አልፎ አልፎ ለጉዳያቸው ወዲያ ወዲህ ከሚሉ ሰዎች በቀር መንገዱ ያለ ወትሮው ጭር ብሏል።አንዲት ወጣት በጀርባዋ ሕፃን ልጅ አዝላ ዓይኖቿ አንዳች ነገር በሚፈልግ መልኩ በመንገዱ የሚመላለሱ ሰዎችን በአንክሮ ትመለከታለች።ከመንገዱ ጠርዝ እንዲህ ወጣ ገባ እያለች የሰዎችን እንቅስቃሴ ትቃኛለች።አንገቷን እያሰገገች አካባቢውን ትቃኛለች።ወዲያው በጀርባዋ አዝላው የነበረውን ሕፃን ልጅዋን ከጀርባዋ እንደዘበት አውርዳ የመወርወር ያህል ከመንገዱ ዳር አስተኝታው ቆሻሻ በሚያስቀጣ ቦታ እንደጣለ ሰው መጀመሪያ በፍጥነት እርምጃ ከዚያም በሩጫ አካባቢዋን ለቃ ሮጠች።
የተጣለው ልጅ እሪታውን አቀለጠው። ከዋናው መንገድ መታጠፊያ ጥግ አንዲት ሱቅ በራፍ ላይ ዕቃ በመግዛት ላይ የነበሩት አንዲት አሮጊት የልጅቷን ሁኔታ በአንክሮ ይመለከቱ ነበርና መንገድ ዳር ወደተጣለውና እሪታውን ወደሚያቀልጠው ሕፃን ተጠጉ።ገና የቀናት ዕድሜ ያለው ጨቅላ መሆኑ እናት ናቸውና መገመት አልከበዳቸውም።
«ምንድነው ወዴት ነው ጥላው ምትሄደው?» ለራሳቸው የጠየቁት ጥያቄ ነበር።ሕፃኑን ይበልጥ ተጠግተውት ባልጠነከረ ገላው እየተወራጨ ሲያለቅስ ተመለከቱ።ቆም ብለው እናትየው ወደሸሸችበት አቅጣጫ አማተሩ።እናትየው በፍጥነት ትሮጣለች።«ኧረ በሕግ አምላክ…እናቱ ነሽ ወዴት ነው የምትሄጂው? ልጅሽን
ትተሽ ወዴት ነው የምትሸሽው? እናትዬው መስማት የምትችልበት ርቀት ላይ አልነበረችም።የሆነ ድምፅ የሰማች ይመስል አንገቷን አንዴ ዞር አድርጋ በመመልከት መንገዱን ታጥፋ ሩጫዋን ቀጠለች።
አሮጊቷ የሕፃኑን እናት ለመከተል የሚያስችል ጉልበት አልነበራ ቸውምና ተመልሰው ሕፃኑ ልጅ አጠገብ ቆሙ። የአሮጊቷን ጮሆ መናገር ተከትሎ ሰዎች ከየአቅጣጫው ተሰበሰቡ። «ምን ተፈጥሮ ነው?» ቀርበው እያዩ እርስ በእርስ ተጠያየቁ ቀድመው ወደ ልጁ የተጠጉት ሴትዮ ደጋግመው አስረዱ።ለሕፃኑ የሚያዝን እናቱን ጥላ የሄደችውን ሴት የሚራገም፤ ዘመኑን የሚፀየፍ ሰው በረከተ። ከመሀል አንድ ዕድሜዋ 40ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የምትጠጋ እናት ልጁን ቀርባ ከፋፍታ ልታየው ተጠጋች።ከተሰበሰቡት አንዱ «ኧረ ለሚመለከተው አካል ሳታሳውቁ አትንኩ። ሰበብ ቢሆንባችሁስ ወንጀል ነው፤እንዳትጠየቁ» አለ።ሁሉም ፈርቶ አፈገፈገ።ማንም ሕፃኑን ቆሞ ከማየት በቀር ቀርቦ የነካው አልያም፤ አቅፎ ያነሳው የለም።አንዳንዱ አይቶ አንገቱን እየነቀነቀ መንገዱን ይቀጥላል።የሕፃኑ ለቅሶ እየከረረ ሄዶ በጊዜ ርዝመት እየቀነሰ እየደከመ መጣ።
አንድ ወጣት ሁኔታውን ተመልክቶ አንድ ነገር
ለማድረግ አሰበ። ቆመው የሕፃኑን ሁኔታ ከሚያዩ ሰዎች ነጠል ብሎ በመውጣት በፈጠነ እርምጃ ወደ አንድ አቅጣጫ አመራ።ከ3 ደቂቃ ጉዞው በኋላ የወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሕንፃ ደረጃዎችን በፍጥነት ወጥቶ ወደ አንድ ቢሮ በር አንኳኩቶ ገባ። ሁለት ሴቶች ተራርቀው በየራሳቸው ጠረጴዛ ላይ ባለ ኮምፒዩተር ላይ ዓይናቸውን ተክለዋል።አንደኛዋ ወጣቱን ቀና ብላ ተመለከተችው።
ወጣቱ በትህትና ሰላምታ አቅርቦላት የመጣበትን ጉዳይ ማስረዳት ያዘ። «ይሄውልሽ እህቴ እዚሁ ወረዳ ሰላም ሰፈር ከዋናው መንገድ ገባ ብሎ አንድ ሕፃን ተጥሏል።ልጁ በጣም የተጎዳ መሆኑ ያስታውቃልና በእናንተ በኩል እርዳታ ማግኘት እንዲችል…ለማሳወቅ ነው የመጣሁት፡፡» በማለት ስለሁኔታው ማስረዳት ቀጠለ።ልጅቷ በኀዘን ጭንቅላቷን ነቅንቃ «ይሄውልህ ወንድሜ ሦስተኛ ፎቅ ላይ በግራ በኩል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ አለ፤ እዚያ አሳውቅ» በማለት አሰናበተችው፡፡
