗል። እጁን እየዘረጋ፣ ዓይኖቹን እያንከራተተ ተማጸነ። አብዛኞቹ ልጅነቱን እያዩ አልፈውት ሄዱ።
ለሰዓታት በመኪና ልመና የዋለው ታዳጊ አረፋፍዶ ከአንድ ሾፌር ጋር ተግባባ። አዲስ አበባ መሄድ እንደሚሻ ነገረው። ሾፌሩ ሀሳቡን አልተቃወመም። ያለምንም ክፍያ ከመኪናው አሳፍሮ መሀል አዲስ አበባ ጣለው። ጎበዜ አዲስ አበባ እንደደረሰ ግራ ተጋባ። በዚህ ስፍራ የሚያውቀው ዘመድ አዝማድ የለም። እየጨነቀው፣እየከፋው ከአንድ ጥግ አረፈ።
ከቀናት በኋላ…
አዲስ አበባና ጎበዜ ከተዋወቁ ቀናት ተቆጥረዋል። ዘመድ አልባው ታዳጊ አሁን ከእኩዮቹ ጋር ጎዳና ላይ መዋል ማደር ጀምሯል። በስቴድየም ዙሪያ የሚኖሩ ህጻናት እሱን ተቀብለው ወገናቸው ካደረጉት ቆይተዋል።
ጎበዜ የአዲስ አበባውን ህይወት ለመልመድ ለጊዜው ተቸገረ። ቆይቶ ግን ሁሉን ለመደው። ርሀብ ጥማቱን ተጋርቶ፣ብርድና ውርጩን ተቋቁሞ ክረምት ከበጋ ተሻገረ። የጎዳና ህይወትን አጣጥሞ የኑሮን ባህርይ ቀመሰ። ‹‹ጎዳና ነው ቤቴ››ን ዘምሮ ከእኩዮቹ ጋር መሰለ።
ጎዳና ብዙ ያሳያል። ማስቲችና ቤንዚን መሳቡ፣ታሞ መውደቁ፣የሰው ፊት ማየቱ ፈታኝ ነው። አንዳንዴ የሚነጠቅ ሲገኝ ደግሞ ይዞ መሮጥ ተለምዷል። የተገኘውን ተካፍሎ መብላት፣እራፊን ተጋርቶ መተኛት፣ያለ ነው። የሻሸመኔው ልጅም ከዚህ ማንነት አልራቀም። በእጅ አመል እየተጠረጠረ፣ መታሰር መፈታትን አልፎበታል። ክፉን ከበጎ ተራምዶ ነገን ለማየት ተስፋ አድርጓል።
ወጣትነት…
አሁን ጎበዜ በዕድሜ ጎልብቶ ወጣትነትን ጀምሯል። ይህ ጊዜ ራሱን እንዲችል የሚያሳስበው ቢሆን አርቆ ማሰብ ያዘ። በጎዳና አድሮ ከመለመን የተሻለውን እያሰበም አማራጭ ፍለጋ ባተለ። ይህ ጥረቱ መልካም አጋጣሚን ፈጠረ። ከአንድ የውጭ ድርጅት ዘንድ የእጅ ሙያን ለመማር ተጠጋ።
ድርጅቱ እሱን መሰል ወጣቶች እያሰለጠነ ራስን ያስችላል። ጎበዜም ብየዳን ለመማር ዕድል ባገኘ ጊዜ ደስ አለው። የትናንት ማንነቱን ትቶ ነገውን መልካም ሊያደርግ ለጥረቱ ጎበዘ። ያሳ ዩትን ለምዶ ባለሙያ ሊሆን ታተረ።
ከስልጠናው ማግስት ጎበዜ በሙያው ተቀጥሮ የመስራት አጋጣሚን አገኘ። ደሞዝ እየተከፈለው መኖር ሲጀምር ከጎዳና ህይወት ተላቀቀ። የአቅሙን ቤት ተከራይቶ በጣራ ስር ውሎ አደረ። ጎበዜ መልካም ሙያው ከወር ደሞዙ ተዳምሮ ትናንትን አስረሳው።
ተቀጥሮ የሚሰራበት ድርጅት በርካታ ንብረቶች አሉት፤ በግቢው ያሉ ሰራተኞችም በታማኝነት ሊሰሩ ግድ ይላቸዋል። እሱም ቢሆን ከግቢው ህግና ደንብ ውጭ አንዳች ሊያደርግ አይቻለውም። አንድ ቀን የተፈጠረው አጋጣሚ ግን የጎበዜን ጅምር መንገድ አስከወዲያኛው የሚያቋርጥ ሆነ።
በዚህ ቀን በድርጅቱ ግቢ ካሉ ንብረቶች አንዱ መጥፋቱ ታወቀ። ምርመራው ሲደረግ በጉዳዩ የተጠየቁ ሁሉ ስርቆቱን እንዳልፈጸሙት ምለው ተገዝተው አረጋገጡ። ድርጅቱ የእነሱን ቃል አምኖ ወደ ጎበዜ ፊቱን አዞረ። እሱንም እንደሌሎች ጥያቄ አቅርቦ መረመረው።
ጎበዜ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ያለውን በምክንያት ዘርዝሮ አስረዳ። በተናገረው አልታመነም። በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ። ከድርጅቱ እንዲባረር ተወሰነ።
ጎዳና እንደገና…
ከስራ ሲባረር በእጁ የነበረው ጥቂት ገንዘብ ከዕለት ወጪው አላለፈም፡፤ከድርጅቱ ሲወጣ የያዘው አጉል ስም ሌላ ዘንድ ለመቀጠር ዕድል አልሠጠውም። ይህኔ የተከራየውን ቤት ሊለቅ ግድ አለው። ልብሶቹን ይዞ ቦሌ ፍሬንድ ሺፕ ሀንጻ አጠገብ ካለ ሜዳ መዋል ማደር ጀመረ።
ለጊዚያት ቤት የመኖር ህይወትን ያወቀው ጎበዜ፣ የሜዳ ላይ ኑሮ አልተመቸውም። ብርድና ዝናቡን መቋቋም አልሆነለትም። ዋል አደር ሲል ቦሌ መድሀኒያለም ጀርባ ካሉ የጨረቃ ቤቶች አንዱን ተከራየ። ለጊዜው መኪኖችን እያጠበ ኑሮውን መደጎም ያዘ። ይህ አጋጣሚ ከሌሎች መሰሎቹ አገናኘው።
ቆይቶ ባልንጀሮቹ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ሲግባባ ለመኖር ሌሎች አማራጮች እንዳሉ ገባው። ከስራ መልስ ጎበዜ ከጓደኞቹ ጋር አረቄ ቤት ያመሻል። በዚህ ሰዓት ሁሉም ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን ሀሳብ እያነሱ ያወጋሉ። አብዛኞቹ ጨለማን ተገን አድርገው መዝረፍ የለመዱ ናቸው። ሌሎች ደግሞ በነሱ ተከልለው ጥቅም የመጋራት ልምድ አላቸው።
ጎበዜ ወጣቶቹ ሁሌም በሚያነሱት ሀሳብ እንደተሳበ ነው። ከስራ ይልቅ በዘረፋ ቢሰማራ የተሻለ ገንዘብ መያዝ እንደሚችል ራሱን አሳምኗል። አንዳንዴ እጅ ባጠረው ጊዜ በዚህ ዕቅድ መግፋት እንዳለበት ይወስናል።
ጥር 5 ቀን 2004 ዓም
ገና በጊዜ በአረቄ ቤቱ የታደሙት ባልንጀሮች መለኪያ ጨብጠው ጨዋታ ይዘዋል። ጎበዜ ለዓይን ሳይዝ ካገኛቸው ወጣቶች ጋር አረቄውን ፉት እያለ ነው። ምሽቱ እየገፋ ሞቅታው ሲጀምር የተለመደው ጨዋታ ተነሳ። ይህ ርዕስ ሲወሳ የሁሉም ዓይኖች ይበራሉ። ጆሮዎቻቸው ይነቃሉ።
ዛሬም በተለመደው ‹‹የእንዝረፍ›› ሀሳብ የታቀደው ዝርዝር መቀመጥ ጀምሯል። ውጥኑን የነደፈው ጓደኛቸው በአጋፋሪነት እያብራራ አፋቸውን አስከፍቷል። የሦስቱ ጨዋታ የማረከው ጎበዜ ከእነሱው አብሮ ዕቅድ እያጸደቀ ነው።
ጥቂት ቆይቶ ባልንጀሮቹ በአንድ ሀሳብ ተስማሙ። ወጣ ብለው ያገኙትን ለመዝረፍና ገንዘቡን ለመከፋፈል ወሰኑ። የያዙትን መለኪያ ጨልጠው የተጠየቁትን ተጋርተው ከፈሉ። ዛሬ ያሰቡት ሲሳካ ያሻቸውን ለመጠጣት ተቃጠሩ።
ከአረቄ ቤቱ ሲወጡ ምሽት አምስት ሰዓት ተኩል ሆኗል። አቅጣጫ ለይተው ወደ አትላስ ሆቴል መንገድ ጀመሩ። የሚያዩትን እያጣሩ፣ያጣሩትን እየመረመሩ ተራመዱ። ካዩዋቸው መሀል ዓይን የገባ አላገኙም። እየፈጠኑ ወደ ሸገር ህንጻ ተጠጉ። በመንገዱ ዳር የቆሙ የምሽት ሴቶች ሁኔታቸውን እንዲያውቁ አልፈለጉም። ከእነሱ የቀረበውን እየተጠጉ፣ አቅምና፣ቁመናን ማጣራት ያዙ።
ዓይን አዋጅ…
አንዱ እየሄደ ሌላው ሲመጣ ጓደኛሞቹ የሚይዙት ጠፋ። ማንን አስቀድመው ማንን እንደሚተዉ ግራ ተጋቡ። ያዩት ሁሉ የሚዘረፍ የሚቀማ መሰላቸው።
ለመወሰን ቢቸገሩ ያለ ንግግር ከአንድ ጥግ አደፈጡ።
ጥቂት ቆይቶ የሆነ ሰው ከአንድ ስፍራ ብቅ ሲል ታየ። የአራቱም ዓይኖች አፈጠጡ። ሰውዬው በእጁ ከፍ ያለ ጥቁር ቦርሳ አንጠልጥሏል። አረማመዱ መተማመን ያለበት ይመስላል። ቀረብ ብለው አስተዋሉት። የውጭ ዜጋ ነው። ጸጉሩ የነጣ፣አለባበሱ ያማረ ፈረንጅ።
ይህኔ እርስ በርስ ተያዩ። የምሽት ግዳያቸው እሱ መሆኑን ሲያውቁ ሴቶቹን አልፎ እስኪሄድ ለሽንት የቆሙ መሰሉ። ጥቂት ቆይቶ ‹‹ይህን ዜጋ እንስራው፣እንስራው…›› እያሉ ተከተሉት። አላያቸውም።