ሌላ ምንም ቃላት ሳይለዋወጥ ወደተባለው ቢሮ አመራ። በሩን አንኳኩቶ ሲገባ አንድ ሰፊ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ወጣት በትህትና ተቀበለው። ለወጣቱ የመጣበትን ጉዳይ አስረዳው። «እ.. ይቅርታ እኔ ባለሙያ ነኝ። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለሥራ ወጥተዋል።ግን ለዚህ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት እንድትችል አንደኛ ፎቅ ላይ የወረዳው አስተዳዳሪ በቀጥታ ገብተህ ብታወራቸው ይሻ ላል፡፡» ቆሞ ሌላ ወሬ አላወራውም ወጥቶ ወደ አንደኛ ፎቅ በፍጥነት ደረጃዎቹን መውረድ ጀመረ፡፡
በመስታወት ፍሬም ባማረ መልኩ የተሰራው በር ላይ።«አቶ እንዳሻው በላቸው የወረዳው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ» የሚል ጽሑፍ ይታያል።ወጣቱ ጠጋ ብሎ ሳያንኳኳ ወደ ውስጥ በሩን በመግፋት ዘለቀ። በክፍሉ አንድ ጥግ ተቀምጣ የነበረች ወጣት የወጣቱ መግባት ስትመለከት ተነስታ ተቀበለችው፡፡
«አቤት ምን ልታዘዝ..?» በማለት ጥያቄ አቀረበችለት። «የወረዳውን አስተዳዳሪ ፈልጌ ነበር…» «ጉዳይዎ ምን
ነበር ቀጠሮ ነበሮት? አለችው፡፡» «አይ ቀጠሮ የለኝም ለአስቸኳይ ጉዳይ ነው የፈለኳቸው » «ይቅርታ አሁን ስብሰባ ገቡ። ምን አልባት መልዕክት ልቀበልና ሲመጡ ልንገርልዎ!» የልጅቷ ምላሽ ትህትና ያዘለ ቢሆንም ወጣቱ በሁኔታው ትዕግስት እያጣ መጥቷል።ውጪ ያለው ሕፃን ታወሰው።የሕፃኑን ሁኔታ አስረድቶ እርዳታ እንዲደረግለት ባለው ጽኑ ፍላጎት የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱ ግን አናዶታል።1ሰዓት ከ30 ደቂቃ በላይ ከአንዱ ቢሮ ወደሌላው ቢሮ ሲመላለስ ቆይቷል፡፡
ሳያውቀው በጩኸት «አሁን ላገኛቸው ይገባል ሰው ተጎድቶ ነው አሁኑኑ ላገኛቸው እፈልጋለሁ…ሰዓት የለኝም ለተጎዳ ሰው እርዳታ እንዲያሰጡ ነው የፈለኳቸው፡፡» ልጅቷ የወጣቱን ሁኔታ ስታይ ጠረጴዛው ላይ ወዳለ ስልክ አመራች።እጀታውን አንስታ ቁጥሮችን ነካካች።ወጣቱ እየተቁነጠነጠ ሁኔታውን በጉጉት ይከታተላል።ልጅቷ ወደ አስተዳዳሪው መደወሏ ከንግግሯ ተረዳ።በስልክ የጉዳዩ ምንነት ለጠየቁት ኃላፊ ልጅቷ ከልጁ ሰምታ አስተላለፈች።ልጅቷ ከቆይታ በኋላ ስልኩን ዘግታ «ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የወረዳው ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ነው፤ አራተኛ ፎቅ ላይ ታገኛቸዋለህ»
ወጣቱ ወደሕንፃው መጨረሻ ወለል አቀና።በቢሮው ውስጥ ከተቀመጡ ሠራተኞች ወደአንዱ ተጠግቶ እንደ አዲስ ማስረዳት ያዘ።ይሰማው የነበረው ወጣት ጉዳዩን በፅሞና ከተከታተለው በኋላ «የቱ ጋር ነው አሁንም እዚያው ነው?» የሚል ጥያቄ አቀረበለት።ሰዓቱ ተመለከተ እዚያ ቢሮ ከገባ ሁለት ሰዓት ሆኖታል።«አዎ እዚሁ ሰፈር ነው እባክህን ወንድሜ ፈጥነን እንድረስለት» በማለት ተማፅኖውን አቀረበ።ሠራተኛው ወደአንዱ ጠረጴዛ ተጠግቶ ትንሽ ካወራ በኋላ ካወራት አንዲት ወጣት ሴት ወደ ፖሊስ ስልክ ደውለው ከቢሮ ተያይዘው ወጡ።
ከወረዳው ጎን ካለ ፖሊስ ጣቢያ ሁለት ፖሊሶች ጋር በመሆን ሕፃኑ ተጥሎ የነበረበት ቦታ በፍጥነት ደረሱ።ቅድም ልጁን ቀድመው ያገኙት አሮጊት ሕፃኑን ተጠግተው በተጨነቀ ስሜት ያነባሉ።የበዙ ሰዎች ከበው ሕፃኑን ይመለከታሉ፤ ከንፈር ይመጣሉ።አንዳንዶች ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም።ፖሊስና ከወረዳው የመጡ የጤና ባለሙያዎች የተሰበሰቡ ሰዎች መንገድ አስለቅቀው ወደ ሕፃኑ ተጠጉ።ነገር ግን ሕፃኑን ሳይሆን የጨቅላውን በድን ነበር ያገኙት። ተፈፀመ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ተገኝ ብሩ