እየሮጡ አጠገቡ ሲደርሱ ትብብራቸው ጠና። በላዩ ተጠምጥመው ቦርሳውን ቀሙት። አንገቱን አነቁና ከኪሱ ገቡ። የእጅ ሰልኩን አወጡ። አራት ሺህ ብር ወሰዱ። ፈረንጁ ክፉኛ ታገላቸው። አልቻላቸውም። አቅሙን የገመቱ ዘራፊዎች ሊያሸንፉት ተባበሩ። ከመሀላቸው አንደኛው በያዘው ጩቤ ታፋውንና ጭንቅላቱን ሁለት ጊዜ ወጋው። ሰውዬው ተረታ። ስለቱን ጥለው በጨለማው መንገድ ተፈተለኩ። ፈረንጁ ደሙን እያዘራ ተከተላቸው። አልደረሰባቸውም።
የፖሊስ ምርመራ…
በማግስቱ ቦሌ ክፍለከተማ ፖሊስ መምሪያ ደርሰው ‹‹አቤት…›› ያሉት ሰው በዜግነት ቤልጄማዊ መሆናቸውን አስረዱ። ስማቸው ሚስተር ሴቪን መሆኑን የገለጹት የውጭ ዜጋ ምሽቱን ወደ መኖሪያቸው ሲገቡ ያጋጠማቸውን ዝርፊያና የደረሰባቸውን ጉዳት አንድ በአንድ ተናገሩ።
መርማሪው ምክትል ሳጂን አለማየሁ ሀይሉ ከግለሰቡ የተዘረፈና ግምቱ ሰማንያ ስምንት ሺህ ብር የሚያወጣ አፕል ኮምፒውተር ከነሀርድ ድራይቩ፣ሞባይልና ከሁለት ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የእንግሊዝኛ መጽሀፍት፣ በአጠቃላይ ዘጠና አራትሺህ ሁለት መቶ ብር የሚያወጣ ንብረት መዘረፉን መዘገበ።
በፍጥነት የተዋቀረው የምርመራ ቡድንም ሳይውል ሳያድር አሰሳውን ቀጠለ። ተጠርጣሪዎችን እንደለየ ይገኙበታል በተባለ ስፍራ እየተገኘ አደፈጠ። ለጊዜው አልያዛቸውም። አንድ ቀን ግን ቡድኑ ጎበዜን ካለበት ደርሶ ከእጁ አስገባው። ተጠርጣሪው ስለሌሎቹ ተጠየቀ። የት እንዳሉ እንደማያውቅ ተናገረ።
ጎበዜ ከዝርፊያው በኋላ ስለሆነው እውነት አልደበቀም። እሱና ጓደኞቹ የዛን ዕለት አልጋ ይዘው ማደራቸውንና ሲነጋ ለአንድ የከረንቡላ ቤት ባለቤት ንብረቶቹንና መጽሀፍቱን በሰባትሺህ ብር መሸጣቸውን ተናዘዘ። ገንዘቡን ተካፍለውም ሲበሉና ሲጠጡ መክረማቸውን አስረዳ። እሱም በገንዘቡ ያማረውን ቲሸርትና ስኒከር ጫማ ስለመግዛቱ ቃሉን ሰጠ።
ውሳኔ …
ጥር 14 ቀን 2007 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ ጎበዜ አበበ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ግለሰቡ ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በፈጸመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ጥፋተኛ ስለመሆኑ አረጋግጧል። በመሆኑም ተከሳሹ ይማርበታል፣ ሌሎችንም ያስገነዝባል ያለውን የስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል።
ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ የመጨረሻ ውሳኔ ለማየት በሰአቱ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በፈጸመው ድርጊትም ጥፋተኛ ስለመሆኑ በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች አረጋግጧል። በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራስድስት ዓመት ከአምስት ወራት እስራት ይቀጣልኝ ሲል ብይኑን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በ መልካምስራ አፈወርቅ